በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 100

ጳውሎስና ጢሞቴዎስ

ጳውሎስና ጢሞቴዎስ

በልስጥራ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ወጣት ወንድም ነበር። አባቱ ግሪካዊ ሲሆን እናቱ ደግሞ አይሁዳዊት ነበረች። እናቱ ኤውንቄና አያቱ ሎይድ ጢሞቴዎስን ሕፃን ልጅ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ስለ ይሖዋ አስተምረውታል።

ጳውሎስ ምሥራቹን በተለያዩ ቦታዎች ለመስበክ ለሁለተኛ ጊዜ በተጓዘበት ወቅት ልስጥራን ጎብኝቶ ነበር፤ እዚያ በቆየበት ወቅት ጢሞቴዎስ ወንድሞችን በጣም እንደሚወድና እነሱን መርዳት እንደሚያስደስተው አስተዋለ። በመሆኑም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን አብሮት እንዲጓዝ ጠየቀው። ከዚያም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ጎበዝ የምሥራቹ ሰባኪና አስተማሪ እንዲሆን አሠለጠነው።

ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በሄዱበት ቦታ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ይመራቸው ነበር። አንድ ቀን ጳውሎስ፣ አንድ የመቄዶንያ ሰው ወደ እነሱ መጥቶ እንዲረዳቸው ሲለምነው በራእይ አየ። ስለዚህ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ፣ ሲላስና ሉቃስ ምሥራቹን ለመስበክና ጉባኤዎችን ለማቋቋም ወደ መቄዶንያ ሄዱ።

መቄዶንያ ውስጥ በምትገኘው በተሰሎንቄ ከተማ የሚኖሩ በርካታ ወንዶችና ሴቶች ክርስቲያኖች ሆኑ። ሆኖም አንዳንድ አይሁዳውያን በጳውሎስና በጓደኞቹ ቀኑ። ስለዚህ ሕዝቡን አነሳስተው ወንድሞችን እየጎተቱ ወደ ከተማዋ ገዢዎች ወሰዷቸውና እንዲህ አሉ፦ ‘እነዚህ ሰዎች የሮም መንግሥት ጠላቶች ናቸው!’ በዚህ ጊዜ ወንድሞች፣ አይሁዳውያን ጳውሎስንና ጢሞቴዎስን እንዳይገድሏቸው ስለፈሩ በሌሊት ወደ ቤርያ ላኳቸው።

በቤርያ የሚኖሩት ሰዎች ምሥራቹን ለመስማት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፤ በመሆኑም በዚያ ከሚኖሩት ግሪካውያንና አይሁዳውያን መካከል ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ሆኑ። ሆኖም አንዳንድ አይሁዳውያን ከተሰሎንቄ መጥተው ችግር መፍጠር ሲጀምሩ ጳውሎስ ወደ አቴንስ ሄደ። ጢሞቴዎስና ሲላስ ግን በቤርያ የሚገኙትን ወንድሞች ለማጠናከር ሲሉ እዚያው ቀሩ። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ወደ ተሰሎንቄ ላከው፤ ይህን ያደረገው በተሰሎንቄ የሚገኙ ወንድሞች የሚደርስባቸውን ከባድ ስደት መቋቋም እንዲችሉ ማበረታቻ እንዲሰጣቸው ነው። በኋላም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ወንድሞችን እንዲያበረታታ ወደተለያዩ ጉባኤዎች ልኮታል።

ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‘ይሖዋን ማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች ይሰደዳሉ’ ብሎት ነበር። ጢሞቴዎስ በእምነቱ ምክንያት ስደት ደርሶበታል እንዲሁም ታስሯል። ሆኖም ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት የሚያሳይበት አጋጣሚ በማግኘቱ ተደስቷል።

ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የሚገኙ ክርስቲያኖችን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ ‘ጢሞቴዎስን ወደ እናንተ እልከዋለሁ። እሱም ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ መኖር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ያስተምራችኋል፤ እንዲሁም ለአገልግሎት ያሠለጥናችኋል።’ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ ይተማመን ነበር። ምክንያቱም ለብዙ ዓመታት ጓደኛሞች ነበሩ፤ እንዲሁም ይሖዋን አብረው አገልግለዋል።

“ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝምና። ሌሎቹ ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉ።”—ፊልጵስዩስ 2:20, 21