በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውይይት መጀመር

ምዕራፍ 3

ደግነት

ደግነት

መሠረታዊ ሥርዓት፦ “ፍቅር . . . ደግ ነው።”—1 ቆሮ. 13:4

ኢየሱስ ምን አድርጓል?

1. ቪዲዮውን ተመልከት፤ ወይም ዮሐንስ 9:1-7ን አንብብ። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦

  1.   ሀ. ኢየሱስ ለዓይነ ስውሩ ሰው በቅድሚያ ያደረገው ምንድን ነው? መፈወስ ወይስ ምሥራቹን መንገር?—ዮሐንስ 9:35-38⁠ን ተመልከት።

  2.  ለ. ኢየሱስ ያደረገው ነገር ሰውየው ለምሥራቹ ጆሮ እንዲሰጥ ያደረገው ይመስልሃል? ለምን?

ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

2. የምናነጋግረው ሰው እንደምናስብለት ከተሰማው ምሥራቹን ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስን ምሰል

3. ራስህን በግለሰቡ ቦታ አስቀምጥ። ምን እንደሚሰማው ለመገመት ሞክር

  1.   ሀ. ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ግለሰቡን የሚያሳስበው ነገር ምን ይሆን? የሚጠቅመው ወይም ትኩረቱን የሚስበው ነገር ምን ሊሆን ይችላል?’ ይህን ማድረግህ እንዲያው ለደንቡ ያህል ሳይሆን ከልብ የመነጨ ደግነት እንድታሳይ ያነሳሳሃል።

  2.  ለ. ጆሮ ሰጥተህ በማዳመጥ ግለሰቡ የሚያሳስበው ነገር ግድ እንደሚሰጥህ አሳይ። ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ነግሮህ ወይም ያጋጠመውን ችግር አንስቶልህ ከሆነ የውይይቱን ርዕስ አታስቀይር።

4. በደግነትና በአክብሮት ተናገር። ለግለሰቡ ከራራህለትና ከልብህ ልትረዳው ከፈለግህ፣ በምትናገርበት መንገድ ላይ መንጸባረቁ አይቀርም። የምትጠቀምባቸውን ቃላትና የድምፅህን ቃና በጥንቃቄ አስብበት፤ ቅር የሚያሰኝ ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ።

5. መልካም አድርግለት። ተገቢ እንደሆነ በሚሰማህ ጊዜ ሁሉ ግለሰቡን በተግባር ለመርዳት የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ተጠቀምባቸው። ደግነት ማሳየት ጥሩ ውይይት ለማድረግ መንገድ ሊከፍት ይችላል።