በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትኩረታችሁ ያረፈው ሽልማቱ ላይ ነው?

ትኩረታችሁ ያረፈው ሽልማቱ ላይ ነው?

ትኩረታችሁ ያረፈው ሽልማቱ ላይ ነው?

በሽታው ጉዳት የሚያደርሰው ቀስ በቀስ ነው። መጀመሪያ ላይ ግለሰቡ ከፊት ለፊቱ ካልሆነ በቀር በቀኝና በግራው በኩል የሚከናወኑ ነገሮችን ለማየት እንዲቸገር ያደርገዋል። ሕክምና ካልተደረገለት ከፊት ለፊቱ ያለውንም ነገር ማየት እንዲሳነው ሊያደርገው ይችላል። በመጨረሻም የማየት ችሎታውን ሙሉ በሙሉ ያሳጣዋል። ይህ በሽታ ምንድን ነው? ብዙዎችን ለዓይነ ሥውርነት የሚዳርገው ግላኮማ የተባለው በሽታ ነው።

በሥጋዊ ሁኔታ የማየት ችሎታችንን ሳይታወቀን ቀስ በቀስ ልናጣ እንደምንችል ሁሉ በጣም ውድ የሆነውን መንፈሳዊ እይታችንንም እንዲሁ ልናጣ እንችላለን። እንግዲያው መንፈሳዊ ነገሮችን ከፍ አድርገን መመልከታችን በጣም አስፈላጊ ነው።

ሽልማቱ ላይ ማተኮር

ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ያዘጋጀው የዘላለም ሕይወት ታላቅ ሽልማት በሥጋዊ ዓይናችን ‘ከማይታዩት ነገሮች’ መካከል አንዱ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:18) በእርግጥ ክርስቲያኖች ይሖዋን የሚያገለግሉበት ዋነኛው ምክንያት ስለሚወዱት ነው። (ማቴዎስ 22:37) ያም ቢሆን ይሖዋ ሽልማታችንን በጉጉት እንድንጠባበቅና ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ የሚሰጥ’ ለጋስ አባት መሆኑን እንድንገነዘብ ይፈልጋል። (ዕብራውያን 11:6) በዚህም የተነሳ አምላክን በደንብ የሚያውቁትና የሚወዱት ሰዎች ቃል የገባላቸውን በረከቶች ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸው ከመሆኑም በላይ እነዚህን በረከቶች ለማግኘት ይጓጓሉ።—ሮሜ 8:19, 24, 25

መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን የሚያነብቡ ብዙ ሰዎች ስለ መጪዋ ገነት የሚወጡትን ሥዕሎች ይወዷቸዋል። እርግጥ ምድር ገነት ስትሆን ምን መልክ እንደሚኖራት በትክክል አናውቅም፤ በመጽሔቶቹ ላይ የሚወጡት ሥዕሎችም ቢሆኑ እንደ ኢሳይያስ 11:6-9 ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ከሰፈረው ሐሳብ በመነሳት የተዘጋጁ ናቸው። ያም ቢሆን አንዲት ክርስቲያን ሴት እንዲህ ብላለች:- “በመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ላይ ወደፊት የምትመጣዋን ገነት የሚያመለክት ሥዕል ሲወጣ፣ ስለ ጉዞው የሚገልጸውን ብሮሹር እንደሚመለከት አንድ ቱሪስት በደንብ አድርጌ አያቸዋለሁ። አምላክ በፈቀደው ጊዜ በገነት ውስጥ ለመኖር ተስፋ ስለማደርግ ራሴን በዚያ ቦታ አድርጌ ለማሰብ እሞክራለሁ።”

ሐዋርያው ጳውሎስም ‘ወደ ላይ ስለመጠራቱ’ እንደዚሁ ተሰምቶት ነበር። እስከመጨረሻው ታማኝ መሆን ስለነበረበት ተስፋውን እንዳገኘ አድርጎ አላሰበም። ሆኖም ‘ከፊቱ ያለውን ለመያዝ መዘርጋቱን’ ቀጥሎ ነበር። (ፊልጵስዩስ 3:13, 14) በተመሳሳይ ኢየሱስም “በፊቱ ስላለው ደስታ” በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እስከመሞት ድረስ ጸንቷል።—ዕብራውያን 12:2

ወደ አዲሱ ሥርዓት ስለመግባትህ ጥርጣሬ ተሰምቶህ ያውቃል? የሕይወትን ሽልማት ማግኘታችን እስከመጨረሻው በታማኝነት በመጽናታችን ላይ የተመካ በመሆኑ ከልክ በላይ በራስ መተማመን ተገቢ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 24:13) ይሁን እንጂ አምላክ የሚፈልግብንን ብቃቶች ለማሟላት የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ከሆነ ሽልማቱን እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ “ማንም እንዳይጠፋ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ” እንደሚፈልግ አስታውስ። (2 ጴጥሮስ 3:9) በይሖዋ ከታመንን ግባችን ላይ መድረስ እንድንችል ይረዳናል። በእርግጥም፣ እርሱን ለማስደሰት ከልባቸው የሚጥሩ ሰዎች ሽልማቱን ለማግኘት ብቁ እንዳይሆኑ ለማድረግ ምክንያት መፈላለግ ከባሕሪው ጋር የሚጋጭ ነው።—መዝሙር 103:8-11፤ 130:3, 4፤ ሕዝቅኤል 18:32

ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን አመለካከት ማወቃችን ተስፋ ለማድረግ ምክንያት ይሆነናል፤ ተስፋ የእምነትን ያህል አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:13) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተስፋ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መልካም ነገርን [በጉጉት] መጠባበቅ” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለውን ተስፋ በአእምሮው በመያዝ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።” (ዕብራውያን 6:11, 12) ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን ከቀጠልን ተስፋችን እንደሚፈጸምልን እርግጠኞች መሆን እንደምንችል ልብ በል። በዓለም ላይ ካሉ ከአብዛኞቹ ተስፋዎች በተቃራኒ ይህ ተስፋ “ለዕፍረት አይዳርገንም።” (ሮሜ 5:5) ታዲያ ተስፋችን ብሩሕ ሆኖ እንዲታየንና ከአእምሯችን እንዳይጠፋ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

የመንፈሳዊ እይታችንን ጥራት ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

ሥጋዊ ዓይናችን በአንድ ጊዜ በሁለት ነገሮች ላይ ማተኮር አይችልም። መንፈሳዊ እይታችንን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ትኩረታችን ያረፈው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ባሉ ነገሮች ላይ ከሆነ አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ላይ እንዳናተኩር ሊያደርገን እንደሚችል ግልጽ ነው። ውሎ አድሮ፣ እይታችን በመደብዘዙ ተስፋው ማራኪ መሆኑ እየቀረ ይሄድና ከአእምሯችን ይጠፋል። ይህ እንዴት አሳዛኝ ይሆናል! (ሉቃስ 21:34) እንግዲያው በአምላክ መንግሥትና በዘላለም ሕይወት ሽልማታችን ላይ ያተኮረ “ጤናማ” ዓይን እንዲኖረን ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው!—ማቴዎስ 6:22

ጤናማ ዓይን እንዲኖረን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። በየዕለቱ የሚያጋጥሙን ችግሮች ትኩረታችንን ሊሰርቁት እንዲሁም ሐሳባችንን የሚከፋፍሉ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። እነዚህ ሁኔታዎች እያሉም፣ ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ቸል ሳንል ትኩረታችንን በመንግሥቱና አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ላይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሦስት መንገዶችን እንመልከት።

የአምላክን ቃል በየዕለቱ አጥና። አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማጥናት አእምሯችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳናል። እውነት ነው፣ የአምላክን ቃል ለዓመታት ስናጠና ቆይተን ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም በሕይወት ለመቆየት አዘውትረን ሥጋዊ ምግብ መመገብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ የአምላክንም ቃል ማጥናታችንን ልንቀጥል ይገባል። ባለፉት ዓመታት ስንበላ ስለኖርን አሁን ምግብ አናቆምም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን የቱንም ያህል ብናውቀው ተስፋችን ብሩሕ እንዲሆንና እምነታችንና ፍቅራችን እንዲጠነክር አዘውትረን ልናነበው ይገባል።—መዝሙር 1:1-3

በአምላክ ቃል ላይ በአድናቆት አሰላስል። ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሁለት ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል። በመጀመሪያ፣ ማሰላሰል ያነበብነውን ነገር በሚገባ ለመረዳት የሚያስችለን ሲሆን ስለ ጉዳዩም ጥልቅ አድናቆት እንዲያድርብን ያደርገናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ማሰላሰል ይሖዋንና ድንቅ ሥራዎቹን እንዲሁም በፊታችን ያስቀመጠልንን ተስፋ እንዳንረሳ ይረዳናል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት:- ከሙሴ ጋር ከግብጽ የወጡት እስራኤላውያን የይሖዋን ታላቅ ኃይል ተመልክተው ነበር። ከዚህም በላይ ወደ ተስፋይቱ ምድር በመራቸው ወቅት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ ሲያደርግላቸው አይተዋል። ያም ሆኖ እስራኤላውያን ማጉረምረም የጀመሩት ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመጓዝ ምድረ በዳውን ማቋረጥ እንደጀመሩ ነበር፤ ይህም እምነት እንዳልነበራቸው የሚያሳይ ነው። (መዝሙር 78:11-17) ችግራቸው ምን ነበር?

ሕዝቡ በይሖዋና ከፊታቸው በዘረጋላቸው ግሩም ተስፋዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ጊዜያዊ ለሆነው ምቾታቸውና ሥጋዊ ፍላጎታቸው ቅድሚያ ሰጡ። ድንቅ ተዓምራትን ሲፈጽም በገዛ ዓይናቸው የተመለከቱ ቢሆንም በርካታ እስራኤላውያን እምነት በማጣት አጉረምራሚዎች ሆኑ። መዝሙር 106:13 ይሖዋ “ያደረገውን ወዲያውኑ ረሱ” ይላል። ያ ትውልድ እንደዚህ ያለ በይቅርታ ሊታለፍ የማይችል ቸልተኝነት በማሳየቱ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይገባ ቀረ።

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን ስታነብብ ጊዜ ወስደህ ባነበብከው ነገር ላይ አሰላስል። እንደዚህ ማድረግህ መንፈሳዊ ጤንነትህን ለመጠበቅና እድገት ለማድረግ ይረዳሃል። ለምሳሌ፣ በከፊል ከላይ የተጠቀሰውን መዝሙር 106ን በምታነብበት ጊዜ በይሖዋ ባሕርያት ላይ አሰላስል። ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ምን ያህል ታጋሽና መሐሪ እንደነበረ ለማስተዋል ሞክር። ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ ለመርዳት ያላደረገው ነገር እንደሌለ ልብ በል። በተደጋጋሚ ጊዜ ያምፁበት እንደነበር አስብ። ጨርሶ ምስጋና ቢስ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ምሕረቱንና ትዕግሥቱን ሲፈታተኑት ይሖዋ ምን ያህል እንዳዘነ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ከዚህም በላይ ፊንሐስ ለጽድቅ ሲል የወሰደውን ጠንካራና ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በሚያብራሩት በቁጥር 30 እና 31 ላይ በማሰላሰል ይሖዋ ታማኞቹን እንደማይረሳና አትረፍርፎ እንደሚባርካቸው ማረጋገጫ ማግኘት እንችላለን።

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ አድርግ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስናደርግ የይሖዋ ምክሮች ጠቃሚ እንደሆኑ ከራሳችን ተሞክሮ መመልከት እንችላለን። ምሳሌ 3:5, 6 እንዲህ ይላል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” ሥነ ምግባር የጎደለው አካሄድ የተከተሉ በርካታ ሰዎች ድርጊታቸው ያስከተለባቸውን አእምሯዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ችግር አስብ። እነዚህ ሰዎች ለጊዜያዊ ተድላ በመሸነፋቸው ለዓመታት ይባስ ብሎም ዕድሜያቸውን ሙሉ ለመከራ ተዳርገዋል። ከዚህ በተቃራኒ ‘በቀጠነው መንገድ’ የሚሄዱ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የአዲሱን ሥርዓት ቅምሻ የሚያገኙ ሲሆን ይህም በሕይወት መንገድ ላይ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ብርታት ይሰጣቸዋል።—ማቴዎስ 7:13, 14፤ መዝሙር 34:8

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋል ፈታኝ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ እርምጃ በመውሰድ አፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት እንደምንችል ይሰማን ይሆናል። ለአብነት ያህል፣ በገንዘብ ረገድ ችግር ሲያጋጥመን መንፈሳዊ ነገሮችን በሁለተኛ ደረጃ ለማስቀመጥ እንፈተን ይሆናል። ይሁን እንጂ በእምነት የሚመላለሱና ትኩረታቸውን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚያደርጉ ሁሉ “ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች መልካም እንደሚሆንላቸው” እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። (መክብብ 8:12) አንድ ክርስቲያን አልፎ አልፎ ተጨማሪ ሰዓት መሥራት ያስፈልገው ይሆናል፤ ሆኖም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቦታ ባለመስጠት አቃልሎ እንደተመለከታቸው እንደ ዔሳው መሆን የለበትም።—ዘፍጥረት 25:34፤ ዕብራውያን 12:16

ኢየሱስ ክርስቲያን መሆናችን የሚያስከትልብንን ኃላፊነቶች በግልጽ አስቀምጧል። ‘ከሁሉ አስቀድመን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን መሻት’ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 6:33) እንደዚህ ካደረግን ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች እንድናገኝ በማድረግ አባታዊ ፍቅሩን ያሳየናል። እርሱ እንደሚያሟላልን ቃል ስለገባልን ነገሮች በማሰብ ራሳችንን እንድናስጨንቅ አይፈልግም። እንደዚህ ያለው ከልክ ያለፈ ጭንቀት ለመንፈሳዊ እይታችን እንደ ግላኮማ ሊሆንብን ይችላል፤ ተገቢውን ማስተካከያ ካላደረግን ቀስ በቀስ እይታችንን እያደበዘዘው ትኩረታችን በቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያርፍ ያደርገንና በመጨረሻ በመንፈሳዊ ሁኔታ እንታወራለን። በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ደግሞ የይሖዋ ቀን “እንደ ወጥመድ” ይደርስብናል። ይህ ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል!—ሉቃስ 21:34-36

እንደ ኢያሱ ሽልማቱን በትኩረት ተመልከቱ

ሌሎች ኃላፊነቶቻችን ከሚገባው በላይ ሐሳባችንን እንዳይከፋፍሉት በመጠንቀቅ ስለ አምላክ መንግሥት የተሰጠንን ተስፋ በትኩረት እንመልከት። አዘውትረን የማጥናት፣ የማሰላሰልና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ የማድረግ ልማድ በመኮትኮት ልክ እንደ ኢያሱ ተስፋችን እንደሚፈጸም እርግጠኞች ሆነን መመላለስ እንችላለን። እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቶ ካስገባቸው በኋላ እንዲህ አላቸው:- “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽመዋል።”—ኢያሱ 23:14

የአምላክ መንግሥት ተስፋ ኃይል እንዲሰጥህ እንዲሁም በአስተሳሰብህ፣ ለነገሮች ባለህ አመለካከት፣ በውሳኔዎችህና በምታደርጋቸው ነገሮች ተስፋው እውን እንደሆነልህ በሚያሳይ መንገድ በመመላለስ ልብህ በደስታ እንዲሞላ ምኞታችን ነው።—ምሳሌ 15:15፤ ሮሜ 12:12

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ አዲሱ ሥርዓት እገባ ይሆን ብለህ ተጠራጥረህ ታውቃለህ?

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሰላሰል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዐቢይ ክፍል ነው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሕይወታችሁ ውስጥ መንግሥቱን አስቀድሙ