በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ አምልኮ ሰዎችን አንድ ያደርጋል

እውነተኛ አምልኮ ሰዎችን አንድ ያደርጋል

እውነተኛ አምልኮ ሰዎችን አንድ ያደርጋል

በጥቅሉ ሲታይ ሃይማኖት የሰው ልጆችን የመከፋፈል አዝማሚያ ቢታይበትም እውነተኛ ለሆነው አምላክ ብቻ የሚቀርበው አምልኮ ሰዎችን አንድ የማድረግ ኃይል አለው። እስራኤል የአምላክ ምርጥ ሕዝብ በነበረበት ወቅት ብዙ ቅን ልብ ያላቸው አሕዛብ ወደ እውነተኛው አምልኮ ተስበዋል። ለምሳሌ ያህል ሩት የአገሯን ማለትም የሞዓብን አማልክት በመተው “ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” በማለት ለኑኃሚን ነግራት ነበር። (ሩት 1:​16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አሕዛብ እውነተኛውን አምላክ ማምለክ ጀመሩ። (ሥራ 13:​48፤ 17:​4) በኋላም የኢየሱስ ሐዋርያት ምሥራቹን ራቅ ወዳሉ ክልሎች ማዳረስ ሲጀምሩ ሌሎች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችም ለእውነተኛው አምላክ በሚቀርበው አምልኮ አንድ ሆነዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ታገለግሉ ዘንድ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር ዘወር አላችሁ’ በማለት ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 1:9) በዛሬው ጊዜስ ለእውነተኛው አምላክ የሚቀርበው አምልኮ ሰዎችን አንድ የማድረግ ኃይል ይኖረው ይሆን?

ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች “እውነተኛ አምላኪዎች” ወይም “እውነተኛው አምላክ” ብሎ መናገር ስህተት ነው ይላሉ። እንዲህ የተሰማቸው ምናልባት እውነትን መማር ስለሚቻልበት ምንጭ ምንም ዓይነት ግንዛቤ ስለሌላቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የተለያየ ባህልና አስተዳደግ ያላቸው እውነት ፈላጊዎች አምልኮ የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል። ሊመለክ የሚገባው ብቸኛ አካል የሁሉ ነገሮች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። (ራእይ 4:11) እውነተኛው አምላክ እርሱ ሲሆን እንዴት መመለክ እንዳለበትም የመወሰን መብት አለው።

አምላክ የሚፈልግብንን ብቃቶች በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገልጦልናል። ዛሬ በምድር የሚገኘው እያንዳንዱ ሰው ማለት ይቻላል ሙሉውን ወይም ከፊሉን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ማግኘት ይችላል። ከዚህም በላይ የአምላክ ልጅ “በቃሌ ብትኖሩ . . . እውነትን ታውቃላችሁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:​31, 32) ስለዚህ እውነትን ማወቅ ይቻላል ማለት ነው። እንዲሁም የተለያየ ሃይማኖታዊ እምነት የነበራቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ሰዎች ይህንን እውነት በድፍረት እየተቀበሉና በእውነተኛው አምልኮ አንድ እየሆኑ ነው።​—⁠ማቴዎስ 28:19, 20፤ ራእይ 7:9, 10

በጊዜያችን የታየ ዓለም አቀፍ አንድነት!

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የሶፎንያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አንድ አስደናቂ ትንቢት የተለያየ ባህልና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች በአንድነት ስለሚሰባሰቡበት ጊዜ ይናገራል። እንዲህ ይላል:- “በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።” (ሶፎንያስ 3:9) ይህ ተለውጠው አምላክን በአንድነት የሚያገለግሉትን ሰዎች የሚያመለክት እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው!

ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ሶፎንያስ 3:​8 እንዲህ ይላል:- “መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፣ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፣ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፣ ይላል እግዚአብሔር።” አዎን፣ ይህ የሚሆነው ይሖዋ ብሔራትን በሚሰበስብበት ጊዜ ውስጥ ነው። ሆኖም ቁጣውን በእነርሱ ላይ ከማውረዱ በፊት ለምድር ትሑታን ንጹሑን ልሳን ይሰጣቸዋል። ያ ጊዜ አሁን ነው። ምክንያቱም ሁሉም ብሔራት አርማጌዶን በመባል ለሚታወቀው ሁሉን ቻይ ለሆነው የአምላክ የጦርነት ቀን እየተሰባሰቡ ነው።​—⁠ራእይ 16:14, 16

ይሖዋ ሕዝቡን አንድ ለማድረግ ንጹሕ ልሳን ይሰጣቸዋል። ይህ አዲስ ልሳን ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በትክክል ማስተዋልን ይጨምራል። ንጹሑን ልሳን መናገር ማለት ደግሞ በእውነት ማመንን፣ ይህንን እውነት ለሌሎች ማስተማርንና ከአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖርን ያካትታል። ይህም ከፋፋይ ከሆነው ፖለቲካ መራቅንና የዚህ ዓለም መለያ ምልክት የሆኑትን እንደ ዘረኝነትና ብሔረተኝነት ያሉትን ከራስ ወዳድነት የሚመነጩ ባሕርያት ከልብ ነቅሎ ማውጣትን ይጠይቃል። (ዮሐንስ 17:14፤ ሥራ 10:34, 35) እውነትን የሚወዱ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ይህንን ልሳን መማር ይችላሉ። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት አምስት ግለሰቦች በአንድ ወቅት ፈጽሞ የተለያየ ሃይማኖታዊ እምነት የነበራቸው ቢሆንም እውነተኛ ለሆነው አምላክ ለይሖዋ ብቻ በሚቀርበው አምልኮ እንዴት አንድ እንደሆኑ ተመልከት።

በእውነተኛው አምልኮ አንድ ሆነዋል

አጥባቂ የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረችው ፊዴልያ ለልጅዋ መማሪያ እንዲሆን በማለት አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ገዛች። በኋላም የሞቱት አምስት ልጆችዋ ስላሉበት ሁኔታ እንዲያስረዳት ቄሱን ጠየቀችው። “በጣም የሚያሳዝን ነበር!” በማለት ተናግራለች። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷን ሲያንኳኩ ተመሳሳይ ጥያቄ ጠየቀቻቸው። ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ የሚገልጸውን እውነት በራሷ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስታነብብ ቤተ ክርስቲያን አታልሏት እንደነበር ተገነዘበች። ሙታን አንዳች ነገር ስለማያውቁ በሊምቦ ወይም በሌላ ቦታ እየተሰቃዩ እንዳልሆነ ተረዳች። (መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5) ፊዴልያ ሁሉንም ሃይማኖታዊ ምስሎቿን በማስወገድ ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቃ ወጣች። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። (1 ዮሐንስ 5:21) ፊዴልያ ላለፉት አሥር ዓመታት ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውነት ለሌሎች በማስተማር ደስታ አግኝታለች።

የካትማንዱዋ ታራ ጥቂት የሂንዱ ቤተ መቅደሶች ወደሚገኙበት አገር ስለተዛወረች መንፈሳዊ ፍላጎቴን ያሟላልኛል ብላ በማሰብ ወደ አንድ የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ሄደች። ሆኖም በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚደርሰው ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄዋ መልስ ሳታገኝ ቀረች። በኋላ ግን የይሖዋ ምሥክሮች አገኙዋትና መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ጋበዙዋት። ታራ እንዲህ ትላለች:- “በዓለም ውስጥ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው አፍቃሪ የሆነው አምላክ ሊሆን እንደማይችል ተረዳሁ። . . . ሰላምና ስምምነት ስለሚሰፍንበት አዲስ ዓለም የሚናገረው ተስፋ አስደሳች ሆኖ አገኘሁት።” (ራእይ 21:3, 4) ታራ የሂንዱ ምስሎቿን በሙሉ አስወገደች። እንዲሁም በትውልድ አገሯ የሚዘወተሩትን ልማዶች መከተሏን አቆመች። የይሖዋ ምሥክር በመሆን የሌሎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማርካት የበኩሏን አስተዋጽኦ ማድረግ መቻሏ ከልብ አስደስቷታል።

የቡዲስት እምነት ተከታይ የሆነው ፓንያ ባንኮክ ሳለ የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያነጋግሩት ጠንቋይ ሆኖ ነበር። ከዚህ የተነሣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች ማረኩት። ፓንያ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “አሁን ያለው ሁኔታ ፈጣሪ በመጀመሪያ አስቦት ከነበረው ሁኔታ ለምን እንደተለየ እንዲሁም እርሱንና ሉዓላዊነቱን ለመቀበል አሻፈረኝ ባሉት ፍጥረታት ሳቢያ የመጣውን መከራ ለማስወገድ ምን ዝግጅት እንዳደረገ ስገነዘብ ከዓይኔ ላይ የሆነ ነገር የተገፈፈልኝ ያህል ነበር። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እርስ በርሱ የሚስማማ ሆኖ አገኘሁት። ይሖዋን በግለሰብ ደረጃ መውደድ ስጀምር ትክክል እንደሆነ የማውቀውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ተገፋፋሁ። ሌሎች በሰብዓዊና በአምላካዊ ጥበብ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጓጉቼ ነበር። በእርግጥም እውነተኛ ጥበብ ሕይወቴን ለውጦታል።”

ቨርጂል ከጊዜ በኋላ በሃይማኖታዊ እምነቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ እያደረበት መጣ። ጥቁሮችን ለመርዳት የሚያስችለውን መንገድ እንዲያሳየው አምላክን ከመለመን እንዲሁም ለነጮች ጥላቻ ማሳደርን ያበረታታል ብሎ ስላሰበው ዘረኛ ድርጅት ከመጸለይ ይልቅ ምንም ይሁን ምን፣ የትም ይሁን የት እውነትን ለማግኘት ጸለየ። “ለአምላክ ልባዊ ጸሎት አቅርቤ በሚቀጥለው ቀን ከመኝታዬ ስነሳ” በማለት ያስታውሳል ቨርጂል “ቤት ውስጥ መጠበቂያ ግንብ አገኘሁ። . . . በበሩ ሥር ባለው ክፍተት አሾልከው ያስገቡት መሆን አለበት።” ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በርትቶ ማጥናት ጀመረ። እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እርካታ ተሰማኝ። . . . በውስጤ የተስፋ ጭላንጭል ይታየኝ ጀመር።” ቨርጂል ብዙም ሳይቆይ በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ብቸኛ ተስፋ ለሌሎች ከሚያካፍሉት ጋር መተባበር ጀመረ።

ግላዲስ የተባለች ምሥክር፣ ከላቲን አሜሪካ የመጣችው ቻሮ ትንንሽ ልጆቿ እንደሚያስቸግሩዋት ስትገነዘብ አብራት ገበያ በመሄድ ትረዳት ጀመር። ከጊዜ በኋላ ቻሮ ግላዲስ ያቀረበችላትን ነጻ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ግብዣ ተቀበለች። ቻሮ ሁሉም ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በመስጠት የሰው ልጆችን እንደሚባርክ ከገዛ መጽሐፍ ቅዱስዋ ስትረዳ በጣም ተደነቀች። (መዝሙር 37:11, 29) ዛሬ ቻሮ ራስዋ ይህንን ተስፋ ለሌሎች በማካፈል 15 ዓመታት አሳልፋለች።

መላዋ ምድር ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በአንድነት በሚያመልኩ ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች ስትሞላ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! ይህ ቅዠት አይደለም። ይሖዋ የገባው ቃል ነው። አምላክ በነቢዩ በሶፎንያስ በኩል እንዲህ ብሏል:- “በመካከልሽም የዋህና ትሑት ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በእግዚአብሔርም ስም ይታመናሉ። . . . ኃጢአትን አይሠሩም፣ ሐሰትንም አይናገሩም፣ በአፋቸውም ውስጥ ተንኰለኛ ምላስ አይገኝም፤ . . . የሚያስፈራቸውም የለም።” (ሶፎንያስ 3:12, 13) ይህን ተስፋ ማራኪ ሆኖ ካገኘኸው የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በጥብቅ ተከተል:- “እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”​—⁠ሶፎንያስ 2:3