በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 46

ራስህን ለይሖዋ መወሰንና መጠመቅ ያለብህ ለምንድን ነው?

ራስህን ለይሖዋ መወሰንና መጠመቅ ያለብህ ለምንድን ነው?

ራስህን ለይሖዋ የምትወስነው እሱን ብቻ ለማምለክና በሕይወትህ ውስጥ ለእሱ ፈቃድ ቅድሚያ ለመስጠት ቃል በመግባት ነው፤ ይህንንም የምታደርገው በጸሎት አማካኝነት ነው። (መዝሙር 40:8) ከዚያ ደግሞ ትጠመቃለህ። መጠመቅህ ራስህን ለይሖዋ መወሰንህን ለሌሎች ለማሳየት ያስችልሃል። ራሳችንን ለይሖዋ መወሰን በሕይወታችን ውስጥ ከምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ የበለጠ ቦታ የሚሰጠው ነው። እንዲህ ያለውን ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና መላ ሕይወትህን የሚቀይር ውሳኔ ለማድረግ የሚያነሳሳህ ምንድን ነው?

1. አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ ለመወሰን እንዲነሳሳ የሚያደርገው ምንድን ነው?

ራሳችንን ለይሖዋ ለመወሰን የሚያነሳሳን ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:10, 19) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ምክር ይሰጠናል፦ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።” (ማርቆስ 12:30) ለአምላክ ያለንን ፍቅር የምናሳየው በምንናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን በምናደርገው ነገር ጭምር ነው። በጣም የሚዋደዱ ጥንዶች ትዳር እንደሚመሠርቱ ሁሉ እኛም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ራሳችንን ለእሱ እንድንወስንና እንድንጠመቅ ያነሳሳናል።

2. ይሖዋ የተጠመቁ አገልጋዮቹን የሚባርካቸው እንዴት ነው?

ስትጠመቅ፣ ደስተኛ የሆነው የይሖዋ ቤተሰብ አባል ትሆናለህ። የይሖዋን ፍቅር በብዙ መንገዶች የምታይበትና ከአሁኑ የበለጠ ወደ እሱ የምትቀርብበት አጋጣሚ ታገኛለህ። (ሚልክያስ 3:16-18⁠ን አንብብ።) ይሖዋ አባት ይሆንልሃል፤ በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ አንተንም ሆነ ይሖዋን የሚወዱ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ይኖሩሃል። (ማርቆስ 10:29, 30⁠ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ ከመጠመቅህ በፊት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልግሃል። ስለ ይሖዋ መማር፣ እሱን መውደድና በልጁ ላይ እምነት ማሳደር አለብህ። በመጨረሻም ራስህን ለይሖዋ መወሰን ይኖርብሃል። እነዚህን እርምጃዎች በመውሰድ መጠመቅህ ለዘላለም በደስታ መኖር የምትችልበትን አጋጣሚ ይከፍትልሃል። የአምላክ ቃል “ጥምቀት . . . እያዳናችሁ ነው” ይላል።—1 ጴጥሮስ 3:21

ጠለቅ ያለ ጥናት

ራስህን ለይሖዋ መወሰንህና መጠመቅህ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

3. ሁላችንም ማንን እንደምናገለግል መምረጥ አለብን

በጥንቷ እስራኤል የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ይሖዋንና የሐሰት አምላክ የሆነውን ባአልን በአንድነት ማምለክ እንደሚችሉ አስበው ነበር። ይሖዋ ግን ነቢዩ ኤልያስን በመላክ ይህን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያስተካክሉ ነግሯቸዋል። አንደኛ ነገሥት 18:21ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • እስራኤላውያን ምን ምርጫ ማድረግ ነበረባቸው?

እኛም ልክ እንደ እስራኤላውያን ማንን እንደምናገለግል መምረጥ አለብን። ሉቃስ 16:13ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋንና ሌላ አካልን ወይም ሌላ ነገርን በአንድነት ማምለክ የማንችለው ለምንድን ነው?

  • ይሖዋን ለማምለክ እንደመረጥን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

4. ይሖዋ ለአንተ ባሳየው ፍቅር ላይ አሰላስል

ይሖዋ ግሩም የሆኑ በርካታ ስጦታዎችን ሰጥቶናል። ታዲያ እኛ በምላሹ ምን ልንሰጠው እንችላለን? ቪዲዮውን ተመልከቱ

ይሖዋ አንተን እንደሚወድህ ያሳየባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? መዝሙር 104:14, 15ን እንዲሁም 1 ዮሐንስ 4:9, 10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋ ከሰጠህ ስጦታዎች መካከል አንተ በጣም የምታደንቀው የትኛውን ነው?

