በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 39

አምላክ ለደም ያለው አመለካከት

አምላክ ለደም ያለው አመለካከት

ደም ለሕይወት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ያለደም ማናችንም በሕይወት መቀጠል አንችልም። አምላክ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ደም ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው እንዴት እንደሆነ የመናገር መብት አለው። ይሖዋ ደምን በተመለከተ ምን ብሏል? ደምን መብላት ወይም ለሌሎች መለገስ ተገቢ ነው? በዚህ ረገድ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው?

1. ይሖዋ ለደም ምን አመለካከት አለው?

ይሖዋ በጥንት ዘመን ለነበሩ አገልጋዮቹ “የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ [ነው]” ብሏቸዋል። (ዘሌዋውያን 17:14) በይሖዋ ዓይን ደም ሕይወትን የሚወክል ነገር ነው። ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ቅዱስ ስጦታ ስለሆነ ደምም ቅዱስ ነው።

2. አምላክ ደም ለምን ዓላማ እንዳይውል ከልክሏል?

ይሖዋ ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩ አገልጋዮቹን ደም እንዳይበሉ አዟቸዋል። (ዘፍጥረት 9:4⁠ን እና ዘሌዋውያን 17:10⁠ን አንብብ።) በበላይ አካሉ አማካኝነት ለክርስቲያኖችም ‘ከደም ራቁ’ የሚል ትእዛዝ በመስጠት በዚህ ረገድ ያለው አቋም እንዳልተለወጠ አሳይቷል።—የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29⁠ን አንብብ።

‘ከደም ራቁ’ የሚለው ትእዛዝ ምን ነገሮችን ያካትታል? ሐኪም አልኮል እንዳትወስድ ቢነግርህ የአልኮል መጠጥ እንደማትጠጣ የታወቀ ነው። ሆኖም አልኮል ያለባቸውን ምግቦች ትበላለህ? ወይም በደም ሥርህ አልኮል ለመውሰድ ትሞክራለህ? እንዲህ እንደማታደርግ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም ከደም ራቁ የሚለው የአምላክ ትእዛዝ ደም ከመጠጣት ወይም ደሙ ያልፈሰሰን ሥጋ ከመብላት መቆጠብን ያካትታል። ከዚህም ሌላ ደም የተጨመረበት ምንም ዓይነት ምግብ መብላት አይኖርብንም።

ደምን ለሕክምና ስለመጠቀምስ ምን ማለት ይቻላል? አንዳንድ የሕክምና ዓይነቶች የአምላክን ሕግ በቀጥታ የሚጥሱ ናቸው። እንዲህ ካሉት የሕክምና ዓይነቶች መካከል ሙሉውን ደም ወይም ከዋና ዋናዎቹ የደም ክፍሎች አንዱን መጠቀም ይገኙበታል፤ ዋና ዋና የደም ክፍሎች የሚባሉት ነጭ የደም ሴል፣ ቀይ የደም ሴል፣ ፕሌትሌትና ፕላዝማ ናቸው። ሌሎች የሕክምና ዓይነቶች ደግሞ የአምላክን ሕግ በቀጥታ የማይጥሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሕክምናዎች የዋና ዋናዎቹን የደም ክፍሎች ንዑሳን ክፍልፋዮች በመጠቀም የሚሰጡ ይሆናሉ። የራሱን የታካሚውን ደም በመጠቀም የሚሰጡ የሕክምና ዓይነቶችም አሉ። እያንዳንዱ ሰው እነዚህን የሕክምና አማራጮች ለመጠቀም ወይም ላለመጠቀም የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት። aገላትያ 6:5

ጠለቅ ያለ ጥናት

የምትቀበላቸውን የሕክምና ዓይነቶች በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

3. የሕክምና ምርጫህ ይሖዋን ደስ የሚያሰኝ ይሁን

አምላክ ስለ ደም ካለው አመለካከት ጋር የሚስማማ የሕክምና ምርጫ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ባለው ጥቅም ላይ ተወያዩ፦

  • ጥበብ ለማግኘት ጸልይ።—ያዕቆብ 1:5

  • በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ተግባራዊ በሚሆኑበት መንገድ ላይ ምርምር አድርግ።—ምሳሌ 13:16

  • አንተ በምትኖርበት አካባቢ የትኞቹ የሕክምና አማራጮች እንዳሉ ለማወቅ ጥረት አድርግ።

  • ፈጽሞ የማትቀበላቸውን አማራጮች ለይ።

  • ውሳኔው ሕሊናህ እንዲወቅስህ የሚያደርግ አለመሆኑን እርግጠኛ ሁን።—የሐዋርያት ሥራ 24:16 b

  • ሕሊናህን ተጠቅመህ በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ረገድ የትዳር ጓደኛህን፣ የጉባኤህን ሽማግሌ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚህን ጨምሮ ማንም ሰው ምን ማድረግ እንዳለብህ ሊወስንልህ እንደማይገባ አስታውስ።—ሮም 14:12

  • ውሳኔህን በጽሑፍ አስፍር።

4. የይሖዋ ምሥክሮች ጥራት ያለው ሕክምና ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ

አምላክ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ ሳይጥሱ ያለደም የሚሰጥ ጥራት ያለው ሕክምና ማግኘት ይቻላል። ቪዲዮውን ተመልከቱ

ቲቶ 3:2ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • የሕክምና ባለሙያዎችን ስናነጋግር አክብሮትና ገርነት ልናሳይ የሚገባው ለምንድን ነው?

ተቀባይነት የሌላቸው

ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ውሳኔ የተተዉ

ሀ. የደም ፕላዝማ

የፕላዝማ ክፍልፋዮች

ለ. ነጭ የደም ሴል

የነጭ የደም ሴል ክፍልፋዮች

ሐ. ፕሌትሌት

የፕሌትሌት ክፍልፋዮች

መ. ቀይ የደም ሴል

የቀይ የደም ሴል ክፍልፋዮች

 5. ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎች

ደም አራት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነሱም ቀይ የደም ሴል፣ ነጭ የደም ሴል፣ ፕሌትሌትና ፕላዝማ ናቸው። እነዚህ ዋና ዋና ክፍሎች በርካታ ንዑሳን ክፍልፋዮች አሏቸው። c ከእነዚህ ንዑሳን ክፍልፋዮች መካከል አንዳንዶቹ በሽታን ለመዋጋት ወይም ደምን ለማስቆም በሚሰጡ መድኃኒቶች ውስጥ ይገኛሉ።

ንዑሳን ከሆኑት የደም ክፍልፋዮች ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ንዑሳን ክፍልፋዮችን መጠቀም የሚጠይቁ የሕክምና ዓይነቶችን ላለመቀበል ሊወስኑ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲህ ያሉ ሕክምናዎችን ለመቀበል ሕሊናቸው ይፈቅድላቸው ይሆናል።

ውሳኔ ስታደርግ በሚከተለው ጥያቄ ላይ አስብበት፦

  • አንዳንድ ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን የምወስድበትን ወይም የማልወስድበትን ምክንያት ለሐኪም ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?

አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “ደም መውሰድ ምን ችግር አለው?”

  • አንተ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?

ማጠቃለያ

ይሖዋ ደምን አላግባብ ከመጠቀም እንድንርቅ ይፈልጋል።

ክለሳ

  • ይሖዋ ደምን ቅዱስ አድርጎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?

  • አምላክ ከደም እንድንርቅ የሰጠው ትእዛዝ ደም ከመውሰድ መራቅንም እንደሚጨምር በምን እናውቃለን?

  • ደምን ለሕክምና ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

የራስህን ደም በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎችን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል ስትወስን የትኞቹን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል?

“የአንባቢያን ጥያቄዎች” (መጠበቂያ ግንብ ጥቅምት 15, 2000)

ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን ለሕክምና ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ውሳኔ ስታደርግ የትኞቹን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል?

“የአንባቢያን ጥያቄዎች” (መጠበቂያ ግንብ ሰኔ 15, 2004)

አንድ ሐኪም ይሖዋ ስለ ደም ያለው አመለካከት ምክንያታዊ ነው ብሎ እንዲያምን ያደረገው ምንድን ነው?

“አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ተቀበልኩ” (ንቁ! ጥር 2004)

በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የሚደግፉት እንዴት ነው?

ይሖዋ የታመሙትን ይደግፋል (10:23)

a “ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 35⁠ን ተመልከት።

b “ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎች” የሚለውን  አምስተኛውን ነጥብ እና ተጨማሪ ሐሳብ 3 ላይ የሚገኘውን “ደምን በመጠቀም የሚሰጡ ሕክምናዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c አንዳንድ ሐኪሞች አራቱን ዋና ዋና ክፍሎች እንደ ንዑሳን ክፍልፋዮች ይቆጥሯቸዋል። በመሆኑም ሙሉውን ደም አሊያም ቀይ የደም ሴል፣ ነጭ የደም ሴል፣ ፕሌትሌት ወይም ፕላዝማ ላለመውሰድ ያደረግከውን ውሳኔ ለሐኪምህ በግልጽ ማስረዳት ሊያስፈልግህ ይችላል።