በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመንግሥቱ ተስፋ ደስ ይበላችሁ!

በመንግሥቱ ተስፋ ደስ ይበላችሁ!

በመንግሥቱ ተስፋ ደስ ይበላችሁ!

መጋቢት 10 ቀን 2001 ኒው ዮርክ የሚገኘው ትልቁ የቤቴል ቤተሰብ በሚጠቀምባቸው ሦስት ቦታዎች የተገኙትን 5,784 ሰዎች ያሰባሰባቸው አንድ አስደሳች አጋጣሚ ነበር። ይህ አጋጣሚ የጊልያድ የሚስዮናውያን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የ110ኛው ክፍል ተማሪዎች የምረቃ ፕሮግራም ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ኬሪ ባርበር በቦታው የተገኙትን ሁሉ እንኳን ደህና መጣችሁ ካለ በኋላ “የ110ኛው ክፍል የጊልያድ ተማሪዎች የሚስዮናዊነት ሥልጠና ማግኘታቸውንና ወደ ተለያዩ የምድር ክፍሎች መመደባቸውን ማወቃችን ሁላችንንም አስደስቶናል” በማለት ፕሮግራሙን ከፍቷል።

ደስተኛ ሆኖ መቀጠል የሚቻልበት መንገድ

ከወንድም ባርበር የመክፈቻ ንግግር በኋላ ወንድም ዶን አዳምስ “የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርገናለች” በሚል ርዕስ 48ቱን ተመራቂዎች ጨምሮ ለመላው አድማጭ ንግግር ሰጠ። ንግግሩ የተመሠረተው በምሳሌ 10:​22 ላይ ሲሆን አገልጋዮቹ በሕይወታቸው ውስጥ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ካስቀደሙ ይሖዋ እንደሚደግፋቸውና እንደሚባርካቸው የሚያስታውስ ነበር። ተማሪዎቹ አዲሱን ምድባቸውን ሐዋርያው ጳውሎስ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” የሚል ግብዣ ሲቀርብለት ባሳየው ዓይነት የፈቃደኝነት መንፈስ እንዲቀበሉት አበረታትቷቸዋል። (ሥራ 16:​9) ጳውሎስ ሊቋቋማቸው የሚገቡ ችግሮች ቢኖሩበትም በተመደበበት ቦታ ለመስበክ ፈቃደኛ መሆኑ ብዙ አስደሳች በረከቶች አምጥቶለታል።

ተመራቂዎቹ ለሚስዮናዊነት ሥራ ያዘጋጃቸውን የአምስት ወር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ሥልጠና አጠናቅቀዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዳንኤል ሲድሊክ ተማሪዎቹ ሥልጠናቸውን ቢጨርሱም መማራቸውን ግን ፈጽሞ ማቆም እንደሌለባቸው ገልጿል። “እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ሁኑ” በሚል ጭብጥ በሰጠው ንግግሩ ላይ “ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ዘወትር የኢየሱስን ትዕዛዛት መጠበቅ ማለት ነው” ሲል ተናግሯል። “ይህም ቃሉን፣ መልእክቱንና ትምህርቱን ለማዳመጥ ዘወትር ፈቃደኛ መሆንን ይጨምራል።” የአምላክ ጥበብ በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ስለተንጸባረቀ የእርሱ ደቀ መዛሙርት የጌታቸውን ድምፅ ሳይሰሙ ውሳኔዎችን እንደማያደርጉ ገልጿል። (ቆላስይስ 2:​3) ማንኛችንም ብንሆን የኢየሱስን ድምፅ አንዴ ብቻ ሰምተን ስለ እርሱ ሁሉንም ነገር አውቀናል ብለን መደምደም አይኖርብንም። ስለዚህ ተማሪዎቹ ነፃነት የሚያስገኘውን ክርስቲያናዊ እውነት መማራቸውንና ተግባራዊ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አበረታትቷቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 8:​31, 32

አንድ ሰው በአምላክ አገልግሎት ደስተኛ ሆኖ ለመቀጠል ከፈለገ ተግሳጽና ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለበት። የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ሎውረንስ ቦወን ያቀረበው ጥያቄ “ኩላሊታችሁ ይገስጻችሁ ይሆን?” የሚል ነበር። ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊው ኩላሊት ከአንድ ሰው ጥልቅ ሐሳብና ስሜት ጋር ተያይዞ እንደተገለጸ አብራራ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት እስኪለውጥ ድረስ ጠልቆ ከገባ ኩላሊቱ ይገስጸዋል ሊባል ይችላል። (መዝሙር 16:​7፤ ኤርምያስ 17:​10) ሌላው ቀርቶ የአንድ ሰው የታማኝነት አካሄድ ይሖዋን በጥልቅ ሊነካው ይችላል። ተናጋሪው ምሳሌ 23:​15, 16ን ካነበበ በኋላ “ኩላሊታችሁ ይገስጻችሁ ይሆን?” በማለት ጠየቀ። አክሎም “እንደዚያ እንዲሆን እንጸልያለን። በዚህ መንገድ ይሖዋ ጥልቅ ደስታ እንዲሰማው ታደርጋላችሁ። ውስጣዊ ስሜቱንም ትነካላችሁ። አዎን፣ ምድባችሁን ሙጥኝ ስትሉ የይሖዋን ኩላሊት ታስደስታላችሁ።”

የዚህኛው የፕሮግራሙ ክፍል የመጨረሻ ንግግር የቀረበው የጊልያድ አስተማሪ ከመሆኑ በፊት በኬንያ ሚስዮናዊ ሆኖ ባገለገለው በማርክ ኑሜር ነበር። ንግግሩ “በዓይን ማየት ይሻላል” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ባለን ነገር የመርካትን ዝንባሌ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ያጎላ ነበር። ከመክብብ 6:​9 ጋር በመስማማት እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል:- “እውነታውን ተጋፈጡ። ይህ ‘በዓይን እንደማየት ይቆጠራል።’ ማድረግ ስለምትፈልጉት ነገር ከማለም ይልቅ አሁን ያላችሁበትን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ጥረት አድርጉ። ምክንያታዊ ያልሆኑ ነገሮች በመጠበቅ በሕልም ዓለም መኖር ወይም የአገልግሎት ምድቡን አሉታዊ ገጽታዎች ብቻ ማውጠንጠን እርካታና ደስታ ከመንፈግ ውጪ ምንም የሚፈይዱት ነገር አይኖርም።” አዎን፣ የትም እንሁን የት ወይም ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን ኑሮዬ ይበቃኛል የሚል አምላካዊ አስተሳሰብ ማዳበራችን ታላቁን ፈጣሪያችንን በደስታ እንድናገለግለው ይረዳናል።

ከመስክ አገልግሎትና ከጊልያድ የተገኙ አስደሳች ተሞክሮዎች

እነዚህን ከመሰሉ ተግባራዊ ምክሮች በኋላ ተመራቂዎቹ በጊልያድ ባደረጉት የአምስት ወር ቆይታ ወቅት በመስክ አገልግሎት ያገኟቸውን አንዳንድ አስደሳች ተሞክሮዎች ተናገሩ። የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጅስትራር በሆነው ዋላስ ሊቨራንስ መሪነት ተመራቂዎቹ ራሳቸውን የአምላክ አገልጋዮች አድርገው ያቀረቡት እንዴት እንደሆነ ተናገሩ። (2 ቆሮንቶስ 4:​2) የአምላክ ስጦታ የሆነውን የሰዎች ሕሊና መማረክ ችለዋል። ተሞክሮዎቻቸው በመንገድ ላይ፣ ከቤት ወደ ቤትና በሌሎች ቦታዎች ሲያገለግሉ ያገኟቸውን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንዴት መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት እንደጀመሩ የሚያሳዩ ነበሩ። በተለያዩ አጋጣሚዎች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በይሖዋ ድርጅት የሚዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እውነትን እንዳዘሉ ተናግረዋል። አንዲት የቤት ባለቤት ለአንድ ጥቅስ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ ትገኛለች።

በመቀጠል ጆኤል አዳምስ ከቀድሞዎቹ የጊልያድ ምሩቃን ጋር ቃለ ምልልስ አደረገ። የንግግሩ ጭብጥ “መማራችሁንም ሆነ ይሖዋን ማገልገላችሁን ፈጽሞ አታቁሙ” የሚል ነበር። ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ወንድሞች ለአዳዲሶቹ ሚስዮናውያን ወቅታዊ ምክሮች መለገስ ችለዋል። ሃሪ ጆንሰን የጊልያድ የ26ኛው ክፍል አባል የነበረበትን ጊዜ በማስታወስ እንዲህ አለ:- “ይሖዋ ሕዝቡን ሲመራ እንደኖረና ወደፊትም እንደሚመራ ተምረን ነበር። እንዲህ ያለው ትምክህት ባለፉት ዓመታት ሁሉ ማበረታቻ ሆኖልናል።” የ53ኛው ክፍል አባል የነበረው ዊልያም ኖንኪስ ለተመራቂዎቹ የሚከተለውን ምክር ሰጠ:- “ከምንም ነገር በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች አስታውሱ። አሁንም ሆነ ለዘላለም በምታደርጓቸው ውሳኔዎች እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ አውሏቸው። በውጤቱም ምድባችሁን ሙጥኝ ለማለት ትችላላችሁ። ይሖዋም አትረፍርፎ ይባርካችኋል።”

“የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስችል ጥንካሬ ማግኘት” የሚለው ሪቻርድ ራያን ለክፍሉ የመረጠው ጭብጥ ነበር። ቃለ ምልልስ ካደረገላቸው መካከል የጊልያድ የ30ኛው ክፍል ምሩቅ የሆነውና በስፔይን ለ41 ዓመታት ያገለገለው ጆን ኩርትዝ ይገኝበታል። በጊልያድ ስላለው የትምህርት መርሃ ግብር ሲጠየቅ የሚከተለውን ብሏል:- “ዋነኛው የመማሪያ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ሌሎች መሣሪያዎችም አሉን። እነዚህ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው ሊያገኛቸው የሚችላቸው ነገሮች ናቸው። በጊልያድ ምንም ዓይነት የተለየ ትምህርት አይሰጥም። ይህንን ከመናገር ቦዝኜ አላውቅም። እያንዳንዱ ምሥክር የትም ሳይሄድ በጊልያድ የሚሰጠውን ትምህርት ማግኘት ይችላል።”

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጌሪት ሎሽ “በይሖዋ ክንፎች ሥር ጥበቃ ማግኘት” በሚል ርዕስ የሰጠው ንግግር የዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም መቋጫ ነበር። አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያደርገው ጥበቃና ድጋፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በንስር ክንፎች ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ መቅረቡን ገልጿል። (ዘዳግም 32:​11, 12፤ መዝሙር 91:​4) አንዳንድ ጊዜ ወንዱ ንስር ልጆቹን ከአደጋ ለመጠበቅ ክንፉን ለሰዓታት ዘርግቶ ይቆያል። አንዳንድ ጊዜም ሴቷ ንስር ልጆቿን በክንፎቿ ሥር በመሸሸግ ከብርድ ትከላከልላቸዋለች። በተመሳሳይም ይሖዋ ከዓላማው ጋር በሚስማማ መንገድ በተለይ ታማኝ አገልጋዮቹ መንፈሳዊ አደጋ ላይ ሲወድቁ የእርዳታ እጁን ሊዘረጋላቸው ይችላል። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ከሚችሉት በላይ እንዲፈተኑ አይፈቅድም። ከፈተናው ጋር ደግሞ መውጫውን ያዘጋጅላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:​13) ወንድም ሎሽ ንግግሩን የደመደመው የሚከተለውን በማለት ነበር:- “በመንፈሳዊ ጥበቃ ለማግኘት ከፈለግን በይሖዋ ክንፎች ሥር እንደተጠለልን መቆየት ይኖርብናል። ይህም በራስ የመመራት መንፈስ ከማዳበር መራቅ ይኖርብናል ማለት ነው። ስለዚህ ሁልጊዜ ከይሖዋና ከእርሱ እናት መሰል ድርጅት ጋር ተቀራርበን እንኑር። ራሳችንን ከእነርሱ አመራርና ፍቅራዊ ምክር አናግልል።”

ሊቀ መንበሩ ከዓለም ዙሪያ የተላኩ የመልካም ምኞት መግለጫዎችንና ሰላምታዎችን ካነበበ በኋላ ዲፕሎማ የመስጠቱ ሥነ ሥርዓት ተከናወነ። የጊልያድ ትምህርት ቤት ሲቋቋም ዓላማው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ክፍሎች አሰልጥኖ ማስመረቅ ብቻ ነበር። ሆኖም ይሖዋ አምላክ ትምህርት ቤቱ ለ58 ዓመታት ሥራውን እንዲቀጥል ፈቅዷል። ወንድም ባርበር በመክፈቻ ንግግሩ ላይ እንደገለጸው “ጊልያድ ከተቋቋመበት ከ1943 ጀምሮ የጊልያድ ምሩቃን ያስመዘገቡት ታሪክ ምንኛ አስደናቂ ነው! የተባበረው ጥረታቸው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የምድር ትሑታን ቃል በቃል ወደ ይሖዋ ክብራማ ድርጅት እንዲጎርፉ አድርጓል።” አዎን፣ ይህ የሚስዮናውያን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመንግሥቱ ተስፋ ደስ እንዲላቸው አስተዋጽኦ አድርጓል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ

የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 8

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 18

የተማሪዎቹ ብዛት:- 48

አማካይ ዕድሜ:- 34

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 18

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 110ኛ ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ቫሴክ ኢ፣ ማድላ ኤል፣ ኤቨንዝ ጂ፣ ዋታናቢ ኬ፣ (2) ትራፎርድ ፒ፣ ተርፋ ጄ፣ ዊልሰን ፒ፣ ዊልያምስ አር ፣ ቬበር ኤ፣ (3) ጆንሰን ቲ፣ ሃናዉ ኬ፣ ሞርሉ ኤፍ፣ ሻርፔንትየ ኤፍ፣ ፔካም አር፣ አንድሮሶፍ ፒ፣ (4) ሲገረስ ቲ ፣ ሲገረስ ዲ፣ ቤይሊ ፒ፣ ቤይሊ ኤም፣ ማድላ ኬ፣ ሊፖልድ ኢ፣ ሊፖልድ ቲ፣ (5) ኤቨንዝ ኤን፣ ጎልድ አር፣ ቦልማን ኣይ፣ ቫሴክ አር፣ ኡንጂያን ጄ፣ ዊልሰን ኤን፣ (6) ተርፋ ጄ፣ ዙዲማ ኤል፣ ዙዲማ አር፣ ቤንትሰን ሲ፣ ቤንትሰን ጄ፣ ገሌኖ ኤም፣ ገሌኖ ኤል፣ (7) ፔካም ቲ፣ ሞርሉ ጄ፣ ሻርፔንትየ ሲ፣ ጎልድ ኤም፣ ቦልማን አር፣ ኡንጂያን ኤፍ፣ (8) ቬበር አር፣ ጆንሰን ቢ፣ ሃናዉ ዲ፣ ዋታናቢ ዋይ፣ ዊልያምስ አር፣ ትራፎርድ ጂ፣ አንድሮሶፍ ቲ።