ምዕራፍ 35

ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ጽሑፉን አሳይ ጽሑፉን ደብቅ

ሁላችንም የተለያዩ ውሳኔዎችን ማድረግ ይጠበቅብናል። ከእነዚህ ውሳኔዎች መካከል ብዙዎቹ በእኛ ሕይወት ላይም ሆነ ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ። ለምሳሌ ከምንኖርበት ቦታ፣ ራሳችንን ከምናስተዳድርበት መንገድ ወይም ትዳር ከመመሥረት ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ጥሩ ውሳኔዎችን ስናደርግ ደስተኛ እንሆናለን፤ ይሖዋንም እናስደስታለን።

1. መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመህ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፤ እንዲሁም እሱ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን መርምር። (ምሳሌ 2:3-6⁠ን አንብብ።) አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ ይሖዋ ግልጽ መመሪያ ሰጥቷል። እንዲህ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሁሉ የተሻለው ውሳኔ የይሖዋን መመሪያ መታዘዝ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ግን ምን ማድረግ እንዳለብህ የሚገልጽ ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ላይኖር ይችላል። በዚህ ጊዜስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ‘ልትሄድበት በሚገባህ መንገድ ይመራሃል።’ (ኢሳይያስ 48:17) እንዴት? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልትመራባቸው የምትችል መሠረታዊ ሥርዓቶችን ልታገኝ ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አምላክ ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አስተሳሰብ ወይም ስሜት ለማወቅ የሚረዱ መሠረታዊ እውነቶች ናቸው። በአብዛኛው አምላክ ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አመለካከት የምናውቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝን ታሪክ ስናነብ ነው። ይሖዋ ያለውን አመለካከት ማወቃችን ደግሞ እሱን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ ይረዳናል።

2. ውሳኔ ከማድረግህ በፊት የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል?

መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ . . . አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ይህም ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ጊዜ ወስደን ያሉንን አማራጮች በሚገባ ማሰብ እንዳለብን ይጠቁማል። ያሉህን አማራጮች ስትገመግም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? ውስጣዊ ሰላም የማገኘው የትኛውን ምርጫ ባደርግ ነው? የማደርገው ውሳኔ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? ከሁሉ በላይ ይህ ውሳኔ ይሖዋን ያስደስተዋል?’—ዘዳግም 32:29

ይሖዋ ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር በተመለከተ መመሪያ የመስጠት መብት አለው። ስለ ይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለን እውቀት ሲጨምር እንዲሁም እነዚህን መመሪያዎች በተቻለን መጠን ተግባራዊ ለማድረግ ስንጥር ሕሊናችንን እያሠለጠንን እንሄዳለን። ሕሊና ማለት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የሚነግረን በውስጣችን ያለ ዳኛ ነው። (ሮም 2:14, 15) በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳል።

ጠለቅ ያለ ጥናት

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሕሊናችን ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

3. ውሳኔ ስታደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመራ

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • የመምረጥ ነፃነት ምንድን ነው?

  • ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት የሰጠን ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ የመምረጥ ነፃነታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መጠቀም እንድንችል ምን ሰጥቶናል?

ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዱን ለማየት ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብቡ። ከዚያም የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ‘ጊዜህን በተሻለ መንገድ መጠቀም’ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተወያዩ፦

  • መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ለማንበብ

  • ጥሩ የትዳር ጓደኛ፣ ወላጅ ወይም ልጅ ለመሆን

  • በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት

4. ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ሕሊናህን አሠልጥን

አንድን ጉዳይ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጽ መመሪያ ሲኖር ትክክለኛው ምርጫ የቱ እንደሆነ ለማወቅ አይከብድም። ሆኖም ግልጽ መመሪያ በማይኖርበት ጊዜስ? ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በቪዲዮው ላይ የታየችው እህት ሕሊናዋን ለማሠልጠንና ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ የትኞቹን እርምጃዎች ወስዳለች?

እኛ ልናደርግ የሚገባንን ውሳኔ ሌሎች እንዲያደርጉልን መጠየቅ የሌለብን ለምንድን ነው? ዕብራውያን 5:14ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ሌሎች ለእኛ እንዲወስኑልን መጠየቅ ቀላል ሊመስል ቢችልም የትኛውን ነገር በራሳችን መለየት መቻል ይኖርብናል?

  • ጥሩ ውሳኔ ለማድረግና ሕሊናህን ለማሠልጠን የሚረዱህ ምን ዝግጅቶች አሉ?

ሕሊናችን ልክ እንደ ካርታ የምንጓዝበትን አቅጣጫ ለመወሰን ይረዳናል

5. የሌሎችን ሕሊና አክብር

ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ ውሳኔ ሊያደርጉ ይችላሉ። ታዲያ የሌሎችን ሕሊና እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ ሁለት ሁኔታዎችን እንደ ምሳሌ እንመልከት፦

ምሳሌ 1፦ መኳኳል የምትወድ አንዲት እህት ወደ ሌላ ጉባኤ ተዛወረች፤ በአዲሱ ጉባኤዋ ያሉ ብዙ እህቶች መኳኳል ተገቢ እንደሆነ አይሰማቸውም።

ሮም 15:1ን እና 1 ቆሮንቶስ 10:23, 24ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት እህት ምን ውሳኔ ልታደርግ ትችላለች? አንተ ሕሊናህ የሚፈቅድልህን ነገር ሌላ ሰው ሕሊናው የማይፈቅድለት ከሆነ ምን ታደርጋለህ?

ምሳሌ 2፦ አንድ ወንድም፣ በመጠኑ እስከሆነ ድረስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን መጽሐፍ ቅዱስ እንደማይከለክል ያውቃል። ያም ሆኖ ጨርሶ አልኮል ላለመጠጣት ወስኗል። ይህ ወንድም አንድ ግብዣ ላይ ተገኝቶ ወንድሞች የአልኮል መጠጥ ሲጠጡ ይመለከታል።

መክብብ 7:16ን እና ሮም 14:1, 10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት ወንድም ምን ውሳኔ ሊያደርግ ይችላል? አንተ ሕሊናህ የማይፈቅድልህን ነገር ሌላ ሰው ሲያደርግ ብታይ ምን ታደርጋለህ?

 ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች

1. ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳህ ይሖዋን ለምን።ያዕቆብ 1:5

2. ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች ላይ ምርምር አድርግ። ተሞክሮ ያላቸውን ክርስቲያኖችም ማማከር ትችላለህ።

3. የምታደርገው ውሳኔ በአንተም ሆነ በሌሎች ሕሊና ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስብ።

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የፈለግከውን ነገር ማድረግ መብትህ ነው። ስለ ሌሎች ሰዎች ምን ያስጨንቅሃል?”

  • የምናደርገው ነገር በአምላክም ሆነ በሌሎች ሰዎች ስሜት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

ማጠቃለያ

ይሖዋ ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ማወቃችን እንዲሁም የምናደርገው ነገር በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን በጎ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ማሰባችን ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳናል።

ክለሳ

  • ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

  • ሕሊናህን ማሠልጠን የምትችለው እንዴት ነው?

  • የሌሎች ሰዎችን ሕሊና እንደምታከብር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

ይሖዋ ለእኛ ምክር ስለሚሰጥበት መንገድ ያለህን ግንዛቤ አሳድግ።

ይሖዋ ሕዝቡን ይመራል (9:50)

አንድ ሰው ከባድ ውሳኔ ከፊቱ በተደቀነበት ወቅት ጥሩ ምርጫ ለማድረግ የረዱት ነገሮች ምንድን ናቸው?

በይሖዋ ዘንድ ሁሉም ነገር አስተማማኝ ነው (5:46)