በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ—ልናውቀው የሚገባ አምላክ

ይሖዋ—ልናውቀው የሚገባ አምላክ

ይሖዋ—ልናውቀው የሚገባ አምላክ

በሕይወትህ ውስጥ የጐደለብህ አንድ አስፈላጊ ነገር ይኖር ይሆን? ስለ አምላክ ብዙም የማታውቅ ከሆነ በእርግጥም የጐደለብህ ነገር አለ። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሊገነዘቡ እንደቻሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን አምላክ ማወቅ በሕይወት ውስጥ ጉልህ ጥቅሞች ያስገኛል። እነዚህን ጥቅሞች የምታገኘው ዛሬ ሲሆን ጠቀሜታቸውም ዘላቂ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ የሆነው ይሖዋ አምላክ እንድናውቀው ይፈልጋል። መዝሙራዊው “ስምህም እግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ” በማለት ጽፏል። አምላክ ስለ እሱ በማወቃችን እንደምንጠቀም ስለሚያውቅ “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ . . . አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎናል። የአጽናፈ ዓለሙ ልዑል የሆነውን ይሖዋን በማወቃችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?​—⁠መዝሙር 83:18፤ ኢሳይያስ 48:17

አንዱ ጥቅም በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት የሚያስችለን መመሪያና ለወደፊቱ ጊዜ የተረጋገጠ ተስፋ ይሰጠናል እንዲሁም የአእምሮ ሰላም ያስገኝልናል። ከዚህም በላይ ይሖዋን በሚገባ ማወቃችን ዛሬ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በሚያሳስቧቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ረገድ የተለየ አመለካከት እንድንይዝ ያደርገናል። እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ሕይወትህ ዓላማ አለውን?

የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ ረገድ አስገራሚ የሆኑ እድገቶች ቢያደርግም ግለሰቦች ‘የመኖሬ ዓላማ ምንድን ነው? መጨረሻዬስ ምን ይሆን? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ ለሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎቻቸው መልስ አላገኙም። አንድ ሰው ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ካላገኘ ሕይወቱ ትርጉም ያጣል። እንደዚህ የሚሰማቸው ሰዎች ምን ያህል ናቸው? በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ በጀርመን የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ጥናት ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ አብዛኛውን ጊዜ ወይም አንዳንድ ጊዜ ሕይወት ትርጉም የለሽ እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል። ምናልባት አንተ በምትኖርበት አካባቢም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ይኖር ይሆናል።

አንድ ሰው የሕይወትን ዓላማ ማወቅ ካልቻለ በሕይወቱ ውስጥ ግቦች ለማውጣት ይቸገራል። ብዙዎች በሥራቸው ስኬታማ ለመሆን በመጣር ወይም ሃብት በማከማቸት ይህንን ክፍተት ለማካካስ ይሞክራሉ። ያም ሆኖ ግን ባለባቸው የባዶነት ስሜት መረበሻቸው አይቀርም። እንዲያውም አንዳንዶች ሕይወታቸው ትርጉም የለሽ መሆኑ በጣም ስለሚረብሻቸው መኖር ያስጠላቸዋል። ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡን የተባለው መጽሔት ‘ሃብት ሞልቶ የተረፋቸው ቤተሰቦች ያሏትና ያሻትን ማድረግ የምትችል’ ብሎ የጠራት የአንዲት ቆንጆ ወጣት ሴት ታሪክ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ኑሮዋ የተንደላቀቀ ቢሆንም እንኳን ብቸኛ እንደሆነችና ሕይወቷ ዓላማ እንደሌለው ይሰማት ነበር። በዚህም የተነሳ ከፍተኛ መጠን ያለው የእንቅልፍ መድሃኒት ወስዳ ሞታ ተገኘች። አንተም በብቸኝነት ስሜት የተደቆሱና ሕይወታቸው አሳዛኝ በሆነ መንገድ ያለፈ ሌሎች ሰዎች ታውቅ ይሆናል።

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ሳይንስ ስለ ሕይወት ትርጉም ሊነግረን እንደሚችል ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ዲ ቮክ የተባለው የጀርመን ሳምንታዊ ጋዜጣ እንዲህ ይላል:- ‘ሳይንስ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ቢችልም ከመንፈሳዊ ጉዳዮች አንጻር ግን ድክመት አለበት። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብም ሆነ ኳንተም ፊዚክስ የሚባለው የትምህርት ዘርፍ መጽናኛና መተማመኛ ማስገኘት አልቻሉም።’ ሳይንስ ስለ ሕይወት፣ ስለ ተፈጥሯዊ ዑደቶችና ሕይወትን ጠብቀው ስለሚያቆዩት ነገሮች በማብራራት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ያም ሆኖ ሳይንስ የመኖራችን ዓላማ ምን እንደሆነና የወደፊት ዕጣችን ምን እንደሚሆን ሊነግረን አይችልም። መልስ ለማግኘት የምንሞክረው ከሳይንስ ብቻ ከሆነ ስለ ሕይወት ዓላማ ያሉን ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ ይቀራሉ። በመሆኑም ዙዶይቼ ፃይቱንግ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው “መመሪያ በጣም ያስፈልገናል።”

በዚህ ረገድ ከፈጣሪ የተሻለ መመሪያ ሊሰጠን የሚችል ማን ይኖራል? ሰዎችን ፈጥሮ በምድር ላይ ያስቀመጣቸው እርሱ እንደመሆኑ የመኖራቸው ዓላማ ምን እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠረው ምድርን እንዲሞሏትና እንዲንከባከቧት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። የሰው ልጆች በድርጊቶቻቸው ሁሉ እንደ ፍትሕ፣ ጥበብ እና ፍቅር ያሉትን የፈጣሪ ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ ይጠበቅባቸው ነበር። ይሖዋ ለምን እንደፈጠረን ከተረዳን የመኖራችን ዓላማ ምን እንደሆነ ማወቅ እንችላለን።​—⁠ዘፍጥረት 1:26-28

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ከዚህ ቀደም ‘የመኖሬ ዓላማ ምንድን ነው? መጨረሻዬስ ምን ይሆን? የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው?’ ለሚሉት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አላገኘህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን በቅርብ እንድታውቀው ያበረታታሃል። እንዲያውም ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። ከዚህም በላይ አምላካዊ ባሕርያትን በተለይም ፍቅርን እንድታዳብርና በመጪው የአምላክ መሲሐዊ አገዛዝ ሥር የመኖር ግብ እንድታወጣ እናበረታታሃለን። እንደዚህ ካደረግህ ሕይወትህ ትርጉም ይኖረዋል፤ ለወደፊቱ ጊዜም ድንቅ የሆነ አስተማማኝ ተስፋ ይኖርሃል። እስካሁን ያስጨንቁህ ለነበሩት መሠረታዊ ጥያቄዎችም መልስ ታገኛለህ።​—⁠ዮሐንስ 17:3፤ መክብብ 12:13

ይህ በሕይወትህ ውስጥ ምን ለውጥ ያመጣል? ሃንስ መልሱን ሊነግረን ይችላል። a ከዓመታት በፊት ሃንስ በአምላክ ላይ የተወሰነ እምነት የነበረው ቢሆንም ሕይወቱን እንዲለውጥ ግን አላነሳሳውም። አደገኛ ዕፆችን ይወስድ፣ ልቅ የጾታ ብልግና ይፈጽም እንዲሁም በወንጀል ድርጊቶች ይካፈል ነበር። “ሆኖም ሕይወቴ ባዶና እርካታ የሌለው ነበር” በማለት ይናገራል። ሃንስ በ20ዎቹ ዕድሜው አጋማሽ ላይ ሲደርስ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በማጥናት አምላክን በሚገባ ለማወቅ ይወስናል። ሃንስ ይሖዋን በቅርብ ሲያውቀውና የሕይወትን ዓላማ ሲገነዘብ አኗኗሩን አስተካከለ። ከዚያም ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በአሁኑ ወቅት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ከጀመረ አሥር ዓመት ሆኖታል። እንዲህ ይላል:- “በሕይወት ውስጥ ይሖዋን ከማገልገል የተሻለ ምንም ነገር የለም። ማንኛውም ነገር ከዚህ ጋር ሊወዳደር አይችልም። ይሖዋን ማወቄ ዓላማ ያለው ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል።”

እርግጥ ነው ሰዎችን የሚያሳስባቸው የሕይወታቸውን ትርጉም አለማወቃቸው ብቻ አይደለም። በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች እየተባባሱ በሄዱ መጠን ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች ሌላም የሚያሳስባቸው ነገር ገጥሟቸዋል።

መከራ የሚደርስብን ለምንድን ነው?

