በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሣጥን 1ሀ

አምልኮ ምንድን ነው?

አምልኮ ምንድን ነው?

አምልኮ የሚለው ቃል “እንደ አምላክ ለምናየው አካል አክብሮትና ፍቅር ማሳየት” የሚል ፍቺ ሊሰጠው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ውስጥ የሚገኙት “አምልኮ” ተብለው የተተረጎሙት ቃላት ለፍጡራን ጥልቅ አክብሮት ማሳየትንና መገዛትንም ሊያመለክቱ ይችላሉ። (ማቴ. 28:9) በተጨማሪም እነዚህ ቃላት ለአምላክ ወይም ለአንድ ጣዖት የሚቀርብን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ያመለክታሉ። (ዮሐ. 4:23, 24) የቃላቱን ትርጉም የሚወስነው አውዱ ነው።

ማንም የማይጋራው አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢና ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው። (ራእይ 4:10, 11) በመሆኑም ለይሖዋ ሉዓላዊነት በመገዛትና ስሙን በማክበር ለእሱ አምልኮ እናቀርባለን። (መዝ. 86:9፤ ማቴ. 6:9, 10) የሕዝቅኤል መጽሐፍ ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነትና ስለ ስሙ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ” የሚለው አገላለጽ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ብቻ 217 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን “ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ” እና “ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ” የሚሉት አገላለጾች ደግሞ በድምሩ 55 ጊዜ ተጠቅሰው ይገኛሉ።—ሕዝ. 2:4፤ 6:7

ይሁን እንጂ አምልኳችን እንዲሁ በስሜት ብቻ የሚገለጽ ነገር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ከልብ የመነጨ አምልኮ ድርጊትንም ይጨምራል። (ያዕ. 2:26) ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ለሉዓላዊነቱ ለመገዛትና ስሙን በጥልቅ ለማክበር መሐላ እንገባለን። ኢየሱስ ሰይጣን ላቀረበለት ሦስተኛ ፈተና ምላሽ በሰጠበት ወቅት አምልኮን ‘ከቅዱስ አገልግሎት’ ጋር አያይዞ እንደጠቀሰው አስታውስ። (ማቴ. 4:10) እኛም የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን እሱን የማገልገል ልባዊ ፍላጎት አለን። * (ዘዳ. 10:12) ከአምልኳችን ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ባላቸውና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ በሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች ስንካፈል ለአምላካችን ቅዱስ አገልግሎት እያቀረብን ነው። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ምንድን ናቸው?

ቅዱስ አገልግሎት ብዙ ገጽታዎች አሉት፤ ይሖዋ በየትኛውም መንገድ የምናቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ለሌሎች ስንመሠክር፣ በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ፣ እንዲሁም የስብሰባ አዳራሾችን በመንከባከቡም ሆነ በመገንባቱ ሥራ ስንካፈል ቅዱስ አገልግሎት እያቀረብን ነው። በተጨማሪም የቤተሰብ አምልኮ ስናደርግ፣ ችግር ላይ የወደቁ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ስንደግፍ፣ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የፈቃደኝነት አገልግሎት ስንሰጥና በቤቴል ስናገለግል ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባችን ነው። (ዕብ. 13:16፤ ያዕ. 1:27) በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ለንጹሕ አምልኮ ቀዳሚውን ቦታ የምንሰጥ ከሆነ “ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት” እናቀርባለን። ለአምላካችን ለይሖዋ አምልኮ ማቅረብ እጅግ ያስደስተናል።—ራእይ 7:15

^ አን.5 አምልኮ የሚል ትርጉም ሊሰጣቸው ከሚችሉት የዕብራይስጥ ቃላት አንዱ “ማገልገል” የሚል ትርጉምም አለው። ስለዚህ አምልኮ ማቅረብ፣ የሚመለከውን አካል ማገልገልንም ይጨምራል።—ዘፀ. 3:12 ግርጌ