በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሣጥን 4ሀ

‘ሕያዋን ፍጥረታቱን እየተመለከትኩ ነበር’

‘ሕያዋን ፍጥረታቱን እየተመለከትኩ ነበር’

ሕዝቅኤል በቤተ መንግሥቶችና በቤተ መቅደሶች ደጃፍ ላይ እንደ ጠባቂ ሆነው የቆሙ፣ ክንፍ ያላቸውን በሬዎችና የሰው ራስ ያላቸውን አንበሶች የሚያሳዩ በጣም ግዙፍ የሆኑ ሐውልቶችን አይቶ እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም። በጥንቶቹ አሦርና ባቢሎን እንደነዚህ ያሉትን ሐውልቶች ማየት የተለመደ ነበር። አንዳንዶቹ ሐውልቶች ቁመታቸው እስከ 6 ሜትር ይደርሳል። ሕዝቅኤልም እነዚህን አስደናቂ ሐውልቶች ሲያይ በአግራሞት ተውጦ መሆን አለበት። ሆኖም እነዚህ ሐውልቶች ምንም ያህል አስፈሪ መስለው ቢታዩ ከድንጋይ ተጠርበው የተሠሩ በድን ቅርጻ ቅርጽ ናቸው።

ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከታቸው አራት ፍጥረታት ግን ከእነዚያ በድን ሐውልቶች በተለየ መልኩ “ሕያዋን ፍጥረታት” ነበሩ። ሕዝቅኤል የተመለከተው ነገር በጣም ስላስደነቀው በመጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ “ሕያዋን ፍጥረታት” የሚለውን አገላለጽ ከአሥር ጊዜ በላይ ጠቅሷል። (ሕዝ. 1:5-22) ሕዝቅኤል አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት በአምላክ ዙፋን ሥር እንደ አንድ ሆነው ሲንቀሳቀሱ በራእይ ማየቱ ይሖዋ ሁሉንም ፍጥረታቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር ከአእምሮው በማይጠፋ ሁኔታ አስገንዝቦት መሆን አለበት። በዛሬው ጊዜም ይህ ራእይ የይሖዋን ታላቅነትና ኃያልነት እንዲሁም የሉዓላዊነቱን ታላቅ ግርማ በማይረሳ ሁኔታ እንድናስተውል ያደርገናል።—1 ዜና 29:11