በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 1

“ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ”

“ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ”

ማቴዎስ 4:10

ፍሬ ሐሳብ፦ ንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋሙ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት

1, 2. ኢየሱስ በ29 ዓ.ም. የመከር ወቅት ላይ በይሁዳ ምድረ በዳ ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? በዚያስ ምን አጋጠመው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ጊዜው 29 ዓ.ም. የመከር ወቅት መጀመሪያ ሲሆን ኢየሱስ ከሙት ባሕር በስተ ሰሜን በይሁዳ ምድረ በዳ ይገኛል። ከተጠመቀና ከተቀባ በኋላ ኢየሱስን ወደዚህ ስፍራ የመራው መንፈስ ቅዱስ ነው። ያገጠጡ ድንጋዮችና ገደላ ገደሎች በሞሉበት በዚህ ጠፍ ምድረ በዳ ባሳለፋቸው 40 ቀናት የሚጾምበት፣ የሚጸልይበትና የሚያሰላስልበት አጋጣሚ አግኝቷል። ምናልባትም በዚህ ወቅት ይሖዋ ልጁን በማነጋገር ወደፊት ለሚጠብቀው ነገር አዘጋጅቶት ሊሆን ይችላል።

2 ኢየሱስ በጣም ከመራቡ የተነሳ ተዳክሞ በነበረበት ወቅት ሰይጣን ወደ እሱ ቀረበ። ቀጥሎ የተከናወነው ነገር አንተን ጨምሮ ንጹሕ አምልኮን የሚወዱ ሰዎችን በሙሉ ከሚነካ አንድ አንገብጋቢ ጉዳይ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

“የአምላክ ልጅ ከሆንክ . . .”

3, 4. (ሀ) ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ፈተናዎች የጀመረው በየትኞቹ ቃላት ነው? ይህን ያለውስ ኢየሱስ ስለ ምን ነገር ጥርጣሬ እንዲያድርበት ለማድረግ ፈልጎ ሊሆን ይችላል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ሰይጣን ተመሳሳይ ዘዴዎችን የሚጠቀመው እንዴት ነው?

3 ማቴዎስ 4:1-7ን አንብብ። ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ሁለት ፈተናዎች ያቀረበው “የአምላክ ልጅ ከሆንክ” የሚሉትን ተንኮል ያዘሉ ቃላት በማስቀደም ነበር። ሰይጣን ይህን ያለው ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን ተጠራጥሮ ነው? በፍጹም። ከአምላክ ልጆች አንዱ የነበረው ይህ ዓመፀኛ መልአክ ኢየሱስ የአምላክ የበኩር ልጅ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል። (ቆላ. 1:15) ሰይጣን፣ ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ይሖዋ “በጣም የምደሰትበት የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ከሰማይ ሲናገር እንደሰማም ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴ. 3:17) ምናልባትም የሰይጣን ዓላማ ኢየሱስ፣ አባቱ እምነት የሚጣልበትና ለእሱ ከልብ የሚያስብ መሆኑን እንዲጠራጠር ማድረግ ሊሆን ይችላል። ዲያብሎስ ለኢየሱስ ባቀረበው የመጀመሪያ ፈተና ላይ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” ሲል፣ በተዘዋዋሪ መንገድ ‘የአምላክ ልጅ አይደለህ? ታዲያ በዚህ ጠፍ ምድረ በዳ ውስጥ አባትህ የማይመግብህ ለምንድን ነው?’ ማለቱ ነበር። በሁለተኛው ፈተና ላይ ደግሞ ወደ ቤተ መቅደሱ አናት ወስዶ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ራስህን ወደ ታች ወርውር” ሲለው ‘እንግዲህ የአምላክ ልጅ ነኝ ብለሃል፤ ታዲያ አባትህ በእርግጥ እንደሚጠብቅህ ትተማመናለህ?’ ያለው ያህል ነበር።

4 ሰይጣን በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ ዘዴዎችን ይጠቀማል። (2 ቆሮ. 2:11) ዲያብሎስ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች የሚዳከሙበትን ወይም ተስፋ የሚቆርጡበትን ጊዜ ጠብቆ ጥቃት ይሰነዝራል፤ ብዙውን ጊዜ ጥቃት የሚሰነዝረው ስውር በሆነ መንገድ ነው። (2 ቆሮ. 11:14) ይሖዋ ፈጽሞ ሊወደን እንደማይችል አሊያም በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ልናገኝ እንደማንችል እንድናስብ በማድረግ ሊያታልለን ይሞክራል። በተጨማሪም ፈታኙ፣ ይሖዋ እምነት የማይጣልበት እንደሆነና የገባውን ቃል እንደማይፈጽም አድርገን እንድናስብ ለማድረግ ይጥራል። ሆኖም እነዚህ አደገኛ የሆኑ ውሸቶች ናቸው። (ዮሐ. 8:44) ታዲያ እንዲህ ያሉትን ውሸቶች መቃወም የምንችለው እንዴት ነው?

