በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”

“አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”

“አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”

በአይሁዳውያን አቆጣጠር ኒሳን 14 ኢየሱስ በሞት አንቀላፋ፤ ይህ ቀን የጀመረው ሐሙስ መጋቢት 31, 33 እዘአ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነበር። በዚያን ዕለት ምሽት ኢየሱስ እና ሐዋርያቱ የማለፍን በዓል ለማክበር ኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ደርብ ላይ ተሰባስበዋል። ኢየሱስ “ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት” ሲቃረብ ሐዋርያቱን እስከ መጨረሻው እንደሚወዳቸው አሳይቷል። (ዮሐንስ 13:1) ይህን ያደረገው እንዴት ነው? ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሁኔታ የሚያዘጋጃቸው ግሩም ትምህርት በመስጠት ነው።

ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” አላቸው። (ዮሐንስ 16:33) ኢየሱስ ድፍረት በተሞላበት በዚህ አባባሉ ሊያስተላልፍ የፈለገው ሐሳብ ምን ነበር? እንዲህ ማለቱ ሊሆን ይችላል:- ‘በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው ክፋት ምሬት እንዲያድርብኝም ሆነ አጸፋውን ለመመለስ እንድነሳሳ አላደረገኝም። ዓለም በራሱ መንገድ እንዲቀርጸኝ አልፈቀድኩም። እናንተም እንደዚሁ ማድረግ ትችላላችሁ።’ ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ ሰዓታት ለታማኝ ሐዋርያቱ የሰጣቸው ትምህርት እነርሱም ዓለምን እንዲያሸንፉ ይረዳቸዋል።

ዛሬም በዓለም ላይ ክፋት በጣም ተስፋፍቶ ይገኛል። የፍትሕ መጓደልና ጭፍን የሆነ የኃይል ድርጊት ሲፈጸም ስንመለከት ምን ይሰማናል? እነዚህ ድርጊቶች የጥላቻ ስሜት እንዲያድርብን ወይም አጸፋውን ለመመለስ እንድንነሳሳ ያደርጉናል? በዙሪያችን የሚታየው የሥነ ምግባር ውድቀትስ ምን ተጽዕኖ እያሳደረብን ነው? በዚህ ላይ ደግሞ ሰብዓዊ አለፍጽምናችንና ኃጢአተኛ ዝንባሌያችን የሚያሳድሩብን ተጽዕኖ አለ። በመሆኑም በአንድ በኩል በውጭ ካለው ክፉ ዓለም ጋር በሌላ በኩል ደግሞ በውስጣችን ካለው መጥፎ ዝንባሌ ጋር መዋጋት ይኖርብናል። የአምላክን ድጋፍ ሳናገኝ በዚህ ውጊያ አሸናፊ መሆን እንችላለን? የአምላክን እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ሥጋዊ ዝንባሌዎቻችንን ለማሸነፍ የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ይኖርብናል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን በጣም ለሚወዳቸው ደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን ትምህርት እንመልከት።

ኩራትን በትሕትና ማሸነፍ

ኩራትን ወይም ትዕቢትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ድክመት ሲናገር “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” ይላል። (ምሳሌ 16:18) ቅዱሳን ጽሑፎች “አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና” የሚል ምክርም ይሰጡናል። (ገላትያ 6:3) በእርግጥም ኩራት አጥፊና አታላይ ነው። “ትዕቢትንና እብሪትን” መጥላታችን የጥበብ ጎዳና ነው።​—⁠ምሳሌ 8:13

የኢየሱስ ሐዋርያት በዚህ ረገድ ድክመት ነበረባቸውን? ቢያንስ በአንድ ወቅት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚል ተከራክረዋል። (ማርቆስ 9:33-37) በሌላ ጊዜ ደግሞ ያዕቆብና ዮሐንስ በመንግሥቱ ከሁሉ የተሻለውን ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። (ማርቆስ 10:35-45) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ይህንን ዝንባሌ እንዲያስወግዱ ሊረዳቸው ፈለገ። ስለዚህ የማለፍ በዓልን ማዕድ እየተመገቡ ሳለ ከመቀመጫው ተነሳና ማበሻ ጨርቅ ታጥቆ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ ጀመረ። ከዚያም ሊያስጨብጣቸው የፈለገውን ትምህርት እንዲህ በማለት በግልጽ ነገራቸው:- “እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል።” (ዮሐንስ 13:14) ኩራት ተቃራኒው በሆነው በትሕትና ሊተካ ይገባል።

ሆኖም ኩራት በቀላሉ የሚለቅ ባሕርይ አይደለም። ኢየሱስ ሊክደው ያሴረውን የአስቆሮቱ ይሁዳን ካሰናበተው በኋላ በዚያው ምሽት በአሥራ አንዱ ሐዋርያት መካከል የጦፈ ክርክር ተነሣ። ያጨቃጨቃቸው ጉዳይ ምን ነበር? ከመካከላቸው ታላቅ ማን ነው የሚለው ነበር! ኢየሱስ በዚህ ድርጊታቸው አልተቆጣቸውም፤ ከዚያ ይልቅ ሌሎችን የማገልገልን አስፈላጊነት እንደገና በትዕግሥት አስረዳቸው። እንዲህ አላቸው:- “የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፣ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፣ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን።” ኢየሱስ ቀደም ሲል የተወላቸውን ምሳሌ በማስታወስ “እኔ . . . በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ” አላቸው።​—⁠ሉቃስ 22:24-27

ሐዋርያቱ ነጥቡ ገብቷቸው ይሆን? ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ነጥቡን ተረድተውታል። ከዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8) እኛም ኩራትን በትሕትና ማሸነፋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ታዋቂነትን፣ ሥልጣንን ወይም ክብርን በማሳደድ እንዳንጠመድ መጠንቀቃችን የጥበብ አካሄድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል። (ያዕቆብ 4:6) በተመሳሳይም አንድ ጥንታዊ ምሳሌ “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው” ይላል።​—⁠ምሳሌ 22:4

ጥላቻን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው ሌላው ባሕርይ ጥላቻ ነው። የጥላቻ መነሾ ፍርሃት፣ የእውቀት ማነስ፣ ጭቆና፣ የፍትሕ መጓደል፣ ብሔራዊ ስሜት፣ ጐሰኝነት ወይም ዘረኝነት ሊሆን ይችላል። መንስኤው ምንም ይሁን ምን ጥላቻ በመላው ዓለም ነግሷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) በኢየሱስ ዘመንም ጥላቻ ተስፋፍቶ ነበር። ቀረጥ ሰብሳቢዎች በአይሁድ ሕብረተሰብ ዘንድ የተጠሉ ነበሩ። አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። (ዮሐንስ 4:9) አሕዛብም በአይሁዶች ዘንድ የተናቁ ነበሩ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ያቋቋመው አምልኮ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን የሚያቅፍ ነበር። (ሥራ 10:34, 35፤ ገላትያ 3:28) በመሆኑም ኢየሱስ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ አንድ አዲስ ትምህርት ሰጣቸው።

ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።” ቀጥሎም “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ስላላቸው ይህን ፍቅር ማሳየትን መማር ነበረባቸው። (ዮሐንስ 13:34, 35) ይህ ትእዛዝ አዲስ የተባለው “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ከሚለው ሕግ የበለጠ ስፋት ያለው በመሆኑ ነው። (ዘሌዋውያን 19:18) እንዴት? ኢየሱስ ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እንዲህ አለ:- “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” (ዮሐንስ 15:12, 13) አንዳቸው ለሌላውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች የገዛ ሕይወታቸውን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን ነበረባቸው።

ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሥር የሰደደ ጥላቻን ማስወገድ የሚችሉት እንዴት ነው? የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር በማዳበር ነው። የተለያየ ዘር፣ ባህል፣ ሃይማኖት እና የፖለቲካ አመለካከት የነበራቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ሰዎች ጥላቻን አስወግደዋል። በአሁኑ ወቅት፣ ጥላቻን ድል ባደረገው አንድነት ያለው ዓለም አቀፋዊ የይሖዋ ምሥክሮች የወንድማማች ማህበር ውስጥ ታቅፈዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸውን የሚከተሉትን ቃላት ተግባራዊ ያደርጋሉ:- “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።” (1 ዮሐንስ 3:15) እውነተኛ ክርስቲያኖች በጦርነት የማይሳተፉ ከመሆኑም በላይ አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

ይሁን እንጂ የእምነት ባልንጀሮቻችን ላልሆኑትና ለሚጠሉን ሰዎችስ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ኢየሱስ ተሰቅሎ እያለ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ስለሰቀሉት ሰዎች ጸልዮአል። (ሉቃስ 23:34) ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ከባድ የጥላቻ ስሜት ባደረባቸው ሰዎች በድንጋይ ተወግሮ ሊሞት ሲል “ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው” ብሎ ነበር። (ሥራ 7:60) ኢየሱስና እስጢፋኖስ ለጠላቶቻቸውም እንኳ መልካም ምኞት ነበራቸው። በልባቸው የጥላቻ ስሜት አላሳደሩም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ” በማለት ይመክረናል።​—⁠ገላትያ 6:10

‘የዘላለም ረዳት’

ኢየሱስ ከ11 ታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ በቅርቡ እንደሚለያቸው ነገራቸው። (ዮሐንስ 14:28፤ 16:28) ሆኖም “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ [“ረዳት”፣ NW ] ይሰጣችኋል” በማለት አበረታታቸው። (ዮሐንስ 14:16) ኢየሱስ እልክላችኋለሁ ያላቸው ረዳት መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ የቅዱሳን ጽሑፎችን ጥልቅ ነገር ያስተምራቸዋል፤ እንዲሁም ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ያስተማራቸውን ነገር ያስታውሳቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 14:26

በዛሬው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በመንፈሱ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ አለን። ትንቢቶችን የተናገሩትና መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች ይህን ያደረጉት “በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው” ነበር። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) ቅዱሳን ጽሑፎችን ማጥናታችንና የተማርነውን ተግባራዊ ማድረጋችን እውቀት፣ ጥበብ፣ ማስተዋል እንዲሁም የማመዛዘን እና የማሰብ ችሎታ እንድናገኝ ያደርገናል። ይህ የክፉውን ዓለም ተጽዕኖዎች ለመቋቋም የበለጠ አያስታጥቀንምን?

መንፈስ ቅዱስ በሌላም መንገድ ይረዳናል። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ አምላካዊ ባሕርያትን እንድናዳብር የሚገፋፋ በጎ ኃይል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የመንፈስ ፍሬ . . . ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው” ይላል። የሥነ ምግባር ብልግናን፣ ክርክርን፣ ቅንዓትን፣ ቁጣንና የመሳሰሉትን የሥጋ ምኞቶች ለማሸነፍ የሚያስፈልጉን እንደነዚህ ዓይነት ባሕርያት አይደሉምን?​—⁠ገላትያ 5:19-23

በአምላክ መንፈስ በመታመን ማንኛውንም አስቸጋሪ ወይም አስጨናቂ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችለንን “እጅግ ታላቅ ኃይል” ማግኘትም እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 4:7 አ.መ.ት ) መንፈስ ቅዱስ መከራዎችንና ፈተናዎችን ባያስወግድልንም በጽናት እንድናሳልፋቸው ኃይል ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ሐዋርያው ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:13 አ.መ.ት ) አምላክ እንደዚህ ያለውን ኃይል የሚሰጠው በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! ‘ኢየሱስን ለሚወዱትና ትእዛዙን ለሚጠብቁ’ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 14:15

“በፍቅሬ ኑሩ”

ኢየሱስ ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸውም ነበር:- “ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል።” (ዮሐንስ 14:21) ከዚያም “በፍቅሬ ኑሩ” ሲል አጥብቆ መክሯቸዋል። (ዮሐንስ 15:9) በአብ እና በወልድ ፍቅር መኖራችን በውስጣችን ካለው ኃጢአተኛ ዝንባሌና በውጪ ካለው ክፉ ዓለም ጋር በምናደርገው ፍልሚያ አሸናፊዎች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

የኃጢአት ዝንባሌዎችን ለመዋጋት የሚያስፈልገው ጠንካራ ውስጣዊ ግፊት ሳይኖረን በትግሉ አሸናፊዎች መሆን እንችላለን? ከይሖዋ አምላክና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ካለን ፍላጎት የተሻለ ምን ጠንካራ ግፊት ሊኖር ይችላል? ከአሥራዎቹ ዕድሜው ጀምሮ ሥነ ምግባር በጎደለው መንገድ ይኖር የነበረ ኤርኔስቶ a የተባለ ወጣት ሕይወቱን ለመለወጥ ስላደረገው ከፍተኛ ትግል እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አምላክን የማስደሰት ፍላጎት ነበረኝ፤ ሆኖም አኗኗሬ እንደማያስደስተው ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርኩ። ስለዚህ አኗኗሬን አስተካክዬ በአምላክ መመሪያዎች መሠረት ለመኖር ወሰንኩ። በየዕለቱ በአእምሮዬ እየተመላለሱ የሚያስቸግሩኝን የብልግና ሐሳቦች መዋጋት ነበረብኝ። ሆኖም በውጊያው ለማሸነፍ ቆርጬ የነበረ ከመሆኑም በላይ አምላክ እንዲረዳኝ ያለማቋረጥ እጸልይ ነበር። ከሁለት ዓመታት በኋላ ከባዱን ትግል አሸነፍኩ፤ እርግጥ አሁንም የተሳሳተ እርምጃ እንዳልወስድ በጣም እጠነቀቃለሁ።”

ከዓለም ጋር የምናደርገውን ውጊያ በተመለከተ ኢየሱስ ደርብ ላይ ካለው ክፍል ከመውጣታቸው በፊት ያቀረበውን የመደምደሚያ ጸሎት ተመልከት። ስለ ደቀ መዛሙርቱ ወደ አባቱ የሚከተለውን ልመና አቀረበ:- “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።” (ዮሐንስ 17:15, 16) እንዴት የሚያበረታታ ሐሳብ ነው! ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች ይጠብቃቸዋል፤ ከዓለም ለመለየት በሚያደርጉት ጥረትም ያበረታቸዋል።

“እመኑ”

የኢየሱስን ትእዛዛት የምናከብር ከሆነ ከክፉው ዓለምና ከራሳችን ኃጢአተኛ ዝንባሌ ጋር የምናደርገውን ውጊያ በአሸናፊነት መወጣት እንችላለን። በውጊያው አሸናፊ መሆናችን ወሳኝ ቢሆንም እንኳ ዓለምንም ሆነ የወረስነውን ኃጢአት አያስወግደውም። ያም ቢሆን ግን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም።

መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:17) ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ” ከሞትና ከኃጢአት እንዲድን ሲል ሕይወቱን ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16) ስለ አምላክ ፈቃድና ስለ ዓላማዎቹ ያለን እውቀት እያደገ ሲሄድ “በእግዚአብሔር እመኑ፣ በእኔም ደግሞ እመኑ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ተግባራዊ እናድርግ።​—⁠ዮሐንስ 14:1

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሙ ተለውጧል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሐዋርያቱን “በፍቅሬ ኑሩ” በማለት አሳስቧቸዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቅርቡ ከኃጢአትና ኃጢአት ከሚያስከትላቸው መዘዞች ነፃ እንወጣለን