በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዘፍጥረት 3:22 ላይ ይሖዋ ‘እኛ’ ሲል ስለ ማን መናገሩ ነበር?

ይሖዋ አምላክ “አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ባለ ጊዜ ስለ ራሱና ስለ አንድያ ልጁ የተናገረ ይመስላል። (ዘፍጥረት 3:22) እንዲህ ያልንበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ “ከእኛ እንደ አንዱ” የሚሉትን ቃላት የተናገረው በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ላይ የፍርድ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ነበር። አንዳንዶች ‘እኛ’ የሚለው ቃል አንድ ሰብዓዊ ንጉሥ ስለ ራሱ ሲናገር “እኛ” እያለ እንደሚናገረው ግርማዊነትን የሚያመለክት ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ዶናልድ ኢ ጎዋን ዘፍጥረት 1:26ን እና 3:22ን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “‘እኛ’ የሚለው ቃል ግርማዊነትን፣ . . . ወይም የመለኮትን ከአንድ በላይ መሆን ያመለክታል እንደሚሉ ያሉትን ማብራሪያዎች የሚደግፍ ሐሳብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ አይገኝም። . . . ከእነዚህ መላ ምቶች ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ በዘፍጥረት 3:22 ላይ ለሚገኘው ‘ከእኛ እንደ አንዱ’ ለሚለው ሐረግ አሳማኝ የሆነ ማብራሪያ ሊሆኑ አይችሉም።”

ይሖዋ “ከእኛ እንደ አንዱ” ሲል “መልካምንና ክፉን” በራሱ ለመወሰን እርምጃ የወሰደውንና የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስትም እንዲሁ እንዲያደርጉ የገፋፋቸውን ሰይጣን ዲያብሎስን ማመልከቱ ይሆን? እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። እዚህ ላይ ይሖዋ “ከእኛ እንደ አንዱ” እንዳለ ልብ ማለት ይገባል። ሰይጣን በዚያ ወቅት ይሖዋን በታማኝነት ከሚያገለግሉት እልፍ አእላፋት መላእክት መካከል አንዱ አልነበረም። በመሆኑም ከይሖዋ ጎን ከተሰለፉት እንደ አንዱ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም።

አምላክ “ከእኛ” ያለው ታማኝ መላእክቱንም ጨምሮ ይሆን? እንዲህ ብለን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ይሁን እንጂ ‘እኛ’ የሚል አንድምታ ባለው በዘፍጥረት 1:26 እና 3:22 መካከል ያለው ተመሳሳይነት ፍንጭ ይሰጠናል። ዘፍጥረት 1:26 ይሖዋ ‘ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር’ እንዳለ ይናገራል። ይሖዋ ይነጋገር የነበረው ከማን ጋር ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ መንፈሳዊ ፍጡር የነበረበትን ሁኔታ በሚመለከት “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ . . . በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው” በማለት ተናግሯል። (ቆላስይስ 1:15, 16) አዎን፣ በዘፍጥረት 1:26 ላይ ይሖዋ ይነጋገር የነበረው ሰማይንና ምድርን በፈጠረበት ወቅት አብሮት ከነበረው “ዋና ሠራተኛ” ማለትም ከአንድያ ልጁ ጋር ነው ማለቱ ምክንያታዊ ይመስላል። (ምሳሌ 8:22-31) ይሖዋ በዘፍጥረት 3:22 ላይም ተመሳሳይ አገላለጽ መጠቀሙ ይነጋገር የነበረው ለእርሱ ከማንም ይበልጥ ከሚቀርበው ከአንድያ ልጁ ጋር እንደሆነ ይጠቁማል።

የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካምንና ክፉን” የማወቅ ችሎታ የነበረው ይመስላል። ከይሖዋ ጋር ለረጅም ጊዜ መኖሩና የቅርብ ወዳጅነት መመሥረቱ የአባቱን አስተሳሰብ፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችና የአቋም ደረጃዎች በጥልቀት እንዲማር እንዳስቻለው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ በልጁ እውቀትና ታማኝነት ስለሚተማመን አንዳንድ ጉዳዮችን እርሱን ሳያማክር በራሱ እንዲያከናውን መጠነኛ ነፃነት ሰጥቶት ሊሆን ይችላል። ስለሆነም ልጁ ከገደቡ ሳያልፍ መልካምንና ክፉን የመወሰን ችሎታና ሥልጣን ኖሮት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሰይጣን እንዲሁም አዳምና ሔዋን እንዳደረጉት ክፉውንና ደጉን በተመለከተ ይሖዋ ካወጣው መሥፈርት ጋር የሚጋጭ የራሱን መመሪያ አያወጣም።