በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእውቀት ላይ ራስን መግዛት ጨምሩ

በእውቀት ላይ ራስን መግዛት ጨምሩ

በእውቀት ላይ ራስን መግዛት ጨምሩ

“በእውቀትም ራስን መግዛት . . . ጨምሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:5-8

1. አብዛኞቹ የሰው ልጆች ችግሮች የሚመነጩት ምን ማለት ካለመቻል ነው?

 በዩናይትድ ስቴትስ አደገኛ ዕፅን በመቃወም በተደረገ ዘመቻ ላይ “እምቢ በል” የሚል ማሳሰቢያ ለወጣቶች ተላልፎ ነበር። ሁሉም ሰው አደገኛ ዕፅ መውሰድን ብቻ ሳይሆን ስካርን፣ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ አኗኗርን፣ በንግድ ሥራ ላይ ማጭበርበርንና ‘ለሥጋ ምኞቶች’ መገዛትን እምቢ ቢል ኖሮ ዓለማችን ምን ያህል የተሻለች ትሆን ነበር! (ሮሜ 13:14) ሆኖም እምቢ ማለት እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም ቢባል ማን ሊክድ ይችላል።

2. (ሀ) ክፉ እንድናደርግ የሚገፋፋንን ተጽዕኖ ማሸነፍ ቀላል እንዳልሆነ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ጥቀስ። (ለ) እነዚህ ምሳሌዎች ምን እንድናደርግ ሊያበረታቱን ይገባል?

2 የሰው ልጆች በሙሉ ፍጹማን ባለመሆናቸው የተነሳ ራስን መግዛት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ስለሆነም በዚህ ረገድ ያለብንን ትግል እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል ለመማር ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን ለማገልገል ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አንዳንድ ጊዜ ክፉ እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸውን ተጽዕኖ ማሸነፍ ስላልቻሉ ሰዎች ይናገራል። ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በመፈጸም ኃጢአት የሠራውን ዳዊትን ታስታውስ ይሆናል። እርሱ በሠራው ኃጢአት ምክንያት በዝሙት የተጸነሰው ልጅና የቤርሳቤህ ባል ሕይወታቸውን አጥተዋል። (2 ሳሙኤል 11:1-27፤ 12:15-18) ወይም ደግሞ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም” በማለት በግልጽ የተናገረውን ሐዋርያው ጳውሎስን አስታውስ። (ሮሜ 7:19) አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንደ እርሱ ይሰማሃል? ጳውሎስ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” (ሮሜ 7:22-24) እንደ እነዚህ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ራሳችንን ለመግዛት በምናደርገው ትግል ተስፋ ላለመቁረጥ ያለንን ቁርጠኝነት ሊያጠናክሩልን ይገባል።

ራስን መግዛት—ልናዳብረው የሚገባን ባሕርይ

3. ራስን የመግዛት ባሕርይን ማዳበር ቀላል የማይሆነው ለምን እንደሆነ ግለጽ።

3 መጥፎ ነገር እንድንፈጽም ለሚደረግብን ተጽዕኖ አለመንበርከክን የሚጨምረው ራስን መግዛት በ2 ጴጥሮስ 1:5-7 ላይ ከእምነት፣ ከበጎነት፣ ከእውቀት፣ ከጽናት፣ ለአምላክ ከማደር፣ ከወንድማማች መዋደድና ከፍቅር ጋር አብሮ ተጠቅሷል። ከእነዚህ ባሕርያት ውስጥ የትኛውም ቢሆን በተፈጥሮ የሚገኝ አይደለም። እያንዳንዳቸውን ልናዳብራቸው ይገባል። እነዚህን ባሕርያት በሚገባ ማንጸባረቅ ልባዊ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል። ታዲያ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር ቀላል ይሆንልናል ብለን መጠበቅ ይኖርብናል?

4. ብዙዎች ራስን በመግዛት ረገድ ችግር እንደሌለባቸው የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ይህስ ምን ይጠቁማል?

4 እርግጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ራስን በመግዛት ረገድ ችግር እንደሌለባቸው ይሰማቸው ይሆናል። አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ድርጊታቸው በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ ሳያገናዝቡ ፍጹም ባልሆነው ሥጋቸው ምኞት እየተነዱ ሕይወታቸውን እንዳሻቸው ይመራሉ። (ይሁዳ 10) ሰዎች ክፉ ነገር እንዲያደርጉ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ እምቢ ለማለት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ እንደሌላቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዘመናችን ጎልቶ ይታያል። ይህ ሁኔታ ጳውሎስ በትንቢት በተናገረለት ‘የመጨረሻው ቀን’ ውስጥ እንደምንኖር የሚጠቁም ነው። እንዲህ ብሎ ነበር:- ‘የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ ይሆናሉ’።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3

5. የይሖዋ ምሥክሮች ራስን መግዛትን መማር አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? የትኛውስ ምክር በጊዜያችንም ይሠራል?

5 የይሖዋ ምሥክሮች ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ይገነዘባሉ። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እነርሱም ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው እየኖሩ እርሱን ለማስደሰት ባላቸው ፍላጎትና ፍጹም ያልሆነው ሥጋቸው ክፉ ነገር እንዲያደርጉ በሚያሳድርባቸው ግፊት መካከል ከፍተኛ ትግል እንዳለ ያውቃሉ። ይህን ፍልሚያ በድል አድራጊነት መወጣት የሚችሉበትን መንገድ ለመማር ጥረት ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል። በ1916 የወጣ የዚህ መጽሔት እትም “ራሳችንን፣ አስተሳሰባችንን፣ አነጋገራችንንና ጠባያችንን በመቆጣጠር ረገድ ልንከተለው ስለሚገባን ተገቢ አካሄድ” ተናግሮ ነበር። መጽሔቱ ፊልጵስዩስ 4:8ን ልብ እንድንል ሐሳብ ያቀርባል። ይህ ጥቅስ የያዘው መለኮታዊ ምክር የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ የተሰጠ ቢሆንም በጊዜያችንም ይሠራል። ምናልባት በጊዜያችን ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ከጥንቱ ዘመን ወይም ከ1916 ይበልጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ክርስቲያኖች ለዓለማዊ ምኞቶች እንዲንበረከኩ ለሚደረግባቸው ተጽዕኖ ላለመሸነፍ ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ። ይህም ፈጣሪያቸውን እሺ ብለው ለመታዘዝ ያላቸውን ፈቃደኝነት እንደሚያሳይ ይገነዘባሉ።

6. ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማዳበር በምናደርገው ጥረት ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?

6 ራስን መግዛት በገላትያ 5:22, 23 ላይ “የመንፈስ ፍሬ” አንዱ ክፍል እንደሆነ ተጠቅሷል። ‘ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ እምነትንና የውሃትን’ እንደምናሳይ ሁሉ ራስን መግዛትንም የምናንጸባርቅ ከሆነ በእጅጉ እንጠቀማለን። እንዲህ ማድረጋችን ጴጥሮስ እንደገለጸው “ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች” ከመሆን ይጠብቀናል። (2 ጴጥሮስ 1:8) ይሁን እንጂ እነዚህን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ ለማንጸባረቅ ቶሎ ባይሳካልን ተስፋ ልንቆርጥ ወይም ራሳችንን ልንኮንን አይገባም። በትምህርት ቤት አንድ ተማሪ ከሌሎች በበለጠ ፍጥነት ትምህርቱን የመረዳት ችሎታ ሊኖረው እንደሚችል አስተውለህ ይሆናል። በሥራ መስክ ላይም አንድ ሠራተኛ አንድን አዲስ ሥራ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ ቀድሞ ሊለምድ ይችላል። በተመሳሳይም አንዳንዶች ከሌሎች በተሻለ ፍጥነት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ሊማሩና ተግባራዊ ሊያደርጉ ይችላሉ። ዋናው ቁም ነገር እነዚህን አምላካዊ ባሕርያት አቅማችን የፈቀደውን ያህል ለማንጸባረቅ ጥረት ማድረጋችን ነው። ይሖዋ በቃሉና በጉባኤው አማካኝነት በሚያደርግልን እርዳታ በመታገዝ እንዲህ ማድረግ እንችላለን። ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ግባችን ላይ ለመድረስ የሚወስድብን ጊዜ ሳይሆን እድገት ለማድረግ የምናሳየው ቁርጠኝነት የታከለበት ጥረት ነው።

7. ራስን መግዛት አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?

