በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምሥራቹ በሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ፍሬ አፈራ

ምሥራቹ በሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ፍሬ አፈራ

ምሥራቹ በሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ፍሬ አፈራ

ብዙ ሰዎች ስለ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ እምብዛም ሰምተው አያውቁም ይሆናል። እነዚህ ደሴቶች ለጎብኚዎች በሚዘጋጁ ጽሑፎች ላይ ያን ያህል አይጠቀሱም። እንዲያውም በዓለም ካርታ ላይ ሲታዩ በምዕራብ አፍሪካ በጊኒ ባሕረ ሰላጤ ላይ ያሉ ሁለት ትናንሽ ነጥቦች የሚመስሉ ሲሆን ሳኦ ቶሜ በምድር ወገብ ላይ ፕሪንሲፔ ደግሞ ከምድር ወገብ ትንሽ ፈቀቅ ብሎ በስተሰሜን ምሥራቅ ይገኛሉ። የአገሪቱ የአየር ንብረት ዝናባማና እርጥበት አዘል ስለሆነ እስከ 2,000 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያላቸው የደሴቲቱ ተራሮች ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈኑ ናቸው።

እነዚህ በውቅያኖስና በዘንባባ ዛፎች ባሸበረቁ የባሕር ዳርቻዎች የተከበቡት ደሴቶች በሐሩር ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ተግባቢና ሰው ወዳድ የሆኑት የደሴቶቹ ነዋሪዎች ከአፍሪካና ከአውሮፓ የመጡ መሆናቸው ደስ የሚል የባህል ውህደት እንዲፈጠር አድርጓል። የደሴቶቹ ነዋሪዎች 170,000 የሚያህሉ ሲሆኑ የሚተዳደሩት ካካዋ ወደ ውጪ በመላክ እንዲሁም በእርሻና አሳ በማጥመድ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የዕለት ጉርስ ማግኘት እንኳን አስቸጋሪ እየሆነባቸው መጥቷል።

በ20ኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ አሥር ዓመታት በደሴቲቱ የሚኖሩ የብዙ ሰዎችን ሕይወት የነካ አንድ ክስተት ተፈጽሞ ነበር። በሰኔ 1993 የይሖዋ ምሥክሮች በሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ መንግሥት ሕጋዊ እውቅና ያገኙ ሲሆን ይህም የይሖዋ ምሥክሮች በደሴቶቹ ባሳለፉት ታሪክ ውስጥ ረጅምና አስቸጋሪ የሆነው ምዕራፍ እንዲያበቃ አድርጓል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የተዘራ ዘር

አገሪቱን ለመርገጥ የመጀመሪያው የሆነው የይሖዋ ምሥክር በ1950ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በአፍሪካ ከሚገኙ የፖርቱጋል ቅኝ ግዛቶች የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ ወደ ደሴቶቹ ይላኩ ከነበሩት እስረኞች ጋር የመጣ እንደሆነ ይታመናል። አቅኚ የነበረው ይህ አፍሪካዊ ወንድም የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ምክንያት ከሞዛምቢክ ተባርሮ የመጣ ነበር። ይህ ወንድም በትጋት በመስበኩ በ6 ወራት ውስጥ 13 የሚያህሉ ሌሎች ሰዎችም ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ መካፈል ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች በተመሳሳይ ሁኔታ ከአንጎላ ተባርረው መጡ። እነዚህ ምሥክሮች በደሴቶቹ በግዞት በቆዩባቸው ዓመታት በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለአካባቢው ነዋሪዎች ምሥራቹን ይሰብኩ ነበር።

በ1966 በሳኦ ቶሜ የጉልበት ሥራ ይሠሩ የነበሩት ወንድሞች በሙሉ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ነበር። ቢሆንም በደሴቶቹ የቀሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የመንግሥቱ አስፋፊዎች በድፍረት ማገልገላቸውን ቀጥለው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት አንድ ላይ በመሰብሰባቸው ምክንያት ስደት፣ ድብደባና እስራት ይደርስባቸው የነበረ ሲሆን የሚጎበኛቸውም ሆነ የሚያበረታታቸው አልነበረም። አገሪቱ በ1975 ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ነጻ ስትወጣ የመንግሥቱ እውነት ዘር ቀስ በቀስ ፍሬ ማፍራት ጀመረ።

የአስፋፊዎች ጭማሪና የአዳራሽ ግንባታ

የይሖዋ ምሥክሮች በ1993 ሕጋዊ እውቅና ባገኙበት ወር 100 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ነበራቸው። በዚያው ዓመት ከፖርቱጋል ልዩ አቅኚዎች ተመድበው መጡ። በአካባቢው የሚነገረውን ለየት ያለ የፖርቱጋል ቋንቋ ለመማር ያደረጉት ጥረት በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት አተረፈላቸው። ከዚያም በዋነኝነት ትኩረት የተሰጠው ለመንግሥት አዳራሽ መሥሪያ የሚሆን ቦታ መፈለግ ነበር። ማሪያ የተባለች አንዲት እህት ይህን ስትሰማ ቤቷ ከሚገኝበት መሬት ላይ ግማሹን ሰጠች። መሬቱ አንድ ትልቅ የመንግሥት አዳራሽ ማሠራት የሚችል ነበር። ማሪያ ምንም ወራሽ እንደሌላት ያወቁ የአካባቢው ሀብታሞች መሬቱን ዓይናቸውን ጥለውበት እንደነበር አላወቀችም። አንድ ቀን በአካባቢው የታወቀ አንድ ነጋዴ ማሪያን ሊያነጋግራት መጣ።

“ስለ አንቺ የሰማሁት ወሬ ጥሩ አይደለም! መሬትሽን በነጻ እንደሰጠሽ ይወራል። በከተማው መሃል ስለሚገኝ ብዙ ገንዘብ እንደሚያወጣ አታውቂም?” ሲል ጠየቃት።

“ለአንተ ብሸጥልህ ምን ያህል ትከፍለኛለህ?” በማለት ጠየቀችው። ሰውየው ዝም ሲል “በዓለም ውስጥ ያለውን ገንዘብ ብትሰጠኝ እንኳን እሺ አልልህም፤ ምክንያቱም ገንዘብ ሕይወትን ሊገዛ አይችልም” አለችው።

“ልጆች የሉሽም አይደል?” በማለት ጠየቃት።

ማሪያ ውይይታቸውን መቋጨት ስለፈለገች እንዲህ አለችው፦ “መሬቱ የይሖዋ ነው። ለብዙ ዓመታት አውሶኝ ነበር፤ አሁን ግን መልሼ ሰጥቼዋለሁ። እኔ የምፈልገው የዘላለም ሕይወት ማግኘት ነው።” ከዚያም ሰውየውን “አንተ የዘላለም ሕይወት ልትሰጠኝ ትችላለህ እንዴ?” በማለት ጠየቀችው። ሰውየው አንድም ቃል ሳይመልስላት ፊቱን አዙሮ ሄደ።

ከፖርቱጋል በመጡ ጥሩ የግንባታ ችሎታ ባላቸው ወንድሞች እገዛ በቦታው ላይ ባለ ሁለት ፎቅ የሚያምር ሕንጻ ተገነባ። ሕንጻው ምድር ቤት፣ ሰፊ የመንግሥት አዳራሽና የመኖሪያ ክፍሎች አሉት። እንዲሁም የሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና የአቅኚዎች ኮርስ የሚሰጥባቸው የመማሪያ ክፍሎች አሉት። በአሁኑ ወቅት በዚህ አዳራሽ ሁለት ጉባኤዎች የሚሰበሰቡ ሲሆን በከተማይቱ ውስጥ የንጹሕ አምልኮ የትምህርት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።

በሜሶሺ 60 የሚያህሉ ንቁ አስፋፊዎች የነበሩት አንድ ጉባኤ ነበር። የጉባኤ ስብሰባዎች የሚያደርጉት በሙዝ እርሻ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ አዳራሽ ውስጥ ስለነበር ተስማሚ የሆነ የመንግሥት አዳራሽ ይፈልጉ ነበር። ወንድሞች ሁኔታውን ለማዘጋጃ ቤቱ ባሳወቁ ጊዜ ችግሩን የተረዱ ባለ ሥልጣናት በዋናው የከተማይቱ መንገድ ዳር የሚገኝ ቦታ ሰጧቸው። ከፖርቱጋል የመጡ ወንድሞች ፈጣን የግንባታ ዘዴን ተጠቅመው በሁለት ወር ውስጥ ግሩም የመንግሥት አዳራሽ ገነቡ። የአካባቢው ነዋሪዎች ያዩትን ነገር ማመን አልቻሉም። በከተማው ውስጥ በሌላ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ይሰራ የነበረ አንድ ስዊድናዊ መሃንዲስ ወንድሞችና እህቶች ሲሰሩ ሲመለከት በጣም ከመደነቁ የተነሳ እንዲህ ብሏል፦ “ትንግርት ነው! የይሖዋ ምሥክሮች በሜሶሺም ፈጣን የግንባታ ዘዴን መጠቀማቸው የሚያስገርም ነው! እኛም ፕሮጀክታችንን ለማደራጀት የእነርሱን ዘዴ መጠቀም አለብን።” የመንግሥት አዳራሹ 232 ተሰብሳቢዎች በተገኙበት በሰኔ 12, 1999 ለአምላክ አገልግሎት ተወስኗል። አዳራሹ ወደ ሜሶሺ ከተማ ለሚመጡ ጎብኚዎች ግሩም የዓይን ማረፊያ ሆኗል።

