በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁልጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ያስፈልግሃል?

ሁልጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ያስፈልግሃል?

ሁልጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ያስፈልግሃል?

ትንሽ ልጅ በነበርክበት ጊዜ ወላጆችህ ብዙ ሕጎች አውጥተውልህ ሊሆን ይችላል። እያደግህ ስትሄድ ወላጆችህ እንደዚህ ያደረጉት ለገዛ ደህንነትህ በማሰብ መሆኑን ተገንዝበሃል። አሁን ትልቅ ሰው እንደመሆንህ መጠን በወላጆችህ ቁጥጥር ሥር ባትሆንም እንኳ በሕፃንነትህ በቀረጹብህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ትመራ ይሆናል።

የሰማዩ አባታችን ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ቀጥተኛ የሆኑ በርካታ ሕጎችን ሰጥቶናል። ለምሳሌ ያህል ጣዖት አምልኮን፣ ዝሙትን፣ ምንዝርንና ስርቆትን ከልክሏል። (ዘጸአት 20:1-17፤ የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘በነገር ሁሉ እያደግን’ ስንሄድ ይሖዋ ትእዛዛቱን የሰጠን ለገዛ ጥቅማችን ብሎ እንደሆነና ሕግጋቱም መፈናፈኛ የሚያሳጡ እንዳልሆኑ እንገነዘባለን።—ኤፌሶን 4:15፤ ኢሳይያስ 48:17, 18፤ 54:13

ይሁን እንጂ ቀጥተኛ ሕግ ያልተሰጠባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። በመሆኑም አንዳንድ ሰዎች ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ባልተሰጠባቸው ጉዳዮች ያሻቸውን ለማድረግ ነፃ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ አምላክ በቀጥታ ትእዛዝ በመስጠት ፈቃዱን ይገልጽ ነበር ብለው ይከራከራሉ።

እንዲህ ብለው የሚያስቡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የኋላ ኋላ በጣም የሚጸጸቱበት ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ያደርጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ከመስጠትም ባሻገር የአምላክን አስተሳሰብ የሚጠቁሙ ሐሳቦችም ጭምር እንደያዘ አይገነዘቡም። መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናንና ይሖዋ ለነገሮች ያለውን አመለካከት እየተገነዘብን ስንሄድ በመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች የሠለጠነ ሕሊና የምናዳብር ከመሆኑም በላይ ከእርሱ አመለካከት ጋር የሚስማማ ምርጫ ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ስናደርግም የይሖዋን ልብ ደስ የምናሰኝ ከመሆኑም በላይ ጥበብ ያለበት ውሳኔ በማድረግ የሚገኙትን ጥቅሞች እናገኛለን።—ኤፌሶን 5:1

ግሩም የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች

በጥንት ጊዜ ስለኖሩ የአምላክ አገልጋዮች የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስንመለከት ቀጥተኛ ሕግ ባልነበረበት ጊዜም እንኳ የይሖዋን አመለካከት ከግምት ውስጥ ያስገቡባቸውን ሁኔታዎች እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል ዮሴፍን ተመልከት። የጲጥፋራ ሚስት ከእሷ ጋር እንዲባልግ ስትጋብዘው ምንዝርን የሚከለክል አምላክ የሰጠው በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ አልነበረም። ሆኖም ዮሴፍ ቀጥተኛ ሕግ ባይኖርም እንኳን ማመንዘር በገዛ ሕሊናው ላይ ብቻ ሳይሆን “በእግዚአብሔር [ላይ]” ጭምር የሚሠራ ኃጢአት እንደሆነ ተገንዝቧል። (ዘፍጥረት 39:9) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዮሴፍ ምንዝር በኤደን ከተገለጸው የአምላክ አመለካከትና ፈቃድ ጋር እንደሚጋጭ ተረድቷል።—ዘፍጥረት 2:24

ሌላ ምሳሌም ተመልከት። በሐዋርያት ሥራ 16:3 ላይ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን አስከትሎ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ከመሄዱ በፊት እንደገረዘው ተገልጿል። በቁጥር 4 ላይ ግን ጳውሎስና ጢሞቴዎስ “በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቆረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው” የሚል እናነባለን። ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቆረጡት ሥርዓት መካከል ደግሞ ክርስቲያኖች የመገረዝ ግዴታ እንደሌለባቸው የሚገልጸው ውሳኔ ይገኝበታል! (የሐዋርያት ሥራ 15:5, 6, 28, 29) ታዲያ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ መገረዙ አስፈላጊ እንደሆነ የተሰማው ለምንድን ነው? “በእነዚያም ሥፍራዎች ስለነበሩ አይሁድ ይዞ ገረዘው። [የጢሞቴዎስ አባት] የግሪክ ሰው እንደሆነ ሁሉ ያውቁ ነበርና።” ጳውሎስ ሳያስፈልግ ሌሎችን ቅር ማሰኘት ወይም ማሰናከል አልፈለገም። እርሱን ያሳሰበው ክርስቲያኖች ‘በሰው ሁሉ ኅሊና ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ማቅረባቸው’ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 4:2 አ.መ.ት፤ 1 ቆሮንቶስ 9:19-23

