በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 11

“ጠባቂ አድርጌ ሾሜሃለሁ”

“ጠባቂ አድርጌ ሾሜሃለሁ”

ሕዝቅኤል 33:7

ፍሬ ሐሳብ፦ ይሖዋ ጠባቂ ሾመ፤ የተጣለበትን ኃላፊነትም ገለጸለት

1. ይሖዋ የሾማቸው ጠባቂዎች ወይም ነቢያት ምን ሲያከናውኑ እንደነበረና ከዚያ በኋላ ምን ነገሮች እንደተፈጸሙ ግለጽ።

አንድ ጠባቂ በኢየሩሳሌም ቅጥር ላይ ቆሟል፤ ጀንበሯ በማዘቅዘቅ ላይ ነች። ጠባቂው ዓይኑን ከጨረሩ ከልሎ ከአድማስ ባሻገር ያለውን ለመቃኘት እየሞከረ ነው። በድንገት መለከቱን ያነሳና በኃይል አየር ስቦ መለከቱን በመንፋት የባቢሎን ሠራዊት እየመጣ መሆኑን የሚገልጽ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ያሰማል! ይሁን እንጂ ግድየለሾቹ የከተማዋ ነዋሪዎች የጠባቂውን የመለከት ድምፅ ሰምተው እርምጃ መውሰድ የሚችሉበት ጊዜ አልፎባቸዋል። ይሖዋ የሾማቸው ጠባቂዎች ወይም ነቢያት ይህ ቀን እንደሚመጣ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል፤ ሕዝቡ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። አሁን የባቢሎናውያን ሠራዊት ከተማዋን ከቧል። ወታደሮቹ ለበርካታ ወራት ኢየሩሳሌምን ከበው ከቆዩ በኋላ የከተማይቱን ቅጥሮች ጥሰው በመግባት ቤተ መቅደሱን አወደሙ፤ እምነት የለሽና ጣዖት አምላኪ የሆኑትን የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ገደሉ፤ የቀሩትንም ማርከው ወሰዱ።

2, 3. (ሀ) የምድር ነዋሪዎች በአሁኑ ጊዜ ምን ሁኔታ ከፊታቸው ተደቅኗል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ የሚጠቀምባቸው የቅጣት ፍርድ አስፈጻሚ ኃይሎች እምነት የለሽ ከሆኑት የምድር ነዋሪዎች ጋር ለመዋጋት እየገሰገሱ ነው። (ራእይ 17:12-14) ይህ ውጊያ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቀው ታላቅ መከራ መቋጫ ይሆናል። (ማቴ. 24:21) ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች፣ ይሖዋ የሾማቸው ጠባቂዎች የሚያሰሙትን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እርምጃ መውሰድ የሚችሉበት ጊዜ አሁንም ቢሆን አላለፈባቸውም።

3 ይሖዋ ጠባቂዎችን እንዲሾም ያነሳሳው ምንድን ነው? አንድ ጠባቂ የሚያውጀው ምን ዓይነት መልእክት ነው? በተለያዩ ወቅቶች እንደ ጠባቂ ሆነው ያገለገሉት እነማን ናቸው? እኛስ በዚህ ሥራ ምን ድርሻ አለን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እስቲ እንመርምር።

“ማስጠንቀቂያዬን ንገራቸው”

4. ይሖዋ ጠባቂዎችን የሾመው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 ሕዝቅኤል 33:7ን አንብብ። በጥንት ዘመን ጠባቂዎች የነዋሪዎቹን ደህንነት ለመጠበቅ በከተማ ቅጥሮች ላይ ይቆሙ ነበር። አንዲት ከተማ ጠባቂዎች ያሏት መሆኑ የከተማዋ ገዢ ለተገዢዎቹ ደህንነት እንደሚያስብ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነበር። ጠባቂው የሚያሰማው የመለከት ድምፅ እንቅልፍ ላይ ያሉትን ነዋሪዎች ሊያስደነግጥ ቢችልም ማስጠንቀቂያውን ሰምተው እርምጃ ለሚወስዱ ሰዎች ሕይወታቸውን ያተርፍላቸዋል። ይሖዋም ቢሆን ለእስራኤላውያን ጠባቂዎችን የሾመው የጥፋት መልእክት በማስነገር ሊያስፈራራቸው ስለፈለገ ሳይሆን ለሕዝቦቹ ስለሚያስብና ሕይወታቸውን እንዲያተርፉ ስለሚፈልግ ነው።