ሰዎች መከራ ሲያጋጥማቸው ብዙውን ጊዜ ይህ በእኔ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ቶሎ ወደ አእምሯቸው ይመጣል። ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘታችን የደረሰብንን መከራ ለመቋቋም የሚያስችል ስሜታዊ ጥንካሬ እንድናገኝ ይረዳናል። መከራ የደረሰበት ሰው አጥጋቢ መልስ ማግኘት ካልቻለ ግን ሥቃዩ ሊበረታበትና ሊማረር ይችላል። ለምሳሌ ያህል ቡሩኒ ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት።

አሁን በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ቡሩኒ የተባለች እናት እንዲህ ትላለች:- “ከጥቂት ዓመታት በፊት ሕፃን ልጄን በሞት አጣሁ። በአምላክ አምን ስለነበር መጽናኛ ለማግኘት በአካባቢው ወደሚገኘው ቄስ ሄድኩ። እሱም አምላክ ሱዛንን ወደ ሰማይ እንደወሰዳትና አሁን መልአክ መሆኗን ነገረኝ። በልጄ ሞት ምክንያት ሰማይ የተደፋብኝ ሆኖ የተሰማኝ ከመሆኑም በላይ ልጄን ከእኔ ነጥሎ በመውሰዱ አምላክንም ጠላሁት።” የቡሩኒ ሐዘን ለበርካታ ዓመታት ቀጠለ። “ከዚያም አንዲት የይሖዋ ምሥክር አምላክን የምጠላበት ምንም መሠረት እንደሌለኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየችኝ። ይሖዋ ሱዛንን ወደ ሰማይ እንዳልወሰዳትና መልአክም እንዳልሆነች ነገረችኝ። የታመመችው በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት ሲሆን አሁን በሞት አንቀላፍታ እንደምትገኝና ወደፊት ይሖዋ ከሞት እንደሚያስነሳት ተገነዘብኩ። ከዚህም በላይ አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ መሆኑንና ይህ ዓላማውም በቅርቡ እንደሚፈጸም ተማርኩ። ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ስገነዘብ ወደ እሱ ይበልጥ እየቀረብኩና ሐዘኔም እየቀነሰልኝ መጣ።”​—⁠መዝሙር 37:29፤ ሥራ 24:15፤ ሮሜ 5:12

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተለያየ መከራ ይደርስባቸዋል። በግለሰብ ደረጃ የሚደርስ አሳዛኝ ገጠመኝ፣ ጦርነት፣ ረሃብ ወይም የተፈጥሮ አደጋዎች ከእነዚህ መካከል ይገኙበታል። ቡሩኒ ለሚደርስብን መከራ ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነ፣ የሰው ልጅ እንዲሠቃይ ዓላማው እንዳልነበረና በቅርቡም ክፋት እንደሚወገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማረች በኋላ እፎይታ አግኝታለች። በአሁኑ ጊዜ ክፋት እየተባባሰ መምጣቱ ‘በመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ እንደምንኖር የሚያመለክት ማስረጃ ነው። ሁላችንም በጉጉት የምንጠባበቀው አስደሳች ለውጥ በቅርቡ ይመጣል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:7, 8

አምላክን በቅርብ ማወቅ

ሃንስና ቡሩኒ በአምላክ መኖር ያምኑ የነበረ ቢሆንም ስለ እርሱ የነበራቸው እውቀት ውስን ነበር። ሆኖም ጊዜ ወስደው ይሖዋን በደንብ ለማወቅ ጥረት ማድረጋቸው የሚክስ ሆኖ አግኝተውታል። በጊዜያችን ለሚነሱት በጣም አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ችለዋል። ይህም የአእምሮ ሰላምና ለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ አስገኝቶላቸዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ተሞክሮ አላቸው።

