በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ወደ እናንተ ይቀርባል’

‘ወደ እናንተ ይቀርባል’

‘ወደ እናንተ ይቀርባል’

“[አምላክ] ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።”​ሥራ 17:​27

1, 2. (ሀ) በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ስንመለከት ፈጣሪን በተመለከተ ምን ብለን ልንጠይቅ እንችላለን? (ለ) ሰዎች በይሖዋ ዓይን ከፍ ተደርገው እንደሚታዩ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

 ጥርት ባለ ምሽት በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ተመልክተህ ተደምመህ ታውቃለህ? ለቁጥር የሚታክተው የከዋክብት ብዛትና ዳርቻ የሌለው የሕዋ ስፋት በአድናቆት እንድንዋጥ ያደርገናል። እጅግ ሰፊ በሆነው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ምድር ኢምንት ሆና ትታያለች። ታዲያ እንዲህ ሲባል ‘በምድር ሁሉ ላይ ልዑል’ የሆነው ፈጣሪ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ የሰው ልጆችን ከቁብ አይቆጥርም ወይም ከሰዎች በጣም የራቀና ሊታወቅ የማይችል ነው ማለት ነውን?​—⁠መዝሙር 83:​18

2 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ሰዎችን ዝቅ አድርጎ እንደማይመለከት ይገልጽልናል። እንዲያውም የአምላክ ቃል “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” በማለት አምላክን እንድንፈልገው ያበረታታናል። (ሥራ 17:​27፤ 1 ዜና መዋዕል 28:​9) በእርግጥም ወደ አምላክ ለመቅረብ አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰድን እርሱም ለጥረታችን ምላሽ ይሰጣል። ምን በማድረግ? የ2003 የዓመት ጥቅሳችን ‘ወደ እናንተ ይቀርባል’ በማለት የሚያስደስት መልስ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 4:​8) ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ከሚያዘንብላቸው አስደናቂ በረከቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመርምር።

የይሖዋ ስጦታ

3. ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች የሚሰጣቸው ስጦታ ምንድን ነው?

3 በመጀመሪያ ደረጃ፣ የይሖዋ አገልጋዮች እሱ ለሕዝቡ ያዘጋጀውን ውድ ስጦታ አግኝተዋል። ይህ ሥርዓት የሚያቀርበው ማንኛውም ሥልጣን፣ ሀብትና እውቀት ይህን ስጦታ ሊያስገኝ አይችልም። ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ብቻ የሚሰጠው ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ ምንድን ነው? የአምላክ ቃል እንዲህ የሚል መልስ ይሰጣል:- “ለማስተዋል ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና።” (ምሳሌ 2:3-6) ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች “የአምላክን እውቀት” ማግኘት ይችላሉ እንደተባለ ልብ በል! ይህ ስጦታ ማለትም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውቀት ‘ከተቀበረ ገንዘብ’ ጋር ተመሳስሏል። ለምን?

4, 5. ‘የአምላክ እውቀት ከተቀበረ ገንዘብ’ ጋር የተወዳደረው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

4 አንደኛው ምክንያት የአምላክ እውቀት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ነው። ከሚያስገኛቸው ውድ በረከቶች መካከል አንዱ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ነው። (ዮሐንስ 17:​3) ይሁንና ይህ እውቀት በአሁኑ ጊዜም እንኳ አስደሳች ሕይወት ያስገኝልናል። ለምሳሌ ይህል የአምላክን ቃል በጥንቃቄ በማጥናታችን እንደሚከተሉት ላሉ አበይት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ችለናል:- የአምላክ ስም ማን ነው? (ዘጸአት 6:​31879 ትርጉም ) ሙታን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ? (መክብብ 9:​5, 10) አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው? (ኢሳይያስ 45:​18) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት መምራት ችለናል። (ኢሳይያስ 30:​20, 21፤ 48:​17, 18) የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንቋቋም እንዲሁም እውነተኛ ደስታና እርካታ የሚያስገኝ ሕይወት እንድንመራ የሚረዳንን ትክክለኛ መመሪያ አግኝተናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአምላክን ቃል ማጥናታችን የይሖዋን አስደናቂ ባሕርያት እንድናውቅና ወደ እሱ እንድንቀርብ አስችሎናል። ‘የአምላክን እውቀት’ በመቅሰም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ከመመሥረት የበለጠ ዋጋ ያለው ምን ነገር ሊኖር ይችላል?

5 የአምላክ እውቀት ‘ከተቀበረ ገንዘብ’ ጋር ሊመሳሰል የቻለበት ሌላም ምክንያት አለ። እንደ አብዛኞቹ የተቀበሩ ሀብቶች ሁሉ ይህም እውቀት በዓለም ላይ እንደ ልብ የሚገኝ አይደለም። ከስድስት ቢልዮን የምድር ነዋሪዎች መካከል ‘የአምላክን እውቀት’ ያገኙት ቁጥራቸው ስድስት ሚልዮን የሚያክለው የይሖዋ አምላኪዎች ብቻ ናቸው። ይህም ከ1, 000 ሰዎች መካከል አንዱ እንደማለት ይሆናል። የአምላክ ቃል የያዘውን እውነት የሚረዱት ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ምን ይሆናሉ? የሚለውን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ ብቻ እንመርምር። ነፍስ ሟች መሆኗንና ሙታን ምንም እንደማያውቁ ከቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ተረድተናል። (ሕዝቅኤል 18:​4) ሆኖም በዓለማችን ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች በሰው ውስጥ የምትገኝ ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ አለች የሚል የሐሰት ትምህርት ያስተምራሉ። ይህ ትምህርት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ ሃይማኖቶች መሠረታዊ ትምህርት ነው። የሂንዱ፣ የሲክ፣ የሺንቶ፣ የቡድሃ፣ የታኦ፣ የእስልምና፣ የአይሁድና የጃይኒዝም እምነቶችም ይህን ትምህርት በሰፊው ያስተምራሉ። በዚህ የሐሰት መሠረተ ትምህርት ብቻ እንኳ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተታልለዋል!

6, 7. (ሀ) ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት የሚችሉት እነማን ብቻ ናቸው? (ለ) ይሖዋ ‘ጥበበኞችና አስተዋዮች’ የሆኑ ብዙ ሰዎች ያላገኙትን ማስተዋል በመስጠት እንደባረከን የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው?

6 ብዙ ሰዎች ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት ያልቻሉት ለምንድን ነው? አንድ ሰው የአምላክ ቃል የያዘውን ትርጉም ያለ እርሱ እርዳታ ሙሉ በሙሉ መረዳት ስለማይችል ነው። ይህ እውቀት ስጦታ መሆኑን አትዘንጋ። ይሖዋ ይህን ስጦታ የሚሰጠው ቃሉን በቅን ልቦና ተነሳስተው በትሕትና ለመመርመር ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ነው። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች “እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች” ላይሆኑ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 1:​26) እንዲያውም ከመካከላቸው አብዛኞቹ በዓለም መሥፈርት ሲመዘኑ “መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ” ተደርገው ይታዩ ይሆናል። (ሥራ 4:​13) ሆኖም ዋናው ቁም ነገር ዓለማዊ ትምህርት ማግኘቱ አይደለም። ይሖዋ ‘የአምላክን እውቀት’ የሚሰጠን ልባችን ውስጥ በሚያያቸው ባሕርያት የተነሳ ነው።

7 አንድ ምሳሌ ተመልከት። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ በርካታ ምሁራን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፊ ትንታኔ የሚሰጡ በርካታ የጽሑፍ ሥራዎችን አዘጋጅተዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ የማመሳከሪያ ጽሑፎች የአንድን ነገር ታሪካዊ አመጣጥ፣ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላትን ፍቺዎችና ሌሎች ጉዳዮችን ያብራሩ ይሆናል። እነዚህ ምሁራን ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው መሆኑ በእርግጥ ‘የአምላክን እውቀት’ አስገኝቶላቸዋል? የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ በሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት የይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ መሆኑ በግልጽ ገብቷቸዋል? ይሖዋ አምላክ የሥላሴ ክፍል አለመሆኑን አውቀዋል? እኛ ግን እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት አለን። ለምን? ይሖዋ ‘ጥበበኞችና አስተዋዮች’ የሆኑ ብዙ ሰዎች ሊረዱት ያልቻሉትን መንፈሳዊ እውነት የመረዳት ችሎታ በመስጠት ስለባረከን ነው። (ማቴዎስ 11:​25) ይሖዋ ወደ እሱ የሚቀርቡትን ምንኛ ይባርካቸዋል!

‘ይሖዋ የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል’

8, 9. (ሀ) ዳዊት ወደ ይሖዋ የሚቀርቡ ሰዎች የሚያገኙትን ተጨማሪ በረከት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች መለኮታዊ ጥበቃ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

8 ወደ ይሖዋ የሚቀርቡ ሰዎች ሌላም በረከት ይኸውም መለኮታዊ ጥበቃ ያገኛሉ። ብዙ መከራና ችግር የተፈራረቀበት መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም። እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል።” (መዝሙር 145:18-20) አዎን፣ ይሖዋ ለሚወድዱት ሰዎች ቅርብ በመሆኑ እርዳታ ለማግኘት ለሚያቀርቡት ልመና አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል።

9 መለኮታዊ ጥበቃ ማግኘት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ መኖር ከሚያስከትልባቸው ጫና በተጨማሪ የይሖዋ ቀንደኛ ጠላት የሆነው የሰይጣን ዲያብሎስ ልዩ ዒላማ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ይህ መሠሪ ጠላት እኛን ‘ለመዋጥ’ ቆርጦ ተነስቷል። (1 ጴጥሮስ 5:​8) ሰይጣን ስደትና ፈተና ያደርስብናል። በተጨማሪም የአእምሯችንንና የልባችንን ዝንባሌ ተመልክቶ በዚያ እኛን ለማጥመድ ይጥራል። እምነታችንን የማዳከምና በመንፈሳዊ ሁኔታ እኛን የመዋጥ ዓላማ አለው። (ራእይ 12:​12, 17) ከእንዲህ ዓይነት ኃይለኛ ጠላት ጋር ውጊያ የገጠምን በመሆኑ ‘ይሖዋ የሚወድዱትን ሁሉ እንደሚጠብቅ’ ማወቃችን አያጽናናንም?

10. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚጠብቀው እንዴት ነው? (ለ) ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ጥበቃ የትኛው ነው? ለምንስ?

10 ይሁንና ይሖዋ ሕዝቡን የሚጠብቀው እንዴት ነው? ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመጠበቅ ቃል ገብቶልናል ሲባል በዚህ ሥርዓት ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይደርስብን ዋስትና ሰጥቶናል ወይም ለእኛ ሲል ተዓምር የመሥራት ግዴታ ውስጥ ገብቷል ማለት አይደለም። ይሁንና ይሖዋ ለሕዝቦቹ በቡድን ደረጃ አካላዊ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። ደግሞም ዲያብሎስ እውነተኛ አምላኪዎችን ከምድር ገጽ ላይ ጠራርጎ እንዲያጠፋቸው አይፈቅድለትም! (2 ጴጥሮስ 2:​9) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል። ፈተናዎችን በጽናት እንድንወጣና ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና እንድንጠብቅ የሚያስችለንን ትጥቅ በመስጠት ያስታጥቀናል። ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ጥበቃ መንፈሳዊ ጥበቃ ነው። ለምን? ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና እስከተጠበቀ ድረስ ሌላው ቀርቶ ሞትም እንኳ ቢሆን ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም።​—⁠ማቴዎስ 10:​28

11. ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ምን ዝግጅቶች አድርጓል?

11 ይሖዋ ወደ እሱ የሚቀርቡ ሰዎች መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያገኙበትን በርካታ ዝግጅቶች አድርጓል። በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ማሸነፍ የሚቻልበትን ጥበብ አስፍሮልናል። (ያዕቆብ 1:​2-5) ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የሚገኘውን ተግባራዊ ምክር በሥራ ማዋል በራሱ ጥበቃ ያስገኛል። በተጨማሪም ይሖዋ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን’ ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 11:​13) ይህ መንፈስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል በመሆኑ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ችግር ወይም ፈተና በተሳካ ሁኔታ እንድንወጣ ሊያስታጥቀን ይችላል። ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ሰጥቶናል። (ኤፌሶን 4:​8) እነዚህ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ወንዶች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው እርዳታ በሚሰጡበት ጊዜ የይሖዋን የመሰለ ከልብ የመነጨ የርኅራኄ ስሜት ለማንጸባረቅ ይጥራሉ።​—⁠ያዕቆብ 5:​14, 15

12, 13. (ሀ) ይሖዋ በተገቢው ሰዓት መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብልን በምን አማካኝነት ነው? (ለ) ይሖዋ ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን በማሰብ ስላደረገልን ዝግጅቶች ምን ይሰማሃል?

12 ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው በማቅረብ እኛን ለመጠበቅ የሚያስችል ሌላም ዝግጅት አድርጓል። (ማቴዎስ 24:​45) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ጨምሮ ታትመው በሚወጡ ጽሑፎች እንዲሁም በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች አማካኝነት ይሖዋ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ ያቀርብልናል። በጉባኤ ወይም በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ልብህን የነካውና ብርታትና ማጽናኛ ያገኘህበትን ትምህርት ያዳመጥክበት ጊዜ ትዝ ይልሃል? ከላይ ከተጠቀሱት መጽሔቶች በአንዱ ላይ የወጣ ርዕስ አንብበህ ለአንተ እንደተጻፈ ሆኖ የተሰማህ ጊዜ አለ?

13 ሰይጣን በጣም ውጤታማ ሆኖ ካገኛቸው የማጥቂያ ዘዴዎች አንዱ ተስፋ መቁረጥ ሲሆን እኛም የዚህ ጥቃት ዒላማ ከመሆን ነጻ አይደለንም። ለረጅም ጊዜ በሚዘልቅ ከባድ የከንቱነት ስሜት ከተዋጥን ኃይላችን ሊሟጠጥና በቀላሉ ለጥቃት ልንጋለጥ እንደምንችል ያውቃል። (ምሳሌ 24:​10) ሰይጣን የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መሣሪያ አድርጎ ስለሚጠቀም እርዳታ ማግኘት ያስፈልገናል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ተስፋ መቁረጥን ማሸነፍ የሚቻልባቸውን ዘዴዎች የሚያብራሩ ርዕሶችን በተለያየ ጊዜ አውጥተዋል። አንዲት እህት ከእነዚህ ርዕሶች መካከል አንዱን በተመለከተ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ይህን ርዕስ በየቀኑ አንብቤዋለሁ ማለት እችላለሁ፤ ባነበብኩት ቁጥር እንባዬ ይፈስስ ነበር። የተስፋ መቁረጥ ስሜት በተሰማኝ ቁጥር እንዳነብበው ስል መጽሔቱን አልጋዬ አጠገብ አስቀምጨዋለሁ። እንደዚህ ያሉ ርዕሶች ሳነብብ በይሖዋ እቅፍ ውስጥ እንደገባሁ ያህል ሆኖ ይሰማኛል።” a ይሖዋ በወቅቱ ለሚያቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ አመስጋኞች መሆን አይኖርብንም? ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን ሲል ያደረገልን ዝግጅቶች ለእኛ ቅርብ መሆኑንና በእቅፉ ውስጥ እንዳለን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መሆናቸውን አትዘንጋ።

‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነውን አምላክ ማነጋገር

14, 15. (ሀ) ይሖዋ ወደ እርሱ ለሚቀርቡ ሰዎች የሰጣቸው ግሩም መብት ምንድን ነው? (ለ) በጸሎት ወደ ይሖዋ በነፃነት መቅረብ መቻላችን ግሩም መብት ነው የሚባለው ለምንድን ነው?

14 ሰዎች ሥልጣናቸው እየጨመረ በሄደ መጠን በሥራቸው ያሉ ሰዎች እነርሱን አግኝተው ማነጋገር እንዲህ ቀላል እንደማይሆንላቸው አስተውለህ ታውቃለህ? ታዲያ ከዚህ አኳያ ሲታይ ስለ ይሖዋ አምላክስ ምን ማለት ይቻላል? ካለው የላቀ ቦታ አንጻር ተራ የሆኑ ሰዎች የሚያሰሙትን ጸሎት ከቁም ነገር ቆጥሮ ይሰማል ብሎ መጠበቅ ይቻላልን? እንዴታ! የጸሎት መብት ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች የሰጠው ሌላው በረከት ነው። ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደሆነው አምላክ እንደ ልብ መቅረብ መቻል በእርግጥ ግሩም መብት ነው። (መዝሙር 65:​2) ለምን?

15 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- የአንድ ትልቅ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ በርካታ ኃላፊነቶች አሉት እንበል። የትኞቹን ጉዳዮች እሱ ራሱ በቀጥታ እንደሚያከናውናቸውና የትኞቹን ደግሞ ለሌሎች በኃላፊነት እንደሚሰጥ ይወስናል። በተመሳሳይ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የትኞቹን ጉዳዮች እርሱ ራሱ እንደሚያከናውናቸውና የትኞቹን ደግሞ ለሌሎች እንደሚሰጥ የመወሰን መብት አለው። ይሖዋ ለሚወድደው ልጁ ለኢየሱስ የሰጠውን የሥራ ድርሻ ተመልከት። ወልድ “ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን” ተሰጥቶታል። (ዮሐንስ 5:​27) መላእክት ‘ይገዙለታል።’ (1 ጴጥሮስ 3:​22) ኢየሱስ በምድር ላይ ለሚገኙት ደቀ መዛሙርቱ አመራር መስጠት እንዲችል የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ተሰጥቶታል። (ዮሐንስ 15:​26፤ 16:​7) ከዚህም የተነሳ ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” ሊል ችሏል። (ማቴዎስ 28:​18) ሆኖም ይሖዋ የምናቀርበውን ጸሎት እሱ ራሱ መስማት ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ስም ለይሖዋ ብቻ ጸሎት ማቅረብ እንዳለብን የሚያዝዘን ለዚህ ነው።​—⁠መዝሙር 69:​13፤ ዮሐንስ 14:​6, 13

16. ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

16 ይሖዋ በእርግጥ ጸሎታችንን ይሰማል? ለእኛ የማያስብ ቢሆን ኖሮ ‘በጸሎት እንድንጸና’ ወይም ሸክማችንንና ጭንቀታችንን በእሱ ላይ እንድንጥል አያበረታታንም ነበር። (ሮሜ 12:​12፤ መዝሙር 55:​22፤ 1 ጴጥሮስ 5:​7) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የኖሩ ታማኝ አገልጋዮች ይሖዋ ጸሎታቸውን እንደሚሰማላቸው ፍጹም ትምክህት ነበራቸው። (1 ዮሐንስ 5:​14) በመሆኑም መዝሙራዊው ዳዊት ‘[ይሖዋ] ቃሌን ይሰማኛል’ ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 55:​17) እኛም ብንሆን ይሖዋ ቅርብ መሆኑንና ሐሳባችንንና ጭንቀታችንን በሙሉ ለመስማት ዝግጁ መሆኑን እንድናምን የሚያስችለን አጥጋቢ ምክንያት አለን።

ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ወሮታ ይከፍላል

17, 18. (ሀ) ይሖዋ ማስተዋል ያላቸው ፍጡራኑ የሚያከናውኑትን የታማኝነት አገልግሎት እንዴት ይመለከተዋል? (ለ) በርኅራኄ ስሜት ተነሳስተን የምናደርገው ነገር ከይሖዋ የተሰወረ አለመሆኑን ምሳሌ 19:​17 የሚያሳየው እንዴት ነው?

17 ሰዎች የሚፈለግባቸውን ነገር ቢያደርጉም ባያደርጉም በይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ አድናቆቱን መግለጽ የሚወድድ አምላክ ነው። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራኑ በታማኝነት የሚያከናውኑትን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (መዝሙር 147:​11) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ወሮታ ይከፍላቸዋል። ወደ ይሖዋ የሚቀርቡ ሰዎች ከሚያገኟቸው በረከቶች መካከል አንደኛው ይህ ነው።​—⁠ዕብራውያን 11:​6

18 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያከናውኑትን ሥራ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት በግልጽ ያሳያል። ለምሳሌ ያህል “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፣ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል” የሚል እናነብባለን። (ምሳሌ 19:17) ይሖዋ ለድሆች የሚያሳየው ርኅራኄ በሙሴ ሕግ ላይ ተንጸባርቋል። (ዘሌዋውያን 14:​21፤ 19:​15) ይሖዋ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በመርዳት የእሱን የመሰለ ርኅራኄ ስናንጸባርቅ ምን ይሰማዋል? ውለታ ይመለስልኛል ብለን ሳንጠብቅ ለተቸገረ ሰው የሚያስፈልገውን በምንሰጥበት ጊዜ ይሖዋ ለእሱ እንዳበደርነው አድርጎ ይቆጥረዋል። ይሖዋ ሞገስ በማሳየትና በረከቱን በማዝነብ ብድሩን መልሶ እንደሚከፍል ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 10:​22፤ ማቴዎስ 6:​3, 4፤ ሉቃስ 14:​12-14) አዎን፣ ችግር ላይ ለወደቀ የእምነት ባልንጀራችን ርኅራኄ ስናሳይ አድራጎታችን የይሖዋን ልብ ይነካል። በርኅራኄ ስሜት የምናደርገውን ነገር ሰማያዊ አባታችን እንደሚያየው ማወቃችን ምንኛ ያስደስታል!​—⁠ማቴዎስ 5:​7

19. (ሀ) ይሖዋ በስብከቱና ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ የምናከናውነውን አገልግሎት እንደሚያደንቅ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ መንግሥቱን በመደገፍ ለሚደረግ አገልግሎት ወሮታ የሚከፍለው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ በተለይ ለመንግሥቱ ብለን የምናደርገውን ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ወደ እሱ ስንቀርብ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ሃብታችንን የመንግሥቱን ስብከትና ደቀ መዝሙር የማድረጉን ሥራ በተሟላ መንገድ ለመደገፍ ልናውለው እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 28:​19, 20) አንዳንድ ጊዜ የምናበረክተው ድርሻ በጣም አናሳ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ፍጹም ያልሆነው ልባችን ይሖዋ በምናደርገው ጥረት ይደሰት እንደሆነና እንዳልሆነ ጥርጣሬ ሊገባው ይችላል። (1 ዮሐንስ 3:​19, 20) ሆኖም ይሖዋ ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን እንኳ ከፍቅር የመነጨ ማንኛውንም ስጦታ በአድናቆት ይቀበላል። (ማርቆስ 12:​41-44) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ዕብራውያን 6:10) በእርግጥም ይሖዋ፣ መጠኑ አነስተኛም ቢሆን መንግሥቱን ለመደገፍ የሚደረገውን አገልግሎት የማይዘነጋ ከመሆኑም በላይ ወሮታ የሚከፍል አምላክ ነው። አሁን ከምናገኘው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት በተጨማሪ በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኘውን አስደሳች ሕይወት በጉጉት እንጠባበቃለን። በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች ሁሉ እጁን ከፍቶ ፍላጎታቸውን ያረካላቸዋል!​—⁠መዝሙር 145:​16፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

20. በያዝነው ዓመት የትኛውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል? ይህስ ምን ያስገኝልናል?

20 የ2003ን የዓመት ጥቅስ በአእምሯችን በመያዝ ወደ ሰማያዊ አባታችን ለመቅረብ የማያቋርጥ ጥረት እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ምላሽ እንደሚሰጥ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ደግሞም ይሖዋ ‘አይዋሽም።’ (ቲቶ 1:​2) ወደ ይሖዋ ከቀረብን እሱም ወደ እኛ ይቀርባል። (ያዕቆብ 4:​8) ይህስ ምን ያስገኝልናል? በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፈ በረከት ወደፊት ደግሞ ለዘላለም ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ የመኖር አጋጣሚ ያስገኝልናል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በግንቦት 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28-31 ላይ ለወጣው “ይሖዋ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው” ለሚለው ርዕስ የተላከ የአድናቆት መግለጫ።

ታስታውሳለህን?

• ይሖዋ ወደ እሱ ለሚቀርቡ ሰዎች የሚሰጣቸው ስጦታ ምንድን ነው?

• ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ለመጠበቅ ምን ዝግጅቶች አድርጓል?

• ይሖዋን በጸሎት ማነጋገር ታላቅ መብት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• ይሖዋ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራኑ በታማኝነት የሚያከናውኑትን አገልግሎት እንደሚያደንቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ መንፈሳዊ እውነትን እንድንረዳ በማድረግ ባርኮናል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ የምናቀርበውን ጸሎት ለመስማት ዝግጁ ነው