5, 6. የይሖዋ ፍትሕ የተገለጸበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

5 ይሖዋ ሕዝቅኤልን ጠባቂ አድርጎ መሾሙ ስለ ባሕርያቱ አንዳንድ ነገሮች ያስገነዝበናል። ስለ እነዚህ ባሕርያት የምናገኘው ግንዛቤ በጣም የሚያጽናና ነው። እስቲ ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ሁለቱን ብቻ እንመልከት።

6 ፍትሕ፦ ይሖዋ እያንዳንዱን ሰው በግለሰብ ደረጃ ተመልክቶ ፍርድ የሚሰጥ መሆኑ ፍትሑን ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ የሕዝቅኤልን መልእክት ከሰሙት ሰዎች አብዛኞቹ መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑም ይሖዋ ሁሉንም እስራኤላውያን በጅምላ እንደ ዓመፀኛ አድርጎ አልቆጠራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ግለሰብ በተናጠል ምን ምላሽ እንደሚሰጥ ማወቅ ፈልጓል። “ክፉ ሰው” እና “ጻድቅ ሰው” የሚሉትን አገላለጾች በተደጋጋሚ መጠቀሙ ይህን ያሳያል። ስለዚህ ይሖዋ ፍርድ የሚሰጠው እያንዳንዱ ግለሰብ ለመልእክቱ በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ መረዳት እንችላለን።—ሕዝ. 33:8, 18-20

7. ይሖዋ ለሰዎች ፍርድ የሚሰጠው በምን ላይ ተመሥርቶ ነው?

7 ይሖዋ ለሰዎች ፍርድ የሚሰጥበት መንገድም ፍትሑን ያሳያል። ይሖዋ ለሰዎች ፍርድ የሚሰጠው ቀደም ሲል ባደረጓቸው ነገሮች መሠረት ሳይሆን አሁን እየተነገራቸው ላለው ማስጠንቀቂያ በሚሰጡት ምላሽ ላይ ተመሥርቶ ነው። ይሖዋ ለሕዝቅኤል “ክፉውን ሰው ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልኩት ጊዜ ከኃጢአቱ ቢመለስና ፍትሐዊና ጽድቅ የሆነ ነገር ቢያደርግ . . . በእርግጥ በሕይወት ይኖራል” ብሎታል። አክሎም የሚከተለውን አስገራሚ ሐሳብ ተናግሯል፦ “ከሠራቸው ኃጢአቶች ውስጥ አንዱም አይታወስበትም።” (ሕዝ. 33:14-16) በሌላ በኩል ደግሞ የጽድቅ መንገድ ይከተሉ የነበሩ ሰዎች፣ ቀደም ሲል ያሳዩት ታዛዥነት በአሁኑ ጊዜ ለሚፈጽሙት የዓመፅ ድርጊት ማካካሻ እንደሚሆንላቸው ሊጠብቁ አይችሉም። ይሖዋ አንድ ሰው “በገዛ ጽድቁ ታምኖ መጥፎ ነገር ቢፈጽም፣ ከጽድቅ ሥራው መካከል አንዱም አይታሰብም፤ ይልቁንም መጥፎ ነገር በመፈጸሙ ይሞታል” በማለት ተናግሯል።—ሕዝ. 33:13

8. ይሖዋ ጥፋት ከማምጣቱ በፊት አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ስለ ፍትሑ ምን ያስተምረናል?

8 ይሖዋ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በበቂ መጠን ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ፍትሑን የሚያሳይ ሌላ ማስረጃ ነው። ሕዝቅኤል ሥራውን የጀመረው የባቢሎናውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከማጥፋቱ ከስድስት ዓመት ገደማ በፊት ነው። ይሁን እንጂ የአምላክ ሕዝቦች ለሠሩት ጥፋት ቅጣት እንደሚደርስባቸው የሚገልጸውን ማስጠንቀቂያ ያሰማው የመጀመሪያው ሰው ሕዝቅኤል አልነበረም። ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት ከመቶ የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ይሖዋ ነቢያቱን ሆሴዕን፣ ኢሳይያስን፣ ሚክያስን፣ ኦዴድንና ኤርምያስን ጠባቂዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ልኮ ነበር። ይሖዋ እስራኤላውያንን እንደሚከተለው በማለት በኤርምያስ በኩል አስታውሷቸዋል፦ “እኔም በእናንተ ላይ ጠባቂዎችን ሾምኩ፤ ጠባቂዎቹም ‘የቀንደ መለከቱን ድምፅ በትኩረት አዳምጡ!’ አሉ።” (ኤር. 6:17) በመጨረሻ ባቢሎናውያን የይሖዋን ቅጣት ባስፈጸሙበት ወቅት ለሞቱት ሰዎች ሕይወት ይሖዋም ሆነ ጠባቂዎቹ ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም።

9. ይሖዋ ታማኝ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

9 ፍቅር፦ ይሖዋ ጠባቂዎቹን በመላክ፣ ጻድቃን የሆኑትን ብቻ ሳይሆን ልቡን እጅግ ያሳዘኑትንና ስሙን ያጎደፉትን ክፉዎች ጭምር ማስጠንቀቁ ታማኝ ፍቅሩን የሚያሳይ ነው። እስቲ አስበው፣ እስራኤላውያን የይሖዋ ሕዝቦች በመባል ይታወቁ ነበር። እነሱ ግን በተደጋጋሚ ጀርባቸውን ለይሖዋ በመስጠት ወደ ሐሰት አማልክት ዘወር ብለዋል! ይሖዋ እስራኤላውያን በፈጸሙት ክህደት ምክንያት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ለመግለጽ ብሔሩን አመንዝራ ከሆነች ሚስት ጋር አመሳስሎታል። (ሕዝ. 16:32) ያም ሆኖ ይሖዋ ሕዝቦቹን ወዲያውኑ እርግፍ አድርጎ አልተዋቸውም። ፍላጎቱ እነሱን መበቀል ሳይሆን ከእነሱ ጋር መታረቅ ነበር። እነሱን በሰይፍ ለመቅጣት ከመነሳቱ በፊት መለወጥ የሚችሉበት ብዙ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። ለምን? “በክፉው ሰው ሞት ደስ አልሰኝም፤ ይልቁንም ክፉው ሰው አካሄዱን አስተካክሎ በሕይወት እንዲኖር እፈልጋለሁ” በማለት ለሕዝቅኤል ነግሮታል። (ሕዝ. 33:11) ይሖዋ ጥንትም ሆነ ዛሬ የሚሰማው እንደዚህ ነው።—ሚል. 3:6

10, 11. ይሖዋ ሕዝቦቹን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

10 ይሖዋ እስራኤላውያንን ከያዘበት ፍትሐዊና ፍቅራዊ የሆነ መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የምንሰብክላቸውን ሰዎች በጅምላ ከመፈረጅ ይልቅ እያንዳንዱን ሰው በግለሰብ ደረጃ ማየት እንደሚኖርብን እንማራለን። አንድን ሰው በቀድሞ ምግባሩ፣ በብሔሩ፣ በጎሳው፣ በኑሮ ደረጃው ወይም በቋንቋው ምክንያት መልእክታችንን ሊሰማ እንደማይገባው አድርገን ብንፈርጀው እንዴት ያለ አሳዛኝ ስህተት ይሆናል! ይሖዋ ለሐዋርያው ጴጥሮስ “አምላክ እንደማያዳላ . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት” እንዳለው አስተምሮታል፤ ይህ ትምህርት በዛሬው ጊዜም በጣም አስፈላጊ ነው።—ሥራ 10:34, 35

ሰዎችን የምንመለከተው ይሖዋ እነሱን በሚመለከትበት መንገድ ነው? (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

11 በተጨማሪም ራሳችንን ሁልጊዜ መመርመር እንደሚያስፈልገን እንማራለን፤ ቀደም ሲል የሠራናቸው የጽድቅ ሥራዎች አሁን ለምንፈጽመው መጥፎ ድርጊት ማካካሻ አይሆኑም። እንደምንሰብክላቸው ሰዎች ሁሉ እኛም የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለን ማስታወስ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ የሰጠው ምክር ለእኛም በእኩል መጠን ይሠራል፤ እንዲህ ብሏል፦ “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም።” (1 ቆሮ. 10:12, 13) ጥሩ ሥራ ስለምንሠራ ብቻ፣ መጥፎ ድርጊት ብንፈጽምም ቅጣት እንደማይደርስብን አድርገን በማሰብ ‘በገዛ ጽድቃችን መታመን’ ፈጽሞ አንፈልግም። (ሕዝ. 33:13) የቱንም ያህል ለረጅም ዓመት ይሖዋን ያገለገልን ብንሆን ምንጊዜም ትሑቶችና ታዛዦች መሆናችን በጣም አስፈላጊ ነው።

12. ቀደም ሲል ከባድ ኃጢአት ፈጽመን ከነበረ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

12 በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በፊት በሠራናቸው ከባድ ኃጢአቶች ምክንያት የጸጸት ስሜት የሚሰማን ቢሆንስ? የሕዝቅኤል መልእክት ይሖዋ ንስሐ የማይገቡ ሰዎችን እንደሚቀጣ ያስተምረናል። ይሁንና ይሖዋ በዋነኝነት የፍቅር እንጂ የበቀል አምላክ እንዳልሆነም ተምረናል። (1 ዮሐ. 4:8) ንስሐ እስከገባንና ይህንንም በድርጊታችን እስካሳየን ድረስ አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን እንደማይችል ሆኖ ሊሰማን አይገባም። (ያዕ. 5:14, 15) ይሖዋ መንፈሳዊ ምንዝር የፈጸሙትን እስራኤላውያን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደነበር ሁሉ እኛንም ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው።—መዝ. 86:5

“ለሕዝብህ ልጆች ተናገር”

13, 14. (ሀ) ይሖዋ የሾማቸው ጠባቂዎች ምን ዓይነት መልእክት ያውጁ ነበር? (ለ) ኢሳይያስ ምን ዓይነት መልእክት አውጇል?

13 ሕዝቅኤል 33:2, 3ን አንብብ። ይሖዋ የሾማቸው ጠባቂዎች የሚያውጁት ምን ዓይነት መልእክት ነበር? ዋነኛ ሥራቸው ማስጠንቀቂያ ማወጅ ነበር። ነገር ግን ምሥራችም ያሰሙ ነበር። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

14 ከ778 እስከ 732 ዓ.ዓ. በነቢይነት ያገለገለው ኢሳይያስ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በቁጥጥራቸው ሥር እንደሚያደርጉና ነዋሪዎቿንም በግዞት እንደሚወስዱ አስጠንቅቆ ነበር። (ኢሳ. 39:5-7) ይሁን እንጂ በመንፈስ ተመርቶ የሚከተለውን ሐሳብም ጽፏል፦ “ስሚ! ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ። በአንድነት ሆነው እልል ይላሉ፤ ይሖዋ ጽዮንን መልሶ ሲሰበስብ በግልጽ ያያሉና።” (ኢሳ. 52:8) ኢሳይያስ እውነተኛው አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም በመናገር ከሁሉ የላቀ ምሥራች አብስሯል!

15. ኤርምያስ ያወጀው መልእክት ምን ነበር?

15 ከ647 እስከ 580 ዓ.ዓ. በነቢይነት ያገለገለው ኤርምያስ በብዙዎች ዘንድ እንደ “መዓት ነጋሪ” ይቆጠር ነበር። በእርግጥም ኤርምያስ ይሖዋ ሊያመጣ ስላሰበው ጥፋት ክፉዎቹን እስራኤላውያን በማስጠንቀቅ አስደናቂ ሥራ እንዳከናወነ አይካድም። * ሆኖም የአምላክ ሕዝቦች ወደ ምድራቸው እንደሚመለሱና በዚያም ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም የሚገልጽ ምሥራችም አውጇል።—ኤር. 29:10-14፤ 33:10, 11

16. የሕዝቅኤል መልእክት በባቢሎን የነበሩትን ግዞተኞች የጠቀማቸው እንዴት ነው?

16 ሕዝቅኤል ጠባቂ ሆኖ የተሾመው በ613 ዓ.ዓ. ሲሆን ቢያንስ እስከ 591 ዓ.ዓ. ድረስ በዚህ ምድቡ ሲያገለግል ቆይቷል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 እና 6 ላይ እንደተብራራው ሕዝቅኤል በእስራኤላውያን ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት በቅንዓት በማወጅ፣ በጥፋቱ የተነሳ በሚሞቱት ሰዎች ደም ተጠያቂ ከመሆን ራሱን ነፃ አድርጓል። በዚህ መንገድ ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ ከሃዲዎቹን የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንደሚቀጣ በባቢሎን የነበሩትን ግዞተኞች ከማስጠንቀቅ ያለፈ ነገር አከናውኗል፤ እግረ መንገዱንም እነዚህ ግዞተኞች በመንፈሳዊ ሕያው ሆነው እንዲቀጥሉና ወደፊት ለሚጠብቃቸው ሥራ ብቁ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። የሰባው ዓመት የግዞት ዘመን ሲያበቃ ይሖዋ አይሁዳውያን ቀሪዎችን ወደ እስራኤል ምድር ይመልሳቸዋል። (ሕዝ. 36:7-11) ከእነዚህ ቀሪዎች መካከል አብዛኞቹ፣ ለሕዝቅኤል መልእክት ትኩረት የሰጡ ሰዎች ልጆችና የልጅ ልጆች እንደሚሆኑ ጥያቄ የለውም። በዚህ መጽሐፍ ክፍል 3 ውስጥ በሚገኙት ሌሎች ምዕራፎች ላይ በሰፊው እንደተብራራው ሕዝቅኤል ንጹሕ አምልኮ በኢየሩሳሌም መልሶ እንደሚቋቋም የሚያረጋግጥ ምሥራች አውጇል።

17. ይሖዋ ጠባቂዎችን የሾመው በየትኞቹ ወቅቶች ላይ ነው?

17 ይሖዋ ጠባቂ አድርጎ የሾመው፣ ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. በጠፋችበት ዘመን አካባቢ ለሕዝቦቹ የእሱን መልእክት ይናገሩ የነበሩትን እነዚህን ነቢያት ብቻ ነው? አይደለም። በታሪክ ዘመናት ሁሉ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንድ ወሳኝ ክንውን ከመከሰቱ በፊት ክፉዎችን ለማስጠንቀቅና ምሥራች ለማወጅ ጠባቂዎችን ይሾም ነበር።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ጠባቂዎች

18. መጥምቁ ዮሐንስ ምን ሥራ አከናውኗል?

18 በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጥምቁ ዮሐንስ የጠባቂነት ሥራ ሠርቷል። አምላክ ሥጋዊ እስራኤላውያንን እንደ ሕዝቦቹ አድርጎ መመልከቱን የሚያቆምበት ጊዜ እንደቀረበ ያስጠነቅቅ ነበር። (ማቴ. 3:1, 2, 9-11) ነገር ግን ዮሐንስ ያከናወነው ይህን ብቻ አልነበረም። ለመሲሑ መንገድ እንደሚያዘጋጅ በትንቢት የተነገረለት “መልእክተኛ” ዮሐንስ መሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል። (ሚል. 3:1፤ ማቴ. 11:7-10) ይህ ሥራ “የአምላክ በግ” የሆነው ኢየሱስ እንደመጣና “የዓለምን ኃጢአት” እንደሚያስወግድ የሚገልጸውን ምሥራች መናገርን ያካትት ነበር።—ዮሐ. 1:29, 30

19, 20. ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጠባቂ ሆነው ያገለገሉት እንዴት ነበር?

19 ጠባቂ ሆነው ከተሾሙት ሰዎች ሁሉ የላቀው ኢየሱስ ነው። እንደ ሕዝቅኤል ሁሉ እሱም የተላከው ወደ “እስራኤል ቤት” ነበር። (ሕዝ. 3:17፤ ማቴ. 15:24) ኢየሱስ፣ አምላክ ሥጋዊ እስራኤላውያንን እንደ ሕዝቦቹ አድርጎ መመልከቱን የሚያቆምበት ጊዜ እንደቀረበና ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ አስጠንቅቋል። (ማቴ. 23:37, 38፤ 24:1, 2፤ ሉቃስ 21:20-24) ይሁን እንጂ ዋነኛ ሥራው ምሥራች ማወጅ ነበር።—ሉቃስ 4:17-21