  • እነዚህን ስጦታዎች ስታስብ ስለ ይሖዋ ምን ስሜት ያድርብሃል?

አንድ ሰው በጣም የምንወደውን ነገር ስጦታ አድርጎ ሲሰጠን አድናቆታችንን ለእሱ ማሳየት እንፈልጋለን። ዘዳግም 16:17ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ይሖዋ ስላደረገልህ ነገሮች ስታስብ በምላሹ ለእሱ ምን ለመስጠት ትነሳሳለህ?

5. ራስን ለይሖዋ መወሰን ብዙ በረከቶች ያስገኛል

ብዙ ሰዎች ዝና፣ ጥሩ ሥራ ወይም ሀብት ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ይሰማቸዋል። ሆኖም ይህ እውነት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • በቪዲዮው ላይ የታየው ስፖርተኛ እግር ኳስ መጫወት የሚወድ ቢሆንም ይህን ሙያ ለመተው የመረጠው ለምንድን ነው?

  • ሕይወቱን ለእግር ኳስ ሳይሆን ለይሖዋ ለመስጠት ወሰነ። ያደረገው ውሳኔ ትክክል ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በብዙዎች ዘንድ ከፍ ተደርጎ በሚታይ ሙያ ተሰማርቶ ነበር። ታዋቂ በሆነ አስተማሪ ሥር ሆኖ የአይሁድን ሕግ አጥንቷል። ሆኖም ክርስቲያን ለመሆን ሲል ይህን ሁሉ ነገር ለመተው ወሰነ። ታዲያ ጳውሎስ በውሳኔው ተቆጭቶ ይሆን? ፊልጵስዩስ 3:8ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት የነበሩትን ነገሮች እንደ “ጉድፍ” ወይም ቆሻሻ የቆጠራቸው ለምንድን ነው?

  • በምላሹ ምን በረከት አግኝቷል?

  • ይሖዋን ማገልገልን በሕይወትህ ውስጥ ልታደርጋቸው ከምትችላቸው ሌሎች ነገሮች ጋር ስታነጻጽረው ምን ይሰማሃል?

ጳውሎስ ክርስቲያን በመሆኑ ያገኘው በረከት መሥዋዕት ካደረገው ነገር በእጅጉ ይበልጣል

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የምማረው ነገር እውነት መሆኑን አውቃለሁ። ግን ሕይወቴን ለአምላክ መወሰን ይከብደኛል።”

  • ሕይወትን ለአምላክ መወሰን ጥሩ ምርጫ ነው ብለህ እንድታምን የሚያደርግህ ምንድን ነው?

ማጠቃለያ

ለይሖዋ ያለን ፍቅር ራሳችንን ለእሱ እንድንወስንና እንድንጠመቅ ይገፋፋናል።

ክለሳ

  • ይሖዋን በሙሉ ልባችን ልንወደውና ልናመልከው የሚገባው ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ የተጠመቁ አገልጋዮቹን የሚባርካቸው እንዴት ነው?

  • ራስህን ለይሖዋ መወሰን ትፈልጋለህ?

ግብ

ምርምር አድርግ

አንዲት ሙዚቀኛና አንድ ስፖርተኛ ሕይወታቸውን ለይሖዋ ለመስጠት የወሰኑት ለምን እንደሆነ ተመልከት።

የወጣቶች ጥያቄ—ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?—ትዝታዎች (6:54)

ሕይወታችንን ለይሖዋ እንድንወስን የሚያነሳሱን ሌሎች ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

“ራስህን ለይሖዋ መወሰን ያለብህ ለምንድን ነው?” (መጠበቂያ ግንብ ጥር 15, 2010)

ይህ የሙዚቃ ቪዲዮ ራሳቸውን ለይሖዋ የሚወስኑ ሰዎች የሚያገኙትን ደስታ ያሳያል።

ያንተው ትሁን ነፍሴ (4:30)

‘ለዓመታት “የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?” እያልኩ አስብ ነበር’ የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ አንዲት ሴት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች መለስ ብላ እንድትገመግም ያነሳሳት ምን እንደሆነ ተመልከት።

“መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” (መጠበቂያ ግንብ ኅዳር 1, 2012)