5. ኢየሱስ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ፈተናዎች ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ፈተናዎች ምላሽ የሰጠው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። አባቱ እንደሚወደው ቅንጣት ታክል እንኳ አልተጠራጠረም፤ እንዲሁም በአባቱ ላይ ሙሉ እምነት ነበረው። ኢየሱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአባቱን ቃል በመጥቀስ ያለአንዳች ማመንታት ሰይጣንን ተቃውሟል። የጠቀሳቸው ጥቅሶች ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም የያዙ ናቸው፤ ይህም ተገቢ ነው። (ዘዳ. 6:16፤ 8:3) ደግሞስ አምላክ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ዋስትና የሚሰጠውን ይሖዋ የሚለውን ስም ከመጠቀም የተሻለ በአባቱ ላይ እምነት እንዳለው የሚያሳይ ምን ሌላ መንገድ ይኖራል? *

6, 7. የሰይጣንን ስውር ጥቃቶች መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?

6 እኛም የይሖዋን ቃል በሚገባ በመጠቀምና መለኮታዊው ስም ባለው ትርጉም ላይ በማሰላሰል የሰይጣንን ስውር ጥቃቶች መከላከል እንችላለን። ሰይጣን፣ ይሖዋ ፈጽሞ ሊወደን ወይም ሊደሰትብን እንደማይችል እንድናስብ በማድረግ ሊያታልለን ይሞክራል። ሆኖም ይሖዋ ስሜታቸው የተደቆሰውን አገልጋዮቹን ጨምሮ ለሁሉም አምላኪዎቹ ስላለው ፍቅርና አሳቢነት የሚገልጹ ጥቅሶችን ለእኔ ብለን ማንበባችን እንዲህ ያሉትን ሰይጣናዊ ውሸቶች ለመቃወም ይረዳናል። (መዝ. 34:18፤ 1 ጴጥ. 5:8) በተጨማሪም ይሖዋ ምንጊዜም ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ እርምጃ እንደሚወስድ ካስታወስን የገባውን ቃል በመጠበቅ ረገድ አቻ የሌለው አምላካችን እምነት የሚጣልበት ስለመሆኑ ጥርጣሬ አያድርብንም።—ምሳሌ 3:5, 6

7 ይሁንና የሰይጣን ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው? በእርግጥ ከእኛ የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው? ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበው ሦስተኛ ፈተና የዚህን ጥያቄ መልስ ግልጽ ያደርግልናል።

“አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ”

8. ሰይጣን በሦስተኛው ፈተና ላይ በእርግጥ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው?

8 ማቴዎስ 4:8-11ን አንብብ። ሰይጣን በሦስተኛው ፈተና ላይ ስውር ዘዴ መጠቀሙን ትቶ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ተናገረ። ሰይጣን ለኢየሱስ (በራእይ አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም) “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው”፤ የሚፈጽሙትን መጥፎ ድርጊት ግን አላሳየውም። ከዚያም ኢየሱስን “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። * አዎ፣ ሰይጣን የፈለገው ዋናው ነገር አምልኮ ነበር! የሰይጣን ዓላማ ኢየሱስ ለአባቱ ጀርባውን እንዲሰጥና እሱን እንደ አምላኩ እንዲመለከተው ማድረግ ነበር። ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበለት ግብዣ አቋራጭ መንገድ ሊመስል ይችላል። የእሾህ አክሊል ሳይደረግበት፣ ሳይገረፍ እንዲሁም በእንጨት ላይ ተሰቅሎ መሠቃየት ሳያስፈልገው የመንግሥታትን ሥልጣንና ሀብት በሙሉ ማግኘት እንደሚችል በተዘዋዋሪ መንገድ ገለጸለት። ሰይጣን ያቀረበው ግብዣ በእርግጥም የሚፈትን ነበር፤ ምክንያቱም እነዚህ መንግሥታት በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ናቸው። ኢየሱስም ቢሆን ሰይጣን በዓለም መንግሥታት ላይ ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ ጥያቄ አላነሳም! (ዮሐ. 12:31፤ 1 ዮሐ. 5:19) ደግሞም ሰይጣን፣ ኢየሱስ ለአባቱ ንጹሕ አምልኮ ጀርባውን እንዲሰጥ ማድረግ የሚያስችለው እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም ነገር ከመስጠት አይመለስም ነበር።

