በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአንባብያን ጥያቄዎች

የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በ2 ጴጥሮስ 3:​13 ላይ ስለ “አዲስ ሰማያት [በብዙ ቁጥር ] እና አዲስ ምድር” ሲናገር በራእይ 21:​1 ላይ ግን ስለ “አዲስ ሰማይ [ነጠላ ቁጥር ] እና አዲስ ምድር” የሚተነብየው ለምንድን ነው?

ይህ በመሠረቱ ጽሑፉ በመጀመሪያ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች የሚመለከት ሰዋስዋዊ ጉዳይ ነው። በትርጉሙ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ምንም ዓይነት የተለየ ስውር መልእክት ያለው አይመስልም።

በመጀመሪያ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ተመልከት። “ሰማያት” ተብሎ የተተረጎመው ሻማይም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በተጻፈበት የመጀመሪያ ቋንቋ ላይ ምንጊዜም የሚገኘው በብዙ ቁጥር ነው። በብዙ ቁጥር መጻፉ ከበሬታን የሚገልጽ ሳይሆን “የአንድን ቦታ ስፋት” ወይም “በርካታ ቁጥር ያላቸውን የተለያዩ ክፍሎች ወይም ቦታዎች ያቀፈ አንድ ሙሉ ነገር” የሚያሳይ ይመስላል። ግዑዙ ሰማያት በሁሉም አቅጣጫ ከምድር እጅግ ሰፍቶ ስለሚታይና በቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን ስለያዘ ይህ ምክንያታዊ ነው። ሻማይም ከሚለው ቃል በፊት አመልካች ቃል ሲኖር (ቃል በቃል “ዘ ሄቨንስ”) የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ኢሳይያስ 66:​22 ላይ እንደሚገኘው ሁሉ በሁሉም ቦታዎች ላይ ማለት ይቻላል “ሰማያት” ብሎ ተርጉሞታል። ሻማይም ያለ አመልካች ቃል በሚጻፍበት ጊዜ በነጠላ (“ሰማይ” ዘፍጥረት 1:​8፤ 14:​19, 22፤ መዝሙር 69:​34 ላይ እንደሚገኘው) ወይም በብዙ ቁጥር (“ሰማያት” ዘፍጥረት 49:​25፤ መሳፍንት 5:​4፤ ኢዮብ 9:​8፤ ኢሳይያስ 65:​17 ላይ እንደሚገኘው) ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።

በኢሳይያስ 65:​17ም ሆነ በ66:​22 ላይ ሰማያትን ለማመልከት የገባው የዕብራይስጡ ቃል በብዙ ቁጥር የተቀመጠ ሲሆን “አዲስ ሰማያት እና አዲስ ምድር” በሚል ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ለመተርጎም ተመርጧል።

ዩራኖስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ሰማይ” ማለት ሲሆን ብዙ ቁጥር የሚያመለክተው ዩራኖይ ደግሞ “ሰማያት” ማለት ነው። የግሪክኛው ሴፕቱጀንት ተርጓሚዎች በሁለቱም ቦታዎች ላይ ማለትም በኢሳይያስ 65:​17 እና 66:​22 ላይ በነጠላ ቁጥር መጠቀማቸው ትኩረት የሚስብ ነው።

ታዲያ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሁለት ቦታዎች ላይ ስለሚገኘው “አዲስ ሰማይ [ወይም ሰማያት] እና አዲስ ምድር” ስለሚለው ሐረግ ምን ማለት ይቻላል?

በ2 ጴጥሮስ 3:​13 ላይ ሐዋርያው የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር የሚያመለክት ነው። ከዚያ በፊት (በቁጥር 7, 10, 12) በብዙ ቁጥር ተጠቅሞ አሁን ስላሉት ክፉ “ሰማያት” ተናግሯል። ስለዚህ በተመሳሳይ መንገድ ቁጥር 13 ላይ በብዙ ቁጥር ተጠቅሟል። በተጨማሪም 2 ጴጥሮስ 2:​22 ላይ የዕብራይስጥ ጽሑፍ ከሆነው ከምሳሌ 26:​11 ላይ እንደወሰደ ሁሉ የዕብራይስጡ ቃል በብዙ ቁጥር ከሚገኝበት ከመጀመሪያው ከኢሳይያስ 65:​17 ላይ የጠቀሰ ይመስላል። በመሆኑም ጴጥሮስ “አዲስ ሰማያት [ብዙ ቁጥር] እና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ሲል አመልክቷል።

ትንሽ ለየት ባለ መልኩ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ 21:​1 ላይ ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው በሴፕቱጀንት ትርጉም ኢሳይያስ 65:​17 ላይ ያለውን “ሰማይ” ለማመልከት የገባውን በነጠላ ቁጥር የሚገኘውን የግሪክኛ ቃል እንደተጠቀመ በግልጽ መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አዲስ ሰማይን [ነጠላ ቁጥር] እና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና።”

እነዚህ ነገሮች ከትርጉም ሥራ ጋር የተያያዙ ሰዋስዋዊ ዝርዝር ጉዳዮች ናቸው። አንድ ሰው “አዲስ ሰማያት”ም ሆነ “አዲስ ሰማይ” ብሎ ቢያነብ ወይም ቢናገር በሐሳብ ረገድ የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ በድጋሚ መናገሩ አስፈላጊ ነው። ሁለቱ አባባሎች ተመሳሳይ ሐሳብ ያስተላልፋሉ።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከዋክብት:- Frank Zullo