በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማስተካከያ የተደረገባቸው ትምህርቶች

ማስተካከያ የተደረገባቸው ትምህርቶች

ባለፉት ዓመታት፣ መጠበቂያ ግንብ ከሕዝቅኤል ትንቢት ጋር በተያያዘ ያለን ግንዛቤ እየጠራ እንደመጣ የሚያሳዩ ርዕሶችን ይዞ ወጥቶ ነበር። የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ! የተባለው ይህ መጽሐፍም ሌሎች ተጨማሪ ማስተካከያዎችን ይዟል። እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር።

የሕያዋን ፍጥረታቱ አራት ፊቶች ምን ያመለክታሉ?

ቀደም ሲል የነበረን ግንዛቤ፦ የሕያዋን ፍጥረታቱ ወይም የኪሩቦቹ አራት ፊቶች የይሖዋን አራት ዋና ዋና ባሕርያት ያመለክታሉ።

ማስተካከያ፦ የሕያዋን ፍጥረታቱ አራት ፊቶች በተናጠል ሲታዩ የይሖዋን አራት ዋና ዋና ባሕርያት የሚያመለክቱ ቢሆንም አራቱ ፊቶች አንድ ላይ ሆነው ሲታዩ ይሖዋ ያሉትን ባሕርያት በሙሉ ያመለክታሉ። በተጨማሪም አራቱ ፊቶች የይሖዋን ኃያልነትና ግርማ ጎላ አድርገው ያሳያሉ።

ማስተካከያ የተደረገበት ምክንያት፦ በአምላክ ቃል ውስጥ አራት ቁጥር ሁሉን አቀፍ መሆንን ወይም ሙላትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። በመሆኑም አራቱ ፊቶች በአንድነት ሲታዩ የሚያመለክቱት አራት የተለያዩ ባሕርያትን ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ማንነት መገለጫ የሆኑትን ባሕርያቱን በሙሉ ነው። በተጨማሪም በአራቱም ፊቶች የተወከሉት ፍጥረታት በግርማቸው፣ በጥንካሬያቸውና በኃያልነታቸው የሚታወቁ ናቸው። ይሁን እንጂ በኪሩቦቹ አራት ፊቶች የተወከሉት አራቱም ኃያላን ፍጥረታት የሚገኙት ከይሖዋ ዙፋን ሥር ነው። ይህም ይሖዋ የሁሉም የበላይ ገዢ መሆኑን ያሳያል።

የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ማንን ያመለክታል?

ቀደም ሲል የነበረን ግንዛቤ፦ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ቅቡዓን ቀሪዎችን ያመለክታል። በአሁኑ ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አማካኝነት ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት በሚሆኑ ሰዎች ግንባር ላይ በምሳሌያዊ ሁኔታ ምልክት እያደረጉ ነው።—ራእይ 7:9

ማስተካከያ፦ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል። ኢየሱስ ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትን ‘በጎች ናችሁ’ ብሎ ይፈርድላቸዋል ወይም ምልክት ያደርግባቸዋል።—ማቴ. 24:21

ማስተካከያ የተደረገበት ምክንያት፦ ይሖዋ የመፍረድ ሥልጣን የሰጠው ለልጁ ነው። (ዮሐ. 5:22, 23) በማቴዎስ 25:31-33 ላይ በተገለጸው መሠረት ሰዎችን ‘በጎች’ እና ‘ፍየሎች’ ብሎ በመለየት የመጨረሻውን ፍርድ የሚሰጠው ኢየሱስ ነው።

ዝሙት አዳሪዎቹ እህትማማቾች ኦሆላና ኦሆሊባ በካቶሊክና በፕሮቴስታንት እምነቶች ለተከፈለችው ሕዝበ ክርስትና ትንቢታዊ ጥላ ይሆናሉ?

