በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 88

ኢየሱስ ታሰረ

ኢየሱስ ታሰረ

ኢየሱስና ሐዋርያቱ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ እየተጓዙ ነው። እኩለ ሌሊት አልፏል፤ ጨረቃዋ ሙሉ ሆና ትታያለች። ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ እንደደረሱ ኢየሱስ ሐዋርያቱን “እዚህ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ከዚያም ኢየሱስ ትንሽ ራቅ ብሎ በመንበርከክ መጸለይ ጀመረ። በታላቅ ጭንቀት ተውጦ “የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ይሖዋን ለመነ። ከዚያም ይሖዋ ኢየሱስን እንዲያበረታታው አንድ መልአክ ላከለት። ኢየሱስ ወደ ሐዋርያቱ ሲመለስ ተኝተው አገኛቸው። ከዚያም ‘ተነሱ! ይህ የእንቅልፍ ሰዓት አይደለም! ጠላቶቼ እኔን የሚይዙበት ሰዓት ደርሷል’ አላቸው።

ወዲያውኑም ይሁዳ ሰይፍና ዱላ ከያዙ ሰዎች ጋር መጣ። ይሁዳ ከኢየሱስ ጋር ብዙ ጊዜ ወደዚህ የአትክልት ስፍራ ይመጣ ስለነበር ኢየሱስን እዚህ ሊያገኘው እንደሚችል አውቆ ነበር። ይሁዳ ለወታደሮቹ ኢየሱስ የትኛው እንደሆነ በምልክት እንደሚያሳያቸው ነግሯቸው ነበር። ስለዚህ ወደ ኢየሱስ ሄዶ ‘መምህር፣ ሰላም ለአንተ ይሁን’ አለውና ሳመው። ኢየሱስም ‘ይሁዳ፣ እኔን በመሳም አሳልፈህ ልትሰጠኝ ነው?’ አለው።

ኢየሱስ ወደ ፊት ራመድ ብሎ ሰዎቹን “ማንን ነው የምትፈልጉት?” አላቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” ብለው መለሱለት። እሱም “እኔ ነኝ” አላቸው፤ ከዚያም ሰዎቹ ወደ ኋላ በመሸሽ መሬት ላይ ወደቁ። ኢየሱስም ሰዎቹን በድጋሚ “ማንን ነው የምትፈልጉት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነሱም ደግመው “የናዝሬቱን ኢየሱስ” አሉት። ኢየሱስም ‘እኔ ነኝ አልኳችሁ እኮ። ስለዚህ እነሱን ተዉአቸው’ አላቸው።

ጴጥሮስ ሰዎቹ ኢየሱስን ሊይዙት መሆኑን ሲያይ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ የማልኮስን ጆሮ ቆረጠው። ኢየሱስ ግን የማልኮስን ጆሮ በመዳሰስ ፈወሰው። ከዚያም ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ ‘ሰይፍህን መልስ። በሰይፍ ከተዋጋህ በሰይፍ ትሞታለህ።’ ወታደሮቹ ኢየሱስን ይዘው እጁን አሰሩት፤ በዚህ ጊዜ ሐዋርያቱ ጥለውት ሸሹ። ከዚያም ሰዎቹ ኢየሱስን የካህናት አለቃ ወደሆነው ወደ ሐና ወሰዱት። ሐናም ኢየሱስን የተለያዩ ጥያቄዎችን ከጠየቀው በኋላ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ቤት ላከው። ታዲያ ሐዋርያቱ ምን አጋጥሟቸው ይሆን?

“በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐንስ 16:33