በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት—አዲሱ የምድር አገዛዝ

የአምላክ መንግሥት—አዲሱ የምድር አገዛዝ

የአምላክ መንግሥት​—⁠አዲሱ የምድር አገዛዝ

“[መንግሥቱም] . . . እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”​—⁠ዳንኤል 2:​44

1. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምን ዓይነት ትምክህት ልንጥል እንችላለን?

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ልጆች የገለጠው ራእይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የእግዚአብሔር[ን] ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፣ በእውነት እንዳለ . . . እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ [አልተቀበላችሁትም]።” (1 ተሰሎንቄ 2:​13) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ማወቅ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይዞልናል። ስለ ባሕርያቱ፣ ስለ ዓላማዎቹና ለእኛ ስላወጣቸው የአቋም ደረጃዎች የሚገልጽ ሐሳብ ይዟል። የቤተሰብ ኑሮንና ዕለታዊ አኗኗርን በሚመለከት ተወዳዳሪ የማይገኝለት ምክር ይለግሳል። ባለፉት ጊዜያት ፍጻሜያቸውን ያገኙ፣ በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉና ወደፊት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙ ዝርዝር ትንቢቶችን ይዞልናል። አዎን፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

2. ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስን ጭብጥ ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው መልእክት ሁሉ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው በሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት የአምላክ ሉዓላዊነት (የመግዛት መብት) እንደሚረጋገጥ የሚገልጸው ጭብጥ ነው። የኢየሱስ አገልግሎት በዚህ ጭብጥ ዙሪያ ያተኮረ ነበር። በመሆኑም “ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር” የሚል እናነባለን። (ማቴዎስ 4:​17) “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” የሚል ጥብቅ ምክር በመስጠት በሕይወታችን ውስጥ ምን ቦታ ሊኖረው እንደሚገባ አመልክቷል። (ማቴዎስ 6:​33) በተጨማሪም ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ በማስተማር ይህ ጉዳይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሳይቷል።​—⁠ማቴዎስ 6:​10

አዲስ የምድር አገዛዝ

3. የአምላክ መንግሥት ለሰዎች አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?

3 የአምላክ መንግሥት ለሰዎች ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት የምድርን አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመለወጥ በቅርቡ አንድ እርምጃ ስለሚወስድ ነው። በዳንኤል 2:​44 ላይ ያለው ትንቢት እንዲህ ይላል:- “በእነዚያም [በአሁኑ ጊዜ ምድርን በመግዛት ላይ ባሉት] ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት [በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር] ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት [ምድራዊ መስተዳድሮችን] ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ በሚገዛበት ጊዜ የሰው ልጆች ምድርን ዳግመኛ አይቆጣጠሯትም። ከፋፋይ የሆነውና ብቃት የጎደለው የሰው ልጅ አገዛዝ ለዘላለም ይወገዳል።

4, 5. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ለመሆን ከማንም የበለጠ ብቃት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በቅርቡ ምን እርምጃ ይወስዳል?

4 በይሖዋ የቅርብ አመራር ሥር ሆኖ በሰማያዊው መንግሥት ላይ እንዲገዛ የተሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን እርሱም ከማንም የበለጠ ብቃት አለው። ከአምላክ ፍጥረታት ሁሉ በፊት በኩር እንደመሆኑ መጠን ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በአምላክ ዘንድ “ዋና ሠራተኛ” ነበር። (ምሳሌ 8:​22-31) “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፣ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።” (ቆላስይስ 1:​15, 16) ኢየሱስ በአምላክ ተልኮ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሁሉ የአምላክን ፈቃድ አድርጓል። በጣም አስቸጋሪ ፈተናዎችን በጽናት የተቋቋመ ሲሆን ለአባቱ ታማኝ እንደሆነ ሞቷል።​—⁠ዮሐንስ 4:​34፤ 15:​10

5 ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ በመገኘቱ ወሮታ ተከፍሎታል። አምላክ ከሞት አስነስቶ ወደ ሰማይ እንዲመለስ ካደረገው በኋላ በሰማያዊው መንግሥት ንጉሥ የመሆን መብት ሰጥቶታል። (ሥራ 2:​32-36) ክርስቶስ ኢየሱስ የመንግሥቱ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ኃያል መንፈሳዊ ፍጥረታት እየመራ በምድር ላይ የሚገኘውን ሰብዓዊ አገዛዝ የማስወገድና ምድርን ከማንኛውም ዓይነት ክፋት የማጽዳት አስደናቂ ተልእኮ ከአምላክ ተቀብሏል። (ምሳሌ 2:​21, 22፤ 2 ተሰሎንቄ 1:​6-9፤ ራእይ 19:​11-21፤ 20:​1-3) ከዚያም በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በመላው ምድር ላይ ያለተቀናቃኝ የሚያስተዳድር አዲሱ የምድር ባለ ሥልጣን ይሆናል።​—⁠ራእይ 11:​15

6. የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ምን ዓይነት አገዛዝ ያሰፍናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?

6 የአምላክ ቃል አዲሱን የምድር ገዥ በማስመልከት “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው” በማለት ይናገራል። (ዳንኤል 7:​14) ኢየሱስ የአምላክን ፍቅር ስለሚኮርጅ በእርሱ አገዛዝ ሥር ሰላምና ደስታ ይሰፍናል። (ማቴዎስ 5:​5፤ ዮሐንስ 3:​16፤ 1 ዮሐንስ 4:​7-10) “በፍርድና በጽድቅ . . . ይደግፈው ዘንድ . . . አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።” (ኢሳይያስ 9:​7) በፍቅር፣ በፍትሕና በጽድቅ የሚገዛ እንዲህ ያለ ገዥ ማግኘት ምንኛ በረከት ነው! በዚህም የተነሳ 2 ጴጥሮስ 3:​13 እንዲህ በማለት ይተነብያል:- “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና [የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት] አዲስ ምድር [አዲስ ምድራዊ ኅብረተሰብ] እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”

7. በዛሬው ጊዜ ማቴዎስ 24:​14 ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

7 የአምላክ መንግሥት ትክክል የሆነውን ለሚወዱ ሁሉ አቻ የማይገኝለት ምሥራች እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ አሁን የምንኖርበትን ‘የመጨረሻ ቀን’ ለይተው ከሚያሳውቁት ምልክቶች ጋር በማካተት “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት የተነበየው በዚህ የተነሳ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ ማቴዎስ 24:​14) ይህ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ የሚገኝ ሲሆን በ234 አገሮች የሚገኙ ስድስት ሚልዮን ገደማ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች በመናገር በዓመት ከአንድ ቢልዮን የሚበልጥ ሰዓት ያሳልፋሉ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወደ 90, 000 የሚጠጉ ጉባኤዎች አምልኳቸውን ለማካሄድ የሚጠቀሙባቸው ቦታዎች የመንግሥት አዳራሽ ተብለው መጠራታቸው የተገባ ነው። ሰዎች ወደነዚህ ቦታ⁠ዎች በመምጣት ስለ አዲሱ መስ​ተዳደር ይማራሉ።

ተባባሪ ገዥዎች

8, 9. (ሀ) ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙት የተመረጡት ከየት ነው? (ለ) በንጉሡና በተባባሪ ገዥዎቹ አገዛዝ ላይ ምን ዓይነት ትምክህት ልንጥል እንችላለን?

