በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር ገነት እንደምትሆን የሚያሳይ ማስረጃ

ምድር ገነት እንደምትሆን የሚያሳይ ማስረጃ

ምድር ገነት እንደምትሆን የሚያሳይ ማስረጃ

በታሪክ ዘመናት ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምድርን ትተው ወደ ሰማይ መሄዳቸው እንደማይቀር ሲያምኑ ቆይተዋል። አንዳንዶች ፈጣሪ ምድርን የፈጠረው የሰው ልጆች ቋሚ መኖሪያ ለማድረግ አስቦ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። የባሕታውያን አመለካከት ደግሞ ለየት ያለ ነው። አብዛኞቹ ምድርም ሆነች ቁሳዊ ነገሮች መንፈሳዊ ፍላጎታችንን እንዳናሟላና ወደ አምላክ እንዳንቀርብ እንቅፋት የሚፈጥሩብን ክፉ ነገሮች እንደሆኑ ይሰማቸዋል።

ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ አመለካከቶች ያላቸው ሰዎች አንድም አምላክ ምድራዊ ገነትን በሚመለከት ምን እንዳለ አያውቁም አሊያም ላለመቀበል መርጠዋል። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ ብዙዎች አምላክ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስጻፈውን ለመመርመር ምንም ፍላጎት የላቸውም። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሆኖም የሰዎችን ጽንሰ ሐሳብ ከመቀበል ይልቅ የአምላክን ቃል ማመኑ የተሻለ አይሆንም? (ሮሜ 3:4) እንዴታ! እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ኃይለኛ ሆኖም የማይታይ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ሰዎችን መንፈሳዊ ዓይናቸውን እንዳሳወራቸውና ‘ዓለሙን ሁሉ እያሳተ’ እንደሆነ ስለሚናገር ከሰዎች አመለካከት ይልቅ የአምላክን ቃል መቀበላችን የግድ አስፈላጊ ነው።​—⁠ራእይ 12:9፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4

የአመለካከት ልዩነት የተፈጠረው ለምንድን ነው?

አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ አስመልክቶ ሰዎች የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው የቻለው ነፍስን በሚመለከት በሚነገሩት እርስ በርስ የማይጣጣሙ ሐሳቦች የተነሳ ነው። ብዙዎች ሰው ከሥጋ የተለየችና የማትሞት ነፍስ አለችው ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ነፍስ የሰው አካል ከመፈጠሩም በፊት ነበረች የሚል እምነት አላቸው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳስቀመጠው ግሪካዊው ፈላስፋ ፕላቶ ነፍስ “በሰማይ በነበረችበት ጊዜ ለሠራችው ኃጢአት እንድትቀጣ በሥጋ ውስጥ ታስራለች” የሚል አመለካከት ነበረው። በተመሳሳይም በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረው ኦሪጀን የተባለው የሃይማኖት ምሑር “ነፍስ ከሥጋ ጋር ከመቆራኘቷ በፊት [በሰማይ] ኃጢአት እንደሠራችና ለዚህ ሥራዋ ቅጣት እንዲሆናት [በምድር ላይ በሥጋ] ውስጥ እንደታሰረች” ተናግሯል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ምድር ሰው ወደ ሰማይ ከመሄዱ በፊት የሚፈተንባት ቦታ ነች ብለው ያምናሉ።

በተጨማሪም ሰው ሲሞት ነፍሱ ምን እንደምትሆን የሚገልጹ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። ሂስትሪ ኦቭ ዌስተርን ፊሎዞፊ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ግብጻውያን “የሙታን ነፍሳት ወደ ጥልቁ ይወርዳሉ” የሚል አመለካከት ነበራቸው። ከጊዜ በኋላ የተነሱ ፈላስፋዎች ደግሞ የሙታን ነፍሳት ወደ ጥልቁ በመውረድ ፋንታ በሰማይ ወደሚገኝ መንፈሳዊ ዓለም ያርጋሉ ብለው ይከራከራሉ። ግሪካዊው ፈላስፋ ሶቅራጥስ ሰው ሲሞት ነፍሱ “ወደማይታይ ዓለም በመሄድ . . . ቀሪ ሕይወቷን ከአማልክት ጋር ታሳልፋለች” የሚል እምነት እንደነበረው ይነገራል።

መጽሐፍ ቅዱስስ ምን ይላል?

