በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 14

“የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው”

“የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው”

ሕዝቅኤል 43:12

ፍሬ ሐሳብ፦ ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ በእሱ ዘመን ለነበሩት ሰዎችም ሆነ ለእኛ የያዘው ትምህርት

1, 2. (ሀ) ባለፈው ምዕራፍ ላይ ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየውን ራእይ በተመለከተ ምን ተምረናል? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኞቹን ሁለት ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ሕዝቅኤል በራእይ ያየው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ያብራራውን ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ እንዳልሆነ ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ ተምረናል። በተጨማሪም የራእዩ ዓላማ አምላክ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣቸው መሥፈርቶች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ የአምላክን ሕዝቦች ማስተማር መሆኑን ተገንዝበናል። የይሖዋ ሕዝቦች ከእሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማደስ የሚችሉት እነዚህን መሥፈርቶች ከተከተሉ ብቻ ነው። ይሖዋ “የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው” የሚለውን ሐሳብ በአንድ ጥቅስ ላይ ብቻ ሁለት ጊዜ የተናገረው ይህን ነጥብ ለማጉላት ነው።—ሕዝቅኤል 43:12ን አንብብ።

2 ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ፣ ሁለት ተጨማሪ ጥያቄዎችን እንመረምራለን። አንደኛ፣ አይሁዳውያን ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ካየው ራእይ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በተመለከተ ምን ትምህርት አግኝተዋል? ሁለተኛ፣ ይህ ራእይ በመከራ በተሞሉት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ለምንኖረው ለእኛ ምን ትርጉም አለው? የመጀመሪያው ጥያቄ መልስ የሁለተኛውን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳናል።

ራእዩ በጥንት ዘመን ለነበሩት ሰዎች ምን ትምህርት ሰጥቷቸዋል?

3. በራእይ የታየው ቤተ መቅደስ በትልቅ ተራራ ላይ የሚገኝ መሆኑ የአምላክን ሕዝቦች እንዲያፍሩ የሚያደርጋቸው ለምንድን ነው?

3 የመጀመሪያውን ጥያቄ ለመመለስ፣ በራእይ የታየው ቤተ መቅደስ ባሉት አንዳንድ ጎላ ያሉ ገጽታዎች ላይ ትኩረት እናድርግ። ትልቅ ተራራ። ሕዝቡ ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ በትልቅ ተራራ ላይ እንደሚገኝ ሲሰሙ፣ ኢሳይያስ ስለ መልሶ መቋቋም የተናገረውን አስደሳች ትንቢት አስታውሰው መሆን አለበት። (ኢሳ. 2:2) ሆኖም የይሖዋ ቤት እንዲህ ባለ ትልቅ ተራራ ላይ እንደሚገኝ ማወቃቸው ምን አስተምሯቸዋል? ንጹሕ አምልኮ ከፍ ከፍ ሊደረግና ከምንም ነገር በላይ የላቀ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ አስተምሯቸዋል። እርግጥ ነው፣ ንጹሕ አምልኮ “ከሌሎች አማልክት ሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ከፍ” ያለው አምላክ ያደረገው ዝግጅት እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም ቢሆን ከፍ ያለ ነው። (መዝ. 97:9) ይሁን እንጂ ሕዝቡ የበኩላቸውን ድርሻ አልተወጡም። ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ንጹሕ አምልኮ ችላ እንዲባልና እንዲበከል ፈቅደዋል። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የአምላክ ቅዱስ ቤት ከፍ ከፍ ተደርጎና የሚገባውን የተከበረ ቦታ አግኝቶ ማየታቸው በራሳቸው እንዲያፍሩ አድርጓቸው መሆን አለበት።

4, 5. ሕዝቅኤል ራእዩን የነገራቸው ሰዎች ከቤተ መቅደሱ ረጃጅም በሮች ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

4 ረጃጅም በሮች። ሕዝቅኤል በራእዩ መጀመሪያ ላይ፣ መልአኩ በሮቹን ሲለካ ተመልክቷል። እነዚህ በሮች 30 ሜትር የሚያክል ከፍታ ነበራቸው። (ሕዝ. 40:14) በመግቢያው ላይ የዘብ ጠባቂ ክፍሎችም ነበሩ። ታዲያ ይህ ሁሉ የቤተ መቅደሱን ንድፍ ለሚያጠኑት ሰዎች ምን መልእክት ያስተላልፋል? ይሖዋ ለሕዝቅኤል “የቤተ መቅደሱን መግቢያ . . . ልብ በል” ብሎታል። ለምን? ምክንያቱም አይሁዳውያኑ “ልባቸውንና ሥጋቸውን ያልተገረዙ” ሰዎችን ወደ አምላክ ቅዱስ የአምልኮ ቤት ያስገቡ ነበር። ይህስ ምን አስከትሏል? ይሖዋ የእነዚህ ሰዎች መግባት ‘ቤተ መቅደሱን እንደሚያረክሰው’ ተናግሯል።—ሕዝ. 44:5, 7

