በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 13

“ስለ ቤተ መቅደሱ ግለጽላቸው”

“ስለ ቤተ መቅደሱ ግለጽላቸው”

ሕዝቅኤል 43:10

ፍሬ ሐሳብ፦ ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ያለው ትርጉም

1-3. (ሀ) ሕዝቅኤል ግዙፍ ስለሆነው ቤተ መቅደስ ያየው ራእይ አጽናንቶት መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

ሕዝቅኤል አሁን 50 ዓመት ሆኖታል። ያለፉትን 25 ዓመታት ያሳለፈው በግዞት ነው። በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ የፍርስራሽ ክምር ከሆነ ቆይቷል። ሕዝቅኤል በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ካህን ሆኖ ለማገልገል ተስፋ ያደርግ ከነበረ ይህ ምኞቱ መና ሆኖ ቀርቷል። የግዞቱ ዘመን የሚያበቃው ገና ከ56 ዓመት ገደማ በኋላ ነው፤ በመሆኑም ሕዝቅኤል ቤተ መቅደሱ ዳግመኛ ተገንብቶ ማየት ይቅርና የይሖዋ ሕዝቦች ወደ አገራቸው ተመልሰው ለማየት የሚያስችል ዕድሜ እንደሌለው ያውቃል። (ኤር. 25:11) ይህን ሁሉ ሲያስብ ልቡ አዝኖ ይሆን?

2 ይሖዋ በዚህ ጊዜ ላይ ለዚህ ታማኝ ሰው ብዙ ዝርዝር ጉዳይ የያዘ አጽናኝና ተስፋ ሰጪ የሆነ ራእይ ማሳየቱ እንዴት ያለ ደግነት ነው! ነቢዩ በዚህ ራእይ አማካኝነት በትውልድ አገሩ ወደሚገኝ አንድ ትልቅ ተራራ ተወሰደ። በዚህ ተራራ ላይ ሳለ “መዳብ የሚመስል መልክ ካለው አንድ ሰው” ጋር ተገናኘ። ከሕዝቅኤል ጋር የተገናኘው ይህ መልአክ ሕዝቅኤልን አንድን ግዙፍ ቤተ መቅደስ እያዘዋወረ አስጎበኘው። (ሕዝቅኤል 40:1-4ን አንብብ።) ሁሉም ነገር በእውን ያለ ይመስላል! ሕዝቅኤል ራእዩን ማየቱ እምነቱን አጠናክሮለት፣ አስደንቆትና ምናልባትም ትንሽ ግራ አጋብቶት ሊሆን ይችላል። በራእይ የሚያየው ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ጋር ብዙ የሚያመሳስሉት ነገሮች ቢኖሩም ብዙ ልዩነቶችም አሉት።

3 የሕዝቅኤል መጽሐፍ የመጨረሻ ዘጠኝ ምዕራፎች ስለዚህ አስገራሚ ራእይ የሚገልጹ ናቸው። እስቲ አሁን፣ ይህን ራእይ በምንመረምርበትና ለመረዳት በምንጥርበት ጊዜ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን እንደሚገባ እንመልከት። ከዚያም ሕዝቅኤል የተመለከተው ቤተ መቅደስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ሰፊ ማብራሪያ ከሰጠበት ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ጋር አንድ መሆን አለመሆኑን እንመረምራለን። በመጨረሻም ራእዩ ለሕዝቅኤልና ለግዞተኛ ወገኖቹ ምን ትርጉም እንደነበረው እንመለከታለን።

የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት

4. ሕዝቅኤል በራእይ ያየውን ቤተ መቅደስ ቀደም ሲል የምናብራራው በምን መንገድ ነበር? አሁን ግን ምን ዓይነት ማብራሪያ መስጠት ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል?

4 ቀደም ሲል ጽሑፎቻችን ሕዝቅኤል የተመለከተው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የገለጸውን ታላቅ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ እንደሆነ ይገልጹ ነበር። * እንዲህ ዓይነት ግንዛቤ ስለነበረን፣ ጳውሎስ ስለ ማደሪያ ድንኳኑ የሰጠውን ማብራሪያ እንደ መነሻ በመጠቀም ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ቤተ መቅደስ ያሉት የተለያዩ ገጽታዎች ምን ምሳሌያዊ ትርጉም ወይም ጥላነት እንዳላቸው ለማብራራት እንሞክር ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቅኤል ያየውን ራእይ በተመለከተ ጸሎት የታከለበት ተጨማሪ ምርምር ማድረጋችንና በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰላሰላችን ለዚህ ራእይ ቀለል ያለ ማብራሪያ መስጠት እንዳለብን አስገንዝቦናል።

5, 6. (ሀ) ጳውሎስ የማደሪያ ድንኳኑን አንዳንድ ገጽታዎች በተመለከተ ምን ብሏል? ይህስ ጳውሎስ ትሑት መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) እኛስ ሕዝቅኤል በራእይ ያየውን ቤተ መቅደስ የምንረዳበትን መንገድ በተመለከተ ተመሳሳይ ዝንባሌ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

5 ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ቤተ መቅደስ ያለው እያንዳንዱ ገጽታ ምን ትንቢታዊ ወይም ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳለው ለማብራራት ከመሞከር መቆጠቡ የጥበብ አካሄድ ይመስላል። ለምን? አንድ ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ ስለ ማደሪያ ድንኳኑና ስለ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ባብራራበት ወቅት እንደ ወርቁ ጥና፣ የታቦቱ መክደኛና መና የተቀመጠበት የወርቅ ማሰሮ ስላሉ ዝርዝር ነገሮች ጠቅሶ ነበር። ታዲያ ጳውሎስ እነዚህ የተለያዩ ዕቃዎች ምን ትንቢታዊ ትርጉም እንዳላቸው ተናግሯል? መንፈስ ቅዱስ እንዲህ እንዲያደርግ እንዳልገፋፋው መረዳት ይቻላል። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ “ስለ እነዚህ ነገሮች በዝርዝር ለመናገር አሁን ጊዜው አይደለም” ብሏል። (ዕብ. 9:4, 5) ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለመቀበልና ይሖዋን በትሕትና ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበር።—ዕብ. 9:8

6 ሕዝቅኤል በራእይ ካየው ቤተ መቅደስ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይህ ራእይም ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ነው። ስለዚህ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልግ ከሆነ ይሖዋ ራሱ ጉዳዩን ግልጽ እስኪያደርግልን ድረስ መጠበቁ የተሻለ ይሆናል። (ሚክያስ 7:7ን አንብብ።) ታዲያ ይህ ሲባል ከዚህ ራእይ ጋር በተያያዘ የይሖዋ መንፈስ የገለጠልን ምንም የእውቀት ብርሃን የለም ማለት ነው? በፍጹም!

ሕዝቅኤል የተመለከተው ታላቁን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነው?

7, 8. (ሀ) ቀደም ሲል በነበረን በየትኛው ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ አድርገናል? (ለ) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ ጳውሎስ ከገለጸው መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚለየው እንዴት ነው?

7 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ላለፉት በርካታ ዓመታት ጽሑፎቻችን ሕዝቅኤል የተመለከተው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የገለጸውን ታላቅ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ እንደሆነ ይገልጹ ነበር። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ ያደረግነው ተጨማሪ ምርምር ሕዝቅኤል የተመለከተው ታላቁን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሊሆን እንደማይችል አስገንዝቦናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

8 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሕዝቅኤል የተመለከተው ቤተ መቅደስ ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ስለ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ከሰጠው መግለጫ ጋር አይስማማም። እስቲ ይህን ልብ በል፦ ሐዋርያው ጳውሎስ በሙሴ ዘመን የነበረው የማደሪያ ድንኳን ለአንድ የላቀ ነገር ጥላና ምሳሌ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። ይህ ድንኳንም ሆነ ከድንኳኑ ጋር በተመሳሳይ ንድፍ የተሠሩት የሰለሞንና የዘሩባቤል ቤተ መቅደሶች “ቅድስተ ቅዱሳን” የሚባል ክፍል ነበራቸው። ጳውሎስ ይህ ክፍል ‘በሰው እጅ የተሠራ የእውነተኛው ቅዱስ ስፍራ አምሳያ’ እንጂ እውነተኛው ነገር ራሱ እንዳልሆነ ገልጿል። ታዲያ እውነተኛው ነገር ምንድን ነው? ጳውሎስ እውነተኛው ቅዱስ ስፍራ “ሰማይ” እንደሆነ ተናግሯል። (ዕብ. 9:3, 24) ታዲያ ሕዝቅኤል የተመለከተው ሰማይን ነበር? አልነበረም። ሕዝቅኤል በራእይ ያየው በሰማይ ላይ ያሉ ነገሮችን እንደሆነ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም።—ከዳንኤል 7:9, 10, 13, 14 ጋር አወዳድር።