9. (ሀ) ሰይጣን ከአምላክ አገልጋዮች የሚፈልገው ነገር ምንድን ነው? ሊፈትነን የሚሞክረውስ እንዴት ነው? (ለ) የምናቀርበው አምልኮ ምን ነገሮችን ይጨምራል? (“አምልኮ ምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

9 በዛሬው ጊዜም ሰይጣን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እሱን እንድናመልከው ይፈልጋል። “የዚህ ሥርዓት አምላክ” እንደመሆኑ መጠን በታላቂቱ ባቢሎን የተወከሉት የሐሰት ሃይማኖቶች የሚያቀርቡት አምልኮ በሙሉ ዞሮ ዞሮ የሚቀርበው ለእሱ ነው። (2 ቆሮ. 4:4) ሆኖም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የሚያቀርቡለት አምልኮ አልበቃው ብሎ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮችም ለአምላክ ፈቃድ ጀርባቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ይፈልጋል። ‘ለጽድቅ ሲሉ መከራ መቀበልን’ የሚጠይቀውን የክርስትና ጎዳና ከመከተል ይልቅ በዚህ ዓለም ውስጥ ሀብትና ሥልጣን ለማግኘት እንድንሯሯጥ ሊያባብለን ይሞክራል። (1 ጴጥ. 3:14) ንጹሕ አምልኮን እንድንተውና የሰይጣን ዓለም ክፍል እንድንሆን በሚቀርብልን ፈተና ከተሸነፍን ሰይጣንን እንደ አምላካችን አድርገን በመቀበል ተደፍተን እንዳመለክነው ይቆጠራል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ፈተና መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

10. ኢየሱስ ለሦስተኛው ፈተና ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? ለምንስ?

10 ኢየሱስ ለሦስተኛው ፈተና ምላሽ የሰጠው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። ፈታኙን ወዲያውኑ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” በማለት ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ከዚያም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ፈተናዎች በቀረቡለት ወቅት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም መለኮታዊውን ስም የያዘ አንድ ጥቅስ ጠቀሰ፤ ከዘዳግም መጽሐፍ ላይ በመጥቀስ “‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏልና” አለው። (ማቴ. 4:10፤ ዘዳ. 6:13) በዚህ መንገድ ኢየሱስ መከራ የሌለበትና የተደላደለ ሕይወት ለመምራት እንዲሁም ከፍ ያለ ሥልጣን ለማግኘት የሚያስችል ሆኖም ለረጅም ጊዜ የማይዘልቅ አካሄድ እንዲከተል የቀረበለትን ግብዣ ውድቅ አድርጓል። ኢየሱስ፣ ሊመለክ የሚገባው አባቱ ብቻ እንደሆነና ሰይጣንን አንድ ጊዜም እንኳ ‘ተደፍቶ ማምለክ’ የእሱ ተገዢ ከመሆን ተለይቶ እንደማይታይ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ከአቋሙ ፍንክች ባለማለት መሠሪ የሆነውን ይህን ፈታኝ አምላኩ አድርጎ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን አሳይቷል። ዲያብሎስም ዕቅዱ እንዳልተሳካለት ሲያይ ኢየሱስን “ትቶት ሄደ።” *

“አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

11. ሰይጣንን መቃወምና የሚያቀርባቸውን ፈተናዎች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

11 እኛም ሰይጣንን መቃወምና እሱ የሚቆጣጠረው ክፉ ዓለም የሚያቀርብልንን ፈተናዎች መቋቋም እንችላለን። ምክንያቱም እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የመምረጥ ነፃነት አለን። ይሖዋ ውድ የሆነውን ይህን ስጦታ ሰጥቶናል። በመሆኑም የትኛውም አካል ሌላው ቀርቶ ኃያልና ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ፈታኙ ሰይጣንም እንኳ ንጹሕ አምልኮን እንድንተው ሊያስገድደን አይችልም። ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ‘በእምነት ጸንተን በመቆም ሰይጣንን ስንቃወም’ እኛም “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” እንዳልነው ይቆጠራል። (1 ጴጥ. 5:9) ኢየሱስ በጥብቅ በተቃወመው ጊዜ ሰይጣን ትቶት እንደሄደ አስታውስ። ለእኛም መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ያዕ. 4:7

የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸውን ፈተናዎች መቋቋም እንችላለን (አንቀጽ 11, 19⁠ን ተመልከት)

የንጹሕ አምልኮ ጠላት

12. በኤደን ገነት ውስጥ ሰይጣን የንጹሕ አምልኮ ጠላት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

12 ሰይጣን ለኢየሱስ ያቀረበለት የመጨረሻው ፈተና የንጹሕ አምልኮ የመጀመሪያ ጠላት እሱ መሆኑን አረጋግጧል። ሰይጣን ለይሖዋ አምልኮ ያለውን ጥላቻ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየው በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤደን ገነት ውስጥ ነበር። ሰይጣን ሔዋንን ያታለላት ሲሆን እሷ ደግሞ አዳምን በማግባባት የይሖዋን ትእዛዝ እንዲጥስ አደረገችው፤ በዚህ መንገድ ሰይጣን ሁለቱም በእሱ አገዛዝና ቁጥጥር ሥር እንዲወድቁ አደረገ። (ዘፍጥረት 3:1-5ን አንብብ፤ 2 ቆሮ. 11:3፤ ራእይ 12:9) አዳምና ሔዋን ወደዚህ የተሳሳተ ውሳኔ የመራቸውን አካል ትክክለኛ ማንነት ላያውቁ ቢችሉም ይህ አካል አምላካቸው ሆኗል፤ እነሱም አምላኪዎቹ ሆነዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን በኤደን ዓመፅ እንዲቀሰቀስ በማድረግ የይሖዋን ሉዓላዊነት ማለትም የመግዛት መብት ከመገዳደር አልፎ በንጹሕ አምልኮ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። እንዴት?

13. ንጹሕ አምልኮ ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት ከተነሳው ጥያቄ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?

13 የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ ከንጹሕ አምልኮ ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው። አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው ‘ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው’ ሉዓላዊው አምላክ ብቻ ነው። (ራእይ 4:11) ይሖዋ ፍጹማን የነበሩትን አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ በኤደን የአትክልት ቦታ ውስጥ ሲያስቀምጣቸው ዓላማው ውሎ አድሮ መላዋ ምድር በፈቃደኝነትና በንጹሕ ልብ ተነሳስተው ንጹሕ አምልኮ በሚያቀርቡለት ፍጹማን ሰዎች እንድትሞላ ነበር። (ዘፍ. 1:28) ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት የተገዳደረው ለሉዓላዊው ጌታ ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለማግኘት ስለተመኘ ነው።—ያዕ. 1:14, 15

14. ሰይጣን በንጹሕ አምልኮ ላይ የሰነዘረው ጥቃት ተሳክቶለታል? አብራራ።

14 ሰይጣን በንጹሕ አምልኮ ላይ የሰነዘረው ጥቃት ተሳክቶለታል? እርግጥ ነው፣ አዳምንና ሔዋንን ከአምላክ ማራቅ ችሏል። ከዚያ ጊዜ ወዲህም ቢሆን ሰይጣን በእውነተኛው አምልኮ ላይ ጦርነት በመክፈት የቻለውን ያህል ብዙ ሰዎች ከይሖዋ አምላክ እንዲርቁ ለማድረግ ሲጥር ቆይቷል። ሰይጣን በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩትን የይሖዋ አምላኪዎች ከመፈተን ወደኋላ ያለበት ጊዜ አልነበረም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ደግሞ የክርስቲያን ጉባኤን የሚበክል ክህደት እንዲስፋፋ በማድረጉ ንጹሕ አምልኮ ፈጽሞ የጠፋ የመሰለበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። (ማቴ. 13:24-30, 36-43፤ ሥራ 20:29, 30) ከሁለተኛው መቶ ዘመን አንስቶ የይሖዋ አምላኪዎች በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ በምታመለክተው በታላቂቱ ባቢሎን መንፈሳዊ ግዞት ሥር የወደቁ ሲሆን ይህም ለረጅም ዘመናት ዘልቋል። ይሁን እንጂ ሰይጣን፣ አምላክ ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ ማክሸፍ አልቻለም። አምላክ ዓላማውን ዳር እንዳያደርስ ምንም ነገር ሊያግደው አይችልም። (ኢሳ. 46:10፤ 55:8-11) ይህ ስሙን የሚመለከት ጉዳይ ነው፤ ይሖዋ ደግሞ መቼም ቢሆን እንደ ስሙ የሚኖር አምላክ ነው። ይሖዋ ምንጊዜም ዓላማውን ዳር ያደርሳል።