ጳውሎስና ጢሞቴዎስ እንዲህ ያለ አመለካከት ማሳየታቸው የተለመደ ነበር። እንደ ሮሜ 14:15, 20, 21 እና 1 ቆሮንቶስ 8:9-13፤ 10:23-33 ያሉትን ጥቅሶች አንብብና ጳውሎስ የሌሎች፣ በተለይም ደግሞ ከእውነታው አንጻር ሲታይ ምንም ስህተት በሌለው ነገር ሊሰናከሉ የሚችሉ ሰዎች መንፈሳዊ ደህንነት ምን ያህል በጥልቅ ያሳስበው እንደነበረ ተመልከት። ስለ ጢሞቴዎስም ቢሆን ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንደ እርሱ ያለ፣ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፣ ማንም የለኝምና፤ ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፣ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ።” (ፊልጵስዩስ 2:20-22) እነዚህ ሁለት ክርስቲያኖች በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል! ቀጥተኛ መለኮታዊ ሕግ ባልተሰጠበት ሁኔታ የግል ምቾታቸውን ወይም ምርጫቸውን ከማስቀደም ይልቅ ውሳኔያቸው የሌሎችን መንፈሳዊነት እንዳይነካ በመጠንቀቅ የይሖዋንና የልጁን ፍቅር ኮርጀዋል።

ከሁሉ የላቀ ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስንም ተመልከት። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የአምላክን ሕጎች መንፈስ የተረዳ ሰው አንድ ነገር በቀጥታ ትእዛዝ ያልተሰጠበት ወይም ያልተከለከለ ቢሆንም እንኳ እንደሚታዘዝ በግልጽ አስረድቷል። (ማቴዎስ 5:21, 22, 27, 28) ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ እንዲሁም ጢሞቴዎስና ዮሴፍ አንድ የተወሰነ መለኮታዊ ሕግ ከሌለ አንድ ሰው ደስ ያሰኘውን ነገር ማድረግ ይችላል የሚል አመለካከት አልነበራቸውም። እነዚህ ሰዎች አስተሳሰባቸውን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር በማስማማት ኢየሱስ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጡ ብሎ በጠራቸው ሁለት ትእዛዛት፣ ማለትም ለአምላክና ለባልንጀሮቻቸው ባላቸው ፍቅር ተመርተዋል።—ማቴዎስ 22:36-40

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችስ?

መጽሐፍ ቅዱስን እያንዳንዱን ግዴታ በዝርዝር እንደሚተነትን ሕጋዊ ሰነድ መቁጠር እንደሌለብን ግልጽ ነው። ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጽ የተወሰነ ሕግ በማይኖርበትም ጊዜ እንኳ የአምላክን አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ ምርጫ ስናደርግ የይሖዋን ልብ እናስደስታለን። በሌላ አነጋገር አምላክ ምን እንደሚፈልግብን ሁልጊዜ እንዲነገረን ከመጠበቅ ይልቅ ‘የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ እናስተውላለን።’ (ኤፌሶን 5:17፤ ሮሜ 12:2) ይህ ይሖዋን የሚያስደስተው ለምንድን ነው? ከግል ምርጫችንና ከመብታችን በላይ የሚያሳስበን ይሖዋን ማስደሰት መሆኑን ስለሚያሳይ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ያሳየንን ፍቅር እንደምናደንቅና ይህ ደግሞ ለተግባር እንዲያንቀሳቅሰን በመፍቀድ የአምላክን ፍቅር ለመኮረጅ እንደምንፈልግ ያሳያል። (ምሳሌ 23:15፤ 27:11) ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ሐሳብ ላይ የተመሠረቱ እርምጃዎች መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ጤንነትም ያስገኛሉ።

ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በግል ጉዳዮች ረገድ እንዴት በተግባር ሊውል እንደሚችል እንመልከት።

የመዝናኛ ምርጫ

አንድ ዓይነት የሙዚቃ አልበም ለመግዛት የሚፈልግ የአንድ ወጣትን ሁኔታ እንውሰድ። ከአልበሙ ላይ የሰማውን ሙዚቃ በጣም ወዶታል። ይሁን እንጂ የአልበሙ ሽፋን እንደሚጠቁመው ግጥሞቹ ለብልግና የሚጋብዙና አስነዋሪ መሆናቸው አሳስቦታል። ከዚህም በላይ አብዛኞቹ የዚህ አርቲስት ዘፈኖች ቁጠኝነትና ጠበኝነት የሚንጸባረቅባቸው እንደሆኑ ያውቃል። ይህ ወጣት ይሖዋን የሚወድ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ስለጉዳዩ ያለውን አመለካከትና ስሜት ማወቅ ይፈልጋል። ታዲያ አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ፈቃድ ሊያስተውል የሚችለው እንዴት ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሥጋ ሥራዎችንና የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች በዝርዝር ጽፏል። በአምላክ መንፈስ ፍሬዎች ውስጥ ምን ምን ባሕርያት እንደሚካተቱ ሳታውቅ አትቀርም፤ እነርሱም ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃትና ራስን መግዛት ናቸው። ይሁን እንጂ የሥጋ ሥራዎች እንደሆኑ የሚቆጠሩት ምን ዓይነት ተግባራት ናቸው? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፣ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”—ገላትያ 5:19-23

በሥጋ ሥራዎች ዝርዝር ውስጥ በመጨረሻ የተጠቀሰውን ‘እንደዚህ ያሉትን’ የሚለውን አባባል ልብ በል። እዚህ ላይ ጳውሎስ የሥጋ ሥራ ሆነው ሊቆጠሩ የሚችሉትን ነገሮች በሙሉ አልዘረዘረም። ይህም አንድ ሰው ‘ጳውሎስ በሥጋ ሥራዎች ዝርዝር ውስጥ ባልጠቀሰው ማንኛውም ተግባር ለመካፈል ቅዱስ ጽሑፉ ይፈቅድልኛል’ እንዲል ምክንያት ሊሆነው አይችልም። ከዚህ ይልቅ አንባቢው በዝርዝሩ ላይ ባይጠቀሱም ‘እንደዚህ ያሉት’ ከተባሉት ውስጥ ምን ነገሮች ሊካተቱ እንደሚችሉ ለይቶ ለማወቅ የማስተዋል ችሎታውን መጠቀም ያስፈልገዋል። በዝርዝሩ ውስጥ ባይጠቀሱም ‘እንደዚህ ያሉት’ በሚባሉ ተግባራት እየተካፈሉ ንስሐ የማይገቡ ሰዎች የአምላክ መንግሥት የምታመጣቸውን በረከቶች አይወርሱም።

በመሆኑም ይሖዋን የማያስደስቱትን ነገሮች ማስተዋል ወይም ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ይሆንብሃል? ፍራፍሬና አትክልት በርከት አድርገህ እንድትበላ እንደ ብስኩት፣ አይስ ክሬምና የመሳሰሉትን ግን እንድትተው ሐኪም ቢመክርህ ኬክ ከየትኛው ወገን እንደሚመደብ ማወቅ ይቸግርሃል? አሁን እስቲ የመንፈስ ፍሬና የሥጋ ሥራዎችን ዝርዝር እንደገና ተመልከት። ከላይ የተጠቀሰው የሙዚቃ አልበም በየትኛው ዝርዝር ውስጥ ይመደባል? እንደ ፍቅር፣ ቸርነትና ራስን መግዛት ያሉትን ወይም ከአምላክ መንፈስ ፍሬዎች ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ሌሎች ባሕርያት እንደማያንጸባርቅ እሙን ነው። አንድ ሰው እንደዚህ ያለው ሙዚቃ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እንደማይጣጣም ለማስተዋል ቀጥተኛ የሆነ ሕግ አያስፈልገውም። ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ለሚነበቡ ነገሮች፣ ለፊልሞች፣ ለቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ለኮምፒውተር ጨዋታዎች፣ ለኢንተርኔትና ለመሳሰሉት ሁሉ ይሠራል።