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ ላይ ሰው የማትሞት ነፍስ አለችው ብሎ አይናገርም። እስቲ ዘፍጥረት 2:7ን [አ.መ.ት ] አውጥተህ አንብብ። እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር አፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” ይህ ግልጽና የማያሻማ ነው። አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ሲፈጥር በውስጡ በዓይን የማይታይ አንድ ረቂቅ ነገር አላስገባበትም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ነው። አዳም በውስጡ ነፍስ ያለው ሳይሆን እርሱ ራሱ ነፍስ ነበር።

ይሖዋ ምድርንና የሰውን ዘር ሲፈጥር ሰዎች እንዲሞቱ ዓላማው አልነበረም። የአምላክ ዓላማ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። አዳም የሞተው የአምላክን ሕግ ባለመታዘዙ ምክንያት ነው። (ዘፍጥረት 2:8, 15-17፤ 3:1-6፤ ኢሳይያስ 45:18) አዳም ሲሞት የሄደው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ነበር? በፍጹም! ራሱ ነፍስ የነበረው አዳም ወደተፈጠረበት አፈር ተመልሷል።​—⁠ዘፍጥረት 3:17-19

ሁላችንም ከመጀመሪያው አባታችን ከአዳም ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል። (ሮሜ 5:12) ይህ ሞት ልክ እንደ አዳም ከህልውና ውጪ መሆንን ያመለክታል። (መዝሙር 146:3, 4) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ነፍስ” የሚለውን ቃል “ዘላለማዊ” ወይም “የማይሞት” ከሚሉት ቃላት ጋር አያይዞ የተጠቀመበት አንድም ቦታ አይገኝም። በተቃራኒው ቅዱሳን ጽሑፎች ነፍስ ማለትም ሰውየው ራሱ ሟች እንደሆነ በግልጽ ይናገራሉ። አዎን፣ ነፍስ ሟች ናት።​—⁠መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4

ቁሳዊ ነገሮች በሙሉ መጥፎ ናቸው?

ምድርን ጨምሮ ቁሳዊ ነገሮች በሙሉ መጥፎ ናቸው የሚለውስ አመለካከት ትክክል ነው? በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ፋርስ ውስጥ ማኒ በተባለ ሰው የተመሠረተው ማኒኬይዝም የተባለ ሃይማኖት ተከታዮች እንዲህ ያለ አመለካከት ነበራቸው። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “ማኒኬይዝምን የወለደው በመከራ የተሞላው የሰው ልጅ ሕይወት ነው” በማለት ይናገራል። ማኒ ሰው መሆን ራሱ “ተፈጥሯዊ ያልሆነ፣ በመከራ የተሞላ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ክፉ ነው” ብሎ ያምን ነበር። ከዚህ “መከራ” መላቀቅ የሚቻለው ነፍስ ከሥጋ ተለይታ ምድርን ለቅቃ በመሄድ በመንፈሳዊ ዓለም መንፈሳዊ ሕይወት ስታገኝ ብቻ ነው የሚል አመለካከት ነበረው።

በአንጻሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ምድርንና የሰውን ዘር በፈጠረበት ጊዜ ‘ያደረገው ሁሉ’ በፊቱ “እጅግ መልካም” እንደነበረ ይገልጽልናል። (ዘፍጥረት 1:31) በዚያን ጊዜ የሰው ልጆችና አምላክ ነጻ የሐሳብ ግንኙነት ነበራቸው። ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ከሚኖረው አባቱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንደነበረው ሁሉ አዳምና ሔዋንም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው።​—⁠ማቴዎስ 3:17

የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን የኃጢአት ጎዳና ባይከተሉ ኖሮ ከይሖዋ አምላክ ጋር ዘላለማዊ ወዳጅነት መሥርተው ገነት በሆነችው ምድር ላይ መኖር ይችሉ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች “እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው” በማለት እንደሚናገሩት ሕይወትን የጀመሩት በገነት ውስጥ ነበር። (ዘፍጥረት 2:8) ሔዋንም የተፈጠረችው በዚህ ገነት ውስጥ ነበር። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ባይሠሩ ኖሮ እነርሱም ሆኑ ፍጹም የሆኑ ልጆቻቸው መላዋን ምድር ገነት በማድረጉ አስደሳች ሥራ በጋራ መሥራት ይችሉ ነበር። (ዘፍጥረት 2:21፤ 3:23, 24) ገነት የሆነችው ምድር የሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ ትሆን ነበር።

አንዳንድ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱት ለምንድን ነው?