9, 10. ከመሥዋዕቶች ጋር በተያያዘ፣ ሕዝቅኤል በራእይ ባየው ቤተ መቅደስና ጳውሎስ በገለጸው መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ መካከል ምን ልዩነት አለ?

9 ሕዝቅኤል ባየው ራእይና ጳውሎስ በሰጠው መግለጫ መካከል ልዩነት እንዳለ የሚያሳይ ይበልጥ አሳማኝ የሆነ ማስረጃ አለ፤ ይህም ከመሥዋዕቶች ጋር የተያያዘ ነው። ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ ለሕዝቡ፣ ለአለቆቹና ለካህናቱ መሥዋዕት ከማቅረብ ጋር የተያያዘ ዝርዝር መመሪያ ሲሰጥ ሰምቷል። እነዚህ ሰዎች ለኃጢአታቸው መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር። በተጨማሪም የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው፤ ምናልባትም ይህን መሥዋዕት በቤተ መቅደሱ የመመገቢያ ክፍሎች ውስጥ ሊበሉት ይችላሉ። (ሕዝ. 43:18, 19፤ 44:11, 15, 27፤ 45:15-20, 22-25) ታዲያ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲህ ያሉ ተደጋጋሚ መሥዋዕቶች ይቀርባሉ?

ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ቤተ መቅደስ ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አይደለም

10 መልሱ ግልጽና የማያሻማ ነው። ጳውሎስ እንዲህ በማለት አብራርቷል፦ “ክርስቶስ አሁን ላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራው ይኸውም ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነው ይበልጥ ታላቅና ፍጹም ወደሆነው ድንኳን ገብቷል። ወደ ቅዱሱ ስፍራ የገባው የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ራሱን ደም ይዞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ፤ ደግሞም ለእኛ ዘላለማዊ መዳን አስገኘልን።” (ዕብ. 9:11, 12) ስለዚህ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚቀርበው አንድ መሥዋዕት ብቻ ነው። እሱም የቤዛው መሥዋዕት ሲሆን ያቀረበው ደግሞ ታላቁ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። በመሆኑም ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው የፍየሎችና የወይፈኖች መሥዋዕት በተደጋጋሚ የሚቀርብበት ቤተ መቅደስ ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው።

11. በሕዝቅኤል ዘመን አምላክ ታላቁን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚመለከቱ እውነቶችን የሚገልጥበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

11 አሁን ደግሞ ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ታላቁን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሊሆን አይችልም እንድንል የሚያደርገንን ሁለተኛ ምክንያት እንመልከት፦ በሕዝቅኤል ዘመን አምላክ እንደነዚህ ያሉትን እውነቶች የሚገልጥበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር። ሕዝቅኤል በመጀመሪያ ራእዩን የተናገረው በባቢሎን ለነበሩ አይሁዳውያን ግዞተኞች እንደነበር አስታውስ። እነዚህ አይሁዳውያን በሙሴ ሕግ ሥር ነበሩ። የግዞት ዘመኑ ሲያበቃ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱንና መሠዊያውን ዳግመኛ በመገንባት ሕጉ በሚያዘው መሠረት ንጹሕ አምልኮ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ከዚያም ለስድስት መቶ ዓመታት ያህል በዚህ መልኩ መሥዋዕት ማቅረባቸውን ይቀጥላሉ። ሕዝቅኤል በራእይ ያየው መንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ ቢሆን ኖሮ፣ ይህ በአይሁዳውያን ላይ ምን ስሜት ሊያሳድርባቸው እንደሚችል ገምት። በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሊቀ ካህናቱ አንዴ የገዛ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ በኋላ ሌሎቹ መሥዋዕቶች በሙሉ ይቀራሉ። እነዚህ አይሁዳውያን እንዲህ ያለውን ራእይ ሲሰሙ ምን አመለካከት የሚያድርባቸው ይመስልሃል? የሙሴን ሕግ ለመጠበቅ የነበራቸው ቁርጠኝነት አይዳከምም? ይሖዋ ምንጊዜም መንፈሳዊ እውነቶችን የሚገልጠው በትክክለኛው ጊዜና ሕዝቦቹ እነዚህን እውነቶች መረዳት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ሲደርሱ ነው።

12-14. ሕዝቅኤል በተመለከተው ቤተ መቅደስና ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ በሰጠው ማብራሪያ መካከል ምን ዝምድና አለ? (“የተለያዩ ቤተ መቅደሶች፣ የተለያዩ ትምህርቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

12 ታዲያ ሕዝቅኤል በራእይ ባየው ቤተ መቅደስና ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ በሰጠው መግለጫ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? የጳውሎስ ማብራሪያ የተመሠረተው ሕዝቅኤል በራእይ ባየው ቤተ መቅደስ ላይ ሳይሆን በሙሴ ዘመን በነበረው የማደሪያ ድንኳን ላይ እንደሆነ ልብ በል። እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ የጠቀሳቸው የማደሪያ ድንኳኑ በርካታ ገጽታዎች በሰለሞንና በዘሩባቤል ቤተ መቅደስም ሆነ ሕዝቅኤል በራእይ ባየው ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቅኤልና ጳውሎስ ትኩረት ያደረጉት በተለያየ ነገር ላይ ነው። * አንዱ የጻፈው ሐሳብ የሌላውን የሚያስተጋባ ሳይሆን የሚያሟላ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

13 በሁለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች መካከል ያለውን ዝምድና በዚህ መንገድ ልንገልጸው እንችላለን፦ ጳውሎስ የሰጠው ማብራሪያ ይሖዋ ለአምልኮ ስላደረገው ዝግጅት ያስተምረናል፤ የሕዝቅኤል ራእይ ደግሞ ይሖዋ ለአምልኮ ስላወጣው መሥፈርት ያስተምረናል። ጳውሎስ ሊቀ ካህናቱን፣ መሥዋዕቶቹን፣ መሠዊያውንና ቅድስተ ቅዱሳኑን ጨምሮ የመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ አንዳንድ ገጽታዎች ያላቸውን ትርጉም በመግለጽ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ስላደረገው ዝግጅት ትምህርት እንድናገኝ አድርጎናል። ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ ደግሞ የይሖዋ መሥፈርቶች በአእምሯችን ቁልጭ ብለው እንዲታዩን የሚያደርጉ ዝርዝር መግለጫዎችን በመጠቀም ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ስላወጣው ከፍ ያለ መሥፈርት ጎላ አድርጎ ይገልጻል።

14 ታዲያ ካገኘነው ግንዛቤ አንጻር ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? የሕዝቅኤል ራእይ በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛ ብዙም ትርጉም እንደሌለው አድርገን ልናስብ አይገባም። ይህ ራእይ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን ለማየት፣ በሕዝቅኤል ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ ለኖሩት ታማኝ አይሁዳውያን ምን ጥቅም እንዳስገኘላቸው እንመርምር።

ራእዩ ለግዞተኞቹ አይሁዳውያን ምን ትርጉም ነበረው?

15. (ሀ) ሕዝቅኤል ያየው ራእይ አጠቃላይ ትንቢታዊ መልእክት ምን ነበር? (ለ) በሕዝቅኤል ምዕራፍ 8 እና ከምዕራፍ 40 እስከ 48 መካከል ምን ሰፊ ልዩነት አለ?

15 መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ለማግኘት ስለ ጉዳዩ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረን የሚያስችሉ አንዳንድ ተዛማጅ ጥያቄዎችን እናንሳ። አንደኛ፣ የራእዩ አጠቃላይ ትንቢታዊ መልእክት ምን ነበር? በአጭር አነጋገር የራእዩ አጠቃላይ መልእክት ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም የሚገልጽ ነው! ሕዝቅኤል ይህን በግልጽ ተረድቶ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ሕዝቅኤል በምዕራፍ 8 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የጻፈው ከዚህ አስቀድሞ ነበር፤ በዚህ ምዕራፍ ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መቅደስ እንዴት ባለ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ በግልጽ አሳይቶት ነበር። አሁን ደግሞ ከምዕራፍ 40 እስከ 48 ላይ የሚገኘውን ከዚህ ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ሁኔታ በዝርዝር ሲጽፍ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። እነዚህ ምዕራፎች የሚናገሩት ንጹሕ አምልኮ ምን ያህል እንደተበከለ ሳይሆን ንጹሕ አምልኮ ወደ ትክክለኛ ቦታው ተመልሶ በሙሴ ሕግ መሠረት ፍጹም በሆነ መንገድ እንደሚቀርብ ነው።

16. ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ ኢሳይያስ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

16 የይሖዋ አምልኮ ወደ ተገቢ ቦታው እንዲመለስ ከተፈለገ በወቅቱ ከነበረበት ሁኔታ ከፍ ከፍ መደረግ ነበረበት። ከመቶ ዓመት ገደማ በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን ሐሳብ ጽፎ ነበር፦ “በዘመኑ መጨረሻ የይሖዋ ቤት ተራራ ከተራሮች አናት በላይ ጸንቶ ይቆማል፤ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ብሔራትም ሁሉ ወደዚያ ይጎርፋሉ።” (ኢሳ. 2:2) ኢሳይያስ የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋምና በረጅም ተራራ ላይ የተቀመጠ ያህል ከፍ እንደሚል በግልጽ ተንብዮአል። ታዲያ ሕዝቅኤል በመለኮታዊ ራእይ ያየው ቤተ መቅደስ የሚገኘው የት ነበር? “በአንድ ትልቅ ተራራ” ላይ ነበር! (ሕዝ. 40:2) በመሆኑም የሕዝቅኤል ራእይ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም ያረጋግጣል።

ሕዝቅኤል ያየው ቤተ መቅደስ የሚገኘው ከፍ ያለ ተራራ ላይ ነበር (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

17. ከሕዝቅኤል ምዕራፍ 40 እስከ 48 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በአጭሩ ግለጽ።

17 በሕዝቅኤል መጽሐፍ ከምዕራፍ 40 እስከ 48 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሕዝቅኤል ራእይ በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክር። ሕዝቅኤል መልአኩ የቤተ መቅደሱን በሮች፣ ቅጥሩን፣ ግቢዎቹንና መቅደሱን ሲለካ ተመለከተ። (ሕዝ. 40 እስከ 42) ከዚያም አንድ አስደናቂ ነገር ተከናወነ፤ ይሖዋ በታላቅ ግርማ ወደ ቤተ መቅደሱ መጣ! ከዚያም የተሳሳተ ጎዳና ለተከተሉት ሕዝቦቹ፣ ለካህናቱና ለአለቆቹ እርማትና መመሪያ ሰጠ። (ሕዝ. 43:1-12፤ 44:10-31፤ 45:9-12) ሕዝቅኤል አንድ ወንዝ ከመቅደሱ ወጥቶ ሲፈስ እንዲሁም በሚፈስበት ቦታ ሁሉ ሕይወትና በረከት እያስገኘ ወደ ሙት ባሕር ሲገባ ተመለከተ። (ሕዝ. 47:1-12) በተጨማሪም ምድሪቷ ተለክታ ስትከፋፈልና ማዕከላዊው ክፍል ለንጹሕ አምልኮ እንዲውል ሲደረግ አየ። (ሕዝ. 45:1-8፤ 47:13 እስከ 48:35) የዚህ ሁሉ ነገር አጠቃላይ መልእክት ምንድን ነው? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋምና ከፍ ከፍ እንደሚደረግ ለሕዝቦቹ ዋስትና እየሰጣቸው ነበር። ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በመገኘት የአምልኮ ቤቱን ይባርከዋል፤ በተጨማሪም ከቤተ መቅደሱ በሚፈሰው በረከት አማካኝነት በምድሪቱ ላይ ፈውስ እንዲካሄድ፣ ሕይወት እንዲያብብና ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል።

ሕዝቅኤል ያየው ቤተ መቅደስ ይሖዋ ንጹሕ አምልኮን አስደናቂ በሆነ መንገድ መልሶ እንደሚያቋቁም የሚያሳይ ነበር (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

18. የቤተ መቅደሱ ራእይ ቃል በቃል የሚወሰድ ነበር? አብራራ።

18 ሁለተኛ፣ ራእዩ ቃል በቃል የሚወሰድ ነው? አይደለም። ሕዝቅኤልም ሆነ ራእዩን የነገራቸው ግዞተኛ ወገኖቹ ራእዩ ቃል በቃል የሚወሰድ እንዳልሆነ ወዲያውኑ ሳይገባቸው አልቀረም። ራእዩ ቃል በቃል ሊወሰድ አይችልም የምንለው ለምንድን ነው? ሕዝቅኤል ይህን ቤተ መቅደስ ያየው “ትልቅ ተራራ” ላይ እንደነበር አስታውስ። ይህ ከኢሳይያስ ትንቢት ጋር የሚስማማ ቢሆንም መግለጫው በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መቅደስ ከሚገኝበት ቦታ ጋር አይጣጣምም። የሰለሞን ቤተ መቅደስ ይገኝ የነበረው ኢየሩሳሌም ባለው የሞሪያ ተራራ ላይ ሲሆን በኋላም ዳግመኛ የሚገነባው እዚሁ ቦታ ላይ ነው። ታዲያ የሞሪያ ተራራ “ትልቅ ተራራ” ነበር? አልነበረም። እንዲያውም የሞሪያ ተራራ ከእሱ ጋር የሚመጣጠን ወይም የሚበልጥ ከፍታ ባላቸው ተራሮች የተከበበ ነበር። በተጨማሪም ሕዝቅኤል የተመለከተው ቤተ መቅደስ በጣም ግዙፍ ነበር። በቅጥር የታጠረው የቤተ መቅደሱ ግቢ በጣም ሰፊ በመሆኑ የሞሪያ ተራራ ሊበቃው አይችልም። በሰለሞን ዘመን የነበረችው የኢየሩሳሌም ከተማ ስፋት እንኳ ሊበቃው አይችልም! በተጨማሪም ግዞተኞቹ ቃል በቃል አንድ ወንዝ ከመቅደሱ ወጥቶ ወደ ሙት ባሕር እንደሚገባና ሕይወት አልባ የሆነውን ይህን ባሕር እንደሚፈውሰው ሊጠብቁ እንደማይችሉ የታወቀ ነው። በመጨረሻም ተራራማ መልክዓ ምድር ያላትን ተስፋይቱን ምድር በራእዩ ላይ እንደተገለጸው ቀጥተኛ በሆኑ ትይዩ መስመሮች ከፋፍሎ ለየነገዱ መስጠት አይቻልም። ስለዚህ ራእዩ ቃል በቃል ሊወሰድ እንደማይችል ግልጽ ነው።

19-21. ይሖዋ ሕዝቅኤል ያየው ራእይ በሕዝቡ ላይ ምን ስሜት እንዲያሳድር ፈልጎ ነበር? ራእዩ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርባቸው የሚያደርገውስ ለምንድን ነው?