8 በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የሚገዙ ሰዎች ይኖራሉ። ራእይ 14:​1-4 ‘ከሰዎች መካከል’ 144, 000 ሰዎች ‘እንደሚዋጁና’ ለሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ እንደሚያገኙ ይተነብያል። እነዚህም ሌሎች እንዲያገለግሏቸው ከመጠበቅ ይልቅ አምላክንና ሰዎችን በትህትና ያገለገሉ ወንዶችንና ሴቶች ይጨምራሉ። “የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።” (ራእይ 20:​6) ብዛታቸው የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት ከሚያልፉት “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ከተባሉት ሰዎች ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ ነው። እነዚህም ቢሆኑ ለአምላክ “ሌሊትና ቀን” ‘ቅዱስ አገልግሎት’ ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ ለሰማያዊ ሕይወት አልተጠሩም። (ራእይ 7:​9, 15 NW ) የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ተገዥዎች በመሆን የአዲሱ ምድር አስኳል ይሆናሉ።​—⁠መዝሙር 37:​29፤ ዮሐንስ 10:​16

9 ይሖዋ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ የመረጠው በሕይወት ዘመናቸው የተለያዩ ችግሮችን የቀመሱ ታማኝ ሰዎችን ነው። በሰው ልጆች ላይ የደረሰ እነዚህ ነገሥታት የሆኑ ካህናት ያልቀመሱት መከራ የለም ለማለት ይቻላል። ስለዚህ በምድር መኖራቸው በሰዎች ላይ ለመግዛት የሚያስፈልገውን ብቃት ያስገኝላቸዋል። ሌላው ቀርቶ ራሱ ኢየሱስ እንኳ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን” ተምሯል። (ዕብራውያን 5:​8) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፣ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም።” (ዕብራውያን 4:​15) ጽድቅ በሰፈነበት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አፍቃሪና አዛኝ በሆኑ ነገሥታትና ካህናት የሚገዙ መሆናቸውን ማወቃቸው ምንኛ የሚያጽናና ነው!

መንግሥቱ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ነበር?

10. ሰማያዊው መንግሥት የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ክፍል ያልነበረው ለምንድን ነው?

10 ሰማያዊው መንግሥት አምላክ አዳምንና ሔዋንን በፈጠረበት ጊዜ የነበረ የመጀመሪያ ዓላማ ነበርን? በዘፍጥረት የፍጥረት ዘገባ ውስጥ ሰዎችን ስለሚገዛ መንግሥት የሚናገር አንድም ሐሳብ አናገኝም። ገዥያቸው ይሖዋ ሲሆን እርሱን እስከ ታዘዙ ድረስ ሌላ አገዛዝ ማቋቋም የሚያስፈልግበት ምንም ምክንያት አልነበረም። ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እንደሚያሳየው ይሖዋ በሰማያዊው የበኩር ልጁ አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም ከአዳምና ከሔዋን ጋር ይነጋገር ነበር። ዘገባው ‘እግዚአብሔር እንዲህ አላቸው’ እና “እግዚአብሔርም አለ” እንደሚሉት ባሉት መግለጫዎች ይጠቀማል።​—⁠ዘፍጥረት 1:​28, 29፤ ዮሐንስ 1:​1

11. የሰው ልጅ ምን ፍጹም ጅምር ነበረው?

11 መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም መልካም ነበረ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:​31) በኤደን ገነት ውስጥ ሁሉ ነገር ሙሉ በሙሉ ፍጹም ነበር። አዳምና ሔዋን የሚኖሩት በገነት ውስጥ ነበር። ፍጹም የሆነ አእምሮና ፍጹም የሆነ አካል ነበራቸው። ፈጣሪያቸውን ያነጋግሩታል እሱም ያነጋግራቸው ነበር። ታማኝ ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ ፍጹም የሆኑ ልጆችን መውለድ ይችሉ ነበር። ስለዚህ አዲስ ሰማያዊ መስተዳድር አያስፈልግም ነበር።

12, 13. ፍጹማን የሆኑ የሰው ልጆች በቁጥር እየበዙ ሲሄዱም አምላክ ከእነርሱ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ፈጽሞ የማያስቸግረው ለምንድን ነው?

12 የሰው ልጅ ቤተሰብ በቁጥር እያደገ ሲሄድ አምላክ ከሁሉም ጋር እንዴት የሐሳብ ግንኙነት ያደርግ ነበር? የሰማይ ከዋክብትን ተመልከት። በጠፈር ላይ እንደ ደሴት እዚህም እዛም ክምችት ብለው የሚታዩ ከዋክብት ያሉ ሲሆን እነዚህም ጋላክሲ ተብለው ይጠራሉ። አንዳንድ ጋላክሲዎች አንድ ቢልዮን ከዋክብት ይይዛሉ። ሌሎች ደግሞ አንድ ትሪልዮን የሚያክሉ ከዋክብት ይኖሯቸዋል። እንዲሁም ሳይንቲስቶች እስከ አሁን በሚታየው ጠፈር ውስጥ ወደ 100 ቢልዮን የሚጠጉ ጋላክሲዎች እንዳሉ ይገምታሉ። ሆኖም ፈጣሪ እንዲህ ይላል:- “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።”​—⁠ኢሳይያስ 40:​26

13 አምላክ እነዚህን ሰማያዊ አካላት ጠንቅቆ የሚያውቃቸው ከሆነ ከነዚህ በቁጥር በጣም የሚያንሱትን የሰው ልጆች ለማወቅ ምንም አይቸግረውም። በአሁኑ ጊዜ እንኳ በሚልዮን የሚቆጠሩ አገልጋዮቹ በየዕለቱ ወደ እርሱ ይጸልያሉ። እነዚህ ጸሎቶች በቅጽበት ወደ አምላክ ይደርሳሉ። ስለዚህ ፍጹማን ከሆኑ ሰዎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ለእርሱ ምንም ዓይነት ችግር አይፈጥርበትም። የእነሱን ሁኔታ ለመከታተል ሰማያዊ መንግሥት ማቋቋም አያስፈልገውም። በይሖዋ አገዛዝ ሥር መሆን፣ ከእርሱ ጋር በቀጥታ መነጋገር መቻልና መሞት የሚባል ነገር ሳይኖር ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንዴት ያለ ድንቅ ዝግጅት ነው!

‘ከሰው አይደለም’

14. የሰው ልጅ የይሖዋ አገዛዝ ለዘላለም የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

14 ይሁን እንጂ ሰዎች፣ ፍጹም የሆኑትም ጭምር የይሖዋ አገዛዝ ለዘላለም ያስፈልጋቸዋል። ለምን? ይህ የሆነበት ምክንያት ይሖዋ ሰዎችን ከእርሱ አገዛዝ ውጭ ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ አድርጎ ስላልፈጠራቸው ነው። ነቢዩ ኤርምያስ እንደገለጸው ይህ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ሕግ ነው። “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም። አቤቱ፣ ቅጣኝ” በማለት ተናግሯል። (ኤርምያስ 10:​23, 24) የሰው ልጆች ከይሖዋ አገዛዝ ውጭ ሆነው የራሳቸውን ኅብረተሰብ በተሳካ መንገድ ማስተዳደር ይችላሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ይህ ከአፈጣጠራቸው ጋር የሚቃረን ነው። ከይሖዋ አገዛዝ ነፃ መሆን ራስ ወዳድነትን፣ ጥላቻን፣ ጭካኔን፣ ዓመፅን፣ ጦርነትንና ሞትን ማስከተሉ የማይቀር ነው። ‘ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።’​—⁠መክብብ 8:​9 NW

15. የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የተሳሳተ ምርጫ ማድረጋቸው ምን ውጤት አስከተለ?

15 የሚያሳዝነው ግን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የአምላክ አገዛዝ እንደማያስፈልጋቸው በመወሰን ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር መረጡ። በዚህም ምክንያት አምላክ ፍጹም ሆነው እንዲኖሩ ሳይፈቅድላቸው ቀረ። ኃይል ከሚያገኝበት ምንጭ እንደተቋረጠ የኤሌክትሪክ መሣሪያ ቀስ በቀስ እየደከሙ ሄደው መጨረሻ ላይ ይሞታሉ። ጉድለት እንዳለበት ንድፍ ከመሆናቸውም በላይ ለልጆቻቸውም ማስተላለፍ የሚችሉት ይህንኑ ጉድለት ሆነ። (ሮሜ 5:​12) “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትሕ የሞላበት፣” NW ] ነው፤ . . . እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ነውርም አለባቸው።” (ዘዳግም 32:​4, 5) አዳምና ሔዋን በኋላ ሰይጣን በተባለው ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር ተጽዕኖ የደረሰባቸው መሆኑ እሙን ቢሆንም ፍጹም አእምሮ ስለነበራቸው የእሱን የተሳሳተ ሐሳብ መቃወም ይችሉ ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 3:​1-19፤ ያዕቆብ 4:​7

16. በአምላክ አልመራም ማለት ስለሚያስከትለው ውጤት ታሪክ ምን ይመሰክራል?

16 ከአምላክ ማፈንገጥ የሚያስከትላቸውን ውጤቶች ታሪክ በብዙ መንገድ ይመሠክራል። ሰዎች ላለፉት ሺህ ዓመታት የተለያዩ መስተዳድሮችን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሥርዓቶችን ሞክረዋል። ሆኖም ክፋት ‘እየባሰ’ መሄዱን አላቆመም። (2 ጢሞቴዎስ 3:​13) ሃያኛው መቶ ዘመን ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። ሃያኛው መቶ ዘመን በታሪክ ዘመን ሁሉ ዓረመኔያዊ ጥላቻና ታይቶ በማያውቅ ዓመፅ፣ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ድህነትና ሥቃይ የተሞላ ነበር። በሕክምናው ዓለም የተደረገው እድገት የቱንም ያህል ከፍተኛ ቢሆን ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ሁሉም ሰው ይሞታል። (መክብብ 9:​5, 10) የሰው ልጆች እርምጃቸውን ለማቅናት ባደረጉት ጥረት መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም አምላክ” ብሎ ለሚጠራው ለሰይጣንና ለአጋንንቱ ራሳቸውን አሳልፈው ከመስጠት በቀር ምንም የፈየዱት ነገር የለም።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​4

ስጦታ የሆነው የመምረጥ ነፃነት

17. የአምላክ የነፃ ምርጫ ስጦታ እንዴት ሊሠራበት ይገባ ነበር?

17 ይሖዋ የሰው ልጆች በራሳቸው መንገድ እንዲጓዙ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት ይሖዋ የነፃ ምርጫ ስጦታ ማለትም የፈለጉትን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶ ስለፈጠራቸው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት [“ነፃነት፣” NW ] አለ” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 3:​17) ቀኑን ሙሉ ምን መናገርና ምን ማድረግ እንዳለበት የሚወስንለት ሰው እንዲኖረው በሌላ አባባል እንደ ሮቦት መሆን የሚፈልግ ሰው የለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ያንን አስደናቂ የነፃ ምርጫ ስጦታ በኃላፊነት እንዲጠቀሙበትና የእርሱን ፈቃድ ማድረግና ለእርሱ ተገዢ ሆኖ መኖር ጥበብ መሆኑን እንዲገነዘቡ ይፈልጋል። (ገላትያ 5:​13) ስለዚህ ተሰጥቷቸው የነበረው ነፃነት ገደብ የለሽ አልነበረም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ሥርዓት አልበኝነት ይሰፍን ነበር። አምላክ ባወጣቸው በጎ ሕግጋት ውስጥ የሚወሰኑ ነበሩ።

18. አምላክ ሰዎች ነፃ ምርጫቸውን እንዲጠቀሙበት በመፍቀድ ምን ነገር እንዲረጋገጥ አድርጓል?

18 አምላክ የሰው ዘር ቤተሰብ በራሱ ጎዳና እንዲሄድ በመፍቀድ የእርሱ አገዛዝ እንደሚያስፈልገን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲረጋገጥ አድርጓል። ትክክለኛው ጎዳና የእርሱ አገዛዝ ማለትም የእርሱ ሉዓላዊነት ብቻ ነው። ይህም ታላቅ ደስታ፣ እርካታና ብልጽግና ያስገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት ይሖዋ አእምሯችንና አካላችን እርሱ ካወጣቸው ሕግጋት ጋር ከተስማሙ በተሻለ መንገድ መሥራት እንዲችሉ አድርጎ ስለፈጠራቸው ነው። “ታዳጊህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” (ኢሳይያስ 48:​17) በአምላክ ሕግጋት የተገደበ ነፃ ምርጫ ሸክም አይደለም። ከዚያ ይልቅ በምግብ፣ በቤት፣ በሥነ ጥበብና በሙዚቃ ረገድ ብዙ አስደሳች ምርጫዎች ይኖሩናል። ነፃ ምርጫ ተገቢ በሆነ መንገድ ቢሠራበት ኖሮ ገነት በሆነች ምድር ላይ አስደናቂና ማራኪ የሆነ ሕይወት ይኖር ነበር።

