በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች”

“የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች”

“የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች”

ትንሽ እሳት አንድን ደን ሙሉ በሙሉ ሊያወድም እንደሚችል ሁሉ ይህ ትንሽ ብልትም የአንድን ሰው መላ ሕይወት ሊያበላሽ ይችላል። መርዝ ሊያመነጭ አሊያም “የሕይወት ዛፍ” ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 15:4) ሞትና ሕይወት በእጁ ናቸው። (ምሳሌ 18:21) ይህ ትንሽ የሰውነት አካል ማለትም አንደበት፣ መላውን ሰውነት ሊያጎድፍ ይችላል። (ያዕቆብ 3:5-9) በመሆኑም አንደበታችንን መቆጣጠራችን ጥበብ ይሆናል።

የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የምሳሌ መጽሐፍ 12ኛ ምዕራፍ ሁለተኛ ክፍል ላይ አንደበታችንን በአግባቡ እንድንጠቀም የሚያበረታታ ጠቃሚ ምክር ሰጥቷል። ጠቢቡ ንጉሥ እጥር ምጥን ያሉ ሆኖም ከፍተኛ ትርጉም ያዘሉ ምሳሌዎችን በመጠቀም ከአንደበታችን የሚወጣው ቃል ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሊሆን እንደሚችልና የአንድን ሰው ማንነት ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ አመልክቷል። ሰሎሞን በመንፈስ አነሳሽነት የሰጠው ምክር ‘ለከንፈሮቹ መዝጊያ ለማድረግ’ ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።​—⁠መዝሙር 141:3

‘ወጥመድ የሚሆን ኃጢአት’

ሰሎሞን “ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፤ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል” ብሏል። (ምሳሌ 12:13) ውሸት የከንፈር ኃጢአት ነው። በመሆኑም ለሚዋሽ ሰው ወደ ሞት የሚመራ ወጥመድ ሊሆንበት ይችላል። (ራእይ 21:8) ከቅጣት ወይም ከአንድ አሳፋሪ ሁኔታ ለማምለጥ ቀላሉ መንገድ መዋሸት ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ውሸት አብዛኛውን ጊዜ ተጨማሪ ውሸቶችን ይወልድ የለምን? ሁኔታው ትንሽ ገንዘብ እያስያዘ ቁማር መጫወት ከጀመረ ሰው ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህ ሰው የተበላውን ገንዘብ ለማስመለስ በሚያደርገው ጥረት ቀስ በቀስ ከፍ ያለ ገንዘብ አስይዞ መወራረድ እንደሚጀምር ሁሉ ውሸታም ሰውም ሳያስበው በውሸት ተተብትቦ ይያዛል።

ውሸት ወጥመድ የሚሆንበት ሌላም መንገድ አለ፤ ውሸታም ሰው ውሎ አድሮ ራሱንም መዋሸት ሊጀምር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ውሸታም ሰው በጣም የተማረና አዋቂ እንደሆነ አድርጎ ሊያስብ ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ያለው እውቀት ትንሽ ይሆናል። በመሆኑም ውሸቱን እውነት ለማስመሰል ሲል የውሸት ሕይወት መምራት ይጀምራል። “በአንደበቱ ሸንግሎአልና፤ ኃጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል” የሚለው አባባል ይደርስበታል። (መዝሙር 36:2) በእርግጥም ውሸት እንዴት ያለ ወጥመድ ነው! በሌላ በኩል ግን ጻድቅ ሰው እንደዚህ ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አይገባም። በመከራ ውስጥ እያለ ቢሆንም እንኳ አይዋሽም።

‘የሚያጠግብ ፍሬ’

ሐዋርያው ጳውሎስ “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” በማለት አስጠንቅቋል። (ገላትያ 6:7) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ንግግራችንንም ሆነ ድርጊታችንን እንደሚመለከት ግልጽ ነው። ሰሎሞን እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፣ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል።”​—⁠ምሳሌ 12:14

‘ጥበብን የሚናገር’ አፍ የሚያጠግብ ፍሬ ያፈራል። (መዝሙር 37:30 አ.መ.ት ) ጥበብ በእውቀት ላይ የተመካ ነው፤ የእውቀት ሁሉ ምንጭ የሆነ ሰው ደግሞ የለም። በመሆኑም ሁሉም ሰው ምክርን መስማትና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልገዋል። የእስራኤል ንጉሥ “የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል” ብሏል።​—⁠ምሳሌ 12:15

ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ ይኸውም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች አማካኝነት ጠቃሚ ምክር ይሰጠናል። (ማቴዎስ 24:45፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) የሚሰጠንን መልካም ምክር ችላ ብለን በራሳችን አመለካከት ብንመራ እንዴት ያለ ሞኝነት ይሆናል! “ለሰው እውቀትን የሚያስተምረው” ይሖዋ አምላክ በመገናኛ መሥመሩ በኩል የሚሰጠንን ምክር ‘ለመስማት የፈጠንን’ ልንሆን ይገባል።​—⁠መዝሙር 94:10፤ ያዕቆብ 1:19

ጥበበኛ ሰውና ሰነፍ ሰው ዘለፋ ወይም መሠረተ ቢስ ትችት ሲሰነዘርባቸው ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው? ሰሎሞን እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል፦ “የሰነፍ ቁጣ ቶሎ ይታወቃል፤ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል።”​—⁠ምሳሌ 12:16

ሰነፍ ሰው ትችት ሲሰነዘርበት በቁጣ “ቶሎ” ምላሽ ይሰጣል። አስተዋይ ሰው ግን ራሱን መግዛት እንዲችል አምላክ መንፈሱን እንዲሰጠው ይጸልያል። በአምላክ ቃል ውስጥ በሰፈረው ምክር ላይ ጊዜ ወስዶ ያሰላስላል፤ እንዲሁም “ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ያስባል። (ማቴዎስ 5:39) ብልህ ሰው ‘ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን መመለስ’ ስለማይፈልግ እንዳመጣለት ላለመናገር ይጠነቀቃል። (ሮሜ 12:17) እኛም በተመሳሳይ የሚሰነዘርብንን ማንኛውንም ነቀፋ ችለን በማሳለፍ ተጨማሪ ውዝግብ እንዳይፈጠር ማድረግ እንችላለን።

‘ፈውስ የሚያስገኝ ምላስ’

ውሸት በፍርድ ጉዳይ ረገድ ከፍተኛ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል። የእስራኤል ንጉሥ “እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፤ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል” ብሏል። (ምሳሌ 12:17) ሐቀኛ ምሥክር እውነተኛ ነገር ስለሚናገር የሚሰጠው ቃል አስተማማኝና እምነት የሚጣልበት ነው። የሚሰጠው ምሥክርነት ፍትሕ እንዲፈጸም አስተዋጽኦ ያደርጋል። ሐሰተኛ ምሥክር ግን በተንኮል ስለሚናገር ፍትሕ እንዲጓደል ያደርጋል።

በመቀጠልም ሰሎሞን “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው [“ፈውስን ያመጣል፣” አ.መ.ት ]” ብሏል። (ምሳሌ 12:18) ቃላት እንደ ሰይፍ በመውጋት ወዳጅነትን ሊያበላሹና ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ። ወይም ደግሞ አስደሳችና ማራኪ በመሆን ወዳጅነትን ሊያጠናክሩ ይችላሉ። ደግሞስ ማንቋሸሽ፣ መጮህ፣ መተቸትና ማዋረድ ከባድ ስሜታዊ ቁስል የሚያስከትል ሰይፍ አይደለምን? አምልጦን ተገቢ ያልሆነ ነገር ብንናገር እንኳ ከልብ ይቅርታ በመጠየቅ ፈዋሽ ቃላት መናገራችን ምንኛ መልካም ነው!

የምንኖርበት ጊዜ አስቸጋሪ በመሆኑ ብዙዎች ‘ልባቸውና መንፈሳቸው የተሰበረ’ መሆኑ ምንም አያስገርምም። (መዝሙር 34:18) ‘የተጨነቁትን ነፍሳት ስናጽናና እና ደካሞችን ስንረዳ’ አንደበታችንን ፈዋሽ በሆነ መንገድ መጠቀማችን አይደለም? (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW ) በእርግጥም በርኅራኄ የተነገሩ ቃላት ጎጂ ከሆነ የእኩዮች ተጽዕኖ ጋር ለሚታገሉ ወጣቶች የብርታት ምንጭ ይሆኑላቸዋል። በዕድሜ የገፉትን አሳቢነት በተሞላበት መንገድ ስናነጋግራቸው ተፈላጊና ተወዳጅ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል። የታመሙ ሰዎች በደግነት ስናነጋግራቸው እንደሚደሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም። ሌላው ቀርቶ ምክር “በየውሃት መንፈስ” ሲሰጥ ለመቀበል ቀላል ይሆናል። (ገላትያ 6:1) ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች የሚናገር አንደበትም ከፍተኛ የመፈወስ ኃይል እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም!