‘መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሰማይ ስለሚሄዱ ሰዎች ይናገር የለም?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አዎን ይናገራል። አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ይሖዋ ከአዳም ዘሮች መካከል የተመረጡ ሰዎች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ‘በምድር ላይ የሚነግሱበት’ ሰማያዊ መንግሥት ለማቋቋም አሰበ። (ራእይ 5:9, 10፤ ሮሜ 8:16, 17) እነዚህ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ ለዘላለም ይኖራሉ። አጠቃላይ ቁጥራቸው 144, 000 ሲሆን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት የኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያዎቹ ናቸው።​—⁠ሉቃስ 12:32፤ 1 ቆሮንቶስ 15:42-44፤ ራእይ 14:1-5

ይሁን እንጂ ጻድቅ ሰዎች ምድርን ትተው ወደ ሰማይ እንዲሄዱ ማድረግ የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ አልነበረም። እንዲያውም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፣ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13) አምላክ “የሰው ልጅ” ተብሎ በተጠራው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የቤዛ ዝግጅት ያደረገ ሲሆን በዚህ መሥዋዕት የሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ሮሜ 5:8) ታዲያ እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚኖሩት የት ነው?

የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ይፈጸማል

አምላክ በሰማይ በሚገኘው መንግሥቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገዙ ሰዎችን ወደዚያ የመውሰድ ዓላማ ቢኖረውም ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ማለት ግን አይደለም። ይሖዋ ምድርን የፈጠረው የሰው ልጆች የሚኖሩባት ገነት እንድትሆን ብሎ ነው። በቅርቡ ይህን የመጀመሪያ ዓላማውን ያስፈጽማል።​—⁠ማቴዎስ 6:9, 10

በኢየሱስ ክርስቶስና በተባባሪ ገዥዎቹ አመራር ሥር በመላው ምድር ላይ ሰላምና ደስታ ይሰፍናል። (መዝሙር 37:9-11) በመታሰቢያው መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ትንሣኤ ካገኙ በኋላ ፍጹም ጤንነት አግኝተው ይኖራሉ። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ታዛዥ የሰው ልጆች ለአምላክ ታማኝ መሆናቸውን በማሳየታቸው ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ያጡትን ገነት በሆነችው ምድር ላይ በፍጽምና የመኖር መብት ያገኛሉ።​—⁠ራእይ 21:3, 4

ይሖዋ አምላክ ዓላማውን ከግብ ሳያደርስ አይቀርም። በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል:- “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣ ምድርን እንደሚያረካት፣ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፣ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፣ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”​—⁠ኢሳይያስ 55:10, 11

ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጿል። በገነት ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” አይልም። (ኢሳይያስ 33:24) እንስሳት ለሰው ልጆች ስጋት አይፈጥሩም። (ኢሳይያስ 11:6-9) ሰዎች የሚያማምሩ ቤቶችን ሠርተው እነርሱ ራሳቸው ይኖሩባቸዋል፤ እህልም አምርተው እስኪጠግቡ ይበላሉ። (ኢሳይያስ 65:21-25) እንዲሁም አምላክ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”​—⁠ኢሳይያስ 25:8

በቅርቡ ታዛዥ የሰው ልጆች እንዲህ ባለ አስደሳች ሁኔታ መኖር ይጀምራሉ። ‘ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥተው ለአምላክ ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት ይደርሳሉ።’ (ሮሜ 8:21) ቃል በተገባልን ምድራዊ ገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር እንዴት የሚያስደስት ነው! (ሉቃስ 23:43) ከቅዱሳን ጽሑፎች የምታገኘውን እውቀት ተግባራዊ የምታደርግ እንዲሁም በይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምን ከሆነ አንተም በገነት ውስጥ መኖር ትችላለህ። ምድር ገነት ትሆናለች ብሎ ማመንም ተገቢ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሰዎች. . .

ቤቶችን ይሠራሉ

ወይን ይተክላሉ

የይሖዋን በረከት ያገኛሉ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

U.S. Fish & Wildlife Service, Washington, D.C./NASA