5 “ሥጋቸውን ያልተገረዙት” ሰዎች ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ የተሰጠውን የይሖዋን ግልጽ ትእዛዝ ጥሰዋል። (ዘፍ. 17:9, 10፤ ዘሌ. 12:1-3) ‘ልባቸውን ያልተገረዙት’ ሰዎች ደግሞ ከዚህም የከፋ ችግር ነበረባቸው። እነዚህ ሰዎች ሆን ብለው በይሖዋ ላይ የሚያምፁ ከመሆኑም ሌላ እሱ የሚሰጣቸውን መመሪያና ምክር ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም። እንደዚህ ያሉት ሰዎች ቅዱስ ወደሆነው የይሖዋ የአምልኮ ቤት እንዲገቡ ሊፈቀድላቸው አይገባም ነበር! ይሖዋ ግብዝነትን ይጠላል፤ ሕዝቦቹ ግን በቤቱ ውስጥ ግብዝነት እንዲስፋፋ ፈቅደው ነበር። በራእይ የታየው ቤተ መቅደስ የነበሩት በሮችና የዘብ ጠባቂ ክፍሎች የሚያስተላልፉት ግልጽ መልእክት የሚከተለው ነው፦ ከአሁን በኋላ ማንም የይሖዋን ቤት እንደፈለገ አይፈነጭበትም! ወደ አምላክ ቤት ለመግባት የሚያስፈልገው ከፍ ያለ መሥፈርት መከበር ይኖርበታል። ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚያቀርቡትን አምልኮ የሚባርከው ይህ ሲሆን ብቻ ነው።

6, 7. (ሀ) ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ባለው ቅጥር አማካኝነት ለሕዝቡ ምን መልእክት አስተላልፏል? (ለ) ቀደም ሲል የይሖዋ ሕዝቦች ከቤተ መቅደሱ ጋር በተያያዘ ምን አድርገዋል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

6 በዙሪያው ያለው ቅጥር። ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ ያለው ሌላ ልዩ ገጽታ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያለው ውጨኛ ቅጥር ነው። ሕዝቅኤል የቅጥሩ እያንዳንዱ ጎን 500 ዘንግ ወይም 1555 ሜትር ርዝመት እንዳለው ተናግሯል፤ ይህም ከአንድ ኪሎ ሜትር ተኩል በላይ ማለት ነው! (ሕዝ. 42:15-20) የቤተ መቅደሱ ሕንፃዎችና ግቢዎች ያረፉበት ቦታ ግን እያንዳንዱ ጎኑ 500 ክንድ ወይም 259 ሜትር ብቻ ነው። (ሕዝ. 45:2) ስለዚህ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ በጣም ሰፊ የሆነ ክፍት ቦታ ያለ ሲሆን ይህም በውጨኛው ቅጥር ታጥሯል። * እንዲህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?

7 ይሖዋ “ከእንግዲህ የሚፈጽሙትን መንፈሳዊ ምንዝር ያስወግዱ፤ የንጉሦቻቸውንም ሬሳ ከእኔ ያርቁ፤ እኔም በመካከላቸው ለዘላለም እኖራለሁ” ብሏል። (ሕዝ. 43:9) ‘የንጉሦቻቸው ሬሳ’ የሚለው አገላለጽ ጣዖታትን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። ስለዚህ ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ሰፊ ቦታ እንዲኖር ሲያደርግ በተዘዋዋሪ መንገድ “እንዲህ ያለውን ርኩሰት በሙሉ አርቁ። ትንሽ እንኳ እንዳታቀርቡት” ያለ ያህል ነው። በዚህ መንገድ አምልኳቸው ከርኩሰት የጸዳ እንዲሆን ካደረጉ ይሖዋ በቤተ መቅደሱ በመገኘት ይባርካቸዋል።

8, 9. ይሖዋ ኃላፊነት ላላቸው ወንዶች ከሰጠው ጠንከር ያለ ምክር ሕዝቡ ምን ትምህርት ሊያገኝ ይችላል?

8 በኃላፊነት ቦታ ላይ ላሉ ሰዎች የተሰጠ ጠንካራ ምክር። ይሖዋ በሕዝቡ መካከል ትልቅ ኃላፊነት ለነበራቸው ወንዶች ጠንከር ያለ፣ ግን ፍቅራዊ የሆነ ምክር ሰጥቷቸዋል። ሕዝቡ ወደ ጣዖት አምልኮ ባዘነበለበት ወቅት እሱን ለተዉት ሌዋውያን ጠንካራ እርማት የሰጣቸው ሲሆን ‘እስራኤላውያን ከእሱ በራቁ ጊዜ የመቅደሱን አገልግሎት ያከናውኑ የነበሩትን የሳዶቅ ልጆች’ ግን አመስግኗቸዋል። ሁለቱንም ቡድኖች እንደ ሥራቸው መጠን ፍትሐዊ በሆነና ምሕረት በሚንጸባረቅበት መንገድ ይዟቸዋል። (ሕዝ. 44:10, 12-16) የእስራኤል አለቆችም በተመሳሳይ ጠንከር ያለ እርማት ተሰጥቷቸዋል።—ሕዝ. 45:9

9 በዚህ መንገድ ይሖዋ ሥልጣንና ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን መንገድ በተመለከተ በእሱ ፊት ተጠያቂ እንደሚሆኑ በግልጽ አሳይቷል። እነዚህ ሰዎች ኃላፊነት ስላላቸው ብቻ ምክር፣ እርማትና ተግሣጽ አያስፈልጋቸውም ማለት አይደለም። እንዲያውም የይሖዋን መሥፈርቶች በመደገፍ ረገድ ግንባር ቀደም መሆን ነበረባቸው!

10, 11. ከግዞት ከተመለሱት እስራኤላውያን መካከል አንዳንዶቹ ሕዝቅኤል ካየው ራእይ ትምህርት እንዳገኙ የሚጠቁም ምን ማስረጃ አለ?

10 ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያን ከሕዝቅኤል ራእይ ያገኙትን ትምህርት ተግባራዊ አድርገዋል? እርግጥ ነው፣ በዚያ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ስለዚህ አስደናቂ ራእይ ሲሰሙ ምን እንደተሰማቸው በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ያም ቢሆን የአምላክ ቃል ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያን ምን እንዳደረጉና ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ምን ዓይነት አመለካከት እንዳዳበሩ በዝርዝር ይናገራል። ታዲያ እነዚህ እስራኤላውያን የሕዝቅኤል ራእይ የያዛቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ አድርገዋል? አዎ፣ በተለይ ከባቢሎን ግዞት በፊት ከነበሩት ዓመፀኛ አባቶቻቸው አንጻር ሲታይ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ አድርገዋል።

11 እንደ ነቢዩ ሐጌ፣ ነቢዩ ዘካርያስ፣ ካህኑ ዕዝራና ገዢው ነህምያ ያሉ ታማኝ ወንዶች ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ ከያዛቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚመሳሰሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለሕዝቡ በትጋት አስተምረዋል። (ዕዝራ 5:1, 2) ንጹሕ አምልኮ ከፍ ከፍ መደረግ እንዳለበት እንዲሁም ከቁሳዊ ጉዳዮችም ሆነ ከግል ጥቅም ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ሕዝቡን አስተምረዋል። (ሐጌ 1:3, 4) በተጨማሪም በንጹሕ አምልኮ መካፈል የሚፈልጉ ሰዎች በሙሉ አስፈላጊውን መሥፈርት እንዲያሟሉ ለማድረግ የተቻላቸውን አድርገዋል። ለምሳሌ ዕዝራና ነህምያ፣ ባዕዳን ሚስቶች ያገቡ ሁሉ የሕዝቡን መንፈሳዊነት እያዳከሙ ያሉትን እነዚህን ሚስቶቻቸውን እንዲያሰናብቱ በጥብቅ አሳስበዋል። (ዕዝራ 10:10, 11ን አንብብ፤ ነህ. 13:23-27, 30) ጣዖት አምልኮን በተመለከተስ ምን እርምጃ ተወስዷል? ከግዞቱ በኋላ ብሔሩ በታሪክ ዘመኑ በሙሉ በተደጋጋሚ ወጥመድ ሆኖበት ለቆየው ለዚህ ኃጢአት ጥላቻ ሳያዳብር አልቀረም። ስለ ካህናቱና ስለ ሕዝቡ አለቆች ወይም ስለ መኳንንቱስ ምን ማለት ይቻላል? በሕዝቅኤል ራእይ ላይ እንደተገለጸው፣ ይሖዋ ምክርና እርማት ከሰጣቸው ሰዎች መካከል እነዚህ ሰዎችም ይገኙበታል። (ነህ. 13:22, 28) ብዙዎቹም ምክሩን በትሕትና ተቀብለዋል።—ዕዝራ 10:7-9, 12-14፤ ነህ. 9:1-3, 38

ነህምያ ከሕዝቡ ጋር አብሮ እየሠራ ስለ ንጹሕ አምልኮ አስተምሯቸዋል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

12. እስራኤላውያን ከግዞት ከተመለሱ በኋላ ይሖዋ የባረካቸው በምን መንገድ ነው?

12 ይሖዋም በምላሹ ሕዝቡን ባርኳል። ሕዝቡ ለረጅም ዘመን አግኝቶት የማያውቀውን ዓይነት መንፈሳዊ ብልጽግና፣ ጤንነትና ሰላም ማግኘት ችሏል። (ዕዝራ 6:19-22፤ ነህ. 8:9-12፤ 12:27-30, 43) እንዲህ ያለውን በረከት ሊያገኝ የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሕዝቡ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን የጽድቅ መሥፈርት ማክበር ጀምሮ ነበር። ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ሰዎች የቤተ መቅደሱ ራእይ የሚያስተላልፈውን ትምህርት ተግባራዊ አድርገዋል። በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ ግዞተኞቹን በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ጠቅሟቸዋል ማለት ይቻላል። (1) ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ስላወጣቸው መሥፈርቶችና እነዚህን መሥፈርቶች ማክበር ስለሚችሉበት መንገድ አስተምሯቸዋል። (2) ወደፊት ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋምና ሕዝቡ ንጹሑን አምልኮ እስከደገፉ ድረስ ይሖዋ እንደሚባርካቸው ዋስትና ሰጥቷቸዋል። ይሁን እንጂ ‘ይህ ራእይ በአሁኑ ጊዜስ ተፈጻሚነት ይኖረዋል?’ የሚለውን ጥያቄ መልስ ማወቅ እንደምንፈልግ የታወቀ ነው።

በዘመናችን ከሕዝቅኤል ራእይ የምናገኘው ትምህርት

13, 14. (ሀ) ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ በእኛም ዘመን ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ራእዩ በየትኞቹ ሁለት መንገዶች ይጠቅመናል? (“የተለያዩ ቤተ መቅደሶች፣ የተለያዩ ትምህርቶች” የሚለውን ሣጥን 13ሀንም ተመልከት።)

13 ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ ለእኛስ የያዘው ትምህርት አለ? አዎ! ሕዝቅኤል በራእይ ባየው “በአንድ ትልቅ ተራራ” ላይ የሚገኝ ቤተ መቅደስና ኢሳይያስ “የይሖዋ ቤት ተራራ ከተራሮች አናት በላይ ጸንቶ [እንደሚቆም]” በተናገረው ትንቢት መካከል ተመሳሳይነት እንዳለ አስታውስ። ኢሳይያስ ትንቢቱ ፍጻሜውን የሚያገኘው “በዘመኑ መጨረሻ” ወይም “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። (ሕዝ. 40:2፤ ኢሳ. 2:2-4 ግርጌ፤ ሚክያስ 4:1-4⁠ንም ተመልከት።) እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ ማለትም ንጹሕ አምልኮ መልሶ ከተቋቋመበትና በትልቅ ተራራ ላይ የተቀመጠ ያህል ከፍ ከፍ ከተደረገበት ከ1919 ጀምሮ ባለው ጊዜ ነው። *

14 ስለዚህ የሕዝቅኤል ራእይ በዛሬው ጊዜ ከምናቀርበው ንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘም እንደሚሠራ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ይህ ራእይ በጥንት ዘመን የነበሩትን አይሁዳውያን ግዞተኞች እንደጠቀማቸው ሁሉ እኛንም በሁለት መንገዶች ይጠቅመናል። (1) ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን መሥፈርት እንዴት ማክበር እንደምንችል ያስተምረናል። (2) ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋምና የይሖዋን በረከት እንደምናገኝ ዋስትና ይሰጠናል።

በዛሬው ጊዜ ያለው የንጹሕ አምልኮ መሥፈርት

15. ሕዝቅኤል በራእይ ካየው ቤተ መቅደስ ትምህርት ለማግኘት ስንሞክር ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?

15 እስቲ አሁን የሕዝቅኤልን ራእይ አንዳንድ ገጽታዎች በዝርዝር እንመልከት። ከሕዝቅኤል ጋር ሆነን ይህን አስደናቂ ቤተ መቅደስ በመጎብኘት ላይ እንዳለን አድርገን እናስብ። እርግጥ ነው፣ እየጎበኘን ያለነው ታላቁን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በምናቀርበው አምልኮ ረገድ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የምንችላቸውን ትምህርቶች ለማግኘት እየሞከርን ነው። ከምናገኛቸው ትምህርቶች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

16. በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ እያንዳንዱ ነገር መለካቱ ምን ያስተምረናል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

16 ይህን ሁሉ ነገር መለካት ለምን አስፈለገ? መዳብ የሚመስል መልክ የነበረው መልአክ፣ ሕዝቅኤል እያየው ግንቦቹን፣ የዘብ ጠባቂ ክፍሎቹን፣ ግቢዎቹንና መሠዊያውን ጨምሮ መላውን ቤተ መቅደስ አንድ በአንድ ለካ። አንድ ሰው ይህን ዘገባ ሲያነብ የዝርዝር መግለጫዎቹ ብዛት ግራ ሊያጋባው ይችላል። (ሕዝ. 40:1 እስከ 42:20፤ 43:13, 14) ይሁን እንጂ እንዲህ ካለው ዝርዝር መረጃ ልናገኝ የምንችለውን ትምህርት አስብ። ይሖዋ እያንዳንዱ ነገር እንዲለካ በማድረግ፣ የእሱ መሥፈርቶች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ አበክሮ ገልጿል። መሥፈርቶቹን የሚያወጣው እሱ እንጂ ማንም ተራ ሰው አይደለም። አምላክ በየትኛውም መንገድ ቢመለክ ለውጥ እንደማያመጣ የሚያስቡ ሰዎች ካሉ በጣም ተሳስተዋል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ቤተ መቅደሱ አንድ በአንድ እንዲለካ ማድረጉ ንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋሙ እንደማይቀር ዋስትና ይሰጣል። የእያንዳንዱ ነገር ልክ በትክክል መጠቀሱ አምላክ የገባው ቃል በትክክል እንደሚፈጸም ማረጋገጫ ይሆናል። ሕዝቅኤል በዚህ መንገድ ንጹሕ አምልኮ በመጨረሻዎቹ ቀኖች መልሶ እንደሚቋቋም ዋስትና ሰጥቷል!

ቤተ መቅደሱ አንድ በአንድ መለካቱ ምን ያስተምረናል? (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

17. በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያለው ቅጥር ምን ያስገነዝበናል?

17 በዙሪያው ያለው ቅጥር። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሕዝቅኤል በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ቅጥር እንዳለ በራእዩ ላይ ተመልክቷል። ይህ ቅጥር የአምላክ ሕዝቦች የትኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ርኩሰት ከንጹሕ አምልኮ ማራቅና የአምላክን ቤት ከብክለት መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ኃይለኛ ማሳሰቢያ ነበር። (ሕዝቅኤል 43:7-9ን አንብብ።) ዛሬም ቢሆን ይህ ምክር በእጅጉ ያስፈልገናል! የአምላክ ሕዝቦች ለበርካታ መቶ ዘመናት ከቆየው የታላቂቱ ባቢሎን መንፈሳዊ ግዞት ነፃ ከወጡ በኋላ ክርስቶስ በ1919 ታማኝና ልባም ባሪያን ሾመ። በተለይ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአምላክ ሕዝቦች ከጣዖትና ከአረማዊ አምልኮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መሠረተ ትምህርቶችና ልማዶች ለማስወገድ ብዙ ጥረት አድርገዋል። መንፈሳዊ ርኩሰትን ከንጹሕ አምልኮ ለማራቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን። ሌላው ቀርቶ የተለመዱ ዕለታዊ ጉዳዮች እንኳ ከአምልኳችን ጋር እንዲቀላቀሉ ስለማንፈልግ በስብሰባ አዳራሾቻችን ውስጥ የንግድ ጉዳዮችን ከማከናወን እንቆጠባለን።—ማር. 11:15, 16

18, 19. (ሀ) በራእይ የታየው ቤተ መቅደስ ካሉት ረጃጅም በሮች ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? (ለ) ከፍተኛ የሆኑትን የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ዝቅ ለማድረግ ለሚሞክሩ ሰዎች ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? አንድ ምሳሌ ስጥ።

18 ረጃጅም በሮች። ሕዝቅኤል ስለተመለከታቸው ረጃጅም በሮች በማሰላሰል ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? ግዞተኞቹ አይሁዳውያን በራእይ የታየው ቤተ መቅደስ ስላለው ስለዚህ ገጽታ ማሰባቸው ይሖዋ ያወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጣም ከፍ ያሉ እንደሆኑ እንዳስተማራቸው ጥርጥር የለውም። ይሖዋ በጥንት ዘመን ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አውጥቶ ከነበረ በዛሬው ጊዜስ ምን ማለት ይቻላል? በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ አምልኮ የምናቀርበው በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ከመሆኑ አንጻር ግብዝነት የሌለበት ንጹሕ ምግባር ያለን መሆኑ ይበልጥ አስፈላጊ አይሆንም? (ሮም 12:9፤ 1 ጴጥ. 1:14, 15) በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ እሱ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ እንዲከተሉ ደረጃ በደረጃ መመሪያ ሲሰጣቸው ቆይቷል። * ለምሳሌ ንስሐ የማይገቡ ክፉ አድራጊዎች ከጉባኤ ይወገዳሉ። (1 ቆሮ. 5:11-13) በተጨማሪም በበሮቹ መግቢያዎች ላይ ያሉት የዘብ ጠባቂ ክፍሎች በዛሬው ጊዜም የይሖዋን ሞገስ ያላገኘ ማንኛውም ሰው እሱን ማምለክ እንደማይፈቀድለት ያስታውሱናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሁለት ዓይነት ሕይወት የሚመራ ሰው ወደ ስብሰባ አዳራሽ ሊገባ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም በአምላክ ፊት ያለውን አቋም ካላስተካከለ የይሖዋን ሞገስ ማግኘት አይችልም። (ያዕ. 4:8) ይህ ደግሞ በሥነ ምግባር ባዘቀጠው በዚህ ዘመን ለንጹሕ አምልኮ ትልቅ ጥበቃ ነው።

19 መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዓለም ወደ መጨረሻው እየቀረበ ሲሄድ ይበልጥ በሥነ ምግባር ያዘቀጠ እንደሚሆን ተንብዮአል። “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች እያሳሳቱና እየተሳሳቱ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” እንደሚሄዱ ይናገራል። (2 ጢሞ. 3:13) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ መሥፈርቶች ከልክ በላይ ጥብቅ፣ ዘመን ያለፈባቸው አልፎ ተርፎም ትክክል እንዳልሆኑ በማሰብ የሚሳሳቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። አንተስ እንዲህ ባለው አስተሳሰብ ትታለላለህ? ለምሳሌ አንድ ሰው አምላክ ግብረ ሰዶምን በተመለከተ ያወጣው መሥፈርት ትክክል እንዳልሆነ ሊያሳምንህ ቢሞክር አመለካከቱን ትቀበላለህ? ወይስ እንደዚህ ያሉትን ድርጊቶች እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች “አስነዋሪ ነገር” እያደረጉ እንዳሉ በቃሉ ላይ በግልጽ ካሰፈረው ከይሖዋ አምላክ ጋር ትስማማለህ? አምላክ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን ምንም ችግር እንደሌላቸው አድርገን እንዳንመለከት ያሳስበናል። (ሮም 1:24-27, 32) እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ረጃጅም በሮች ያሉት ቤተ መቅደስ ወደ አእምሯችን ሊመጣና ይህ ክፉ ዓለም ምንም ያህል ተጽዕኖ ቢያሳድር ይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ዝቅ እንደማያደርግ ልናስታውስ ይገባል። ከሰማዩ አባታችን ጋር በመስማማት ትክክል ለሆነው ነገር ጥብቅና እንቆማለን?

በንጹሕ አምልኮ ስንካፈል “የውዳሴ መሥዋዕት” እናቀርባለን

20. ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ከሕዝቅኤል ራእይ ምን የሚያበረታታ ሐሳብ ማግኘት ይችላሉ?

20 ግቢዎቹ። ሕዝቅኤል ሰፊ የሆነውን የቤተ መቅደሱን ውጨኛ ግቢ ሲመለከት ይሖዋን በደስታ የሚያመልኩ ምን ያህል ብዙ ሰዎች በዚያ ሊሰበሰቡ እንደሚችሉ በማሰብ ሳይደሰት አይቀርም። ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች አምልኳቸውን የሚያከናውኑት ከዚያ ይበልጥ እጅግ ቅዱስ በሆነ ስፍራ ነው። በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውጨኛ ግቢ ውስጥ ይሖዋን የሚያመልኩት ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ከሕዝቅኤል ራእይ የሚያበረታታ ሐሳብ ማግኘት ይችላሉ። (ራእይ 7:9, 10, 14, 15) ሕዝቅኤል በግቢው ዙሪያ የመመገቢያ ክፍሎች እንዳሉ ተመልክቶ ነበር። የኅብረት መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች፣ ካመጡት መሥዋዕት ላይ የተወሰነውን በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ይበሉ ነበር። (ሕዝ. 40:17) እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ አምላክ ጋር አብረው እንደተመገቡ ሊቆጠር ይችላል፤ ይህም በይሖዋና በእነሱ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት መኖሩን የሚያሳይ ምልክት ነው! እርግጥ ነው፣ እኛ በሙሴ ሕግ ሥር እንደነበሩት አይሁዳውያን መሥዋዕት አናቀርብም። ሆኖም በንጹሕ አምልኮ ስንካፈል፣ ለምሳሌ በስብሰባዎቻችን ላይ ሐሳብ ስንሰጥ ወይም አገልግሎት ወጥተን ስለ እምነታችን ስንናገር “የውዳሴ መሥዋዕት” እያቀረብን ነው። (ዕብ. 13:15) በተጨማሪም ይሖዋ የሚያቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ እንመገባለን። “በሌላ ቦታ አንድ ሺህ ቀን ከመኖር በቅጥር ግቢዎችህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላል” ብለው ለይሖዋ የዘመሩትን የቆሬን ልጆች ሐሳብ እንደምንጋራ ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝ. 84:10

21. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሕዝቅኤል ራእይ ላይ ስለ ካህናቱ ከተገለጸው ነገር ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

21 ካህናቱ። ሕዝቅኤል ባየው ራእይ ላይ ካህናቱና ሌዋውያኑ ወደ ውስጠኛው ግቢ የሚገቡባቸው በሮች፣ ካህናት ያልሆኑት ነገዶች ወደ ውጨኛው ግቢ ከሚገቡባቸው በሮች ጋር ተመሳሳይ ነበሩ። ይህም ካህናቱም ቢሆኑ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በሙሉ ማሟላት እንደሚኖርባቸው ያስታውሳቸዋል። በዛሬው ጊዜ ከዚህ ትምህርት የሚያገኙት እነማን ናቸው? በዘመናችን በአምላክ አገልጋዮች መካከል በዘር ውርሻ የሚተላለፍ የክህነት አገልግሎት የለም፤ ይሁን እንጂ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘እናንተ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት ናችሁ’ ተብለዋል። (1 ጴጥ. 2:9) በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ካህናት አምልኳቸውን የሚያቀርቡት ለእነሱ በተለየው ውስጠኛ ግቢ ነበር። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች አምልኮ የሚያቀርቡት ቃል በቃል ከእምነት ባልንጀሮቻቸው የተለየ ቦታ ላይ ሆነው አይደለም፤ ሆኖም ይሖዋ እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለወሰዳቸው ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና አላቸው። (ገላ. 4:4-6) ይሁንና ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሕዝቅኤል ራእይ ጠቃሚ ማሳሰቢያ ሊያገኙ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ካህናቱም ምክርና ተግሣጽ ተሰጥቷቸው እንደነበር ልብ ማለት ይኖርባቸዋል። ሁላችንም ብንሆን ‘በአንድ እረኛ’ ሥር የምናገለግል “አንድ መንጋ” መሆናችንን ማስታወስ ያስፈልገናል።—ዮሐንስ 10:16ን አንብብ።

22, 23. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ ከተጠቀሰው አለቃ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ? (ለ) ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል?

22 አለቃው። በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ አለቃው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጉልህ ስፍራ ተሰጥቶታል። እርግጥ አለቃው ከካህናቱ ነገድ አይደለም፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ከሚከናወነው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ለካህናቱ አመራር መገዛት ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ሕዝቡን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት ነበረው፤ በተጨማሪም አንዳንድ መሥዋዕቶችን በማቅረብ ረገድ ሕዝቡን ይረዳ ነበር። (ሕዝ. 44:2, 3፤ 45:16, 17፤ 46:2) ስለሆነም በዛሬው ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ለተጣለባቸው ክርስቲያን ወንዶች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ምክንያቱም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ጨምሮ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ለተቀባው ታማኝ ባሪያ መገዛት ይኖርባቸዋል። (ዕብ. 13:17) እነዚህ ወንድሞች የአምላክ ሕዝቦች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና በአገልግሎት የውዳሴ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ለማገዝ ተግተው ይሠራሉ። (ኤፌ. 4:11, 12) በተጨማሪም ሽማግሌዎች፣ የእስራኤል አለቆች ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀማቸው ይሖዋ እንዴት እንደገሠጻቸው ልብ ሊሉ ይገባል። (ሕዝ. 45:9) እነሱም በተመሳሳይ ምክርና እርማት እንደማያስፈልጋቸው ሆኖ አይሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በእረኝነትና በበላይ ተመልካችነት ሥራቸው ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይችሉ ዘንድ እነሱን ለማጥራት ባደረጋቸው ዝግጅቶች በሚገባ ይጠቀማሉ።—1 ጴጥሮስ 5:1-3ን አንብብ።

23 ይሖዋ ወደፊት ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜም ብቃት ባላቸውና አፍቃሪ በሆኑ የበላይ ተመልካቾች መጠቀሙን ይቀጥላል። ብዙ ሽማግሌዎች በገነት ውስጥ ሌሎችን የሚረዱና ብቃት ያላቸው እረኞች መሆን እንዲችሉ ከአሁኑ ሥልጠና እያገኙ እንዳለ ሊቆጠር ይችላል። (መዝ. 45:16) እነዚህ ወንዶች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን ያህል ጠቃሚ ሥራ ማከናወን እንደሚችሉ ማሰብ በእጅጉ አያስደስትም? ስለ መልሶ መቋቋም እንደሚናገሩት ሌሎች ትንቢቶች ሁሉ ስለ ሕዝቅኤል ራእይ ያለን ግንዛቤም ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ይበልጥ እየጠራ ይሄድ ይሆናል። ምናልባትም አንዳንዶቹ የራእዩ ገጽታዎች አሁን ፈጽሞ ልንገምተው በማንችለው መንገድ ወደፊት ፍጻሜያቸውን ሊያገኙ ይችላሉ። ይህን ጊዜ ያሳየናል።

ረጃጅሞቹ በሮችና ግቢዎቹ ስለ አምልኳችን ምን ያስተምሩናል? (ከአንቀጽ 18-21⁠ን ተመልከት)

ይሖዋ ንጹሕ አምልኮን ይባርካል

24, 25. የሕዝቅኤል ራእይ የይሖዋ ሕዝቦች ንጹሕ አምልኮን እስከደገፉ ድረስ የሚያገኟቸውን በረከቶች የሚገልጸው እንዴት ነው?

24 በመጨረሻም በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የተከናወነውን አንድ ታላቅ ክንውን እንመልከት። ይሖዋ በራእይ ወደታየው ቤተ መቅደስ መጣ፤ ከዚያም ሕዝቦቹ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በታማኝነት እስከጠበቁ ድረስ በዚያ እንደሚኖር ቃል ገባላቸው። (ሕዝ. 43:4-9) ይሖዋ በዚያ መኖሩ በሕዝቡና በምድራቸው ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?

25 ራእዩ የሚከተሉትን ሁለት ትንቢታዊ መግለጫዎች በመጠቀም አምላክ የሚያፈስላቸውን በረከት ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ይገልጻል፦ (1) አንድ ወንዝ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ በመፍሰስ በምድሪቱ ላይ ልምላሜና ሕይወት ይዘራል፤ እንዲሁም (2) ምድሪቱ ሥርዓት ባለውና በተስተካከለ መንገድ ተለክታ ትከፋፈላለች፤ ቤተ መቅደሱና ቅጥር ግቢውም መሃል ላይ እንዲሆን ይደረጋል። በራእዩ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ትንቢታዊ መግለጫዎች የምንረዳቸው እንዴት ነው? አሁን የምንኖረው ይሖዋ ወደ ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በመግባት ቤተ መቅደሱን ባጠራበት እንዲሁም በዚያ የሚቀርበውን እጅግ ቅዱስ የሆነ አምልኮ እየተቀበለ ባለበት ዘመን ውስጥ ከመሆኑ አንጻር እነዚህ ትንቢታዊ መግለጫዎች ለእኛ ትልቅ ትርጉም አላቸው። (ሚል. 3:1-4) በዚህ መጽሐፍ ከምዕራፍ 19 እስከ 21 ላይ ስለ እነዚህ ትንቢታዊ መግለጫዎች እንመረምራለን።

^ አን.6 እዚህ ላይ ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ቀደም ሲል ከቅዱስ ቤቱ ጋር በተያያዘ ያደርጉ ከነበረው ነገር በእጅጉ የተለየ ሁኔታ እንደሚኖር መግለጹ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በእኔና በእነሱ መካከል ግንቡ ብቻ ሲቀር፣ ደፋቸውን ከቤቴ ደፍ አጠገብ፣ መቃናቸውንም ከቤቴ መቃን አጠገብ በማድረግ በሠሯቸው አስጸያፊ ነገሮች ቅዱስ ስሜን አርክሰዋል።” (ሕዝ. 43:8) በጥንቷ ኢየሩሳሌም የይሖዋን ቤተ መቅደስ ከግለሰቦች መኖሪያ ቤት የሚለየው አንድ ግንብ ብቻ ነበር። ሕዝቡ ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች እየራቁ ሲሄዱ ርኩሰታቸውንና የጣዖት አምልኳቸውን የይሖዋ ቤት አጠገብ ድረስ አምጥተው ነበር። ይህ በቸልታ የሚታለፍ ጉዳይ አልነበረም!

^ አን.13 ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ፍጻሜያቸውን ካገኙ፣ ስለ መልሶ መቋቋም የሚናገሩ ሌሎች ትንቢቶች ጋር ዝምድና አለው። ለምሳሌ በሕዝቅኤል 43:1-9 እና በሚልክያስ 3:1-5 እንዲሁም በሕዝቅኤል 47:1-12 እና በኢዩኤል 3:18 መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ልብ በል።

^ አን.18 መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ኢየሱስ በተጠመቀበትና ሊቀ ካህናት ሆኖ ማገልገል በጀመረበት ወቅት ማለትም በ29 ዓ.ም. ነው። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ባሉት በርካታ መቶ ዓመታት በዚህ ምድር ላይ ንጹሕ አምልኮ ችላ ተብሎ ቆይቷል። እውነተኛው አምልኮ ከፍ የተደረገው በተለይ ከ1919 ወዲህ ነው።