19 ሦስተኛ፣ ራእዩ በሕዝቅኤል ወገኖች ላይ ምን ዓይነት ስሜት ሊያሳድር ይገባል? ሕዝቡ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ስላወጣው ከፍተኛ መሥፈርት ሲያስቡ ኀፍረት ሊሰማቸው ይገባ ነበር። ይሖዋ ሕዝቅኤልን ‘ለእስራኤል ቤት ሰዎች ስለ ቤተ መቅደሱ እንዲገልጽላቸው’ አዞታል። ሕዝቅኤል ለሕዝቡ ስለ ቤተ መቅደሱ ዝርዝር መግለጫ መስጠት ይጠበቅበታል፤ ይህም እስራኤላውያን ‘ንድፉን እንዲያጠኑ’ ያስችላቸዋል። እስራኤላውያን ስለዚህ ቤተ መቅደስ ማጥናት የነበረባቸው ለምንድን ነው? ይህን ቤተ መቅደስ ለመገንባት ሊሆን እንደማይችል ቀደም ሲል የተመለከትነው መረጃ ያሳያል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ስለ ቤተ መቅደሱ እንዲያጠኑ የፈለገው “ከሠሩት በደል የተነሳ ኀፍረት እንዲሰማቸው” ነው።—ሕዝቅኤል 43:10-12ን አንብብ።

20 ይህ ራእይ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ሕሊናቸው እንዲወቅሳቸውና ኀፍረት እንዲሰማቸው ሊያደርግ የሚችለው ለምንድን ነው? ሕዝቅኤል ምን እንደተባለ ልብ በል፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ ስለ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ደንቦችና ሕጎች የምነግርህን ሁሉ በትኩረት ተከታተል፤ በዓይኖችህም ተመልከት እንዲሁም በጥሞና አዳምጥ።” (ሕዝ. 44:5) ሕዝቅኤል በዚህ ራእይ ውስጥ ስለ ደንቦችና ሕጎች በተደጋጋሚ ሰምቷል። (ሕዝ. 43:11, 12፤ 44:24፤ 46:14) በተጨማሪም ሕዝቅኤል ስለ ይሖዋ መሥፈርቶች፣ ሌላው ቀርቶ አንድ ክንድ ሊኖረው ስለሚገባው ርዝመትና የክብደት መለኪያዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው ትክክለኛ መጠን ይሖዋ ያወጣውን መሥፈርት ጭምር እንዲያስብ የሚያደርጉ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ሰምቷል። (ሕዝ. 40:5፤ 45:10-12፤ ከምሳሌ 16:11 ጋር አወዳድር።) እንዲያውም በበኩረ ጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት ከመለኪያና ከመስፈሪያ ጋር የተያያዙ ቃላት በዚህ ራእይ ውስጥ ብቻ ከ50 ጊዜ በላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ።

21 ይሖዋ ስለ መስፈሪያዎች፣ መለኪያዎች፣ ሕጎችና ደንቦች ሲናገር ለሕዝቦቹ ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው? የሚከተለውን ወሳኝ እውነት አስረግጦ ሊነግራቸው የፈለገ ይመስላል፦ ለንጹሕ አምልኮ መሥፈርት የሚያወጣው ይሖዋ ብቻ ነው። ከእነዚህ መሥፈርቶች የራቁ ሁሉ ኀፍረት ሊሰማቸው ይገባል! ይሁን እንጂ ይህ ራእይ አይሁዳውያኑ እንዲህ ዓይነት ትምህርት እንዲያገኙ የሚያደርገው በምን መንገድ ነው? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመለከታለን። እንዲህ ማድረጋችን ራእዩ ለዘመናችን ያለው ትርጉም ምን እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን ያደርጋል።

የቤተ መቅደሱ ራእይ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ኀፍረት እንዲሰማቸው ሊያደርግ የሚችለው ለምንድን ነው? (ከአንቀጽ 19-21⁠ን ተመልከት)

^ አን.4 መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ለንጹሕ አምልኮ ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። ይህ ቤተ መቅደስ ወደ ሕልውና የመጣው በ29 ዓ.ም. እንደሆነ እንገነዘባለን።

^ አን.12 ለምሳሌ፣ ጳውሎስ በሊቀ ካህናቱና በዓመታዊው የስርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ በሚያከናውነው ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። (ዕብ. 2:17፤ 3:1፤ 4:14-16፤ 5:1-10፤ 7:1-17, 26-28፤ 8:1-6፤ 9:6-28) ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይ ግን ስለ ሊቀ ካህናቱም ሆነ ስለ ስርየት ቀን የተጠቀሰ ነገር የለም።