በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውሳኔ ማድረግ—ልንሸሸው የማንችለው ፈተና

ውሳኔ ማድረግ—ልንሸሸው የማንችለው ፈተና

ውሳኔ ማድረግ—ልንሸሸው የማንችለው ፈተና

በ19ኛው መቶ ዘመን የፈረንሳይ ንጉሥ የነበረው ናፖሊዮን ቦናፓርት በአንድ ወቅት “ውሳኔ የማድረግን ያህል ከባድና ውድ የሆነ መብት የለም” ብሎ ነበር። በዚህ አባባል ሳትስማማ አትቀርም። ምክንያቱም ሰዎች ስንባል የራሳችንን ሕይወት በራሳችን መምራትን እንደ ውድ መብት አድርገን እንመለከተዋለን። ሆኖም አብዛኞቻችን ውሳኔ ማድረግ ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነም እንገነዘባለን።

ቀላልም ይሁን ከባድ ውሳኔ ማድረግ ልንሸሸው የማንችለው ጉዳይ ነው። በየዕለቱ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ የተለያዩ ጉዳዮች ያጋጥሙናል። ጠዋት ከመኝታችን ከምንነሳበት ጊዜ ጀምሮ ምን እንደምንለብስ፣ ቁርሳችንን ምን እንደምንበላ እንዲሁም በቀኑ ውስጥ የሚያጋጥሙንን ሌሎች ነገሮችም እንዴት እንደምንወጣ መወሰን ይኖርብናል። ከእነዚህ ውሳኔዎች ውስጥ አብዛኞቹ ያን ያህል ከባድ ስላልሆኑ ብዙም ማሰብ አይጠይቁብንም። እነዚህን ውሳኔዎች ካደረግን በኋላ ውሳኔዬ ትክክል ነበር ወይስ የተሳሳተ ብለን አንጨነቅም።

በሌላ በኩል ግን አንዳንድ ውሳኔዎች በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ናቸው። በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ወጣቶች ወደፊት የሚሰማሩበትን የሥራ መስክ በተመለከተ፣ ምን ዓይነት ትምህርት መማር እንዳለባቸውና እስከምን ድረስ በትምህርታቸው መግፋት እንዳለባቸው ከወዲሁ መወሰን ይኖርባቸው ይሆናል። ውሎ አድሮ ደግሞ ብዙዎቹ ለማግባት ወይም በነጠላነት ለመቀጠል ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለማግባት የሚፈልጉ ከሆነ ‘በዕድሜም ሆነ በአስተሳሰብ በስያለሁ? የምፈልገው የትዳር ጓደኛ ምን ዓይነት ነው? ከሁሉም በላይ ደግሞ ምን ዓይነት የትዳር ጓደኛ ነው የሚያስፈልገኝ?’ እንደሚሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይገባቸዋል። የትዳር ጓደኛ ምርጫን ያህል በሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ውሳኔዎች በጣም ጥቂት ናቸው።

ከፍተኛ ቦታ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ረገድ ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ ማድረጉ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በሕይወት ውስጥ ደስተኛ መሆናችን በአብዛኛው የተመካው እንዲህ በማድረጋችን ላይ ነው። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን በማድረግ ረገድ የተካኑ ስለሆኑ የማንም እርዳታ እንደማያሻቸው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ተገቢ ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የምንመለከተው ይሆናል።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ናፖሊዮን:- From the book The Pictorial History of the World