ታሪካዊ ስብሰባ

በጥር 1994 በሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው “መለኮታዊ ትምህርት” የተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ በደሴቶቹ ላይ ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች የማይረሳ ታሪካዊ ክንውን ነበር። ስብሰባው የተካሄደው በአገሪቱ ውስጥ አለ በሚባለው የአየር ማቀዝቀዣ ባለው አዳራሽ ውስጥ ነበር። አንድ መቶ አሥራ ስድስት የሚያህሉት የመንግሥቱ አስፋፊዎች በስብሰባው ላይ 405 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች እንደተገኙ ሲሰሙ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማ ሲመለከቱና አዳዲስ ጽሑፎችን ሲያገኙ ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት አያዳግትህም። ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑት 20 የሚያህሉ አስፋፊዎች የተጠመቁት በባሕር ዳርቻ ነበር።

የስብሰባው ልዑካን በደረታቸው ላይ የለጠፉት ካርድ የአካባቢውን ሕዝብ ትኩረት ስቦ ነበር። ከፖርቱጋልና ከአንጎላ 25 የሚያህሉ እንግዶች መምጣታቸው ስብሰባውን ዓለም አቀፋዊ ይዘት አላብሶታል። በወንድሞች መካከል ሞቅ ያለ ክርስቲያናዊ ፍቅር ስለተመሠረተ ስብሰባው አልቆ ሲሰነባበቱ አብዛኞቹ እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም።—ዮሐንስ 13:35

ከአገሪቱ ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ የመጡ ጋዜጠኞች ለስብሰባው የበላይ ተመልካች ቃለ መጠይቅ አድርገውለት ነበር። እንዲሁም ከአንዳንድ ንግግሮች ላይ የተቀነጨቡ ሐሳቦችን በሬዲዮ አስተላልፈዋል። በእርግጥም ስብሰባው ታሪካዊ ክንውን ሊባል የሚችል ሲሆን እነዚህ ለዓመታት ተገልለው የኖሩ ታማኝ ምሥክሮች ወደ ይሖዋ ምድራዊ ድርጅት እንደቀረቡ እንዲሰማቸው አድርጓል።

ይሖዋን የሚያስከብር ፍሬ ማፍራት

የመንግሥቱ መልእክት ከሚያፈራቸው ፍሬዎች አንዱ ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ የሚያመጣ ግሩም ባሕርይ ነው። (ቲቶ 2:9, 10) በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ አንዲት ወጣት ልጃገረድ በየሳምንቱ በምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ የምትማረው ነገር ያስደስታት ነበር። ይሁንና አባቷ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ ከለከላት። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያለውን ጠቀሜታና እርሷም ከስብሰባው መቅረት እንደማትፈልግ በአክብሮት ስትነግረው ይባስ ብሎ ከቤት አባረራት። ሌሎች ወጣቶች እንደሚያደርጉት ወዲያውኑ የሚያስተዳድራት ወንድ ፈልጋ የምትገባ መስሎት ነበር። ይሁን እንጂ ንጽሕናዋን ጠብቃ ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያናዊ ሕይወት እንደምትመራ ሲመለከት ወደ ቤት እንድትመለስ የፈቀደላት ከመሆኑም በላይ ይሖዋን ለማገልገል ሙሉ ነጻነት ሰጣት።

የመንግሥቱ መልእክት የባሕርይ ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው ሌላው ሰው ደግሞ የአንድ የሙዚቃ ባንድ መሪ ነው። ይከተለው በነበረው ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ሕይወት የተነሳ ተስፋ ቆርጦ ነበር። የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ ጥረት እያደረገ ሳለ የይሖዋ ምሥክሮች አገኙት። በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መስፈርቶች ሕይወቱን መምራት ሲጀምር የከተማው ሕዝብ ስለ እርሱ ማውራት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ከመጥፎ ጓደኞቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋረጠ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ከዚያም ራሱን ወስኖ በመጠመቅ ወሳኝ እርምጃ ወሰደ።

የተወሰኑ ወጣቶች እውነተኛውን ሃይማኖት ለማወቅ ጥረት ያደርጉ ነበር። በዚህም ምክንያት ከተለያዩ ወንጌላዊ ቡድኖች ፓስተሮች ጋር ይወያዩ ነበር። ይህ ግን ይበልጥ ግራ እንዲጋቡና ተስፋ እንዲቆርጡ አደረጋቸው እንጂ ምንም አልፈየደላቸውም። በዚህም የተነሳ ሥርዓት አልበኞች የሆኑ ሲሆን በማንኛውም ሃይማኖት ላይም ማፌዝ ጀመሩ።

አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ሚስዮናዊ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት እየሄደ እያለ እነዚህ ወጣቶች በሚሰባሰቡበት ቦታ አለፈ። ወጣቶቹ ሚስዮናዊው አንዳንድ ጥያቄዎቻቸውን እንዲመልስላቸው ስለፈለጉ ወደ ጓሮ ወሰዱትና ትንሽ በርጩማ ላይ እንዲቀመጥ ጋበዙት። ከዚያም ነፍስን፣ ሲኦልን፣ ወደ ሰማይ መሄድንና የዓለም ፍጻሜን የመሳሰሉ ጉዳዮችን በተመለከተ የጥያቄ መዓት አወረዱበት። ሚስዮናዊው የቡድኑ መሪ በሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሞ ጥያቄዎቻቸውን በሙሉ መለሰላቸው። ከአንድ ሰዓት በኋላ ላ ተብሎ የሚጠራው የቡድኑ መሪ እንዲህ አለው፦ “ጥያቄያችንን እንድትመልስልን የጠራንህ በሌሎች ሃይማኖቶች አባላት ላይ እንደምናደርገው ልናሾፍብህ አስበን ነበር። ማንም ቢሆን እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ እንደማይችል ይሰማን ነበር። አንተ ግን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ በመጠቀም መልሰህልናል። እኔም እንዳንተ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ማወቅ የምችለው እንዴት ነው?” ላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ከዚያም ከቀድሞ ቡድኑ ጋር የነበረውን ግንኙነት ያቋረጠ ከመሆኑም በላይ የዓመጽ አኗኗሩን እርግፍ አድርጎ ተወ። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠመቀ። አሁን የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ እያገለገለ ነው።

በአካባቢው ሥር ከሰደዱ ልማዶች አንዱ በሕግ ሳይጋቡ አብሮ መኖር ነው። ብዙዎች በዚህ ሁኔታ ለዓመታት አብረው የኖሩ ሲሆን ልጆችም አፍርተዋል። አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት መቀበል ይከብዳቸዋል። አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ይህን እንቅፋት እንዴት ማሸነፍ እንደቻለ እስቲ እንመልከት።—2 ቆሮንቶስ 10:4-6፤ ዕብራውያን 4:12

አንቶንዮ ትዳሩን ሕጋዊ ማድረግ እንዳለበት ሲገነዘብ የበቆሎ ምርቱ ሲደርስ በሚያገኘው ገንዘብ ሠርግ ደግሶ ለመጋባት አቀደ። በቆሎውን ለመሰብሰብ ባሰበበት ዕለት ዋዜማ ሌሊቱን ሌቦች መጥተው ዘረፉት። ስለዚህ ጋብቻውን ሕጋዊ የማድረጉን ጉዳይ የሚቀጥለው ዓመት የበቆሎ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ለማቆየት ወሰነ፤ በዚያም ዓመት ሌቦች ሰብሉን ዘረፉበት። አንቶንዮ ለሠርጉ የሚሆነውን ገንዘብ ለማግኘት ያደረገው ሌላ ሙከራ ሲከሽፍበት ዋነኛው ጠላቱ ማን እንደሆነ ተገነዘበ። “ሰይጣን ከዚህ በኋላ አይጫወትብኝም፤ ድግስ ኖረም አልኖረም ከአንድ ወር ተኩል በኋላ ጋብቻችንን ሕጋዊ እናደርጋለን” በማለት ወሰነ። ከዚያም እንዳለው ጋብቻቸውን ሕጋዊ ያደረጉ ሲሆን ወዳጆቻቸው ፈጽሞ ያልጠበቁትን ለሠርጉ የሚሆኑ ዶሮዎች፣ ዳክዬዎችና ፍየል አመጡላቸው። አንቶንዮና ሚስቱ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ካደረጉ በኋላ ከ6 ልጆቻቸው ጋር ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ተጠመቁ።

