በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውይይት መጀመር

ምዕራፍ 4

ትሕትና

ትሕትና

መሠረታዊ ሥርዓት፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።”—ፊልጵ. 2:3

ጳውሎስ ምን አድርጓል?

1. ቪዲዮውን ተመልከት፤ ወይም የሐዋርያት ሥራ 26:2, 3ን አንብብ። ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦

  1.   ሀ. ጳውሎስ ንጉሥ አግሪጳን ሲያነጋግር ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?

  2.  ለ. ጳውሎስ ወደ ራሱ ትኩረት ከመሳብ ይልቅ የአድማጮቹን ትኩረት ወደ ይሖዋና ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት ያዞረው እንዴት ነው?—የሐዋርያት ሥራ 26:22ን ተመልከት።

ከጳውሎስ ምን እንማራለን?

2. መልእክታችንን በትሕትናና በአክብሮት መናገራችን የሰዎችን ልብ የመማረክ ኃይል አለው።

ጳውሎስን ምሰል

3. ራስህን እንዳታመጻድቅ ተጠንቀቅ። አንተ ሁሉን አዋቂ እንደሆንክ፣ የምታነጋግረው ሰው ደግሞ ምንም እንደማያውቅ በሚያስመስል መንገድ አትናገር። ግለሰቡን እንደምታከብረው በሚያሳይ መንገድ ተናገር።

4. የምታስተምረው ትምህርት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ግልጽ አድርግ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ሐሳቦች የሰዎችን ልብ ይነካሉ። ሰዎችን ስናነጋግር የአምላክን ቃል መጠቀማችን እምነታቸው በትክክለኛው መሠረት ላይ እንዲገነባ ያደርጋል።

5. ምንጊዜም ገር ሁን። ‘እኔ ያልኩትን ካልተቀበልክ’ ብለህ ድርቅ አትበል። እኛ የመከራከር ፍላጎት የለንም። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ስሜትህን በመቆጣጠርና ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ግለሰቡን ትተህ በመሄድ ትሕትና አሳይ። (ምሳሌ 17:14፤ ቲቶ 3:2) በገርነት መልስ መስጠትህ ግለሰቡ ሌላ ጊዜ ለመልእክቱ ጆሮ እንዲሰጥ ሊያደርግ ይችላል።