በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 41

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?

ብዙ ሰዎች ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራት ይከብዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ሆኖም ጨዋነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ይናገራል። የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ እኛን የሚጠቅም መረጃ ይዟል። ይህ መሆኑ አያስገርምም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን ይሖዋ ያጻፈው መጽሐፍ ነው። ይሖዋ ደግሞ ለእኛ የተሻለውን ነገር ያውቃል። እሱን ለማስደሰትና ለዘላለም በደስታ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል።

1. ይሖዋ ለፆታ ግንኙነት ምን አመለካከት አለው?

የፆታ ግንኙነት ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ ነው። ይሖዋ ትዳር የመሠረቱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ደስታ እንዲያገኙ ይፈልጋል። ይህ ስጦታ ባለትዳሮች ልጆች እንዲወልዱ ብቻ ሳይሆን አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ተፈጥሯዊ በሆነና እርካታ በሚያስገኝ መንገድ እንዲገልጹ ያስችላቸዋል። የአምላክ ቃል “ከወጣትነት ሚስትህ . . . ጋር ደስ ይበልህ” የሚለው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 5:18, 19) ይሖዋ ትዳር የመሠረቱ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ እንዲሆኑ ይፈልጋል፤ በመሆኑም ባለትዳሮች ምንዝር ከመፈጸም ሊርቁ ይገባል።—ዕብራውያን 13:4⁠ን አንብብ።

2. የፆታ ብልግና ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሴሰኞች [የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች] የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ’ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የፆታ ብልግናን ለመግለጽ ፖርኒያ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅመዋል። ይህ ቃል (1) ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት a (2) ግብረ ሰዶምን እና (3) ከእንስሳት ጋር የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት ያካትታል። ‘ከፆታ ብልግና መራቃችን’ ይሖዋን የሚያስደስት ከመሆኑም ሌላ እኛንም ይጠቅመናል።—1 ተሰሎንቄ 4:3

ጠለቅ ያለ ጥናት

ከፆታ ብልግና መራቅ የምትችለው እንዴት እንደሆነና የሥነ ምግባር ንጽሕናህን መጠበቅህ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ እንመለከታለን።

3. ከፆታ ብልግና ሽሽ

ዮሴፍ የተባለ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሥነ ምግባር ንጽሕናውን ለመጠበቅ ብዙ ትግል አድርጓል። ዘፍጥረት 39:1-12ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ዮሴፍ የሸሸው ለምንድን ነው?—ቁጥር 9⁠ን ተመልከት።

  • ዮሴፍ ያደረገው ነገር ትክክል ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የዮሴፍን ምሳሌ በመከተል ከፆታ ብልግና መሸሽ የሚችሉት እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ

ይሖዋ ሁላችንም ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ይፈልጋል። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:18ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • የፆታ ብልግና ወደመፈጸም ሊመሩ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

  • ከፆታ ብልግና መሸሽ የምትችለው እንዴት ነው?

4. ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ትችላለህ

የፆታ ብልግና እንድንፈጽም የሚደረግብንን ጫና መቋቋም ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በቪዲዮው ላይ የታየው ወንድም፣ የሚያስባቸውና የሚያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች ለባለቤቱ ያለውን ታማኝነት እንዲያጓድል ሊያደርጉት እንደሚችሉ ሲገነዘብ ምን አደረገ?

ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ አስተሳሰባቸው ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ለማድረግ መታገል ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የብልግና ሐሳቦችን እንዳታውጠነጥን ምን ይረዳሃል? ፊልጵስዩስ 4:8ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ስለ ምን ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል?

  • መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈላችን ኃጢአት ለመፈጸም ስንፈተን የሚረዳን እንዴት ነው?

5. ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተላችን ይጠቅመናል

ይሖዋ ለእኛ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነና እንዲህ ማድረጋችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን ገልጾልናል። ምሳሌ 7:7-27ን አንብቡ ወይም ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ወጣት ራሱን ፈተና ውስጥ ያስገባው እንዴት ነው?—ምሳሌ 7:8, 9⁠ን ተመልከት።

  • ምሳሌ 7:23, 26 ላይ እንደተገለጸው የፆታ ብልግና መፈጸም አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቃችን ከየትኞቹ ችግሮች ያድነናል?

  • የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቃችን ለዘላለም በደስታ ለመኖር የሚያስችለን እንዴት ነው?

አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን አስመልክቶ የሚናገረው ሐሳብ ፍቅር የጎደለው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ሁሉም ሰው ለዘላለም በደስታ እንዲኖር ይፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር አለብን። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በዚህ ጥቅስ መሠረት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ግብረ ሰዶም ብቻ ነው?

አምላክን ለማስደሰት ሁላችንም የተለያዩ ለውጦች ማድረግ ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ ነው? መዝሙር 19:8, 11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋ ያወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምክንያታዊ ወይም ተገቢ ይመስሉሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ብዙዎች እሱ ካወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር እንዲችሉ ረድቷል። አንተንም ሊረዳህ ይችላል

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ማንም ሰው ከፈለገው ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይችላል። ዋናው ነገር መዋደዳቸው ነው።”

  • አንተ ምን ትላለህ?

ማጠቃለያ

የፆታ ግንኙነት ትዳር በመሠረቱ ወንድና ሴት መካከል ብቻ ሊፈጸም የሚገባ የይሖዋ ስጦታ ነው።

ክለሳ

  • የፆታ ብልግና ምን ነገሮችን ያካትታል?

  • ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ምን ይረዳናል?

  • ይሖዋ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

ግብ

ምርምር አድርግ

አምላክ አብረው መኖር የሚፈልጉ ወንድና ሴት ትዳር እንዲመሠርቱ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

“መጽሐፍ ቅዱስ ሳይጋቡ አብሮ መኖርን በተመለከተ ምን ይላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም የሚያስተምረው ትምህርት ጥላቻን የሚያስፋፋ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

“ግብረ ሰዶም ስህተት ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

አምላክ ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና ጋር በተያያዘ ያወጣው ሕግ ጥበቃ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

“በአፍ የሚፈጸም ወሲብ የፆታ ግንኙነት ነው ሊባል ይችላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

“የያዙኝ በአክብሮት ነበር” የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ ግብረ ሰዶማዊ የነበረ አንድ ሰው አምላክን ለማስደሰት ሲል አኗኗሩን እንዲቀይር ያነሳሳው ምን እንደሆነ ተመልከት።

“መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” (መጠበቂያ ግንብ ሚያዝያ 1, 2011)

a በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የፆታ ግንኙነት በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ ግንኙነትን፣ የሌላን ግለሰብ የፆታ ብልት ማሻሸትንና እንዲህ የመሳሰሉ ሌሎች ድርጊቶችን ያካትታል።