ቀደም ሲል የነበረን ግንዛቤ፦ ታላቅየዋ እህት ማለትም ኦሆላ (የእስራኤል ዋና ከተማ የሆነችው ሰማርያ) የካቶሊክ እምነትን ታመለክታለች፤ ታናሽ እህት የሆነችው ኦሆሊባ (የይሁዳ ዋና ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም) ደግሞ የፕሮቴስታንት እምነትን ታመለክታለች።

ማስተካከያ፦ ዝሙት አዳሪዎቹ እህትማማቾች ለሕዝበ ክርስትና ትንቢታዊ ጥላ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ስለ እነሱ የሚገልጸው ዘገባ፣ ይሖዋ በአንድ ወቅት ታማኝ ሕዝቦቹ የነበሩ ሰዎች መንፈሳዊ ምንዝር ሲፈጽሙ ምን እንደሚሰማው ያስተምረናል። ይሖዋ ስለ ሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ያለው አመለካከት ተመሳሳይ ነው።

ማስተካከያ የተደረገበት ምክንያት፦ ኦሆላና ኦሆሊባ ለሕዝበ ክርስትና ትንቢታዊ ጥላ እንደሆኑ የሚያሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ የለም። እስራኤልና ይሁዳ በአንድ ወቅት ለይሖዋ እንደ ታማኝ ሚስቶች ነበሩ፤ ሕዝበ ክርስትና ግን ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና ኖሯት አያውቅም። በተጨማሪም ታማኝ ያልሆኑትን የአምላክ ሕዝቦች ከዝሙት አዳሪዎች ጋር እያወዳደረ የሚገልጸው በሕዝቅኤል ምዕራፍ 16 እና 23 ላይ የሚገኘው ዘገባ፣ ኢየሩሳሌምና ሰማርያ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንደሚመለሱ የሚጠቁም ተስፋ ይሰጣል። የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ግን እንዲህ ዓይነት ተስፋ የላትም።

ከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ ነች?

ቀደም ሲል የነበረን ግንዛቤ፦ ከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ ነች። በመሆኑም የኢየሩሳሌም ጥፋት ሕዝበ ክርስትና እንደምትጠፋ የሚያመለክት ትንቢታዊ ጥላ ነው።

ማስተካከያ፦ ጣዖት አምልኮንና ምግባረ ብልሹነትን ጨምሮ በከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ውስጥ ይታዩ የነበሩት ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚታየውን ሁኔታ ያስታውሱናል። ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ አይደለችም።

ማስተካከያ የተደረገበት ምክንያት፦ ኢየሩሳሌም ለሕዝበ ክርስትና ጥላ እንደሆነች የሚጠቁም ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለም። የጥንቷ ኢየሩሳሌም በአንድ ወቅት ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ታቀርብ ነበር፤ ሕዝበ ክርስትና ግን ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ አቅርባ አታውቅም። በተጨማሪም ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ለተወሰነ ጊዜ ያህል ይቅር ብሏት ነበር፤ ሕዝበ ክርስትና ግን ዳግመኛ የማንሰራራት ተስፋ የላትም።

በደረቁ አጥንቶች ስለተሞላው ሸለቆ የሚገልጸው ራእይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

ቀደም ሲል የነበረን ግንዛቤ፦ የአምላክ ሕዝቦች በ1918 ስደት ሲደርስባቸው በታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ሥር የወደቁ ሲሆን እንደሞቱ ያህል ሆነው ነበር። ይሖዋ በ1919 እንዲያንሰራሩና የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነው እንዲቀጥሉ ባደረገበት ወቅት ይህ አጭር የግዞት ዘመን አበቃ።

ማስተካከያ፦ በሞት የተመሰለው መንፈሳዊ ግዞት ለረጅም ዘመን የዘለቀ ሲሆን የጀመረውም ከ1918 በጣም ቀደም ብሎ ነው። የግዞት ዘመኑ የጀመረው በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሲሆን ያበቃው ደግሞ በ1919 ዓ.ም. ነው። ይህ የግዞት ዘመን ኢየሱስ በምሳሌው ላይ ከጠቀሰው፣ ስንዴውና እንክርዳዱ አብረው ካደጉበት ረጅም ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ማስተካከያ የተደረገበት ምክንያት፦ የጥንቷ እስራኤል የግዞት ዘመን ለረጅም ጊዜ ይኸውም ከ740 ዓ.ዓ. እስከ 537 ዓ.ዓ. ዘልቋል። የሕዝቅኤል ትንቢት አጥንቶቹ “በጣም ደርቀው” እንደነበር ይናገራል፤ ይህም ሰዎቹ ሞተው የቆዩት ለረጅም ዘመን እንደሆነ ይጠቁማል። በተጨማሪም አጥንቶቹ ተመልሰው ሕያው የሆኑት ደረጃ በደረጃና ቀስ በቀስ እንደሆነ ተገልጿል።

የሁለቱ በትሮች አንድ መሆን ምን ያመለክታል?

