በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 99

አንድ የእስር ቤት ጠባቂ ክርስቲያን ሆነ

አንድ የእስር ቤት ጠባቂ ክርስቲያን ሆነ

በፊልጵስዩስ የምትኖር ጋኔን የያዛት አንዲት አገልጋይ ነበረች። እሷም ጋኔኑ እንድትጠነቁል ወይም ወደፊት ስለሚሆነው ነገር እንድትናገር ያደርጋት ስለነበር ለጌቶቿ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር። ጳውሎስና ሲላስ ወደ ፊልጵስዩስ ከመጡ በኋላ ለብዙ ቀናት ትከተላቸው ነበር። ‘እነዚህ ሰዎች የልዑሉ አምላክ ባሪያዎች ናቸው’ እያለች ትጮኽ ነበር። በመጨረሻም ጳውሎስ ጋኔኑን ‘ከእሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ስም አዝሃለሁ!’ አለው። በዚህ ጊዜ ጋኔኑ ከእሷ ወጣ።

የዚህች አገልጋይ ጌቶች ከዚያ በኋላ እየጠነቆለች ገንዘብ እንደማታመጣላቸው ሲያውቁ በጣም ተናደዱ። በመሆኑም ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ወሰዷቸውና እንዲህ አሉ፦ ‘እነዚህ ሰዎች ሕግ አያከብሩም፤ ደግሞም መላ ከተማዋን እየረበሹ ነው።’ የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎችም ጳውሎስና ሲላስ እንዲገረፉና እስር ቤት እንዲገቡ አዘዙ። የእስር ቤቱ ጠባቂም ጨለማ ወደሆነው የእስር ቤቱ ውስጠኛ ክፍል ወስዶ በእግር ግንድ አሰራቸው።

ጳውሎስና ሲላስ ግን ሌሎቹ እስረኞች እየሰሟቸው ይሖዋን በመዝሙር ያወድሱ ነበር። እኩለ ሌሊት ላይ በድንገት ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ እስር ቤቱን ከላይ እስከ ታች አናወጠው። የእስር ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ እስረኞቹ የታሰሩባቸው ሰንሰለቶችም ተፈቱ። የእስር ቤቱ ጠባቂ ወደ እስር ቤቱ ውስጠኛ ክፍል እየሮጠ ሲመጣ በሮቹ መከፈታቸውን አየ። እስረኞቹ በሙሉ ያመለጡ ስለመሰለው ራሱን ለመግደል ሰይፍ መዘዘ።

በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ‘በራስህ ላይ ጉዳት አታድርስ! ሁላችንም አለን!’ አለው። የእስር ቤቱ ጠባቂም በፍጥነት ሄዶ በጳውሎስና በሲላስ ፊት ተንበረከከ። ከዚያም “ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” በማለት ጠየቃቸው። እነሱም ‘አንተም ሆንክ ቤተሰብህ በኢየሱስ ማመን አለባችሁ’ አሉት። ከዚያም ጳውሎስና ሲላስ ለእስር ቤቱ ጠባቂና ለቤተሰቦቹ የይሖዋን ቃል አስተማሯቸው፤ እነሱም ወዲያውኑ ተጠመቁ

“ሰዎች ይይዟችኋል፤ ስደት ያደርሱባችኋል እንዲሁም ለምኩራብና ለወህኒ ቤት አሳልፈው ይሰጧችኋል። በስሜም ምክንያት በነገሥታትና በገዢዎች ፊት ያቀርቧችኋል። ይህም ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትላችኋል።”—ሉቃስ 21:12, 13