በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበላይ አካሉ መልእክት

የበላይ አካሉ መልእክት

ውድ የእምነት አጋሮቻችን፦

የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቃል ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አድናቆት አለን። መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ታሪክ፣ አስተማማኝ መመሪያ እንዲሁም ይሖዋ ለሰው ልጆች ምን ያህል ፍቅር እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ እንደያዘ ሙሉ በሙሉ እናምናለን። (መዝሙር 119:105፤ ሉቃስ 1:3፤ 1 ዮሐንስ 4:19) ሌሎች ሰዎችም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ውድ እውነቶች እንዲማሩ መርዳት እንፈልጋለን። “ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?” የተባለው ይህ መጽሐፍ ይህን ዓላማ ዳር ለማድረስ እንደሚረዳ እናምናለን። እስቲ ስለ መጽሐፉ ይዘት አንዳንድ ሐሳቦችን እናካፍላችሁ።

ይህ መጽሐፍ በዋነኝነት የተዘጋጀው ለልጆች ነው። ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ የሚፈልጉ ትላልቅ ሰዎችንም ለመርዳት ሊያገለግል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ሰው የሚሆን መጽሐፍ እንደመሆኑ መጠን ሁላችንም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች በማንበብ እንደምንጠቀም ጥርጥር የለውም፤ ይህን ማድረጋችን እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል።

ይህ መጽሐፍ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ መሠረት በማድረግ ከፍጥረት ጊዜ አንስቶ ያለውን የሰው ልጆች ታሪክ ይተርካል። የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪኮች ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ እንዲሁም ክንውኖቹ በተፈጸሙበት ቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።

ሆኖም የዚህ መጽሐፍ ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪኮች እንዲሁ መተረክ ብቻ አይደለም። ውስጡ ያለው ሐሳብም ሆነ ሥዕሎቹ የተዘጋጁት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እውን ሆኖ እንዲታየንና የባለ ታሪኮቹ ስሜት እንዲገባን በሚያስችል መንገድ ነው።

ይህ መጽሐፍ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ስለታዘዙና ስላልታዘዙ ሰዎች የሚገልጽ ዘገባ የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። እንዲሁም እነሱ ከተዉት ምሳሌ ጠቃሚ ትምህርት እንድናገኝ ያበረታታናል። (ሮም 15:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:6) መጽሐፉ 14 ክፍሎች አሉት። በእያንዳንዱ ክፍል መጀመሪያ ላይ በዚያ ክፍል ውስጥ የተካተቱት ትምህርቶች የያዟቸውን ዋና ዋና ነጥቦች እናገኛለን።

ወላጅ ከሆንክ፣ ከልጅህ ጋር አንዱን ትምህርት ካነበባችሁ በኋላ በሥዕሉ ላይ ልትወያዩ ትችላላችሁ። ከዚያም ትምህርቱ የተመሠረተባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማንበብ ትችላላችሁ። ልጅህ ከመጽሐፉ የሚማረው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ እንዲገነዘብ እርዳው። አንድ ትልቅ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ መልእክት እንዲገነዘብ በምትረዳበትም ወቅት ተመሳሳይ ነገር ማድረግህ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።

ይህ መጽሐፍ በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በሙሉ የአምላክን ቃል እንዲማሩና የሚያገኙትን ትምህርት ሥራ ላይ እንዲያውሉ እንደሚረዳቸው ተስፋ እናደርጋለን። ይህን ካደረጉ እነሱም የይሖዋ ቤተሰብ አባል ሆነው እሱን ማምለክ ይችላሉ።

ወንድሞቻችሁ፣

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል