በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 16

‘በግንባራቸው ላይ ምልክት አድርግ’

‘በግንባራቸው ላይ ምልክት አድርግ’

ሕዝቅኤል 9:4

ፍሬ ሐሳብ፦ በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩ ታማኝ ሰዎች ከጥፋት እንዲተርፉ ምልክት የተደረገባቸው እንዴት ነው? ምልክቱ ለዘመናችን ያለው ትርጉምስ ምንድን ነው?

1-3. (ሀ) ሕዝቅኤል የደነገጠው ለምንድን ነው? ከኢየሩሳሌም ጥፋት ጋር በተያያዘስ ምን ነገር ተገነዘበ? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ሕዝቅኤል ክው ብሏል! ከሃዲ የሆኑ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ድርጊቶች በራእይ ማየቱ በጣም አስደንግጦታል። * እነዚህ ዓመፀኞች በእስራኤል የነበረውን የንጹሕ አምልኮ ማዕከል አርክሰዋል። ነገር ግን የረከሰው ቤተ መቅደሱ ብቻ አልነበረም። በመላው የይሁዳ ምድር ዓመፅ ነግሦ የነበረ ሲሆን ሁኔታው ምንም ተስፋ ያለው አይመስልም። ይሖዋ የተመረጡ ሕዝቦቹ ይፈጽሙት በነበረው ድርጊት እጅግ ስላዘነ ሕዝቅኤልን “በቁጣ እርምጃ እወስዳለሁ” አለው።—ሕዝ. 8:17, 18

2 ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ በኢየሩሳሌምና በአንድ ወቅት ቅዱስ በነበረው ቤተ መቅደሷ ላይ መቆጣቱ ብሎም ሊያጠፋቸው መወሰኑ በጣም አሳዝኖት መሆን አለበት። ሕዝቅኤል ‘በከተማዋ ውስጥ ያሉ ታማኝ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? ከጥፋቱ ይተርፉ ይሆን? ከሆነስ የሚተርፉት እንዴት ነው?’ ብሎ ሳያስብ አይቀርም። ሆኖም መልሱን ለማወቅ ብዙ መጠበቅ አላስፈለገውም። በኢየሩሳሌም ላይ የተላለፈውን ኃይለኛ ፍርድ ከሰማ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ ድምፅ የመለኮታዊውን ፍርድ አስፈጻሚዎች ሲጣራ ሰማ። (ሕዝ. 9:1) ሕዝቅኤል ራእዩን መመልከቱን ሲቀጥል፣ የሚጠፉት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑና መዳን የሚገባቸው ሰዎች ከጥፋቱ እንደሚተርፉ ተገነዘበ። ይህን ማወቁ እፎይታ እንዲሰማው አድርጎት መሆን አለበት።

3 እኛም የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ከፊታችን የተደቀነብን ከመሆኑ አንጻር ‘ከመጪው ታላቅ ጥፋት የሚድነው ማን ይሆን?’ ብለን ማሰባችን አይቀርም። ስለዚህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመራችን ተገቢ ነው፦ (1) ሕዝቅኤል በራእዩ ላይ ቀጥሎ የተመለከተው ነገር ምንድን ነው? (2) ራእዩ በሕዝቅኤል ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (3) ይህ ትንቢታዊ ራእይ ለዘመናችን ምን ትርጉም አለው?

“ከተማዋን የሚቀጡት . . . እንዲመጡ ጥሯቸው”

4. ሕዝቅኤል በራእዩ ላይ ቀጥሎ ያየውና የሰማው ነገር ምንድን ነው?

4 ሕዝቅኤል በራእዩ ላይ ቀጥሎ ያየውና የሰማው ነገር ምንድን ነው? (ሕዝቅኤል 9:1-11ን አንብብ።) ሰባት ሰዎች “በሰሜን ትይዩ ባለው በላይኛው በር በኩል” መጡ፤ ምናልባትም የመጡት የቅናት ጣዖት ምልክት ከቆመበት ወይም ሴቶች ታሙዝ ለተባለው አምላክ ከሚያለቅሱበት ቦታ አቅራቢያ ሊሆን ይችላል። (ሕዝ. 8:3, 14) ሰባቱ ሰዎች ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ግቢ ገቡና ከመዳብ በተሠራው መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። ሆኖም ሰዎቹ በዚያ የቆሙት መሥዋዕት ለማቅረብ አልነበረም። ይሖዋ በዚያ ቤተ መቅደስ የሚቀርቡ መሥዋዕቶችን የሚቀበልበት ጊዜ አልፏል። ስድስቱ ሰዎች “እያንዳንዳቸው በእጃቸው የማጥፊያ መሣሪያ” ይዘው ቆመዋል። ሰባተኛው ሰው ግን ከእነሱ የተለየ ነው። ይህ ሰው በፍታ የለበሰ ሲሆን የያዘውም የማጥፊያ መሣሪያ ሳይሆን “የጸሐፊ የቀለም ቀንድ” ወይም የግርጌ ማስታወሻው እንደሚለው “የጸሐፊ ቀለም መያዣ” ነበር።

5, 6. ምልክት የተደረገባቸውን ሰዎች በተመለከተ ምን ማለት ይቻላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

5 የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው የሚያከናውነው ሥራ ምንድን ነው? ይሖዋ ራሱ የሚከተለውን ከባድ ተልእኮ ሰጠው፦ “በከተማዋ መካከል ይኸውም በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፤ በከተማዋ ውስጥ እየተፈጸሙ ባሉት አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ እያዘኑና እየቃተቱ ባሉት ሰዎች ግንባር ላይም ምልክት አድርግ።” ምናልባትም ሕዝቅኤል ይህን ሲሰማ በጥንት ጊዜ የበኩር ልጆቻቸው ከጥፋት እንዲተርፉ በበራቸው ጉበንና መቃኖች ላይ የደም ምልክት ያደረጉትን ታማኝ እስራኤላውያን ወላጆች አስታውሶ ይሆናል። (ዘፀ. 12:7, 22, 23) በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው በሰዎቹ ግንባር ላይ የሚያደርገው ምልክትስ ሰዎቹ ከኢየሩሳሌም ጥፋት የሚተርፉ መሆኑን የሚያመለክት ይሆን?

6 የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ምልክት የሚደረግባቸው ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ መመልከት ይኖርብናል። ምልክቱ የሚደረገው “በከተማዋ ውስጥ እየተፈጸሙ ባሉት” አስጸያፊ ነገሮች “እያዘኑና እየቃተቱ” ባሉት ሰዎች ግንባር ላይ ነው። እንግዲያው ምልክት የተደረገባቸውን ሰዎች በተመለከተ ምን ማለት ይቻላል? አንደኛ ነገር፣ እነዚህ ሰዎች ከልባቸው ያዘኑት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይፈጸም በነበረው ጣዖት አምልኮ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ኢየሩሳሌምን በሞላው ዓመፅ፣ የሥነ ምግባር ብልግናና ምግባረ ብልሹነት ጭምር ነው። (ሕዝ. 22:9-12) በተጨማሪም ሰዎቹ የተሰማቸውን ሐዘን በውስጣቸው ብቻ ይዘው የነበረ አይመስልም። ቅን ልብ ያላቸው እነዚህ ሰዎች በምድሪቱ ይፈጸሙ በነበሩት ነገሮች ምክንያት የተሰማቸውን ሐዘንና ለንጹሕ አምልኮ ያላቸውን ታማኝነት በንግግራቸውም ሆነ በድርጊታቸው በግልጽ አሳይተው መሆን አለበት። መሐሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ መትረፍ የሚገባቸውን እነዚህን ሰዎች ከጥፋቱ ያድናቸዋል።

7, 8. የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ሰዎች ተልእኳቸውን የሚፈጽሙት እንዴት ነው? በመጨረሻስ ምን ሆነ?

