በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ከተዉት አርአያ እየተጠቀምክ ነውን?

ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ከተዉት አርአያ እየተጠቀምክ ነውን?

ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ከተዉት አርአያ እየተጠቀምክ ነውን?

“በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው።” ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈው በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ነበር። በእርግጥም ለሌሎች ክርስቲያኖች የተዉት ምሳሌ የሚያስመሰግናቸው ነበር። የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በበኩላቸው ጳውሎስና ባልደረቦቹ ለተዉላቸው ምሳሌ ምላሽ መስጠታቸው ነበር። ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ። ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀበላችሁ፣ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ።”​—⁠1 ተሰሎንቄ 1:​5-7

አዎን፣ ጳውሎስ እንዲሁ በቃል በመስበክ ብቻ አልተወሰነም። መላ ሕይወቱ የእምነት፣ የጽናት እንዲሁም የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ምሳሌ ነው። በዚህ ምክንያት ጳውሎስና ባልደረቦቹ በተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር እውነትን “በብዙ መከራ” እንዲቀበሉ አነሳስቷቸዋል። ቢሆንም በእነዚህ አማኞች ሕይወት ውስጥ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳደሩት ጳውሎስና ባልደረቦቹ ብቻ አልነበሩም። የደረሰባቸውን መከራ በጽናት የተቋቋሙ የሌሎች ክርስቲያኖች ምሳሌነት ማበረታቻ ሆኖላቸው ነበር። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “እናንተ፣ ወንድሞች ሆይ፣ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፣ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና።”​—⁠1 ተሰሎንቄ 2:​14

የላቀው ምሳሌ​—⁠ክርስቶስ ኢየሱስ

ምንም እንኳ ጳውሎስ እሱ ራሱ ሊኮረጅ የሚገባው ጥሩ ምሳሌ የተወ ቢሆንም ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባ የላቀ ምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ሳይጠቁም አላለፈም። (1 ተሰሎንቄ 1:​6) ክርስቶስ አሁንም ሆነ ወደፊት የላቀ ምሳሌያችን ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።”​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​21

ሆኖም ኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወቱ ካበቃ 2,000 ዓመት ሊሆነው ምንም አልቀረውም። አሁን የማይሞት መንፈሳዊ ፍጥረት በመሆኑ “ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል።” ስለሆነም “አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም።” (1 ጢሞቴዎስ 6:​16) ታዲያ ምሳሌውን ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚናገሩትን አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በማጥናት ነው። ወንጌሎች ስለ ባሕርያቱ፣ ስለ ሕይወቱና ስለ ‘አስተሳሰቡ’ የጠለቀ ማስተዋል ይሰጡናል። (ፊልጵስዩስ 2:​5-8) ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ያከናወናቸውን ድርጊቶች በዝርዝርና በጊዜ ቅደም ተከተል የሚያብራራውን እስከዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ጥሩ አድርጎ በማጥናት ተጨማሪ ማስተዋል ማግኘት ይቻላል። a

ኢየሱስ ያሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ምሳሌ በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ ኃይለኛ ግፊት አሳድሯል። ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ አላቸው:- “እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ።” (2 ቆሮንቶስ 12:​15) እንዴት ያለ ክርስቶስን የመምሰል ዝንባሌ ነው! እኛም ክርስቶስ በተወልን ፍጹም ምሳሌ ላይ ባሰላሰልን መጠን በአኗኗራችን ፈለጉን ለመከተል መገፋፋት ይኖርብናል።

ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን በተመለከተ አምላክ በገባው ቃል ላይ መተማመን እንዳለብን አስተምሮናል። ሆኖም እሱ ከዚህም በላይ አድርጓል። በየዕለቱ ይህን የመሰለ እምነትና በይሖዋ የመተማመን ባሕርይ አሳይቷል። እንዲህ አለ:- “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፣ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም።” (ማቴዎስ 6:​25፤ 8:​20) ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅህ አስተሳሰብህንና ድርጊትህን ይቆጣጠረዋልን? ወይስ አኗኗርህ የመንግሥቱን ጉዳዮች እንደምታስቀድም በግልጽ ያሳያል? የይሖዋን አገልግሎት በተመለከተ ያለህ ዝንባሌስ እንዴት ነው? እንደ ምሳሌያችን እንደ ኢየሱስ ነው? ኢየሱስ ሌሎች በቅንዓት እንዲያገለግሉ መስበክን ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ አምልኮ ያለው ቅንዓት እንደሚያንገበግበው በተደጋጋሚ ጊዜ በተግባር ማሳየቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዮሐንስ 2:​14-17) ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ፍቅርን በተመለከተ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ለደቀ መዛሙርቱ ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት እስከ ማድረግ ደርሷል! (ዮሐንስ 15:​13) ለክርስቲያን ወንድሞችህ ፍቅር በማሳየት የኢየሱስን አርአያ እየኮረጅህ ነውን? ወይስ የአንዳንዶች አለፍጽምና ለእነርሱ ያለህን ፍቅር እንዳታሳይ ጋሬጣ ይሆንብሃል?

የክርስቶስን ምሳሌ ለመከተል ስንጣጣር ብዙ ጊዜ አይሳካልን ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ጌታን እርሱን ክርስቶስን ለመልበስ’ በምናደርገው ጥረት በእርግጥ ደስ ይሰኝብናል።​—⁠ሮሜ 13:​14

‘ለመንጋው ምሳሌ የሚሆኑ’

በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉ ሰዎች ይኖሩ ይሆን? እንዴታ፣ አሉ እንጂ! በተለይ በኃላፊነት እንዲሠሩ የተሾሙ ወንድሞች ምሳሌ መሆን ይገባቸዋል። ጳውሎስ በቀርጤስ ጉባኤ ያገለግልና የበላይ ተመልካቾችን ይሾም ለነበረው ለቲቶ እያንዳንዱ የተሾመ ሽማግሌ “የማይነቀፍ” መሆን እንደሚገባው ነግሮት ነበር። (ቲቶ 1:​5, 6) ሐዋርያው ጴጥሮስም በተመሳሳይ ‘ሽማግሌዎች ለመንጋው ምሳሌ’ እንዲሆኑ አጥብቆ አሳስቧል። (1 ጴጥሮስ 5:​1-3) የጉባኤ አገልጋይ ሆነው በማገልገል ላይ ስለሚገኙትስ ምን ማለት ይቻላል? እነርሱም እንደዚሁ ‘በመልካም ማገልገል’ ይጠበቅባቸዋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 3:​13

እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ በእያንዳንዱ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ይዋጣለታል ብሎ መጠበቅ ከእውነታው መራቅ ይሆናል። ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ሲናገር “እንደተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን” ብሏል። (ሮሜ 12:​6) የተለያዩ ወንድሞች በተለያየ መስክ የላቀ ችሎታ አላቸው። ሽማግሌዎች የሚያደርጉትም ሆነ የሚናገሩት እያንዳንዱ ነገር ፈጽሞ ስህተት አይኖረውም ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠ያዕቆብ 3:​2 ላይ “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው” ይላል። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች ፍጹም ባይሆኑም እንኳን እንደ ጢሞቴዎስ “በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ [ምሳሌዎች]” ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 4:​12) ሽማግሌዎች እንደዚህ ካደረጉ በመንጋው ውስጥ ያሉ ደግሞ በ⁠ዕብራውያን 13:​7 ላይ “የእግዚአብሔር ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” የሚለውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ አይከብዳቸውም።

በዚህ ዘመን ያሉ ሌሎች ምሳሌዎች

ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎች ጥሩ ምሳሌዎች ሆነዋል። በባዕድ አገሮች ክርስቲያናዊ ተልዕኳቸውን ለመወጣት ሲሉ “ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን” ትተው የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ስላደረጉ በሺ የሚቆጠሩ ሚስዮናውያን ምን ለማለት ይቻላል? (ማቴዎስ 19:​29) እንዲሁም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን፣ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮዎች የሚያገለግሉትን ፈቃደኛ ሠራተኞች እንዲሁም በጉባኤያቸው አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉትን መመልከት ትችላለህ። እንደዚህ ያለው ምሳሌነት ሌሎችን ሊያንቀሳቅስ አይችልም? በእስያ የሚያገለግል አንድ ክርስቲያን ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ስለነበረ ስለ አንድ ሚስዮናዊ የሚያስታውሰው ነገር አለው። ይህን ታማኝ ወንድም አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ አለ:- “ውርር የሚያደርጉትን የወባ ትንኞች እንዲሁም ጭንቅ የሚያደርገውን የአየር ፀባይ ለመቋቋም ፈቃደኛ ሆኗል። . . . ይበልጥ የሚያስገርመኝ እንግሊዛዊ ቢሆንም በቻይንኛና በማላይ ቋንቋ ሲሰብክ በጣም ጎበዝ መሆኑ ነው።” ይህ ጥሩ ምሳሌነት ምን ውጤት አስገኘ? ወንድም እንዲህ ይላል:- “ረጋ ማለቱና እምነቱ ሳድግ ሚስዮናዊ እሆናለሁ የሚል ፍላጎት አሳድሮብኝ ነበር።” ይህ ወንድም አድጎ ሚስዮናዊ መሆኑ ምንም አያስገርምም።

መጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የወጡ በጣም ብዙ የሕይወት ታሪኮችን በዝርዝር ይዟል። እነዚህ ታሪኮች ዓለማዊ ሥራቸውንና ግባቸውን ስለተዉ፣ ድክመቶቻቸውን ስላሸነፉ፣ አስደናቂ የባሕርይ ለውጥ ስላደረጉ፣ መከራ ሲደርስባቸው አዎንታዊ አመለካከታቸውን ጠብቀው ስለቆዩ እንዲሁም ታታሪነትን፣ ጽናትን፣ ታማኝነትን፣ ትሕትናንና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ስላሳዩ ሰዎች ይናገራሉ። አንዲት አንባቢ እነዚህን ታሪኮች አስመልክታ ስትጽፍ እንዲህ ብላለች:- “እነርሱ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ ሳነብ ይበልጥ ትሁትና አመስጋኝ ክርስቲያን ያደርገኛል፤ እንዲሁም ስለራሴ ከመጠን በላይ እንዳላስብ ወይም ራስ ወዳድ እንዳልሆን ረድቶኛል።”

ከዚህ በተጨማሪ አንተ ባለህበት ጉባኤ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ አትዘንጋ:- የቤተሰባቸውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ያለመታከት የሚሠሩ የቤተሰብ ራሶች፤ ነጠላ እናቶችን ጨምሮ ልጅ ማሳደግ የሚፈጥረውን ጫና እየታገሉ ጎን ለጎን በአገልግሎት የሚተጉ እህቶች፤ እርጅና ቢጫጫናቸውና የጤና እክል ቢያጋጥማቸውም ታማኝነታቸውን የጠበቁ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች። እነዚህ ሰዎች በሚያሳዩት ምሳሌነት አትበረታታም?

ዓለም በመጥፎ ምሳሌዎች መሞላቱ አያጠራጥርም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​13) ቢሆንም ጳውሎስ በይሁዳ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የሰጠውን ምክር ልብ በል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጥንት የነበሩ ብዙ የእምነት ወንዶችና ሴቶች ያሳዩትን በምሳሌነት የሚጠቀስ ባሕርይ ካስታወሰ በኋላ “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ . . . የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጣቸው። (ዕብራውያን 12:​1, 2) ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም “እንደ ደመና” የሆኑ ጥንታዊና ዘመናዊ ግሩም ምሳሌዎች አሉላቸው። በእርግጥ እነርሱ ከተዉት ምሳሌ እየተጠቀምክ ነውን? ‘ክፉውን ሳይሆን በጎ የሆነውን ለመምሰል’ ቆርጠህ ከተነሳህ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ።​—⁠3 ዮሐንስ 11

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እያንዳንዱ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ በእያንዳንዱ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ይዋጣለታል ብሎ መጠበቅ ከእውነታው መራቅ ይሆናል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች “ለመንጋው ምሳሌ” መሆን አለባቸው