ፕሪንሲፔን ደግሞ እንመልከት

በቅርብ ዓመታት በሳኦ ቶሜ የሚገኘው የወረዳ የበላይ ተመልካችና ሌሎች አቅኚዎች 6,000 የሚያህሉ ነዋሪዎች ወዳሏት ወደ ፕሪንሲፔ አልፎ አልፎ እየሄዱ ያገለግሉ ነበር። የደሴቲቱ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባዮች ሲሆኑ ምሥክሮቹ የሚነግሯቸውንም በጉጉት ያዳምጡ ነበር። አንድ ሰውዬ አቅኚዎቹ ትተውለት የሄዱትን ትራክት ካነበበ በኋላ በማግሥቱ ፈልጎ አገኛቸውና ትራክቱን በማሠራጨት ሊረዳቸው እንደሚፈልግ ነገራቸው። አቅኚዎቹ ሥራው መሠራት ያለበት በእነርሱ እንደሆነ ቢነግሩትም አብሯቸው ከቤት ወደ ቤት እየሄደ የቤቱ ባለቤቶች እንዲያዳምጧቸው ሊነግርላቸው እንደሚፈልግ ገለጸላቸው። ሰውየው በመጨረሻ ሲሄድ አቅኚዎቹን ለሚያከናውኑት ጠቃሚ ሥራ ከልብ አመሰገናቸው።

በ1998 ሁለት አቅኚዎች ከሳኦ ቶሜ ወደ ፕሪንሲፔ የተዛወሩ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ 17 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አግኝተዋል። ሥራው እድገት ማድረጉን ቀጠለና በአጭር ጊዜ በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ 16፣ በሕዝብ ንግግር ላይ ደግሞ 30 የሚያህሉ አማካይ ተሰብሳቢዎች መገኘት ጀመሩ። ወንድሞች የመሰብሰቢያ አዳራሽ መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ለከተማው ማዘጋጃ ቤት አመለከቱና ያለ ብዙ ውጣ ውረድ መሬት ተሰጣቸው። በፈቃደኝነት ከሳኦ ቶሜ የመጡ ወንድሞች ለሁለት ልዩ አቅኚዎች የሚሆን መኖሪያ ያለው አንድ አነስተኛ የመንግሥት አዳራሽ ሠሩላቸው።

የአምላክ መንግሥት ምሥራች በእነዚህ ርቀው የሚገኙ ደሴቶች ላይ ብዙ ፍሬ እያፈራ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። (ቆላስይስ 1:5, 6) በጥር 1990 በሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ 46 አስፋፊዎች ብቻ ነበሩ። በ2002 የአገልግሎት ዓመት ግን 388 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ተገኝቷል። ከእነዚህ ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ላይ ሲሆኑ 1,400 የሚያህሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየተመሩ ነው። በ2001 በተከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ 1,907 የደረሰ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ተገኝቷል። አዎን፣ በሐሩራማው ክልል በሚገኙት በእነዚህ ደሴቶች ላይ የይሖዋ ቃል በፍጥነት እየተሰራጨና ክብር እየተጎናጸፈ ነው።—2 ተሰሎንቄ 3:1

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተወዳጅነት ያተረፉ የሬዲዮ ፕሮግራሞች

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ በእነዚህ ደሴቶች ላይ ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፏል። በየሁለት ሳምንቱ በዚህ መጽሐፍ ርዕስ የተሰየመ የ15 ደቂቃ ፕሮግራም በአገሪቱ ብሔራዊ ሬዲዮ ይተላለፋል። ለምሳሌ ያህል የፕሮግራሙ አቅራቢ በመግቢያው ላይ “ወጣቶች እውነተኛ ፍቅር ወይስ ወረት መሆኑን እንዴት ታውቃላችሁ?” ብሎ ይጠይቅና ከመጽሐፉ ላይ የተወሰኑ ክፍሎችን ያነብባል። (ምዕራፍ 31ን ተመልከት።) አንድ ሌላ ተመሳሳይ ፕሮግራም ደግሞ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ አንዳንድ ክፍሎችን መርጦ ያቀርባል። a

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1994 በሳኦ ቶሜ የተገነባው የመጀመሪያው የመንግሥት አዳራሽ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. በሜሶሺ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነባ የመንግሥት አዳራሽ

2. በዚህ አዳራሽ ውስጥ ታሪካዊ የአውራጃ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር

3. እጩ ተጠማቂዎች በአውራጃ ስብሰባ ላይ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሉል፦ Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.