በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 84

ኢየሱስ በውኃ ላይ ሄደ

ኢየሱስ በውኃ ላይ ሄደ

ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን ከመፈወስና የሞቱ ሰዎችን ከማስነሳት በተጨማሪ ነፋስንና ዝናብን የመቆጣጠር ችሎታም ነበረው። ኢየሱስ በተራራ ላይ ሲጸልይ ቆይቶ ወደ ታች ወደ ገሊላ ባሕር ሲመለከት አውሎ ነፋስ ባሕሩን ሲያናውጠው አየ። ሐዋርያቱ ከነፋሱ በተቃራኒ አቅጣጫ ጀልባውን ለመቅዘፍ እየታገሉ ነበር። ኢየሱስ ከተራራው ወርዶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባው መጣ። ሐዋርያቱ በውኃው ላይ የሚሄድ ሰው ሲያዩ በጣም ደነገጡ። ኢየሱስ ግን ‘እኔ ነኝ። አትፍሩ’ አላቸው።

ከዚያም ጴጥሮስ ‘ጌታ ሆይ፣ በእርግጥ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ’ አለው። ኢየሱስም ጴጥሮስን ‘ወደ እኔ ና!’ አለው። ስለዚህ ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወርዶ በአውሎ ነፋሱ መሃል በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ ሄደ። ሆኖም ወደ ኢየሱስ እየቀረበ ሲመጣ አውሎ ነፋሱን አየና ፈራ። ከዚያም መስመጥ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ‘ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!’ ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም እጁን ያዘውና እንዲህ አለው፦ “አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርክ?”

ኢየሱስና ጴጥሮስ ጀልባው ላይ ወጡ፤ አውሎ ነፋሱም ወዲያው ጸጥ አለ። ሐዋርያቱ ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ? ኢየሱስን “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” አሉት።

ኢየሱስ የአየር ሁኔታን መቆጣጠር እንደሚችል ያሳየው በዚህ ጊዜ ብቻ አልነበረም። በአንድ ወቅት ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወደ ባሕሩ ማዶ በጀልባ እየተሻገሩ ሳሉ ኢየሱስ በጀልባው የኋለኛ ክፍል ተኝቶ ነበር። እሱ ተኝቶ ሳለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነሳ። ማዕበሉም ከጀልባው ጋር እየተላተመ ወደ ውስጥ ይገባ ጀመር፤ በመሆኑም ጀልባው በውኃ ተሞላ። ሐዋርያቱም ኢየሱስን ቀስቅሰው ከፍ ባለ ድምፅ ‘መምህር፣ መሞታችን ነው! እርዳን!’ አሉት። ኢየሱስም ተነስቶ ባሕሩን “ጸጥ በል!” አለው። ወዲያውኑም ነፋሱና ባሕሩ ጸጥ አለ። ከዚያም ኢየሱስ ሐዋርያቱን ‘እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትፈራላችሁ?’ አላቸው። እነሱም እርስ በርሳቸው “ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል” ተባባሉ። ሐዋርያቱ ሙሉ በሙሉ በኢየሱስ እስከተማመኑ ድረስ ምንም ነገር መፍራት እንደማያስፈልጋቸው ተገነዘቡ።

“በሕያዋን ምድር የይሖዋን ጥሩነት አያለሁ የሚል እምነት ባይኖረኝ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር!”—መዝሙር 27:13