የንጹሕ አምልኮ ዋነኛ ጠበቃ

15. ይሖዋ ዓላማው ዳር እንዲደርስና ዓመፀኞቹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ ምን እርምጃ ወሰደ?

15 ይሖዋ ዓላማው ዳር እንዲደርስና ዓመፀኞቹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የሚያደርግ እርምጃ ወዲያውኑ ወሰደ። (ዘፍጥረት 3:14-19ን አንብብ።) ገና አዳምና ሔዋን እዚያው ኤደን ገነት ውስጥ እንዳሉ ይሖዋ ሦስቱ ዓመፀኞች ኃጢአት በሠሩበት ቅደም ተከተል መሠረት መጀመሪያ በሰይጣን፣ ከዚያም በሔዋን፣ በመጨረሻም በአዳም ላይ ፍርድ አስተላለፈ። ይሖዋ በስውር ሆኖ ዓመፁን ለጠነሰሰው ለሰይጣን ባስተላለፈው ፍርድ ላይ ዓመፁ የሚያስከትለውን ውጤት በሙሉ የሚሽር “ዘር” እንደሚመጣ ተነበየ። ይህ ተስፋ የተደረገበት “ዘር” ይሖዋ ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ ዳር በማድረስ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

16. በኤደን ከተነሳው ዓመፅ በኋላ ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ መሥራቱን የቀጠለው እንዴት ነው?

16 ይሖዋ በኤደን ከተነሳው ዓመፅ በኋላም ቢሆን ዓላማውን ዳር ለማድረስ መሥራቱን ቀጥሏል። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንደምንመለከተው ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዲያመልኩት የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል። (ዕብ. 11:4 እስከ 12:1) በተጨማሪም ኢሳይያስን፣ ኤርምያስንና ሕዝቅኤልን ጨምሮ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋም የሚናገሩ አስደሳች ትንቢቶችን እንዲጽፉ በመንፈሱ መርቷቸዋል። ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም የሚናገረው ሐሳብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ነው። እነዚህ ትንቢቶች በሙሉ የሚፈጸሙት ተስፋ በተደረገበት “ዘር” አማካኝነት ነው፤ ይህ “ዘር” በዋነኝነት የሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። (ገላ. 3:16) ኢየሱስ ለሦስተኛው ፈተና ከሰጠው መልስ በግልጽ እንደምንመለከተው እሱ የንጹሕ አምልኮ ዋነኛ ጠበቃ ነው። ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም የሚገልጹ ትንቢቶችን እንዲያስፈጽም ይሖዋ የመረጠው ኢየሱስን ነው። (ራእይ 19:10) የአምላክን ሕዝብ ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ በማውጣት ንጹሕ አምልኮ ወደ ትክክለኛ ቦታው እንዲመለስ የሚያደርገው እሱ ነው።

አንተስ ከንጹሕ አምልኮ ጎን ትቆማለህ?

17. ስለ ንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋም የሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው?

17 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ስለ ንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋም የሚገልጹ ትንቢቶች መመርመር በጣም የሚያስደስትና እምነት የሚያጠናክር ነው። ሁላችንም በሰማይና በምድር ያሉ ፍጥረታት በሙሉ በአንድነት ለሉዓላዊው ጌታ ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ የሚያቀርቡበትን ጊዜ ስለምንናፍቅ እንዲህ ያሉት ትንቢቶች ትኩረታችንን ይስቡታል። በተጨማሪም እነዚህ ትንቢቶች ልባችን በተስፋ እንዲሞላ ያደርጋሉ፤ ምክንያቱም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ የሚያጽናኑ ተስፋዎች ከእነዚህ ትንቢቶች ጋር የተያያዙ ናቸው። ይሖዋ የሰጠን ተስፋዎች ሲፈጸሙ ለማየት የማይጓጓ ማን አለ? ሁላችንም በሞት ያጣናቸው የምንወዳቸው ዘመዶቻችን ከሞት ሲነሱና መላዋ ምድር ገነት ስትሆን ለማየት እንዲሁም ፍጹም ጤንነት ኖሮን ለዘላለም ለመኖር እንደምንናፍቅ የታወቀ ነው።—ኢሳ. 33:24፤ 35:5, 6፤ ራእይ 20:12, 13፤ 21:3, 4

18. በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

18 ይህ መጽሐፍ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን አስደሳች ትንቢቶች ያብራራል። ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል ብዙዎቹ ስለ ንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋም የሚገልጹ ናቸው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሕዝቅኤል ትንቢቶች ከሌሎች ትንቢቶች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ፣ በክርስቶስ አማካኝነት እንዴት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙና እኛን በግል እንዴት እንደሚመለከቱን እንመረምራለን።—“የሕዝቅኤል መጽሐፍ አጠቃላይ ይዘት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

19. ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? ለምንስ?

19 ሰይጣን ጥንት በ29 ዓ.ም. በይሁዳ ምድረ በዳ ኢየሱስ ለንጹሕ አምልኮ ጀርባውን እንዲሰጥ ለመፈተን ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። ዛሬም ቢሆን ሰይጣን እኛን ከእውነተኛው አምልኮ ለማራቅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጦ ተነስቷል። እኛስ እንደ ኢየሱስ የሰይጣንን ጥቃት ማክሸፍ እንችል ይሆን? (ራእይ 12:12, 17) ይህ መጽሐፍ ፈታኙን ለመቃወም ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እንደሚያጠናክርልን ተስፋ እናደርጋለን። ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ” ከሚሉት ቃላት ጋር ሙሉ በሙሉ እንደምንስማማ የሚያሳይ ይሁን። እንዲህ ካደረግን የይሖዋ ክብራማ ዓላማ ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ይኸውም በሰማይና በምድር ያሉ ሁሉ አምልኮ ለሚገባው ለይሖዋ ከንጹሕ ልብ የመነጨ ንጹሕ አምልኮ በአንድነት የሚያቀርቡበትን ጊዜ የማየት አጋጣሚ እናገኛለን።

^ አን.5 አንዳንዶች ይሖዋ የሚለው ስም ትርጉም “እንዲሆን ያደርጋል” ማለት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ትርጉም ይሖዋ ፈጣሪ መሆኑንና ዓላማውን ዳር የማድረስ ችሎታ እንዳለው ጥሩ አድርጎ ይገልጻል።

^ አን.8 አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ሰይጣን የተናገራቸውን ቃላት በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ጥያቄው አዳምና ሔዋን እንደወደቁበት እንደ መጀመሪያው ፈተና . . . ከሰይጣን ፈቃድና ከአምላክ ፈቃድ አንዱን የመምረጥ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ወይ ለዚህ ወይ ለዚያ አምልኮ ከማቅረብ ጋር የተያያዘ ነው። ሰይጣን ራሱን በእውነተኛው አምላክ ቦታ አድርጎ መመለክ ይፈልጋል።”

^ አን.10 የሉቃስ ወንጌል ፈተናዎቹን የሚያስቀምጥበት ቅደም ተከተል ከማቴዎስ ወንጌል የተለየ ነው። ይሁን እንጂ የማቴዎስ ዘገባ በጊዜ ቅደም ተከተል የተቀመጠ ይመስላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት። (1) ማቴዎስ ሁለተኛውን ፈተና የጀመረው “ከዚያም” በማለት ነው። ይህም ቀጥሎ የተከናወነ ድርጊት እንደሆነ ይጠቁማል። (2) ሰይጣን ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል የመጀመሪያውን ትእዛዝ የሚያስጥሰውን ግልጽ ፈተና ያቀረበው “የአምላክ ልጅ ከሆንክ” በሚሉት ቃላት የሚጀምሩትን ሁለት ስውር ፈተናዎች ካቀረበ በኋላ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስላል። (ዘፀ. 20:2, 3) (3) ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” በማለት የተናገረው ሦስተኛውና የመጨረሻው ፈተና በቀረበለት ጊዜ ነው የሚለው ሐሳብ ይበልጥ አሳማኝ ነው።—ማቴ. 4:5, 10, 11