7 ታዲያ የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ስድስት ሰዎች ተልእኳቸውን የሚፈጽሙት እንዴት ነው? ሕዝቅኤል ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች የሰጠውን መመሪያ ሰምቷል፤ ሰዎቹ የቀለም ቀንድ የያዘውን ሰው ተከትለው እንዲሄዱና በግንባራቸው ላይ ምልክት ከተደረገባቸው ሰዎች በስተቀር ሁሉንም ሰው እንዲገድሉ ታዘዋል። ይሖዋ ‘ከመቅደሴ ጀምሩ’ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ሕዝ. 9:6) የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ሰዎች ሥራቸውን የሚጀምሩት በኢየሩሳሌም እምብርት ከሚገኘውና የይሖዋን ሞገስ ካጣው ቤተ መቅደስ ነው። በመጀመሪያ የተገደሉት ‘በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት የነበሩት ሽማግሌዎች’ ማለትም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሐሰት አማልክት ያጥኑ የነበሩት ሰባዎቹ የእስራኤል ሽማግሌዎች ናቸው።—ሕዝ. 8:11, 12፤ 9:6

8 በመጨረሻስ ምን ሆነ? ሕዝቅኤል ራእዩን ማየቱን ሲቀጥል የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው “ልክ እንዳዘዝከኝ አድርጌአለሁ” በማለት ለይሖዋ ሪፖርት ሲያቀርብ ሰማ። (ሕዝ. 9:11) ታዲያ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ምን ደርሶባቸው ይሆን? ከጥፋቱ የተረፉ ታማኝ ሰዎች ይኖሩ ይሆን?

ራእዩ በሕዝቅኤል ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?

9, 10. ከኢየሩሳሌም ጥፋት ከዳኑት ታማኝ ሰዎች መካከል እነማን ይገኙበታል? እነዚህን ሰዎች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

9 ሁለተኛ ዜና መዋዕል 36:17-20ን አንብብ። የሕዝቅኤል ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ607 ዓ.ዓ. የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ባጠፋበት ጊዜ ነበር። ይሖዋ ‘በእጁ እንዳለ ጽዋ’ የሆኑትን ባቢሎናውያንን ተጠቅሞ በከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም ላይ ቁጣውን በማፍሰስ የቅጣት ፍርዱን አስፈጸመ። (ኤር. 51:7) ጥፋቱ ጅምላ ጨራሽ ነበር? በፍጹም። ሕዝቅኤል ባየው ራእይ ላይ በባቢሎናውያን የማይገደሉ ሰዎች እንደሚኖሩ ተገልጿል።—ዘፍ. 18:22-33፤ 2 ጴጥ. 2:9

10 ሬካባውያንን፣ ኢትዮጵያዊው ኤቤድሜሌክን፣ ነቢዩ ኤርምያስንና ጸሐፊው ባሮክን ጨምሮ የተወሰኑ ታማኝ ሰዎች ከጥፋቱ ተርፈዋል። (ኤር. 35:1-19፤ 39:15-18፤ 45:1-5) እነዚህ ሰዎች በኢየሩሳሌም ውስጥ ‘እየተፈጸሙ ባሉት አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ ያዝኑና ይቃትቱ’ እንደነበር ሕዝቅኤል ያየው ራእይ ይጠቁማል። (ሕዝ. 9:4) ገና ጥፋቱ ከመድረሱ በፊት፣ ለክፋት ያላቸውን ልባዊ ጥላቻና ለንጹሕ አምልኮ ያላቸውን ታማኝነት እንዳሳዩ ምንም ጥያቄ የለውም፤ በዚህም ምክንያት ከጥፋቱ ለመትረፍ በቅተዋል።

11. የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ስድስት ሰዎችና የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው እነማንን ይወክላሉ?

11 እነዚህ ታማኝ ሰዎች ከጥፋት ለመትረፍ የሚያስችል ምልክት ቃል በቃል ተደርጎባቸው ነበር? ሕዝቅኤልም ሆነ ሌላ ማንም ነቢይ በኢየሩሳሌም ከተማ እየተዘዋወረ በታማኝ ሰዎች ግንባር ላይ ምልክት እንዳደረገ የሚገልጽ ታሪክ የለም። በመሆኑም የሕዝቅኤል ትንቢታዊ ራእይ የሚያሳየው ከሰብዓዊ ዓይን እይታ ውጭ በሆነው በመንፈሳዊው ዓለም ይከናወን የነበረውን ነገር መሆን አለበት። በራእዩ ላይ የታዩት የማጥፊያ መሣሪያ የያዙ ስድስት ሰዎችና የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው፣ ምንጊዜም የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም በተጠንቀቅ የሚጠብቁትን ታማኝ መንፈሳዊ ፍጡራን ይወክላሉ። (መዝ. 103:20, 21) ይሖዋ በከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ላይ የተወሰደውን የፍርድ እርምጃ ለመምራት በመላእክቱ ተጠቅሞ እንደነበረ አያጠራጥርም። መላእክቱ ፍርዱ ጅምላ ጨራሽ ሳይሆን ጥፋት የሚገባቸውን ብቻ መርጦ የሚያጠፋ እንዲሆን አድርገዋል፤ በዚህ መንገድ ከጥፋቱ በሚተርፉት ሰዎች ግንባር ላይ ምልክት እንዳደረጉ ሊቆጠር ይችላል።

የሕዝቅኤል ራእይ ለዘመናችን ምን ትርጉም አለው?

12, 13. (ሀ) ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣውን ያፈሰሰው ለምን ነበር? በዘመናችንም የቁጣ እርምጃ ይወስዳል ብለን መጠበቅ የምንችለውስ ለምንድን ነው? (ለ) ከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ ነች? አብራራ። (“ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ ነች?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

12 በዚህ ዘመን የምንኖር ሰዎች፣ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ተወዳዳሪ የሌለው መለኮታዊ ፍርድ የሚፈጸምበት “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ” ከፊታችን ተደቅኖብናል። (ማቴ. 24:21) ከዚህ ወሳኝ ክንውን ጋር በተያያዘ አንዳንድ ቁልፍ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፦ በመጪው ጥፋት ወቅት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ? ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ የሚያቀርቡ ሰዎች ከጥፋቱ እንዲተርፉ ምልክት ይደረግባቸዋል? በሌላ አባባል፣ የቀለም ቀንድ ስለያዘው ሰው የሚገልጸው የሕዝቅኤል ትንቢታዊ ራእይ በዘመናችን ፍጻሜ ይኖረዋል? የሦስቱም ጥያቄዎች መልስ ‘አዎ’ የሚል ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መልሱን ለማግኘት የሕዝቅኤልን ራእይ መለስ ብለን እንመልከት።

13 ይሖዋ በጥንቷ ኢየሩሳሌም ላይ ቁጣውን ያፈሰሰው ለምን እንደነበር ታስታውሳለህ? እስቲ ሕዝቅኤል 9:8, 9በድጋሚ እንመልከት። (ጥቅሱን አንብብ።) ሕዝቅኤል መጪው ጥፋት “የእስራኤልን ቀሪዎች ሁሉ” ያጠፋ ይሆን የሚል ስጋት ባደረበት ወቅት ይሖዋ ጥፋቱን እንዲያመጣ ያነሳሱትን አራት ምክንያቶች ገለጸለት። አንደኛ፣ ብሔሩ የፈጸመው “በደል እጅግ በጣም ታላቅ” ነበር። * ሁለተኛ፣ የይሁዳ ምድር “በደም ተጥለቅልቃለች።” ሦስተኛ፣ የይሁዳ መንግሥት ዋና ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም “በክፋት ተሞልታለች።” አራተኛ፣ ሕዝቡ “ይሖዋ አያይም” ብለው በማሰብ ለክፉ መንገዳቸው ሰበብ ያቀርቡ ነበር። እነዚህ መግለጫዎች በዛሬው ጊዜ ያለውን በሥነ ምግባር ያዘቀጠ፣ ዓመፀኛ፣ በክፋት የተሞላና እምነት የለሽ የሆነ ዓለም ጥሩ አድርገው የሚገልጹ አይደሉም? በእርግጥም ይሖዋ ‘ስለማይለወጥ’ በሕዝቅኤል ዘመን የጽድቅ ቁጣውን የቀሰቀሱት ነገሮች በዘመናችንም እንደሚያስቆጡት ጥያቄ የለውም። (ያዕ. 1:17፤ ሚል. 3:6) በመሆኑም የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ስድስት ሰዎችም ሆኑ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው በዘመናችንም የሚያከናውኑት ሥራ ይኖራል ብለን መጠበቅ እንችላለን።

የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ስድስት ሰዎች በቅርቡ የሚያከናውኑት ሥራ ይኖራቸዋል (አንቀጽ 12, 13⁠ን ተመልከት)

14, 15. ይሖዋ ጥፋት ከማምጣቱ በፊት ሰዎችን እንደሚያስጠነቅቅ የትኞቹ ምሳሌዎች ያሳያሉ?

14 ታዲያ የሕዝቅኤል ትንቢታዊ ራእይ በዘመናችን ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? ራእዩ በጥንት ዘመን እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ ማየታችን በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት ምን እንደሚከናወን መገንዘብ እንድንችል ይረዳናል። ከሕዝቅኤል ትንቢት ጋር በተያያዘ እስካሁን የተፈጸሙትንም ሆነ ወደፊት የሚፈጸሙትን ክንውኖች እስቲ እንመልከት።

15 ይሖዋ ጥፋት ከማምጣቱ በፊት ሰዎችን ያስጠነቅቃል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ሕዝቅኤልን “ለእስራኤል ቤት ጠባቂ” አድርጎ ሾሞታል። (ሕዝ. 3:17-19) ከ613 ዓ.ዓ. ጀምሮ ሕዝቅኤል በመምጣት ላይ ስለነበረው ጥፋት እስራኤላውያንን በግልጽ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። ኢሳይያስንና ኤርምያስን ጨምሮ ሌሎች ነቢያትም በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚመጣው ጥፋት ማስጠንቀቂያ አሰምተዋል። (ኢሳ. 39:6, 7፤ ኤር. 25:8, 9, 11) በዘመናችንም ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈን አንድ ቡድን በመጠቀም፣ ‘ቤተሰቦች’ የተባሉትን በንጹሕ አምልኮ የሚካፈሉ ሰዎች እየመገበ ከመሆኑም ሌላ በፍጥነት እየቀረበ ስላለው ታላቅ መከራ ሰዎችን በማስጠንቀቅ ላይ ነው።—ማቴ. 24:45

16. ከጥፋት በሚተርፉት ሰዎች ላይ ምልክት የሚያደርጉት የይሖዋ ሕዝቦች ናቸው? አብራራ።

16 ከጥፋት በሚተርፉት ሰዎች ላይ ምልክት የሚያደርጉት የይሖዋ ሕዝቦች አይደሉም። በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ በሚድኑት ላይ ምልክት እንዲያደርግ የታዘዘው ሕዝቅኤል እንዳልሆነ አስታውስ። በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችም ከጥፋት መትረፍ በሚገባቸው ሰዎች ላይ ምልክት የማድረግ ተልእኮ አልተሰጣቸውም። ከዚህ ይልቅ የክርስቶስ ቤተሰቦች እንደመሆናችን መጠን የመስበክ ተልእኮ ተሰጥቶናል። የአምላክን መንግሥት ምሥራች በቅንዓት ለሰዎች በማካፈልና ይህ ክፉ ዓለም ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ መሆኑን በማስጠንቀቅ ይህን ተልእኮ አክብደን እንደምንመለከት እናሳያለን። (ማቴ. 24:14፤ 28:18-20) በዚህ መንገድ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በንጹሕ አምልኮ እንዲካፈሉ በመርዳቱ ሥራ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።—1 ጢሞ. 4:16

17. ሰዎች ወደፊት ከጥፋት ለመትረፍ የሚያስችለው ምልክት እንዲደረግባቸው ከወዲሁ ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?

17 ሰዎች ከመጪው ጥፋት ለመዳን ከወዲሁ እምነት እንዳላቸው ማስመሥከር አለባቸው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በ607 ዓ.ዓ. ከደረሰው የኢየሩሳሌም ጥፋት የተረፉት፣ ለክፋት ያላቸውን ጥላቻና ለንጹሕ አምልኮ ያላቸውን ታማኝነት አስቀድመው ያስመሠከሩ ሰዎች ናቸው። በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሰዎች በሕይወት ለመትረፍ፣ ጥፋቱ ከመምጣቱ በፊት በዓለም ላይ ባለው ክፋት ከልባቸው ‘ማዘንና መቃተት’ አለባቸው። በተጨማሪም ስሜታቸውን በውስጣቸው ብቻ ከመያዝ ይልቅ ለንጹሕ አምልኮ ያላቸውን ታማኝነት በቃልም ሆነ በድርጊት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ እየተከናወነ ለሚገኘው የስብከት ሥራ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት፣ ክርስቶስን በመምሰል፣ ራሳቸውን ለይሖዋ በመወሰንና በመጠመቅ እንዲሁም የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት በመደገፍ ነው። (ሕዝ. 9:4፤ ማቴ. 25:34-40፤ ኤፌ. 4:22-24፤ 1 ጴጥ. 3:21) ከጥፋቱ እንዲተርፉ ምልክት የሚደረግባቸው ከወዲሁ እነዚህን እርምጃዎች የሚወስዱና ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ከንጹሕ አምልኮ ጎን የሚሰለፉ ሰዎች ብቻ ናቸው።

18. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ መዳን በሚገባቸው ሰዎች ላይ ምልክት የሚያደርገው መቼና እንዴት ነው? (ለ) ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምልክት ይደረግባቸዋል? አብራራ።

18 ከጥፋት በሚተርፉት ሰዎች ላይ ምልክት የማድረጉ ሥራ የሚከናወነው በመንፈሳዊው ዓለም ነው። በሕዝቅኤል ዘመን መላእክት ከጥፋት በሚድኑት ሰዎች ላይ ምልክት በማድረጉ ሥራ ተካፍለው ነበር። በዘመናችን የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው በሕዝቦች ሁሉ ላይ ለመፍረድ “በክብሩ” የሚመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል። (ማቴ. 25:31-33) ኢየሱስ ፈራጅ ሆኖ የሚመጣው በታላቁ መከራ ወቅት የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ነው። * በዚያ ወሳኝ ወቅት፣ ማለትም ልክ አርማጌዶን ከመጀመሩ በፊት ኢየሱስ ሰዎችን በጎች ወይም ፍየሎች ብሎ በመለየት ፍርድ ይሰጣል። ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ‘በጎች ናችሁ’ ተብለው ይፈረድላቸዋል ወይም ምልክት ይደረግባቸዋል፤ ይህም ‘ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚሄዱ’ ያመለክታል። (ራእይ 7:9-14፤ ማቴ. 25:34-40, 46) ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱ ከአርማጌዶን ለመትረፍ ምልክቱ አያስፈልጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ከመሞታቸው በፊት ወይም ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻው ማኅተም ይደረግባቸዋል። ከዚያም በታላቁ መከራ ወቅት በምድር ላይ የሚኖሩ ቅቡዓን፣ አርማጌዶን ከመጀመሩ በፊት ወደ ሰማይ ይሄዳሉ።—ራእይ 7:1-3

19. ከኢየሱስ ጋር በመሆን በዚህ ሥርዓት ላይ የጥፋት ፍርድ የሚያስፈጽሙት እነማን ናቸው? (“ማዘንና መቃተት፣ ምልክት ማድረግ፣ ማጥፋት—መቼና እንዴት?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

19 በሰማይ ሆኖ የሚገዛው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስና ሰማያዊ ሠራዊቱ በዚህ ሥርዓት ላይ የቅጣት ፍርድ ያስፈጽማሉ። በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ስድስት ሰዎች ጥፋቱን የጀመሩት በፍታ የለበሰው ሰው ምልክት አድርጎ ከጨረሰ በኋላ እንደነበር አስታውስ። (ሕዝ. 9:4-7) በተመሳሳይም መጪው ጥፋት የሚጀምረው ኢየሱስ በሕዝቦች ሁሉ ላይ ከፈረደና በጎቹ ከጥፋት እንዲተርፉ ምልክት ካደረገባቸው በኋላ ነው። ከዚያም በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ኢየሱስ ቅዱሳን መላእክትንና አብረውት የሚገዙትን 144,000 ቅቡዓን በሙሉ ያቀፈውን ፍርድ አስፈጻሚ ሠራዊት በማሰለፍ ከዚህ ክፉ ዓለም ጋር ይዋጋል፤ ይህን ክፉ ዓለም ሙሉ በሙሉ ካጠፋ በኋላ ከንጹሕ አምልኮ ጎን የቆሙትን ሰዎች ጽድቅ ወደሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ያስገባቸዋል።—ራእይ 16:14-16፤ 19:11-21

20. የጸሐፊ የቀለም ቀንድ ስለያዘው ሰው ከሚገልጸው የሕዝቅኤል ራእይ ምን አበረታች ትምህርት እናገኛለን?

20 የጸሐፊ የቀለም ቀንድ ስለያዘው ሰው ከሚገልጸው የሕዝቅኤል ራእይ ላገኘነው አበረታች ትምህርት ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይሖዋ ጻድቃንን ከክፉዎች ጋር እንደማያጠፋ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች እንድንሆን አድርጎናል። (መዝ. 97:10) ወደፊት ከጥፋት ለመትረፍ የሚያስችል ምልክት እንዲደረግብን ከወዲሁ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ተምረናል። የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን በሰይጣን ዓለም ውስጥ በሚሠራው ክፋት ለሚያዝኑና ለሚቃትቱ ሰዎች ምሥራቹን በማወጁና ስለ መጪው ጥፋት ሰዎችን በማስጠንቀቁ ሥራ አቅማችን በፈቀደው መጠን ለመካፈል ቆርጠናል። በዚህ መንገድ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ያላቸው ሰዎች አብረውን ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ እንዲያቀርቡ የመርዳት መብት እናገኝ ይሆናል፤ ይህም እነዚህ ሰዎች ከጥፋት ለመትረፍ የሚያስችለው ምልክት እንዲደረግባቸውና ጽድቅ ወደሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ዓለም ለመግባት እንዲበቁ ያስችላቸዋል።—ሥራ 13:48

^ አን.1 ሕዝቅኤል በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይከናወኑ ስለነበሩት አስጸያፊ ነገሮች የተመለከተው ራእይ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ላይ ተብራርቷል።

^ አን.13 አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው “በደል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት” የሚል ሐሳብ ሊያስተላልፍ ይችላል። ሌላ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ደግሞ ይህ ቃል “ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሳ ቃል ሲሆን ሁልጊዜ ማለት ይቻላል፣ በአምላክ ዓይን ስህተት ወይም ጥፋት የሆነ ድርጊት መፈጸምን ለማመልከት” እንደሚሠራበት ገልጿል።

^ አን.18 ታላቂቱ ባቢሎን ትጠፋለች ሲባል የሐሰት ሃይማኖት አባላት በሙሉ ይሞታሉ ማለት እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። በዚያ ጊዜ አንዳንድ ቀሳውስት እንኳ ሳይቀሩ የሐሰት ሃይማኖትን ሊክዱና ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ኖሯቸው እንደማያውቅ ሊናገሩ ይችላሉ።—ዘካ. 13:3-6