19. አምላክ የሰው ልጆችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ የሚጠቀምበት ወኪል ምንድን ነው?

19 ይሁን እንጂ ባደረጉት የተሳሳተ ምርጫ የተነሳ ሰዎች ራሳቸውን ከይሖዋ ማራቅ ብቻ ሳይሆን ፍጽምና የጎደላቸውና ቀስ በቀስ እየተዳከሙ ሄደው በመጨረሻ ሟች እንዲሆኑ አደረጋቸው። ስለዚህ ከዚህ አሳዛኝ ማጥ ውስጥ እንዲወጡና ወደ ቀድሞው ዝምድና ተመልሰው የአምላክ ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆች እንዲሆኑ መቤዠት አስፈለጋቸው። አምላክ ይህን ለመፈጸም የሚጠቀምበት ወኪል መንግሥቱ ሲሆን የሚቤዣቸው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዮሐንስ 3:​16) ኢየሱስ በምሳሌው ላይ እንደጠቀሰው ኮብላይ ልጅ ከልባቸው ንሥሐ የሚገቡ ሰዎች በዚህ ዝግጅት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ሊታረቁና በእርሱ ዘንድ የልጅነትን መብት ሊያገኙ ይችላሉ።​—⁠ሉቃስ 15:​11-24፤ ሮሜ 8:​21፤ 2 ቆሮንቶስ 6:​18

20. የአምላክ ዓላማ በመንግሥቱ አማካኝነት ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

20 የይሖዋ ፈቃድ ያላንዳች ጥርጥር በምድር ላይ ይፈጸማል። (ኢሳይያስ 14:​24, 27፤ 55:​11) አምላክ በክርስቶስ በሚመራው መንግሥቱ አማካኝነት በእኛ ላይ ልዑል የመሆን መብት እንዳለው ያረጋግጣል። መንግሥቱ በዚህ ምድር ላይ የሚገኘውን የሰውንና የአጋንንትን አገዛዝ አስወግዶ ያለ ማንም ተቀናቃኝ ከሰማይ ለአንድ ሺህ ዓመት ምድርን ያስተዳድራል። (ሮሜ 16:​20፤ ራእይ 20:​1-6) ይሁን እንጂ በዚያን ወቅት የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆኑ የሚረጋገጠው እንዴት ነው? ከሺው ዓመት በኋላ መንግሥቱ ምን ሚና ይኖረዋል? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።

ለክለሳ የሚሆኑ ነጥቦች

• የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ምንድን ነው?

• የምድር አዲስ አገዛዝ የተዋቀረው በእነማን ነው?

• ከአምላክ ያፈነገጠው ሰብዓዊ አገዛዝ ፈጽሞ ሊሳካለት የማይችለው ለምንድን ነው?

• ነፃ ምርጫ ሊሠራበት የሚገባው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ትምህርት በመንግሥቱ በኩል የሚገለጠውን የአምላክን አገዛዝ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች በሁሉም የምድር ክፍል መንግሥቱን ዋነኛ የትምህርታቸው ክፍል ያደርጋሉ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ አልገዛም ማለት መጥፎ ውጤት እንደሚያስከትል ታሪክ ይመሰክራል

[ምንጭ]

የአንደኛው የዓለም ጦርነት ወታደሮች:- U.S. National Archives photo; ማጎሪያ ካምፕ:- Oświęcim Museum; ልጅ:- UN PHOTO 186156/J. Isaac