ተቀባይነት ያለው አለባበስ

መጽሐፍ ቅዱስ አለባበስንና አጋጌጥን የሚመለከቱ መሠረታዊ ሥርዓቶችም ይዟል። ይህም እያንዳንዱ ክርስቲያን ተስማሚና ማራኪ አለባበስ እንዲኖረው ይረዳዋል። እዚህ ላይም ቢሆን አንድ ይሖዋን የሚወድ ሰው ይህን ጉዳይ የሚመለከተው ለራሱ ደስ ያለውን ለማድረግ ሳይሆን የሰማዩ አባት የሚደሰትበትን ለማድረግ እንደሚያስችለው አጋጣሚ አድርጎ ነው። ቀደም ሲል እንዳየነው ይሖዋ በአንድ ጉዳይ ላይ የተወሰነ ደንብ አልሰጠም ማለት ሕዝቦቹ ያሻቸውን ቢያደርጉ ደንታ የለውም ማለት አይደለም። አለባበስና አጋጌጥ ከቦታ ቦታ ይለያያል። በአንድ አካባቢም እንኳን በየወቅቱ ሊለዋወጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አምላክ በማንኛውም ዘመንና በሁሉም ሥፍራ የሚኖሩ ሕዝቦቹን የሚመሩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቷል።

ለምሳሌ ያህል 1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 እንዲህ ይላል:- “እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፣ መልካም በማድረግ እንጂ በሹሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።” በመሆኑም ክርስቲያን ሴቶች እንዲሁም ወንዶች በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች “እግዚአብሔርን እንፈራለን” ከሚሉ ሰዎች ምን ዓይነት አለባበስ እንደሚጠብቁ ሊያስቡበት ይገባል። በተለይም አንድ ክርስቲያን አለባበሱና አጋጌጡ ሰዎች ለሚነግራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምን ስሜት እንዲያድርባቸው እንደሚያደርግ ሊያስብበት ይገባል። (2 ቆሮንቶስ 6:3) ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ ክርስቲያን ከራሱ ምርጫ ወይም መብት ይልቅ ይበልጥ የሚያስበው ሌሎችን ቅር እንዳያሰኝ ወይም እንዳያሰናክል ነው።—ማቴዎስ 18:6፤ ፊልጵስዩስ 1:10

አንድ ክርስቲያን አለባበሱ ወይም የፀጉር አበጣጠሩ ሌሎችን የሚያስቀይም ወይም የሚያሰናክል እንደሆነ ካወቀ ከራሱ ምርጫ ይልቅ ለሌሎች መንፈሳዊ ደህንነት በማሰብ ሐዋርያው ጳውሎስን ሊመስል ይችላል። ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 11:1)ጳውሎስ ስለ ኢየሱስም “ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና” በማለት ጽፏል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ለሁሉም ክርስቲያኖች ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ግልጽ ነው። ይኸውም “እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል። እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ” የሚል ነው።—ሮሜ 15:1-3

የማስተዋል ችሎታችንን ማሳደግ

የተወሰነ መመሪያ ባልተሰጠበት ጉዳይ ላይ ይሖዋ የሚደሰትበትን ነገር ለማወቅ እንዲያስችለን የማስተዋል ችሎታችንን ልናዳብር የምንችለው እንዴት ነው? ቃሉን በየዕለቱ ካነበብን፣ አዘውትረን ካጠናነውና ባነበብነው ላይ ካሰላሰልን የማስተዋል ችሎታችን ያድጋል። እንዲህ ያለው እድገት ወዲያው አይገኝም። እንደ አንድ ሕፃን ልጅ አካላዊ እድገት ሁሉ መንፈሳዊ እድገትም ቀስ በቀስ የሚመጣ ሲሆን ወዲያውኑ ግልጽ ሆኖ ላይታይ ይችላል። ስለዚህ ትዕግሥት ያስፈልጋል፤ ፈጣን እድገት ባንመለከት መበሳጨት የለብንም። በሌላ በኩል ግን እንዲሁ ረዥም ጊዜ ማለፉ ብቻ የማስተዋል ችሎታችንን አያሳድገውም። ይህ ጊዜ የአምላክን ቃል ከላይ በተገለጸው መንገድ አዘውትረን በመመገብና በተቻለን መጠን ሕይወታችንን በእርሱ መሠረት በመምራት የምናሳልፈው መሆን አለበት።—ዕብራውያን 5:14

የአምላክ ሕጎች ታዛዥነታችንን የሚፈትኑ ሲሆን መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ግን የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀትና እርሱን ለማስደሰት ያለንን ፍላጎት ይፈትናሉ ሊባል ይቻላል። በመንፈሳዊ ሁኔታ እያደግን ስንሄድ ይሖዋንና ልጁን በመምሰል ላይ ይበልጥ ትኩረት እናደርጋለን። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሰፈረው የአምላክ አስተሳሰብ ላይ ተንተርሰን ውሳኔዎቻችንን ለማድረግ እንጓጓለን። በምናደርገው ሁሉ የሰማዩን አባታችንን ባስደሰትን መጠን የራሳችንም ደስታ ይጨምራል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አለባበስ ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም በዚህ ረገድ ምርጫ ስናደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንመራ ይገባል