‘ለዘላለም የሚኖር ከንፈር’

ሰሎሞን “ከንፈር” እና “ምላስ” የሚሉትን ቃላት ተመሳሳይ እንደሆኑ አድርጎ በመጠቀም እንዲህ ይላል፦ “የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች፤ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው።” (ምሳሌ 12:19) “የእውነት ከንፈር” የሚለው ሐረግ በዕብራይስጥ በነጠላ ቁጥር የተቀመጠ ሲሆን እውነትን ከመናገር የበለጠ ጥልቅ ትርጉም አለው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “የማይለወጥ፣ ቋሚ እንዲሁም አስተማማኝ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል” ሲል ገልጿል። “እንደዚህ ዓይነቱ ንግግር . . . እምነት የሚጣልበት በመሆኑ ለዘላለም ይጸናል፤ በተቃራኒው ውሸተኛ ምላስ . . . ለጊዜው ሊያታልል ቢችልም ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመው አይጸናም።”

ጠቢቡ ንጉሥ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፤ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው። ጻድቅን መከራ አያገኘውም፤ ኀጥኣን ግን ክፋትን [“በመከራ፣” አ.መ.ት ] የተሞሉ ናቸው።”​—⁠ምሳሌ 12:20, 21

ተንኰል የሚሸርቡ ሰዎች ትርፋቸው ሥቃይና መከራ ብቻ ነው። ሰላምን የሚመክሩ ሰዎች ግን ትክክል የሆነውን በማድረጋቸው እርካታ ያገኛሉ። እንዲሁም መልካም ፍሬ በማፍራታቸው ይደሰታሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአምላክን ሞገስ ያገኛሉ፤ ምክንያቱም “ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።”​—⁠ምሳሌ 12:22

‘እውቀትን የሚሸሽግ አንደበት’

የእስራኤል ንጉሥ አንደበቱን በአግባቡ በሚጠቀምና በማይጠቀም ሰው መካከል ያለውን ልዩነት መናገሩን በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፤ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል።”​—⁠ምሳሌ 12:23

ብልህ ወይም አስተዋይ የሆነ ሰው መቼ መናገርና መቼ ዝም ማለት እንደሚገባው ያውቃል። አዋቂ መሆኑን ለማሳየት ጉራውን ከመንዛት በመቆጠብ እውቀትን ይሸሽጋል። እንዲህ ሲባል ግን ሁልጊዜ እውቀቱን ይሸሽጋል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እውቀቱን መቼ መግለጥ እንዳለበት ያውቃል። ከዚህ በተቃራኒ ሰነፍ ሰው ለመናገር ችኩል በመሆኑ ስንፍናው በቀላሉ ይታወቃል። እንግዲያው በንግግራችን ቁጥብ በመሆን በጉራ ከመናገር እንራቅ።

ሰሎሞን ንጽጽሩን በመቀጠል በትጉህና በሰነፍ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ድንቅ ነጥብ ይናገራል። እንዲህ ብሏል፦ “የትጉ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች።” (ምሳሌ 12:24) ጠንክሮ መሥራት እድገት ለማግኘትና ራስን ችሎ ለመኖር ይረዳል፤ ስንፍና ግን ወደ ባርነት ይመራል። አንድ ምሁር እንደተናገሩት “በጊዜ ሂደት ሰነፍ ሰው የትጉህ ሰው ባሪያ ይሆናል።”

‘ደስ የሚያሰኝ ቃል’

ንጉሥ ሰሎሞን ስለ ሰው ተፈጥሮ በሚገባ ያጤነውን በመጥቀስ እንደገና ስለ ንግግር ያወሳል። “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” በማለት ተናግሯል።​—⁠ምሳሌ 12:25

ልብ በኀዘን እንዲደቆስ የሚያደርጉ በርካታ ሐሳቦችና ጭንቀቶች አሉ። አሳቢ የሆነ ሰው የሚሰነዝራቸው የማበረታቻ ቃላት ሸክሙን ለማቃለልና ልብ በደስታ እንዲሞላ ለማድረግ ይረዳሉ። ሆኖም በልባችን ያለውን ጭንቀት አውጥተን ካልተናገርን ሌሎች ምን ያህል እንደተጨነቅን እንዴት ማወቅ ይችላሉ? አዎን፣ መከራ ወይም የመንፈስ ጭንቀት ሲያጋጥመን ራሱን በእኛ ቦታ አስቀምጦ ሊረዳን ለሚችል ሰው ጭንቀታችንን ልናዋየው ይገባል። ከዚህም በላይ ስሜታችንን አውጥተን መናገራችን በራሱ የልባችንን ሐዘን ያቀልልናል። እንግዲያው ጭንቀታችንን ለትዳር ጓደኛችን፣ ለወላጃችን ወይም አሳቢ ለሆነና ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ላለው ወዳጃችን ማካፈላችን ይጠቅመናል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የተሻለ የሚያበረታቱ ቃላት ከየት ማግኘት ይቻላል? በመሆኑም በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ ላይ በማሰላሰል ወደ አምላክ እንቅረብ። እንደዚህ ማድረጋችን በጭንቀት የተዋጠው ልባችን በደስታ እንዲሞላና ሐዘን የሚታይበት ዓይናችን እንዲያበራ ሊያደርግ ይችላል። መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ከዚህ ጋር የሚስማማ ሐሳብ ሰጥቷል፦ “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፣ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፣ ዓይንንም ያበራል።”​—⁠መዝሙር 19:7, 8

ወሮታ የሚያስገኝ ጎዳና

የእስራኤል ንጉሥ የቅኖችን አካሄድ ከክፉዎች አካሄድ ጋር በማነጻጸር እንዲህ ይላል፦ “ጻድቅ ለባልንጀራው መንገድን ያሳያል [“ውሎውን በጥንቃቄ ያጤናል፣” NW ]፤ የኀጥአን መንገድ ግን ታስታቸዋለች።” (ምሳሌ 12:26) ጻድቅ ሰው ውሎውን ማለትም አብሯቸው የሚውለውን ሰዎችና ባልንጀሮቹን በመምረጥ ረገድ ጠንቃቃ ነው። አደገኛ የሆነ ወዳጅነት ከመመሥረት በመራቅ ጓደኞቹን በጥበብ ይመርጣል። ክፉዎች ግን ምክርን ችላ ብለው በራሳቸው መንገድ በመሄድ ይስታሉ።

በመቀጠል ንጉሥ ሰሎሞን በሰነፍና በትጉህ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ከሌላ አቅጣጫ ያስቀምጠዋል፦ “ታካች ሰው አደን ምንም አያድንም፤ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው።” (ምሳሌ 12:27) ታካች ወይም “ሰነፍ ሰው” “አደን ምንም አያድንም” እንዲሁም አድኖ ያመጣውን “እንኳ አይጠብስም።” (አ.መ.ት ) በመሆኑም የጀመረውን ሥራ መጨረስ አይችልም። ትጋት ግን ሃብት እንደሆነ ተገልጿል።

ስንፍና በጣም ጎጂ ባሕርይ ከመሆኑ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩት ክርስቲያን ወንድሞቹ ደብዳቤ ለመጻፍ የተገደደ ከመሆኑም በላይ ሥራ ፈት ሆነው በሰው ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ‘ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን’ ማረም አስፈልጎት ነበር። እነዚህ ሰዎች በሌሎች ላይ ከባድ ሸክም ሆነዋል። በመሆኑም ጳውሎስ “በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ” በግልጽ መክሯቸዋል። ይህን ጠንካራ ምክር ካልተቀበሉ ደግሞ ሌሎቹ የጉባኤው አባላት ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ‘እንዲለዩ’ ማለትም በማኅበራዊ ጉዳዮች ከእነርሱ ጋር እንዳይቀራረቡ በጥብቅ አሳስቧቸዋል።​—⁠2 ተሰሎንቄ 3:6-12

ሰሎሞን ትጋትን በተመለከተ የሰጠውን ምክር ብቻ ሳይሆን አንደበታችንን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ የሰጠውን ማሳሰቢያም ልብ ልንል ይገባል። ይህንን ትንሽ የሰውነት ክፍል ፈውስና ደስታ በሚያመጣ መንገድ ለመጠቀምና ውሸትን አስወግደን ቀና መንገድን ለመከተል እንጣር። ሰሎሞን የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ በጎዳናዋም ሞት የለም።”​—⁠ምሳሌ 12:28

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ጠቢብ ምክርን ይሰማል’

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የጠቢባን ምላስ . . . ጤና ነው”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እምነት ለምንጥልበት ወዳጃችን ስሜታችንን ማካፈላችን መጽናኛ ሊያስገኝልን ይችላል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ ቃል ላይ በአድናቆት ማሰላሰል ልብን በደስታ ይሞላል