ቀደም ሲል የነበረን ግንዛቤ፦ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት በታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መካከል ለአጭር ጊዜ ክፍፍል ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በ1919 ተመልሰው አንድ ሆነዋል።

ማስተካከያ፦ ትንቢቱ፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ አንድ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ከ1919 በኋላ፣ ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች በጊዜ ሂደት ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ተቀላቀሉ። ሁለቱም ቡድኖች እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው ይሖዋን በአንድነት እያመለኩ ይገኛሉ።

ማስተካከያ የተደረገበት ምክንያት፦ ትንቢቱ፣ አንድ በትር ለሁለት እንደተሰበረና በኋላ መልሶ አንድ እንደሆነ አይናገርም። ስለዚህ ትንቢቱ አንድ ቡድን እንደሚከፈልና በኋላ መልሶ አንድ እንደሚሆን የሚገልጽ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁለት ቡድኖች እንዴት አንድ እንደሚሆኑ ይገልጻል።

የማጎጉ ጎግ ማን ነው?

ቀደም ሲል የነበረን ግንዛቤ፦ የማጎጉ ጎግ የሚለው ስያሜ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ ከሰማይ ከተባረረ በኋላ የሚጠራበት ትንቢታዊ ስም ነው።

ማስተካከያ፦ የማጎጉ ጎግ የሚለው ስያሜ፣ በታላቁ መከራ ወቅት በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩትን ግንባር የፈጠሩ ብሔራት ያመለክታል።

ማስተካከያ የተደረገበት ምክንያት፦ ጎግ ለተለያዩ አዳኝ አሞሮች መብል ሆኖ እንደሚሰጥና በምድር ላይ የመቃብር ቦታ እንደሚሰጠው የሚናገሩት ትንቢታዊ መግለጫዎች ጎግ መንፈሳዊ ፍጡር ሊሆን እንደማይችል ያመለክታሉ። በተጨማሪም ጎግ ስለሚሰነዝረው ጥቃት የተሰጠው መግለጫ፣ የምድር ብሔራት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስለሚሰነዝሩት ጥቃት ከሚገልጸው በዳንኤልና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ ሐሳብ ጋር ይመሳሰላል።—ዳን. 11:40, 44, 45፤ ራእይ 17:14፤ 19:19

ሕዝቅኤል በራእይ ያየውና የጎበኘው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ የገለጸውን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነው?

ቀደም ሲል የነበረን ግንዛቤ፦ ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከገለጸው መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ጋር አንድ ነው።

ማስተካከያ፦ ሕዝቅኤል ያየው በ29 ዓ.ም. ወደ ሕልውና የመጣውን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ራእዩ አይሁዳውያን ከግዞት ከተመለሱ በኋላ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋምና በሙሴ ሕግ ላይ በተገለጸው መሠረት በትክክለኛው መንገድ እንደሚከናወን የሚያሳይ ነው። ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ስለ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ የሰጠው መግለጫ ታላቁ ሊቀ ካህናት የሆነው ኢየሱስ ከ29 እስከ 33 ዓ.ም. ባከናወነው ሥራ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ባየው ራእይ ላይ ግን ሊቀ ካህናቱ ጨርሶ አልተጠቀሰም። ይህ ራእይ ትኩረት የሚያደርገው በ1919 ዓ.ም. በጀመረው መንፈሳዊ ተሃድሶ ላይ ነው። በመሆኑም ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ ያለው እያንዳንዱ ገጽታና ዝርዝር መግለጫ ምን ትንቢታዊ ጥላነት እንዳለው ለማወቅ አንሞክርም። ከዚህ ይልቅ የሕዝቅኤል ራእይ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን መሥፈርት በተመለከተ የሚሰጠንን ትምህርት ለማስተዋል ጥረት እናደርጋለን።

ማስተካከያ የተደረገበት ምክንያት፦ ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ ከመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ የሚለይባቸው መሠረታዊ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ሕዝቅኤል ባየው ቤተ መቅደስ ውስጥ የእንስሳት መሥዋዕት በተደጋጋሚ ይቀርባል፤ በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ግን አንድ መሥዋዕት “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ቀርቧል። (ዕብ. 9:11, 12) ከዚህም ሌላ፣ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በነበሩት ዘመናት ይሖዋ መንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ በሚመለከት ጥልቅ እውነቶችን የሚገልጥበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር።