በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከገንዘብህ ወይ ከሕይወትህ?

ከገንዘብህ ወይ ከሕይወትህ?

ከገንዘብህ ወይ ከሕይወትህ?

የጥቃታቸው ሰለባ በሆነው ሰው ላይ ጠመንጃ ደቅነው “ከገንዘብህ ወይ ከሕይወትህ!” የሚል ጥያቄ ስለሚያቀርቡ ሽፍቶች ምናልባት ሰምተህ ይሆናል። በዛሬው ጊዜ ይህ ከባድ ጥያቄ በሁላችንም ፊት በተለይ ግን በበለጸጉ አገሮች በምንኖረው ሰዎች ፊት የተደቀነ ምርጫ ሆኗል። ይሁን እንጂ ዛሬ ጥያቄውን የሚያቀርበው ሽፍታ አይደለም። ከዚህ ጥያቄ ጋር የሚያፋጥጠን ሕብረተሰቡ ለገንዘብና ለቁሳዊ ሃብት የሚሰጠው እየጨመረ የመጣ ከፍተኛ ግምት ነው።

ለቁሳዊ ነገሮች የተሰጠው እንዲህ ያለው ግምት ከዚህ ቀደም ጨርሶ ታስበው የማያውቁ ጉዳዮች መሠረታዊ ጥያቄ ሆነው እንዲቀርቡና አዳዲስ ፍላጎቶች እንዲቀሰቀሱ ምክንያት ሆኗል። ገንዘብና ቁሳዊ ሃብት ምን ያህል መሥዋዕትነት ሊከፈልላቸው ይገባል? መጠነኛ በሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ረክተን መኖር እንችል ይሆን? ሰዎች ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ሲሉ “እውነተኛውን ሕይወት” በመሠዋት ላይ ናቸውን? ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ቁልፉ ገንዘብ ነውን?

የገንዘብ ምኞት

ጤናማ ከሆኑትም ሆኑ ካልሆኑት የሰው ልጅ ፍላጎቶች ውስጥ ገንዘብ የመሪነቱን ቦታ ይዞ ይገኛል። ከወሲብና ከምግብ ፍላጎት በተለየ መልኩ የገንዘብ ምኞት የማያቋርጥና መቋጫ የሌለው ሊሆን ይችላል። የእድሜ መግፋትም ቢሆን ይህንን ፍላጎት ጋብ የሚያደርገው አይመስልም። እንዲያውም በብዙ ሁኔታዎች እንደታየው አንድ ሰው ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ ገንዘብንና ገንዘብ የሚገዛቸውን ነገሮች ለማግኘት ይበልጥ ማሰብና መጨነቅ ይጀምራል።

ለገንዘብ መስገብገብ እየጨመረ የመጣ ይመስላል። በአንድ የታወቀ ፊልም ላይ መሪ ተዋናይ ሆኖ የሚሠራው ሰው “ስግብግብነት ያዋጣል፤ ስግብግብነት ጠቃሚ ነው” ብሏል። ብዙዎች የ1980ዎቹን ዓመታት የስግብግብነት ዘመን ብለው ቢሰይሟቸውም ከዚህ ጊዜ በፊትና በኋላ የተፈጸሙት ነገሮች የዓመታት ማለፍ ሰዎች ለገንዘብ ያላቸውን አመለካከት እምብዛም እንዳልለወጠው ያሳያል።

ምናልባት ዛሬ አዲስ የሆነው ነገር ብዙ ሰዎች ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮች በቅጽበት ለማግኘት የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች የሚፈልጉ መሆናቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ቁጥሩ የሚበዛው የዓለም ሕዝብ አብዛኛውን ጉልበቱን የሚያጠፋው ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮች በማምረትና እነዚያን በማካበት ይመስላል። በዛሬው ጊዜ ሰዎች ሃብት ማግኘትና ገንዘብ እንደልብ መምዘዝ የሚቋምጡለት ብዙውን ጊዜም ሌት ተቀን የሚያልሙትና የሚጋደሉለት ጉዳይ እየሆነ መጥቷል ቢባል ሳትስማማ አትቀርም።

ሆኖም ሰዎች በውጤቱ ደስተኞች ናቸውን? ጥበበኛና በጣም ሀብታም የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን ከ3, 000 ዓመታት በፊት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።” (መክብብ 5:​10) በዘመናችን የተደረጉ ማኀበራዊ ጥናቶችም ተመሳሳይ የሆነ አስገራሚ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

ገንዘብና ደስታ

የሰዎችን ባሕርይ አስመልክቶ ከተገኙት የጥናት ውጤቶች ውስጥ አንዱና በጣም አስገራሚው የገንዘብና የቁሳዊ ሃብት መብዛት የሚደከምለትን ያህል የአንድን ሰው ደስታና እርካታ የማይጨምር መሆኑ ነው። ብዙ ተመራማሪዎች የተገነዘቡት ነገር ቢኖር አንድ ሰው የተወሰነ መጠን ያለው ሃብት ካገኘ በኋላ የሚኖረው የደስታና የእርካታ ስሜት ባሉት ቁሳዊ ነገሮች ላይ የተመካ አለመሆኑን ነው።

በመሆኑም ቁሳዊ ሃብትንና ገንዘብን ለማግኘት የሚደረገው ማብቂያ የሌለው ሩጫ ብዙዎችን እንደሚከተለው ብለው እንዲጠይቁ ይገፋፋቸዋል:- ‘የምንገዛው እያንዳንዱ አዲስ ነገር የሚያስደስተን ይመስላል። ታዲያ የምንፈልገውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ምንም የተለየ እርካታ የማይሰማን ለምንድን ነው?’

ደራሲ ጆናታን ፍሪድማን ሃፒ ፒፕል በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “መጠነኛ ገቢ ማግኘት እንደጀመርክ ገንዘብህ ደስታ በማምጣት ረገድ የሚጫወተው ሚና የለም ለማለት ይቻላል። ከድህነት እርከን ለወጡ ሰዎች በሚያገኙት ገቢና በሚኖራቸው ደስታ መካከል ያለው ግንኙነት በጣም አነስተኛ ነው።” ብዙዎች ለአንድ ሰው ደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ነገሮች መንፈሳዊ ሃብት፣ ትርጉም ያለው ሥራና የሥነ ምግባር እሴቶች መሆናቸውን በመገንዘብ ላይ ናቸው። በተጨማሪም ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት እንዲሁም ባሉን ነገሮች እንዳንደሰት እንቅፋት ሊሆኑብን ከሚችሉ አለመግባባቶች ወይም ሌሎች ማነቆዎች ነፃ መሆንም የማይናቅ ድርሻ ያበረክታል።

ከውስጣዊ ስሜት ጋር የተያያዙትን ችግሮች ለመፍታት ቁሳዊ ብልጽግናን እንደ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀሙ አዝማሚያ ዛሬ ላለው ማኀበራዊ ቀውስ መንስኤ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። አንዳንድ የማሕበራዊ ሕይወት ተንታኞች በአጠቃላይ ስለሚታየው አፍራሽ አስተሳሰብና እርካታ የማጣት ዝንባሌ ይናገራሉ። በተጨማሪም በበለጸጉት አገሮች የሚኖሩ ሰዎች የሕይወትን ትርጉምና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ሲሉ ወደ ሕክምና ባለሙያዎች፣ ደብተራዎች፣ ኑፋቄዎችና ለማኅበራዊ ቀውስ መፍትሔ አለን ወደሚሉ ቡድኖች የመሄድ አዝማሚያቸው እየጨመረ እንደመጣ ተንታኞቹ ተናግረዋል። ይህም ቁሳዊ ሃብት ለሕይወት እውነተኛ ትርጉም እንዳላስገኘ የሚያረጋግጥ ሐቅ ነው።

ገንዘብ ያለው ኃይልና ውስን አቅም

እርግጥ ነው ገንዘብ ኃይል አለው። ጥሩ ጥሩ ቤቶችን፣ ምርጥ አልባሳትንና የሚያማምሩ የቤት ውስጥ ዕቃዎችን ሊገዛ ይችላል። በተጨማሪም አድናቆትን፣ የሌሎችን ታዛዥነት ወይም ሽንገላ ሊገዛና አጎብጓቢ የሆኑ ጥቂት ጊዜያዊ ወዳጆችን ሊያፈራልን ይችላል። ይሁንና ገንዘብ ሊያደርገው የሚችለው ነገር ከዚህ አያልፍም። ገንዘብ በጣም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማለትም የአንድን እውነተኛ ወዳጅ ፍቅር፣ የአእምሮ ሰላምንና የሞት ጥላ ሲያጠላብን ከሌሎች ልናገኘው የምንችለውን ልባዊ ማጽናኛ ሊገዛልን አይችልም። ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸውን ዝምድና ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች ደግሞ ገንዘብ የአምላክን ሞገስ ሊያስገኝላቸው እንደማይችል ያውቃሉ።

በዘመኑ ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችላቸው አስደሳች ነገሮች በሙሉ የነበሩት ንጉሥ ሰሎሞን በቁሳዊ ሃብት መታመን ዘላቂ ደስታ እንደማያስገኝ ተገንዝቧል። (መክብብ 5:​12-15) ገንዘብ በባንክ ኪሣራ ወይም በዋጋ ግሽበት ምክንያት ሊጠፋ ይችላል። የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በከባድ ወዠብ ሊወድሙ ይችላሉ። የኢንሹራንስ ዋስትናዎች የጠፉትን ንብረቶች በተወሰነ መጠን ሊተኩ ቢችሉም በስሜት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መጠገን አይችሉም። አክስዮኖችና ቦንዶች በድንገተኛ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ሳቢያ በአንድ ጀንበር ዋጋ ሊያጡ ይችላሉ። ጥሩ ክፍያ ያለው ሥራም ቢሆን ዛሬ ተገኝቶ ነገ ሊታጣ ይችላል።

ታዲያ ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የምንችለው እንዴት ነው? ገንዘብ ወይም ቁሳዊ ሃብት በሕይወታችን ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባው ድርሻ ምንድን ነው? እውነተኛ ዋጋ ያለውን ነገር ማለትም “እውነተኛውን ሕይወት” ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ እባክህ ይህንን ጉዳይ መመርመርህን ቀጥል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቁሳዊ ንብረቶች ዘላቂ ደስታ አያስገኙም