በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቤተሰብ ክልል ውስጥ ፍቅራችሁን ግለጹ

በቤተሰብ ክልል ውስጥ ፍቅራችሁን ግለጹ

በቤተሰብ ክልል ውስጥ ፍቅራችሁን ግለጹ

“እስቲ፣ ልብ ካለሽ አቃጥይው!” በማለት ቶሩ ሚስቱን ዮኮን ተገዳደራት። a እሷ ደግሞ “አቃጥለዋለሁ!” ስትል በቁጣ ዛተችና ሁለቱ አንድ ላይ ሆነው የተነሱትን ፎቶ ለማቃጠል ክብሪት ጫረች። ከዚያም “ቤቱንም ጭምር አጋየዋለሁ!” በማለት በንዴት ተናገረች። ቶሩ ሚስቱን በጥፊ መታት። በቃላት ምልልስ የተጀመረው ንትርክ በድብደባ ተደመደመ።

ከሦስት ዓመት በፊት ቶሩና ዮኮ ተጋብተው አብረው መኖር ሲጀምሩ ትዳራቸው ደስታ የሰፈነበት ነበር። ታዲያ አሁን መጣላትን ምን አመጣው? ምንም እንኳን ቶሩ ጥሩ ሰው ቢመስልም ሚስቱ እንደማይወዳትና እምብዛም ለስሜቶቿ እንደማይጨነቅ ይሰማታል። ቶሩ ለፍቅሯ አጸፋውን መመለስ የሚችል አልመስል ብሏታል። ይህንን ሁኔታ ችላ መኖር ስላልቻለች ቁጡና ብስጩ ሆነች። የእንቅልፍ ማጣት፣ ፍርሃት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ መነጫነጭና የመንፈስ ጭንቀት አልፎ ተርፎም ድንገተኛ የሆነ የመሸበር ስሜት ይታይባት ጀመር። ቶሩ ግን በቤቱ ውስጥ የነገሠው ውጥረት ምንም ግድ የሰጠው አይመስልም። ይህ ለእርሱ አዲስ ነገር አይደለም።

“የሚያስጨንቅ ዘመን”

ይህን የመሳሰሉ ችግሮች በዛሬው ጊዜ የተለመዱ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ በጊዜያችን ሰዎች ‘ፍቅር የሌላቸው’ እንደሚሆኑ ተናግሮ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እዚህ ላይ “ፍቅር የሌላቸው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በቤተሰብ አባላት መሃል ያለውን የተፈጥሮ ፍቅር ለማመልከት ከሚሠራበት ቃል ጋር ተዛማጅነት ያለው ነው። በጊዜያችን እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር እየጠፋ እንደሄደ በግልጽ የሚታይ ነው። የቤተሰብ አባላት የሚዋደዱ ቢሆንም እንኳን አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን ሲገልጹ አይታዩም።

በዛሬው ጊዜ ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር እንዴት እንደሚገልጹ አያውቁም። አንዳንዶቹ ያደጉት ፍቅር በጠፋበት ቤተሰብ ውስጥ በመሆኑ በቤተሰባቸው ውስጥ አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን በመግለጽ ብቻ ሕይወትን ጣፋጭና አስደሳች ማድረግ እንደሚችሉ አይገነዘቡ ይሆናል። የቶሩ ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነበር። በልጅነቱ አባቱ ሁልጊዜ በሥራ ተጠምዶ የሚውል ሲሆን ቤት የሚገባው በጣም አምሽቶ ነበር። ቶሩን እምብዛም አያናግረውም፤ ካናገረውም ደግሞ በስድብና በጩኸት ነበር። እናቱም ሙሉ ቀን የምትሠራ ሲሆን ከቶሩ ጋር የምታሳልፈው ብዙም ጊዜ አልነበራትም። ብቸኛ አጫዋቹ ቴሌቪዥኑ ነበር። በቤተሰባቸው ውስጥ አንዱ ሌላውን የማመስገንም ሆነ እርስ በእርስ የመነጋገር ሁኔታ አልነበረም።

የባሕል ተጽእኖም የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን እንዳይገልጹ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ ክፍሎች አንድ ባል ለሚስቱ ፍቅሩን ለመግለጽ የአካባቢው ባሕል የሚያሳድርበትን ተጽዕኖ ማሸነፍ ይኖርበታል። በአብዛኞቹ የሩቅ ምሥራቅና የአፍሪካ አገሮች ደግሞ ፍቅርን በአንደበትም ሆነ በድርጊት መግለጽ ከአካባቢው ባሕል ጋር ይጋጫል። ባሎች ሚስቶቻቸውን ወይም ልጆቻቸውን “እወድሻለሁ” ወይም “እወዳችኋለሁ” ማለት በጣም የሚያሳፍር ይሆንባቸዋል። ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት ተፈትኖ እስከ መጨረሻው ከዘለቀ አንድ የቤተሰብ ትስስር የምናገኘው ትምህርት አለ።

ምሳሌ የሚሆን የቤተሰብ ትስስር

በቤተሰብ አባላት መካከል ሊኖረው የሚገባውን ፍቅር በተመለከተ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ በይሖዋ አምላክና በአንድያ ልጁ መካከል ያለው የጠበቀ ዝምድና ነው። አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር በመግለጽ ረገድ ፍጹም ምሳሌ ይሆኑናል። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለውና ወደ ምድር የመጣው መንፈሳዊ ፍጡር ለአያሌ ሺህ ዓመታት ከአባቱ ጋር በደስታ ኖሯል። በመካከላቸው የነበረውን የጠበቀ ፍቅር እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፤ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ።” (ምሳሌ 8:30) ኢየሱስ አባቱ እንደሚወደው ፍጹም እርግጠኛ ስለነበር ይሖዋ ዕለት ተዕለት በእርሱ ደስ እንደሚሰኝ አፉን ሞልቶ ለመናገር ችሏል። ከአባቱ ጋር እያለ ምንጊዜም ደስተኛ ነበር።

ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመጣ በኋላም አባቱ እንደሚወደው አረጋግጦለታል። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ አባቱ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ሲናገር ሰምቷል። (ማቴዎስ 3:17) በምድር ላይ እንዲያከናውን የተሰጠውን ተልዕኮ ሀ ብሎ ለሚጀምረው ለኢየሱስ ይህ ምንኛ የሚያበረታታ የፍቅር መግለጫ ነው! በሰማይ ያሳለፈውን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ማስታወስ በቻለበት ወቅት የአባቱን የአድናቆት መግለጫ በመስማቱ በጣም ተደስቶ መሆን አለበት።

ይሖዋ ለጽንፈ ዓለሙ ቤተሰብ በዚህ መንገድ ፍቅሩን ያለ ገደብ በመግለጽ ከሁሉ የላቀ አርኣያ ሆኗል። እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ ካመንን የይሖዋን ፍቅር ማግኘት እንችላለን። (ዮሐንስ 16:27) እንደ ኢየሱስ ከሰማይ ድምፅ ባንሰማም እንኳን ይሖዋ በፍጥረት ሥራው፣ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲሆን በመስጠት ባደረገው ዝግጅትና በሌሎች መንገዶች ፍቅሩን እንደገለጸ መመልከት እንችላለን። (1 ዮሐንስ 4:9, 10) ይሖዋ ጸሎታችንን የሚሰማ ሲሆን ለእኛ በሚበጅ መንገድ መልስ ይሰጠናል። (መዝሙር 145:18፤ ኢሳይያስ 48:17) ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይበልጥ እያጠናከርን ስንሄድ ለፍቅራዊ እንክብካቤው ያለን አድናቆትም እየጨመረ ይሄዳል።

ኢየሱስ ለሌሎች አዛኝ፣ አሳቢና ደግ መሆን የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የተማረው ከአባቱ ነበር። “[አብ] የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፣ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:19, 20) እኛም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የተወልንን ምሳሌ በጥልቀት በመመርመር ለሌሎች ፍቅራችንን መግለጽን መማር እንችላለን።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:8

በቤተሰብ ውስጥ ፍቅርን ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?

‘እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነና’ እኛ ደግሞ የተፈጠርነው ‘በእርሱ መልክ’ ስለሆነ ፍቅርን የማሳየት ችሎታ ያለን ከመሆኑም በላይ ሌሎች ፍቅራቸውን ሲገልጹልን ደስ ይለናል። (1 ዮሐንስ 4:8፤ ዘፍጥረት 1:26, 27) ሆኖም ይህ ችሎታ እኛ ካልተጠቀምንበት በራሱ ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ለትዳር ጓደኛችንም ሆነ ለልጆቻችን ፍቅራችንን ለመግለጽ መጀመሪያውኑ ለእነርሱ ፍቅር ሊያድርብን ይገባል። ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ የትዳር ጓደኛችሁ ወይም ልጆቻችሁ ያን ያህል ደስ የሚል ባሕርይ እንደሌላቸው ሆኖ ሊሰማችሁ ቢችልም ያሏቸውን መልካም ጎኖች ለማስተዋልና በእነዚህ ላይ ለማተኮር በመጣር ለእነሱ ያላችሁን ፍቅር ልታዳብሩ ትችላላችሁ። ‘ባለቤቴ [ልጄ] አንድም መልካም ባሕርይ የለውም/የላትም’ ትሉ ይሆናል። የትዳር ጓደኛቸውን ቤተሰብ ወይም ሌላ ሰው መርጦላቸው የሚያገቡ ሰዎች ለትዳር ጓደኛቸው ብዙም ፍቅር ላይኖራቸው ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ ልጅ የወለዱት ሳይፈልጉ ይሆናል። ቢሆንም በአሥረኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይሖዋ ምሳሌያዊ ሚስቱ ለነበረችው ለእስራኤል ብሔር ምን ዓይነት ስሜት እንደተሰማው ተመልከት። ነቢዩ ኤልያስ ከአሥሩ የእስራኤል ነገዶች መካከል ይሖዋን የሚያመልክ አንድም ሰው የለም ብሎ ደምድሞ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ሕዝቡን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ እርሱን የሚያስደስት ባሕርያት የነበሯቸውን በድምሩ 7, 000 የሚያህሉ ሰዎች አግኝቷል። አንተም የቤተሰብህ አባላት ያሏቸውን መልካም ባሕርያት በመፈለግ የይሖዋን ምሳሌ መኮረጅ ትችላለህ?​—⁠1 ነገሥት 19:14-18

የቤተሰብህ አባላት እንደምትወዳቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ ግን ፍቅርህን ለማሳየት ከልብ መጣር ይኖርብሃል። ሊመሰገኑበት የሚገባ ነገር እንዳለ ስታስተውል አድናቆትህን ከመግለጽ ወደኋላ አትበል። የአምላክ ቃል ልባም ስለሆነች ሚስት ሲናገር “ልጆችዋ ይነሣሉ፣ ምስጋናዋንም ይናገራሉ፤ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል” በማለት የቤተሰቧን አንድ ልዩ ባሕርይ ይጠቅሳል። (ምሳሌ 31:28) የቤተሰቡ አባላት አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን አድናቆት ከመግለጽ ወደኋላ እንደማይሉ ልብ በል። አንድ አባት ሚስቱን የሚያመሰግን ከሆነ ልጁም አድጎ ትዳር በሚይዝበት ጊዜ የትዳር ጓደኛውን እንዲያመሰግን ጥሩ አርዓያ ሊሆነው ይችላል።

ወላጆች ልጆቻቸውንም ማመስገንና ማድነቅ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ልጆቻቸው ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። ደግሞስ አንድ ሰው ለራሱ ጥሩ ግምት ከሌለው ‘ባልንጀራውን እንደ ራሱ መውደድ’ እንዴት ይችላል? (ማቴዎስ 22:39) በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን ፈጽሞ የማያመሰግኗቸውና ሁልጊዜ የሚነቅፏቸው ከሆነ ልጆቹ ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዳይኖራቸውና ለሌሎች ፍቅር ማሳየት እንዲሳናቸው ሊያደርግ ይችላል።​—⁠ኤፌሶን 4:31, 32

እርዳታ ልታገኝ ትችላለህ

ያደግኸው ፍቅር በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ከሆነስ? እንደዚያም ቢሆን ፍቅር ማሳየትን መማር የምትችልበት አጋጣሚ አለህ። የመጀመሪያው እርምጃ ይህ ችግር እንዳለብህ መቀበልና ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ መገንዘብ ነው። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ በእጅጉ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ በመስታወት ሊመሰል ይችላል። በመስታወት በተመሰሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ራሳችንን ስንመረምር በአስተሳሰባችን ላይ ያሉት እንከኖችና ጉድለቶች ቁልጭ ብለው ይታዩናል። (ያዕቆብ 1:23) ማንኛውንም ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አንጻር በመመርመር ማስተካከል እንችላለን። (ኤፌሶን 4:20-24፤ ፊልጵስዩስ 4:8, 9) ‘መልካም ሥራን ለመሥራት ሳንታክት’ አዘውትረን እንዲህ ማድረግ ያስፈልገናል።​—⁠ገላትያ 6:9

አንዳንዶች በአስተዳደጋቸው ወይም በባሕላቸው ምክንያት ለሌሎች ፍቅራቸውን መግለጽ ሊከብዳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት እንዲህ ዓይነት እንቅፋቶችን ማሸነፍ ይቻላል። የአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ዳንኤል ጎልማን ‘ከልጅነታችን ጀምሮ በልባችን ውስጥ ሥር የሰደዱ ልማዶችን እንኳን ማስተካከል እንደሚቻል’ ተናግረዋል። መጽሐፍ ቅዱስም ከ1900 ዓመታት በፊት ሥር የሰደዱ የልባችንን ዝንባሌዎች እንኳን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ማስተካከል እንደሚቻል ገልጾ ነበር። ‘አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፍፋችሁ አዲሱን ሰው ልበሱ’ በማለት ይመክረናል።​—⁠ቆላስይስ 3:9, 10

የቤተሰቡ አባላት ችግሩን አንዴ ለይተው ካወቁ በኋላ የሚያስፈልጋቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ግምት ውስጥ በማስገባት መጽሐፍ ቅዱስን ሊያጠኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍቅርን’ በሚመለከት ምን ምን ሐሳቦች እንደያዘ ለምን ምርምር አታደርጉም? ይህን የመሰለ ጥቅስ ታገኙ ይሆናል:- “ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር [አፍቃሪ፣ NW ] የሚራራም ነውና።” (ያዕቆብ 5:11) ከዚያም ይሖዋ ለኢዮብ ፍቅሩንና ምሕረቱን ላሳየባቸው መንገዶች ትኩረት በመስጠት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የኢዮብን ታሪክ መርምሩ። እናንተም ለቤተሰባችሁ ፍቅርንና ምሕረትን በማሳየት ረገድ ይሖዋን ለመኮረጅ እንደምትነሳሱ አያጠራጥርም።

ይሁን እንጂ ፍጹማን ስላልሆንን በአንደበታችን ‘ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።’ (ያዕቆብ 3:2) በቤተሰባችን ውስጥ አንደበታችንን ሌሎችን በሚያበረታታ መንገድ መጠቀም አልቻልን ይሆናል። ጸሎትና በይሖዋ መታመን የሚያስፈልገው በዚህ ጊዜ ነው። ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ። “ሳታቋርጡ ጸልዩ።” (1 ተሰሎንቄ 5:17) ይሖዋ የቤተሰብ ፍቅር የሚሹትንና ለቤተሰባቸው አባላት ፍቅራቸውን ለመግለጽ ፍላጎቱ እያላቸው እንዲህ ማድረግ ያልቻሉትን ለመርዳት ዝግጁ ነው።

በተጨማሪም ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት እርዳታ የምናገኝበትን ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጎልናል። ያዕቆብ “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 5:14) አዎን፣ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን በመግለጽ ረገድ ችግር ላለባቸው የቤተሰብ አባላት ትልቅ እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ሽማግሌዎች የሥነ ልቦና ሐኪሞች ባይሆኑም የእምነት አጋሮቻቸውን በትዕግሥት ሊረዷቸው ይችላሉ። ይህን የሚያደርጉት የቤተሰቡን አባላት እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ አታድርግ በማለት ሳይሆን ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት እንዲያስታውሱ በመርዳትና አብረዋቸውም ሆነ ብቻቸውን ስለ እነርሱ በመጸለይ ነው።​—⁠መዝሙር 119:105፤ ገላትያ 6:1

ክርስቲያን ሽማግሌዎች ቶሩንና ዮኮን ሁልጊዜ ለችግሮቻቸው ጆሮ ሰጥተው ያዳምጧቸውና ያጽናኗቸው ነበር። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ዮኮ ‘ባልዋን እንድትወድ ልትመክራት’ ከምትችል ተሞክሮ ያላት ክርስቲያን እህት ጋር አብራ ጊዜ በማሳለፍ እንድትጠቀም አንድ ሽማግሌና ባለቤቱ አልፎ አልፎ ቤትዋ ድረስ እየሄዱ ይጠይቋት ነበር። (ቲቶ 2:3, 4) ሽማግሌዎች ክርስቲያን ወንድሞቻቸው የሚያጋጥማቸውን መከራና ሐዘን በመረዳትና አዘኔታ በማሳየት “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” ይሆናሉ።​—⁠ኢሳይያስ 32:1, 2

ቶሩም ሽማግሌዎች በደግነት ባደረጉለት እርዳታ አማካኝነት ስሜቶቹን የመግለጽ ችግር እንዳለበትና ሰይጣን “በመጨረሻው ዘመን” የቤተሰብን አንድነት ለማናጋት ጥቃት እንደሚሰነዝር ተገነዘበ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ከዚያም ይህን ችግር ለማሸነፍ ቆርጦ ተነሳ። ፍቅሩን ለመግለጽ የተቸገረው በልጅነቱ ፍቅር ባለማግኘቱ እንደሆነ ግልጽ እየሆነለት መጣ። ቶሩ መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር በማጥናትና ወደ ይሖዋ በመጸለይ ቀስ በቀስ ለዮኮ ስሜታዊ ፍላጎቶች ተገቢውን ምላሽ ይሰጥ ጀመር።

ዮኮም ምንም እንኳን መጀመሪያ በቶሩ ተበሳጭታ የነበረ ቢሆንም ስለ አስተዳደጉ ስታውቅና የራስዋ ጥፋቶች ሲታይዋት የባሏን መልካም ጎኖች ለመመልከት ከልቧ ጥረት ማድረግ ጀመረች። (ማቴዎስ 7:1-3፤ ሮሜ 5:12፤ ቆላስይስ 3:12-14) ለባልዋ ያላትን ፍቅር ጠብቃ ለመቆየት የሚያስችላትን ጥንካሬ እንዲሰጣት ይሖዋን አጥብቃ በጸሎት ጠየቀችው። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ቶሩም ለሷ ያለውን ፍቅር መግለጽ የጀመረ ሲሆን ይህም ሚስቱን በጣም አስደሰታት።

አዎን፣ በቤተሰብ ውስጥ ፍቅርን መግለጽና ሌሎች ለሚያሳዩህ ፍቅር ምላሽ መስጠት ከባድ ቢሆንብህ እንኳን ልትወጣው የምትችለው ችግር ነው። የአምላክ ቃል በዚህ ረገድ ጥሩ መመሪያ ይሰጠናል። (መዝሙር 19:7) ጉዳዩ ምን ያህል ክብደት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ በመገንዘብ፣ የቤተሰብህ አባላት ያሏቸውን አንዳንድ መልካም ባሕርያት በማስተዋል፣ የአምላክን ቃል በማጥናትና በሥራ ላይ በማዋል፣ በይሖዋ ላይ ትምክህት በመጣል ወደ እርሱ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ እንዲሁም የጎለመሱ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን እርዳታ በመጠየቅ በአንተና በቤተሰብህ መካከል ያለውን የማይገፋ የሚመስል ግድግዳ ማፍረስ ትችላለህ። (1 ጴጥሮስ 5:7) አንድ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ባል እንዲህ በማድረግ ደስታ እንዳገኘ ሁሉ አንተም ልትደሰት ትችላለህ። ለሚስቱ ፍቅሩን እንዲገልጽ ማበረታቻ ተሰጥቶት ነበር። በመጨረሻ እንደ ምንም ራሱን አደፋፍሮ ሚስቱን “እወድሻለሁ” ሲላት እሷ የሰጠችው ምላሽ በጣም አስገረመው። ከደስታዋ የተነሳ ዓይኖቿ እንባ አቅርረው እንዲህ አለችው:- “እኔም እወድሃለሁ፣ ግን እንዲህ ስትለኝ በ25 ዓመት ውስጥ ይህ የመጀመሪያህ ነው።” እናንተም ለትዳር ጓደኛችሁና ለልጆቻችሁ ፍቅራችሁን ለመግለጽ ይህን ያህል ረጅም ጊዜ መቆየት አይኖርባችሁም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እርዳታ ይሰጣል