በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘሌዋውያን መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የዘሌዋውያን መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የዘሌዋውያን መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ከወጡ ገና ዓመት አልሞላቸውም። አሁን እንደ አዲስ ሕዝብ ተደራጅተው ወደ ከነዓን ምድር እያቀኑ ነው። ይሖዋ በዚያ ቅዱስ ብሔር የማቋቋም ዓላማ አለው። ይሁን እንጂ የከነዓናውያኑ የአኗኗር ዘይቤና ሃይማኖታዊ ልማድ በጣም ያዘቀጠ ነበር። በመሆኑም እውነተኛው አምላክ እስራኤላውያን ለእርሱ አገልግሎት የተለዩ ሕዝብ እንዲሆኑ የተለያዩ ሕጎችን ሰጣቸው። እነዚህ ደንቦች በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን በ1512 ከክርስቶስ ልደት በፊት በሲና ምድረ በዳ በነቢዩ ሙሴ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ የሚሸፍነው ጊዜ ከአንድ ወር እምብዛም አይበልጥም። (ዘፀአት 40:17፤ ዘኍልቍ 1:1-3) በመጽሐፉ ውስጥ ይሖዋ አምላኪዎቹን ቅዱሳን እንዲሆኑ በተደጋጋሚ አሳስቧቸዋል።—ዘሌዋውያን 11:44፤ 19:2፤ 20:7, 26

በጊዜያችን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ በሙሴ በኩል በሰጠው ሕግ ሥር አይደሉም። ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ ሞት ይህን ሕግ ሽሮታል። (ሮሜ 6:14፤ ኤፌሶን 2:11-16) ይሁን እንጂ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት መመሪያዎች ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋ አምልኮ ያለንን ግንዛቤ በማስፋት ይጠቅሙናል።

በውዴታና በግዴታ የሚቀርቡ ቅዱስ መሥዋዕቶች

(ዘሌዋውያን 1:1 እስከ 7:38)

በሕጉ መሠረት ከሚቀርቡት መሥዋዕቶች መካከል አንዳንዶቹ በውዴታ ሌሎቹ ደግሞ በግዴታ የሚቀርቡ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የሚቃጠል መሥዋዕት በውዴታ የሚቀርብ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃደኝነት ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ እንደሰጠ ሁሉ ይህም መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ለአምላክ የሚሰጥ ነበር። በፈቃደኝነት የሚቀርበው የኅብረት መሥዋዕት ደግሞ ከፊሉ በመሠውያው ላይ ለአምላክ ይቀርባል፤ ከፊሉን ካህኑ የሚበላው ሲሆን ሦስተኛው ክፍል ደግሞ ለመሥዋዕት አቅራቢው ይሰጥ ነበር። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ለቅቡዓን ቀሪዎች የኅብረት ማዕድ ነው።—1 ቆሮንቶስ 10:16-22

የኃጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት ማቅረብ ግዴታ ነበር። የኃጢአት መሥዋዕት ባለማወቅ ወይም በስህተት የተሠሩ ኃጢአቶችን ያስተሰርያል። የበደል መሥዋዕት ደግሞ የሚቀርበው አንድ ሰው የሌላ ሰውን መብት የጣሰ እንደሆነ ወይም ንሥሐ የገባ ኃጢአተኛ አንዳንድ መብቶች እንዲመለሱለት ለመጠየቅ አሊያም በሁለቱም ሁኔታዎች ነው። ከዚህም በላይ ለይሖዋ ቸርነት ምሥጋና ለመግለጽ የእህል ቁርባን ይቀርብ ነበር። በሕጉ መሠረት የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ለኢየሱስ ክርስቶስና እርሱ ላቀረበው መሥዋዕት ወይም መሥዋዕቱ ለሚያስገኛቸው ጥቅሞች ጥላ ስለሆኑ ስለእነርሱ ማወቃችን ይጠቅመናል።—ዕብራውያን 8:3-6፤ 9:9-14፤ 10:5-10

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

2:11, 12—ይሖዋ ‘በእሳት በሚቀርበው ቁርባን ውስጥ’ ማር እንዳይጨመር የከለከለው ለምን ነበር? እዚህ ላይ የተጠቀሰው ማር ከንብ የሚገኘው ማር ሊሆን አይችልም። ይህ ማር ‘በእሳት በሚቀርበው ቁርባን ውስጥ’ እንዳይጨመር ቢከለከልም ‘ከእርሻ ፍሬ በኩራት’ ጋር ይቀርብ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 31:5) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው እዚህ ላይ የተጠቀሰው ማር የፍራፍሬ ጭማቂ ነው። ይህ ጭማቂ የመፍላት ባሕርይ ስላለው በመሠውያው ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ አይችልም ነበር።

2:13—ጨው በሁሉም “ቁርባን” ላይ መጨመር የነበረበት ለምንድን ነው? እንዲህ የሚደረገው መሥዋዕቱን ለማጣፈጥ ተብሎ አይደለም። ጨው በዓለም ዙሪያ ነገሮችን ሳይበላሹ ለማቆየት ጥቅም ላይ ይውላል። ስለሆነም ከመሥዋዕት ጋር ይቀርብ የነበረው ከብክለትና ከብልሽት ነጻ መሆንን ስለሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

3:17 ስብ ምርጥ የሆነው የእንስሳው ክፍል ተደርጎ ይታይ ስለነበር እስራኤላውያን ስብ እንዳይበሉ መከልከላቸው ለይሖዋ የሚገባው ምርጥ ምርጡ መሆኑን አስገንዝቧቸዋል። (ዘፍጥረት 45:18) ይህ እኛም ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት እንዳለብን ያሳስበናል።—ምሳሌ 3:9, 10፤ ቆላስይስ 3:23, 24