ይሖዋን በቅርበት ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቅ ማጥናት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋና እሱ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ይነግረናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንዶች ያደረጉት ይህንኑ ነበር። ታሪክ ጸሐፊና ሐኪም የነበረው ሉቃስ በግሪክ፣ ቤሪያ ስለነበሩ የአይሁድ ጉባኤ አባላት ሲጽፍ “ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” ብሏል።​—⁠ሥራ 17:10, 11

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በጉባኤ አንድ ላይ ይሰበሰቡ ነበር። (ሥራ 2:41, 42, 46፤ 1 ቆሮንቶስ 1:1, 2፤ ገላትያ 1:1, 2፤ 2 ተሰሎንቄ 1:1) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡና እሱን በማገልገል ደስታ እንዲያገኙ ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ የጉባኤ ስብሰባዎች አሏቸው። ከምሥክሮቹ ጋር መሰብሰብ ሌላም ጥቅም አለው። የሰው ልጆች የሚያመልኩትን አምላክ ባሕርያት ቀስ በቀስ ማንጸባረቃቸው ስለማይቀር የይሖዋ ምሥክሮችም በተወሰነ መንገድ ቢሆንም የይሖዋን ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። በመሆኑም ከምሥክሮቹ ጋር መሰብሰብ ይሖዋን የበለጠ እንድናውቀው ይረዳናል።​—⁠ዕብራውያን 10:24, 25

አምላክን ለማወቅ ይህን ያህል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው? አዎን፣ አስፈላጊ ነው። ጥረት ሳታደርግ በሕይወትህ ውስጥ የሚያስፈልጉህን ነገሮች ማግኘት ትችላለህን? አንድ ታዋቂ አትሌት ውጤታማ ለመሆን ምን ያህል ልምምድ እንደሚያደርግ አስብ። በበረዶ ላይ በሚደረገው የሸርተቴ ውድድር የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ፈረንሳዊው ዣን ክሎድ ኪሊ በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሥልጠናውን መጀመር የሚኖርባችሁ ከአሥር ዓመት በፊት ሲሆን በየዕለቱ ስለ ውድድሩ ታስባላችሁ። . . . ዓመቱን ሙሉ አእምሮንና አካልን ማዘጋጀት የሚጠይቅ ፕሮጀክት ነው።” ይህ ሁሉ ጥረትና ጊዜ የሚውለው በአሥር ደቂቃ ውስጥ ለሚጠናቀቅ ውድድር ነው! ይሖዋን በቅርብ ማወቅ ግን ከዚህ የላቀና ዘለቄታዊ ጥቅም ያስገኛል።

በየጊዜው እየጠበቀ የሚሄድ ወዳጅነት

በሕይወቱ ውስጥ አንድ ጠቃሚ ነገር እንዲቀርበት የሚፈልግ ማን አለ? ማንም አይፈልግም። እንግዲያው ሕይወትህ እውነተኛ ዓላማ እንደሌለው ሆኖ ከተሰማህ ወይም መከራ የሚደርስብን ለምን እንደሆነ ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን አምላክ ማለትም ይሖዋን ለማወቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ስለ እሱ መማርህ ሕይወትህን ለዘላለም በተሻለ መንገድ እንድትመራ ያስችልሃል።

ስለ ይሖዋ መማራችንን የምናቆምበት ጊዜ ይኖር ይሆን? አምላክን ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉት የቆዩ ሰዎች ሰለ እርሱ በተማሯቸውና አሁንም በሚማሯቸው አዳዲስ ነገሮች ይገረማሉ። ስለ እርሱ ብዙ ነገሮችን መማራችን ደስተኛ እንድንሆንና ወደ እርሱ የበለጠ እንድንቀርብ ያደርገናል። እኛም እንደሚከተለው ብሎ የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን ዓይነት አመለካከት የምናስተጋባ እንሁን:- “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፣ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር?”​—⁠ሮሜ 11:33,34

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዛሬም ቢሆን ሰዎች ‘የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? መጨረሻችንስ ምን ይሆን? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ በማለት ይጠይቃሉ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ግንዛቤ እያገኘሁ ስሄድ ወደ እሱ ይበልጥ ቀረብሁ”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በሕይወት ውስጥ ይሖዋን ከማገልገል የተሻለ ምንም ነገር የለም። ማንኛውም ነገር ከዚህ ጋር ሊወዳደር አይችልም። ይሖዋን ማወቄ ዓላማ ያለው ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል”