በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 103

“መንግሥትህ ይምጣ”

“መንግሥትህ ይምጣ”

ይሖዋ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፦ ‘ከዚህ በኋላ ለቅሶ፣ ሥቃይ፣ ሕመም ወይም ሞት አይኖርም። እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ላይ እጠርጋለሁ። በፊት የነበሩ መጥፎ ነገሮች በሙሉ ይረሳሉ።’

ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን በኤደን ገነት ያስቀመጣቸው በሰላምና በደስታ እንዲኖሩ ነበር። የሰማዩን አባታቸውን እንዲያመልኩ እንዲሁም ልጆች ወልደው ምድርን እንዲሞሉ አስቦ ነበር። አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ ዓመፁ፤ ሆኖም የይሖዋ ዓላማ አልተለወጠም። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደተመለከትነው አምላክ የገባውን ቃል በሙሉ ይፈጽማል። ይሖዋ ለአብርሃም ቃል በገባው መሠረት በሰማይ ያለው መንግሥቱ በምድር ላይ አስደሳች በረከቶችን ያመጣል።

በቅርቡ ሰይጣን፣ አጋንንቱና ክፉ ሰዎች በሙሉ ይጠፋሉ። በሕይወት ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ይሖዋን ያመልካሉ። ማንኛችንም ብንሆን አንታመምም እንዲሁም አንሞትም። ከዚህ ይልቅ በየቀኑ ጠዋት ኃይላችን ታድሶ እንነሳለን፤ ሕይወት አስደሳች ይሆንልናል። ምድር ገነት ትሆናለች። ሁሉም ሰው ጥሩ ምግብና ምቹ የሆነ ቤት ይኖረዋል። ጨካኝ ወይም ዓመፀኛ የሆኑ ሰዎች አይኖሩም፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰው ደግና አሳቢ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የዱር እንስሳት ከእኛ አይሸሹም፤ እኛም እነሱን አንፈራቸውም።

ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ማስነሳት ሲጀምር የሚኖረውን ደስታ ለማሰብ ሞክር! በጥንት ዘመን የኖሩ እንደ አቤል፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ሩት፣ አስቴርና ዳዊት ያሉ ሰዎች ከሞት ሲነሱ እንቀበላቸዋለን። እነሱም ምድርን ገነት በማድረጉ ሥራ አብረውን ይካፈላሉ። በዚያን ጊዜ የምንሠራው ብዙ አስደሳች ሥራ ይኖረናል።

ይሖዋ አንተም በገነት ውስጥ እንድትኖር ይፈልጋል። ያን ጊዜ ስለ ይሖዋ ያለህ እውቀት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየጨመረ ይሄዳል። አሁንም ሆነ ለዘላለም በየዕለቱ ወደ ይሖዋ መቅረባችንን እንቀጥል!

“ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11