በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወቅታዊ ምክሮች በማቅረብ ወጣቶችን መርዳት

ወቅታዊ ምክሮች በማቅረብ ወጣቶችን መርዳት

ምሉዓን ሆናችሁና ጽኑ እምነት ኖሯችሁ ቁሙ

ወቅታዊ ምክሮች በማቅረብ ወጣቶችን መርዳት

ኤጳፍራ ወደ ሮም ተጉዞ የነበረ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ነው። ሆኖም ልቡ በትንሿ እስያ በምትገኘው በቆላስይስ ከተማ ቀርቶ ነበር። ደግሞም ለዚህ ጥሩ ምክንያት ነበረው። ኤጳፍራ በቆላስይስ ምሥራቹን የሰበከ ሲሆን በዚያ የሚኖሩ አንዳንዶች የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ሳይረዳቸው አይቀርም። (ቆላስይስ 1:​7) ኤጳፍራ በቆላስይስ የሚገኙት ክርስቲያኖች ደህንነት በጥልቅ አሳስቦት ነበር። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ ሮም ሆኖ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ከጻፈላቸው ደብዳቤ መረዳት ይቻላል:- “ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፣ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።”​—⁠ቆላስይስ 4:​12

በተመሳሳይ ዛሬ ያሉት ክርስቲያን አባቶችና እናቶች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ደህንነት አጥብቀው ይጸልያሉ። እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው በእምነት መጽናት ይችሉ ዘንድ በልባቸው ውስጥ የአምላክን ፍቅር ለመትከል ይጥራሉ።

ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች በትምህርት ቤትና በሌሎች ቦታዎች የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቋቋም የሚያስችላቸውን እርዳታ ለማግኘት ይጠይቃሉ። አንዲት የ15 ዓመት ወጣት “ችግሮቻችን ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱ በመሄድ ላይ ናቸው። ሕይወት በጣም አስፈሪ እየሆነ ነው። እርዳታ ያስፈልገናል!” ስትል ተናግራለች። የእነዚህ ወጣቶች ጥያቄና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች የሚያቀርቡት ጸሎት መልስ አግኝቶ ይሆን? አዎን! ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች ሲቀርቡ ቆይተዋል። (ማቴዎስ 24:​45) በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ‘ምሉዓን ሆነውና ጽኑ እምነት ኖሯቸው’ እንዲቆሙ አስተዋጽኦ ያደረጉት አንዳንድ ጽሑፎች እዚህ ላይ ቀርበዋል። እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።

“እነሆ . . . 15, 000 አዳዲስ ምሥክሮች!”

ነሐሴ 1941 ሴንት ሉዊስ ሚዙሪ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ 115, 000 የሚያክሉ ምሥክሮች እስከዚያ ጊዜ ድረስ ተደርጎ የማያውቅ ትልቅ ስብሰባ አድርገው ነበር። “የልጆች ቀን” በተሰኘው በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ላይ ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ “የንጉሡ ልጆች” በሚል ርዕስ የሰጠውን ንግግር ከመድረኩ አጠገብ የተቀመጡ 15, 000 የሚያክሉ ልጆች በትኩረት አዳምጠዋል። በንግግሩ መደምደሚያ አካባቢ የ71 ዓመቱ ራዘርፎርድ አባታዊ በሆነ ድምፅ እንዲህ አለ:-

“አምላክንና ንጉሡን ለመታዘዝ የተስማማችሁ ልጆች በሙሉ . . . እባካችሁ ብድግ በሉ።” ልጆቹም በአንድነት ከመቀመጫቸው ተነሡ። “እነሆ፣” አለ ወንድም ራዘርፎርድ “ከ15, 000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አዳዲስ ምሥክሮች!” ወዲያው ጭብጨባው አስተጋባ። ተናጋሪው በማከል “በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኛችሁ ልጆች ሁላችሁ ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት . . . ለመንገር አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ የምታደርጉ ከሆነ እባካችሁ አዎን በማለት ምላሽ ስጡ።” ልጆቹም ጮክ ባለ ድምፅ “አዎን!” ብለው መለሱ። ከዚያም ወንድም ራዘርፎርድ ልጆች የተባለ አዲስ መጽሐፍ መውጣቱን ገለጸ። ጭብጨባው ለረዥም ጊዜ ቀጥሎ ነበር።

ከዚህ ቀስቃሽ ንግግር በኋላ ልጆች በረጅሙ ተሰልፈው ተራ በተራ ወደ መድረኩ በመውጣት ከወንድም ራዘርፎርድ እጅ የመጽሐፉን አንዳንድ ቅጂ በስጦታ መልክ ተቀበሉ። ይህ ሁኔታ በቦታው የተገኙትን ሁሉ አስለቅሶ ነበር። ሁኔታውን የታዘበ አንድ የዓይን ምሥክር እንዲህ ብሏል:- “በአምላካቸው በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደሚታመኑ ባሳዩት ልጆች ሁኔታ የማይነካ ድንጋይ ልብ ያለው ሰው ብቻ ነው።”

በዚያ የማይረሳ ስብሰባ ላይ 1,300 ወጣቶች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል። ብዙዎቹም እስካሁን በእምነታቸው እንደጸኑ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ በአካባቢያቸው የሚገኘውን ጉባኤ ይረዳሉ። ሌሎቹ በቤቴል ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው ያገለግላሉ። ሚስዮናዊ ሆነው በውጭ አገር የሚያገለግሉም አሉ። በእርግጥም “የልጆች ቀን” እና ልጆች የተባለው መጽሐፍ በብዙ የልጆች ልብ ውስጥ የማይረሳ ትዝታ ትቶ አልፏል!

“የሚደርሱን ልክ በወቅቱ ነው ማለት ይቻላል”

በ1970ዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ልብ የነኩ ሦስት ተጨማሪ መጻሕፍትን አሳትመዋል። እነዚህም ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ፣ ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት እና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባሉት መጻሕፍት ናቸው። በ1982 ደግሞ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” የሚል አምድ በንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ላይ መውጣት ጀመረ። በዚህ አምድ ሥር የሚወጡት ርዕሰ ትምህርቶች የወጣቶችንም ሆነ የአዋቂዎችን ልብ በእጅጉ ነክተዋል። አንድ የ14 ዓመት ልጅ “አምላክ ርዕሰ ትምህርቶቹ ታትመው እንዲወጡ በማስቻሉ ሁልጊዜ ማታ ማታ አመሰግነዋለሁ” በማለት ተናግሯል። አንዲት የ13 ዓመት ልጅ ደግሞ “ርዕሰ ትምህርቶቹን እወዳቸዋለሁ። የሚደርሱን ልክ በወቅቱ ነው ማለት ይቻላል” ብላለች። ወላጆችም ሆኑ የተሾሙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች ወቅታዊና ጠቃሚ እንደሆኑ ይስማማሉ።

“ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች. . .” በሚለው አምድ ሥር በንቁ! መጽሔት ላይ የወጡት ርዕሰ ትምህርቶች በ1989 ወደ 200 ገደማ ደርሰው ነበር። በዚያው ዓመት በተደረገው “ለአምላክ ማደር” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ ወጣ። ይህ መጽሐፍ ወጣቶች በእምነት ጸንተው እንዲቀጥሉ ረድቷቸው ይሆን? ሦስት ወጣቶች እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ይህ መጽሐፍ ችግሮቻችንን እንድናውቅና እነዚህን ችግሮች መወጣት የምንችልበትን መንገድ እንድናስተውል በማድረግ ረገድ በጣም ጠቅሞናል። ለደህንነታችን ስለምታስቡልን እናመሰግናችኋለን።” በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች በዚህ አባባል ይስማማሉ።

“ስንፈልገው የነበረውን ነገር አግኝተናል”

በ1999 የይሖዋ ምሥክሮች ለወጣቶች ተጨማሪ ወቅታዊ ምክር የያዘ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት የምችለው እንዴት ነው?” የተሰኘ የቪዲዮ ክር አወጡ። ይህ ቪዲዮ መውጣቱ ብዙዎችን በእጅጉ አስደስቷል። አንዲት የ14 ዓመት ልጅ “ይህ ቪዲዮ በጥልቅ ነክቶኛል” ብላለች። አንዲት ነጠላ እናት “ይህ ቪዲዮ ከአሁን በኋላ የመንፈሳዊ ምግባችን ቋሚ ክፍል ይሆናል” በማለት ተናግራለች። አንዲት ወጣት ባለትዳር ደግሞ እንዲህ ብላለች:- “የምስጢር ጓደኛችን የሆነው ይሖዋ ዓለም አቀፍ በሆነው ድርጅቱ ውስጥ የሚገኙትን ወጣቶች ከልብ እንደሚወዳቸውና እንደሚያስብላቸው ማወቁ በእርግጥም የሚያስደስት ነው።”

ይህ ቪዲዮ ምን አከናውኖ ይሆን? ወጣቶች የሚከተሉትን አስተያየቶች ሰጥተዋል:- “ቪዲዮው በጓደኛ ምርጫዬ ረገድ ጠንቃቃ እንድሆን፣ በጉባኤ ውስጥ ወዳጅነቴን እንዳሰፋና ይሖዋን ጓደኛዬ እንዳደርገው ረድቶኛል።” “የእኩዮቼን ተጽእኖ እንድቋቋም ረድቶኛል።” “ይሖዋን አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለማገልገል ባደረግሁት ቁርጥ ውሳኔ እንድጸና ረድቶኛል።” በተጨማሪም አንድ ባልና ሚስት የሚከተለውን ብለዋል:- “ይህን የመሰለ ‘ምግብ’ ስላቀረባችሁልን ከልብ እናመሰግናችኋለን። ስንፈልገው የነበረውን ነገር አግኝተናል።”

ከቅቡዕ ክርስቲያኖች የተውጣጣው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከአምላክ ለተሰጠው ተልእኮ ታማኝ በመሆን ፈቃደኞች ለሆኑ ሁሉ መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ ሲያቀርብ ቆይቷል። እንዲህ ያለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ወጣቶች ‘ምሉዓን ሆነውና በአምላክ ፈቃድ ጽኑ እምነት ይዘው እንዲቆሙ’ እየረዳቸው ያለው እንዴት እንደሆነ ማወቁ ምንኛ ያስደስታል!