7 ራስን መግዛት በመንፈስ ፍሬ ዝርዝር ውስጥ መጨረሻ ላይ መጠቀሱ አስፈላጊነቱን ከሌሎቹ አያሳንሰውም። እንዲያውም በተቃራኒው ነው። ‘ከሥጋ ሥራዎች’ ሙሉ በሙሉ መራቅ የምንችለው ራሳችንን የምንገዛ ከሆነ ብቻ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። ሆኖም ፍጹማን ባለመሆናችን ‘የሥጋ ሥራ’ መገለጫ ለሆኑት እንደ “ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቊጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት” ላሉት ኃጢአቶች የተጋለጥን ነን። (ገላትያ 5:19-21) በመሆኑም መጥፎ ዝንባሌዎችን ከልባችንም ሆነ ከአእምሯችን ነቅለን ለማውጣት ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ በትግሉ መጽናት ይኖርብናል።

አንዳንዶች ትግሉ ያይልባቸዋል

8. አንዳንዶች ራሳቸውን መግዛት የሚከብዳቸው ለምንድን ነው?

8 አንዳንድ ክርስቲያኖች ራስን በመግዛት ረገድ ከሌሎች የተለየ ትግል ማድረግ አስፈልጓቸዋል። ለምን? የወላጅ ሥልጠና አለማግኘታቸው ወይም ቀድሞ ያሳለፉት ሕይወት ራሳቸውን ለመግዛት እንዲቸገሩ ያደርግ ይሆናል። ይህን ባሕርይ ማዳበርና ማንጸባረቅ ለእኛ ያን ያህል አስቸጋሪ የማይሆንብን ከሆነ የሚያስደስት ነው። ሆኖም ራሳቸውን ለመግዛት ከሚቸገሩ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ያለባቸው ድክመት አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎችን ሊያስከትልብን ቢችልም እንኳ ልናዝንላቸውና ችግራቸውን ልንረዳላቸው ይገባል። ሁላችንም ፍጹማን እስካልሆንን ድረስ ራስን የመግዛት ችግር የለብኝም ሊል የሚችል ማነው?—ሮሜ 3:23፤ ኤፌሶን 4:2

9. አንዳንዶች ራስን በመግዛት ረገድ ምን ዓይነት ድክመቶች አሉባቸው? እነዚህን ድክመቶች ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ የምንችለው መቼ ነው?

9 ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- የትንባሆ ወይም የአደገኛ ዕፅ ሱሳቸውን እርግፍ አድርገው የተዉ ሆኖም አልፎ አልፎ ወደዚህ ልማዳቸው የመመለስ ጠንካራ ፍላጎት የሚያስቸግራቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ይኖሩ ይሆናል። ወይም አንዳንዶች በምግብ ወይም በአልኮል መጠጦች ረገድ ልካቸውን መጠበቅ ያስቸግራቸዋል። ሌሎች ደግሞ አንደበታቸውን መግታት ስለሚሳናቸው ብዙ ጊዜ ተገቢ ያልሆነ ነገር ይናገሩ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ድክመቶችን ለማሸነፍ ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማዳበር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ለምን? ያዕቆብ 3:2 እንዲህ በማለት እውነታውን ይገልጻል:- “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” ሌሎች ደግሞ ቁማር የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት ያስቸግራቸው ወይም ቁጣቸውን መቆጣጠር ይሳናቸው ይሆናል። እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ድክመቶችን ማሸነፍ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ምንም እንኳን አሁን ትልቅ መሻሻል ማድረግ ብንችልም የኃጢአት ምኞቶችን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ የምንችለው ፍጽምና ደረጃ ላይ ስንደርስ ብቻ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን ራሳችንን ለመግዛት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችን የቀድሞው ባሕርያችን አገርሽቶብን በኃጢአት እንዳንወድቅ ይረዳናል። በትግል ላይ እስካለን ድረስ ተስፋ እንዳንቆርጥ እርስ በርስ እንበረታታ።—ሥራ 14:21, 22

10. (ሀ) አንዳንዶች ከጾታ ስሜት ጋር በተያያዘ ራስን መግዛት ፈታኝ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ወንድም ምን ለውጥ ለማድረግ ተገድዷል? (በገጽ 16 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

10 አንዳንዶች ራስን ለመግዛት የሚቸገሩበት ሌላው ጉዳይ ከጾታ ጋር የተያያዘ ነው። የጾታ ስሜት ከይሖዋ በተፈጥሮ ያገኘነው ስጦታ ነው። ሆኖም አንዳንዶች ከአምላክ መስፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለጾታ ስሜት ተገቢውን ቦታ መስጠት አቅቷቸዋል። ከፍተኛ የሆነ የጾታ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ደግሞ ችግሩን ያባብስባቸው ይሆናል። የምንኖረው የወሲብ ፍላጎትን በተለያዩ መንገዶች ለማነሳሳት በሚጥር በጾታ ስሜት ባበደ ዓለም ውስጥ ነው። ይህ ደግሞ ሐሳባቸው በትዳር ሳይከፋፈል ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ አምላክን በነጠላነት ለማገልገል ለሚፈልጉ ክርስቲያኖች ችግር ሊፈጥርባቸው ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 7:32, 33, 37, 38) ይሁን እንጂ “በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና” ከሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ክቡር ጋብቻ ለመመሥረት ሊወስኑ ይችላሉ። እንዲህ ሲያደርጉ “በጌታ ይሁን እንጂ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:9, 39) የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ለማክበር ያላቸው ፍላጎት ይሖዋን እንደሚያስደስተው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሌሎች ክርስቲያኖችም እንዲህ ያለ ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም ባላቸው ታማኝ አምላኪዎች መካከል በመሆናቸው በጣም ይደሰታሉ።

11. ለማግባት እየፈለጉ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ያላገኙ ወንድሞችና እህቶችን ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

11 አንድ ክርስቲያን ተስማሚ የሆነ የትዳር ጓደኛ ባያገኝስ? ለማግባት እየፈለገ ያልተሳካለት ሰው ሊሰማው የሚችለውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት አስበው። እርሱ የሚስማማውን የትዳር ጓደኛ ገና እየፈለገ እያለ ጓደኞቹ አግብተው ደስ ብሏቸው ሲኖሩ ይመለከት ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ያለ ሰው ርኩስ በሆነው የማስተርቤሽን ልማድ ሊቸገር ይችላል። ማንም ቢሆን ንጹህ አቋሙን ጠብቆ ለመኖር የሚታገልን ክርስቲያን ባለማወቅም ቢሆን ስሜቱን ላለመጉዳት መጠንቀቅ አለበት። “አንተስ መቼ ነው የምታገባው?” እንደሚሉ ያሉ አሳቢነት የጎደላቸውን አስተያየቶች የምንሰነዝር ከሆነ ሳይታወቀን ሌሎችን ልናሳዝን እንችላለን። እንዲህ የምንለው ሆን ብለን ስሜታቸውን ለመጉዳት አስበን ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም በአንደበታችን አጠቃቀም ረገድ ራሳችንን መግዛታችን ምንኛ የተሻለ ይሆናል! (መዝሙር 39:1) ነጠላ ሆነው ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ልባዊ ምስጋና ልንቸራቸው ይገባል። ተስፋ አስቆራጭ የሆነ ነገር ከመናገር ይልቅ እነርሱን ለማበረታታት ጥረት ማድረግ አለብን። ለምሳሌ ያህል ለምግብ ወይም ለጨዋታ ከተወሰኑ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር በምንሰበሰብበት ጊዜ ያላገቡ ወንድሞችንና እህቶችንም ልንጋብዛቸው እንችላለን።

በትዳርም ውስጥ ራስን መግዛት

12. ያገቡ ሰዎችም እንኳን ራሳቸውን መግዛት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

12 ከጾታ ጋር በተያያዘ ማግባት ብቻውን ራስን የመግዛትን አስፈላጊነት አይቀንሰውም። ለምሳሌ ያህል የባልና የሚስት የጾታ ፍላጎት በእጅጉ ሊለያይ ይችላል። ወይም የአንደኛው የትዳር ጓደኛ አካላዊ ሁኔታ የጾታ ግንኙነት ማድረግን አስቸጋሪ ወይም ከናካቴው የማይቻል ሊያደርግባቸው ይችላል። አንደኛው የትዳር ጓደኛ ከጋብቻ በፊት በደረሰበት መጥፎ ገጠመኝ የተነሳ “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፣ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይቸግረው ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ሌላኛው ወገን ራስን የመግዛት ባሕርይ ማሳየቱ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱም ጳውሎስ ላገቡ ክርስቲያኖች የሰጠውን የሚከተለውን ፍቅራዊ ምክር ልብ ማለት ይኖርባቸዋል:- “ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ።”—1 ቆሮንቶስ 7:3, 5

13. ራሳቸውን ለመግዛት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉትን ወንድሞችና እህቶች ለማገዝ ምን ማድረግ እንችላለን?

13 ባልና ሚስት ይበልጥ በሚያቀራርባቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ራስን የመግዛት ባሕርይ በተገቢ ሁኔታ የሚያንጸባርቁ ከሆነ ደስተኞች ይሆናሉ። በተጨማሪም በጾታ ፍላጎት ረገድ ራሳቸውን ለመግዛት ጥረት በማድረግ ላይ ላሉት አሳቢነት ማሳየት ይኖርባቸዋል። መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ራሳቸውን ለመግዛትና ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶችን ለማሸነፍ የሚያደርጉትን ትግል እንዲቀጥሉ ለመርዳት ይሖዋ ማስተዋል፣ ድፍረትና ቆራጥነት እንዲሰጣቸው መጸለያችንን መዘንጋት የለብንም።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

እርስ በርሳችሁ ተረዳዱ

14. ለክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ርኅራኄና አሳቢነት ማሳየት የሚገባን ለምንድን ነው?

14 አንዳንድ ጊዜ እኛ ብዙም በማንቸገርበት ጉዳይ ላይ ራሳቸውን ለመግዛት የሚታገሉ ክርስቲያኖችን ችግር ለመረዳት ይከብደን ይሆናል። ይሁን እንጂ ሰዎች በተፈጥሯቸው የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶች በቀላሉ በስሜት ይመራሉ፤ ሌሎች ደግሞ እንደዚህ አይደሉም። አንዳንዶች በአንጻራዊ ሁኔታ ራሳቸውን መቆጣጠር ስለሚችሉ በዚህ ባሕርይ ረገድ ችግር አይታይባቸውም። ሌሎች ደግሞ በእጅጉ ይቸገራሉ። ሆኖም ክፉ ነገር ላለማድረግ የሚታገል ሰው መጥፎ ሊባል እንደማይችል አስታውስ። የክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ችግር መረዳትና ርኅራኄ ማሳየት ይገባናል። ራስን በመግዛት ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ላሉት ርኅራኄ የምናሳይ ከሆነ የእኛም ደስታ የዚያኑ ያህል ይጨምራል። በማቴዎስ 5:7 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ይህንን የሚያሳዩ ናቸው።

15. ራስን በመግዛት ረገድ መዝሙር 130:3 የሚያጽናናን እንዴት ነው?

15 አንድ ክርስቲያን አልፎ አልፎ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማሳየት ቢሳነው በፍጹም ልንፈርድበት አይገባም። ክርስቲያን ወንድሞቻችን ራሳችንን ለመግዛት የምናደርጋቸውን ጥረቶች ባያስተውሉም ይሖዋ ራሳችንን መግዛት ያልቻልንበትን አንድ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ራሳችንን መቆጣጠር የቻልንባቸውን በርካታ አጋጣሚዎች እንደሚመለከት ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው። በመዝሙር 130:3 ላይ የሚገኙትን “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” የሚሉትን ቃላት ማስታወሳችን በእጅጉ ያጽናናናል።

16, 17. (ሀ) ራስን ከመግዛት ባሕርይ ጋር በተያያዘ ገላትያ 6:2, 5ን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

16 ይሖዋን ለማስደሰት እንድንችል ሁላችንም ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር አለብን። በዚህ ረገድ የክርስቲያን ወንድሞቻችን ድጋፍ እንደማይለየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እያንዳንዳችን የራሳችንን ሸክም የምንሸከም ቢሆንም ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ እንድንችል አንዳችን ሌላውን እንድንረዳ ተመክረናል። (ገላትያ 6:2, 5) መሄድ ወደማይገባን ቦታ እንዳንሄድ፣ ማየት የማይኖርብንን ነገር እንዳናይ ወይም ማድረግ የማይኖርብንን ነገር እንዳናደርግ የሚከለክሉንን ወላጆቻችንን፣ የትዳር ጓደኞቻችንን ወይም ጓደኞቻችንን በአድናቆት ልንመለከታቸው እንችላለን። ራሳችንን መግዛት እንድንችል ይኸውም ክፉ ነገር እንድንፈጽም የሚደረግብንን ተጽዕኖ እምቢ እንድንልና በውሳኔያችን እንድንጸና እየረዱን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል።

17 ብዙ ክርስቲያኖች ራስን መግዛትን በተመለከተ እስካሁን ከተወያየንባቸው ነጥቦች ምንም የሚጎድላቸው ነገር የለም ይሆናል። ሆኖም ሊያሻሽሉት የሚገባ ነገር እንዳለ ይሰማቸው ይሆናል። ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች የሚጠበቀውን ያህል ራስን የመግዛት ባሕርይ በተሟላ ሁኔታ ለማሳየት ይፈልጉ ይሆናል። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ከሆነ ከመንፈስ ፍሬዎች መካከል አንዱ የሆነውን ይህን ባሕርይ ለማዳበር ምን ማድረግ ትችላለህ? እንዲህ ማድረግህስ ክርስቲያናዊ ግቦችህ ላይ እንድትደርስ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን የሚመለከት ይሆናል።

ታስታውሳለህ?

• ክርስቲያኖች ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር ያለባቸው ለምንድን ነው?

• አንዳንዶች ራሳቸውን መግዛት ፈታኝ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው?

• ራስን መግዛት በትዳር ውስጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ራስን የመግዛት ባሕርይ በማዳበር ረገድ እርስ በርስ መረዳዳት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እምቢ ማለትን ተማረ

በጀርመን የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ የቴክኒክ ክፍል ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። ሥራው 30 የሚያህሉ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞች ሥርጭትን መቆጣጠር የሚጨምር ነበር። በስርጭቶቹ ላይ የቴክኒክ ችግር ሲያጋጥም ችግሩን ለማወቅ የሚተላለፈውን ፕሮግራም መመልከት ይጠይቅበት ነበር። ወንድም እንዲህ ይላል:- “አብዛኛውን ጊዜ የቴክኒክ ችግር ልክ ዓመጽ ወይም የጾታ ብልግና መታየት ሲጀምር ጠብቆ የሚያጋጥም ይመስል ነበር። እነዚህ መጥፎ ትዕይንቶች በአእምሮዬ ውስጥ የታተሙ ያህል ለቀናት አንዳንዴም ለሳምንታት አይረሱኝም።” ይህ በመንፈሳዊነቱ ላይ ምን ጎጂ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በማያቸው የዓመጽ ድርጊቶች የተነሳ ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማንጸባረቅ አስቸጋሪ ስለሆነብኝ ቁጡ ሆንኩ። የማያቸው የጾታ ብልግና ትዕይንቶች በእኔና በባለቤቴ መካከል ውጥረት ፈጠሩብን። በየቀኑ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይጠይቅብኝ ነበር። ስለዚህ በትግሉ ላለመሸነፍ በአነስተኛ ደመወዝ ተቀጥሬም ቢሆን ሌላ ሥራ ለመሥራት ወሰንኩ። ብዙም ሳይቆይ አዲስ ሥራ በማግኘቴ ምኞቴ ተሳካልኝ።”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው እውቀት ራስን የመግዛት ባሕርይን እንድናዳብር ይረዳናል