በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 93

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመለሰ

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመለሰ

ኢየሱስ በገሊላ ከተከታዮቹ ጋር ተገናኘ። ከዚያም የሚከተለውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ትእዛዝ ሰጣቸው፦ ‘ሂዱና ከሁሉም አገሮች ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ። ያስተማርኳችሁን ነገሮች አስተምሯቸው፤ እንዲሁም አጥምቋቸው።’ ቀጥሎም ‘ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ’ በማለት ቃል ገባላቸው።

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በነበሩት 40 ቀናት ውስጥ በገሊላና በኢየሩሳሌም በመቶዎች ለሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርቱ ታየ። በዚህ ወቅት አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ሰጣቸው እንዲሁም ብዙ ተአምራትን ፈጸመ። ከዚያም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ከሐዋርያቱ ጋር ተገናኘ።

ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ሐዋርያቱን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ ‘ከዚህች ከተማ አትውጡ። አባቴ ቃል የገባው ነገር እስኪፈጸም ድረስ እዚሁ ጠብቁ።’ ሐዋርያቱ ግን ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸውም ነበር። ስለዚህ ‘የእስራኤል ንጉሥ የምትሆነው አሁን ነው?’ ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ ‘ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ገና አልደረሰም። በቅርቡ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ ይወርዳል። በዚያን ጊዜ ኃይል ታገኛላችሁ፤ ምሥክሮቼም ትሆናላችሁ። ሂዱና በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ስበኩ።’

ከዚያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ወጣ፤ ደመናም ሸፈነው። ደቀ መዛሙርቱ ወደ ላይ ማየታቸውን ቀጠሉ፤ እሱ ግን ተሰወረ።

ደቀ መዛሙርቱ ከደብረ ዘይት ተራራ ተነስተው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። በዚያም ሰገነት ላይ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ አዘውትረው ይሰበሰቡና ይጸልዩ ነበር። ኢየሱስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተጨማሪ መመሪያ እስኪሰጣቸው ድረስ ሲጠብቁ ቆዩ።

“ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14