20 ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ “ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። (ማቴ. 24:42) እነሱም ትእዛዙን በመከተል ጠባቂ ሆነው አገልግለዋል፤ ይሖዋ ሥጋዊ እስራኤላውያንን እንደ ሕዝቦቹ አድርጎ ማየት እንዳቆመና የኢየሩሳሌምን ከተማ እንደተዋት የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ይናገሩ ነበር። (ሮም 9:6-8፤ ገላ. 4:25, 26) ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ሲል እንደነበሩት ጠባቂዎች ሁሉ ምሥራችም ያውጁ ነበር። ይህ ምሥራች፣ በመንፈስ በተቀባው የአምላክ እስራኤል ውስጥ አሕዛብም መካተት እንደጀመሩና ክርስቶስ በምድር ላይ ንጹሕ አምልኮን መልሶ በሚያቋቁምበት ጊዜ እነሱም የበኩላቸውን ድርሻ የማበርከት መብት እንደሚያገኙ የሚገልጸውን አስደሳች መልእክት የሚጨምር ነበር።—ሥራ 15:14፤ ገላ. 6:15, 16፤ ራእይ 5:9, 10

21. ጳውሎስ ጠባቂ ሆኖ በማገልገል ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?

21 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ጠባቂዎች መካከል ሐዋርያው ጳውሎስ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ጳውሎስ የተጣለበትን ኃላፊነት አክብዶ ተመልክቶታል። እንደ ሕዝቅኤል ሁሉ እሱም ኃላፊነቱን በሚገባ ሳይወጣ ቢቀር በደም ዕዳ እንደሚጠየቅ ያውቅ ነበር። (ሥራ 20:26, 27) እንደ ሌሎቹ ጠባቂዎች ሁሉ ጳውሎስም ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ ምሥራችም አውጇል። (ሥራ 15:35፤ ሮም 1:1-4) እንዲያውም “ምሥራች ይዞ የሚመጣ . . . በተራሮች ላይ እግሮቹ እንዴት ያማሩ ናቸው!” የሚለውን የኢሳይያስ ትንቢት ከጠቀሰ በኋላ ይህ ትንቢት የክርስቶስ ተከታዮች የሚያከናውኑትን ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ ሥራ እንደሚያመለክት በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ጽፏል።—ኢሳ. 52:7, 8፤ ሮም 10:13-15

22. ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ምን ተከሰተ?

22 ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ክህደት ተስፋፋ። (ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰ. 2:3-8) ስንዴውና እንክርዳዱ አብረው ባደጉበት ረጅም ዘመን ውስጥ፣ በስንዴ የተመሰሉት ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች በእንክርዳድ በተመሰሉት አስመሳይ ክርስቲያኖች በመዋጣቸው ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው ግልጽ መልእክት በሐሰት ትምህርቶች ተሸፍኖ ቆየ። (ማቴ. 13:36-43) ይሁን እንጂ ይሖዋ በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ ግልጽ ማስጠንቀቂያ የሚያሰሙና ምሥራቹን የሚያውጁ ጠባቂዎችን በመሾም ዳግመኛ ፍቅሩንና ፍትሑን አሳየ። ታዲያ ይህን የጠባቂነት ኃላፊነት ሲወጡ የተገኙት እነማን ናቸው?

ይሖዋ ክፉዎችን የሚያስጠነቅቁ ጠባቂዎችን ዳግመኛ አስነሳ

23. ቻርልስ ቴዝ ራስልና የሥራ ባልደረቦቹ ምን ሚና ተጫውተዋል?

23 ከ1914 በፊት በነበሩት ዓመታት ቻርልስ ቴዝ ራስልና የሥራ ባልደረቦቹ መሲሐዊው መንግሥት ከመቋቋሙ በፊት ‘መንገድ የሚጠርግ መልእክተኛ’ በመሆን አገልግለዋል። * (ሚል. 3:1) በተጨማሪም ይህ ቡድን የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የተባለውን መጽሔት ተጠቅሞ ስለ መጪው የአምላክ ፍርድ በማስጠንቀቅና የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጅ የጠባቂነት ሥራ አከናውኗል።

24. (ሀ) ታማኙ ባሪያ ጠባቂ ሆኖ ያገለገለው እንዴት ነው? (ለ) ቀደም ባሉት ዘመናት ከነበሩት ጠባቂዎች ምን ትምህርት አግኝተሃል? (“ምሳሌ የሚሆኑ አንዳንድ ጠባቂዎች” የሚለውን ሰንጠረዥ ተመልከት።)

24 መንግሥቱ ከተቋቋመ በኋላ ኢየሱስ ጥቂት ወንድሞችን ያቀፈን አንድ ቡድን ታማኝና ልባም ባሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ሾመ። (ማቴ. 24:45-47) አሁን የበላይ አካል ተብሎ የሚታወቀው ታማኝ ባሪያ ከዚያ ጊዜ አንስቶ የጠባቂነት ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል። ይህ ባሪያ ‘አምላክ ስለሚበቀልበት ቀን’ የማስጠንቀቁንም ሆነ ‘ይሖዋ በጎ ፈቃድ ስለሚያሳይበት ዓመት’ የማወጁን ሥራ ግንባር ቀደም ሆኖ በመምራት ላይ ይገኛል።—ኢሳ. 61:2፤ 2 ቆሮንቶስ 6:1, 2⁠ንም ተመልከት።

25, 26. (ሀ) የክርስቶስ ተከታዮች በሙሉ ምን ይጠበቅባቸዋል? ይህን ማድረግ የሚችሉትስ እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመረምራለን?

25 ግንባር ቀደም ሆኖ የጠባቂነት ሥራ የሚያከናውነው ታማኙ ባሪያ ቢሆንም ኢየሱስ “ሁሉም” ተከታዮቹ ‘ነቅተው እንዲጠብቁ’ አዟል። (ማር. 13:33-37) በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን በመኖርና በዘመናችን ያለውን ጠባቂ በታማኝነት በመደገፍ ይህን ትእዛዝ እንፈጽማለን። ንቁ መሆናችንን የምናሳየው የመስበክ ኃላፊነታችንን በመወጣት ነው። (2 ጢሞ. 4:2) ይህን ሥራ እንድናከናውን የሚያነሳሳን ምንድን ነው? አንዱ ምክንያት የሰዎችን ሕይወት ለማዳን ያለን ፍላጎት ነው። (1 ጢሞ. 4:16) በዘመናችን ያለው ጠባቂ እያስተላለፈ ያለውን ማስጠንቀቂያ ችላ ያሉ እጅግ ብዙ ሰዎች በቅርቡ ጥፋት ይደርስባቸዋል። (ሕዝ. 3:19) በዚህ ሥራ እንድንካፈል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ግን ንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋሙን የሚገልጸውን ከሁሉ የላቀ ምሥራች ለሌሎች ለመንገር ያለን ፍላጎት ነው። በዚህ ዘመን ማለትም ‘ይሖዋ በጎ ፈቃድ በሚያሳይበት ዓመት’ ብዙ ሰዎች ፍትሐዊና አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን አብረውን ማምለክ የሚችሉበት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል። በቅርቡ፣ ከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ የሚተርፉ የምድር ሕዝቦች በሙሉ ምሕረት የሚንጸባረቅበት የክርስቶስ አገዛዝ ከሚያስገኛቸው በረከቶች ተካፋይ ይሆናሉ። ታዲያ እንዲህ ያለውን አስደሳች ምሥራች በማወጅ ላይ የሚገኘውን በዘመናችን ያለውን ጠባቂ ከመደገፍ እንዴት ወደኋላ ልንል እንችላለን!—ማቴ. 24:14

ምሥራቹን በማወጅ በዘመናችን ያለውን ጠባቂ በደስታ እንደግፋለን (አንቀጽ 25⁠ን ተመልከት)

26 ይህ ክፉ ሥርዓት ከማለቁ በፊትም ቢሆን ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሕዝቡን አንድ አድርጓል። የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህ የተከናወነው እንዴት እንደሆነ ያብራራል፤ ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ስለ ሁለት በትሮች የሚገልጸውን ትንቢት እንመረምራለን።

^ አን.15 “ጥፋት” የሚለው ቃል በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ ከ70 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል።

^ አን.23 ስለዚህ ትንቢትና ፍጻሜውን ስላገኘበት መንገድ ማብራሪያ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን “መንግሥቱ በሰማይ ተወለደ” የሚለውን ምዕራፍ 2⁠ን ተመልከት።