7:26, 27:- እስራኤላውያን ደም እንዳይበሉ ተከልክለው ነበር። አምላክ ደምን የሚመለከተው እንደ ሕይወት አድርጎ ነው። ዘሌዋውያን 17:11 “የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና” ይላል። በዛሬውም ጊዜ ቢሆን እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ከደም መራቅ ይጠበቅባቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29

ቅዱስ የክህነት ሥርዓት ተቋቋመ

(ዘሌዋውያን 8:1 እስከ 10:20)

መሥዋዕት ከማቅረብ ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶች የተሰጡት ለእነማን ነበር? ለካህናቱ ነበር። ሙሴ አምላክ በሰጠው መመሪያ መሠረት አሮንን ሊቀ ካህን፣ አራቱን ወንዶች ልጆቹን ደግሞ የበታች ካህናት አድርጎ ቀባቸው። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው የመቀባቱ ሥነ ሥርዓት ሰባት ቀን የፈጀ ሲሆን የክህነት አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩት በቀጣዩ ቀን ነበር።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

9:9የመሥዋዕቱ ደም በመሠውያው ግርጌ መፍሰሱና በመሠውያው ቀንድ ላይ መቀባቱ ምን ያመለክታል? ይህ ይሖዋ ደምን የኃጢአት ማስተሰርያ አድርጎ እንደሚቀበል ያሳያል። ጠቅላላው የስርየት ሥርዓት ከደም ጋር የተያያዘ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “ከጥቂት ነገሮች በስተቀር ሁሉም ነገር በደም መንጻት እንዳለበት ሕጉ ያዛል፤ ደም ሳይፈስ ስርየት የለምና” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 9:22

10:1, 2የአሮን ልጆች የናዳብና የአብዩድ ኃጢአት ምንን የሚጨምር ሊሆን ይችላል? ናዳብና አብዩድ በክህነት አገልግሎታቸው ወቅት ለእነርሱ ያልተፈቀደላቸውን ድርጊት በትዕቢት ከፈጸሙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ካህናት በቤተ መቅደሱ በሚያገለግሉበት ወቅት የወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር መጠጥ እንዳይጠጡ አዟል። (ዘሌዋውያን 10:9) ይህም የአሮን ልጆች ድርጊቱን የፈጸሙት በመጠጥ ኃይል ተገፋፍተው ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። ይሁን እንጂ የሞታቸው ዋነኛ መንስኤ ይሖዋ “ያላዘዛቸውን፣ ያልተፈቀደውን እሳት” ማቅረባቸው ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

10:1, 2 በጊዜያችን ኃላፊነት ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች ከሚፈለግባቸው መለኮታዊ ብቃት ጋር ተስማምተው መኖር አለባቸው። በተጨማሪም ኃላፊነቶቻቸውን ሲያከናውኑ በትዕቢት ቦታቸውን አልፈው መሄድ የለባቸውም።

10:9 የአልኮል መጠጥ ጠጥተን አምላክ የሰጠንን ኃላፊነት በስካር መንፈስ ማከናወን አይኖርብንም።

ቅዱስ አምልኮ ንጽሕናን ይጠይቃል

(ዘሌዋውያን 11:1 እስከ 15:33)

ንጹሕና ርኩስ የሆኑ እንስሳትን በሚመለከት የተሰጠው መመሪያ እስራኤላውያንን በሁለት መንገዶች ይጠቅማቸው ነበር። እነዚህ መመሪያዎች ሕዝቡ ጎጂ በሆኑ ተህዋሲያን እንዳይበከል ከመጠበቃቸውም በላይ በእነርሱና በዙሪያቸው በነበሩት አሕዛብ መካከል የነበረውን ልዩነት የበለጠ አጠናክረውታል። ሌሎቹ መመሪያዎች አስከሬን በመንካት መርከስን፣ ሴቶች በወሊድ ጊዜ የሚጠበቅባቸውን የመንጻት ሥርዓት፣ ከለምጽ ጋር በተያያዘ መደረግ የሚኖርባቸውን ነገሮችና ከወንድና ከሴት የጾታ ብልት ከሚወጡ ፈሳሾች ጋር በተያያዘ መርከስን የሚመለከቱ ነበሩ። ካህናት ከላይ በተጠቀሱት ሁኔታዎች የረከሱ ግለሰቦችን የማንጻት አገልግሎት ያከናውናሉ።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

12:2, 5—ልጅ መውለድ አንዲትን ሴት ‘የሚያረክሳት’ ለምንድን ነው? የመራቢያ አካላት የተፈጠሩት ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት እንዲያስተላልፉ ተደርገው ነው። ይሁን እንጂ በውርስ በሚተላለፈው ኃጢአት ምክንያት ወደ ልጁ የሚተላለፈው ፍጹም ያልሆነና ኃጢአተኛ ሕይወት ነው። በወሊድ እንዲሁም በወር አበባ ጊዜ ወይም ከወንድ ዘር መፍሰስ ጋር በተያያዘ ለተወሰነ ጊዜ ‘ርኩስ’ መሆን እስራኤላውያን ይህንን በውርስ የሚተላለፍ ኃጢአተኝነት እንዲያስታውሱ ይረዳቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 15:16-24፤ መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) ከዚህ ርኩሰት ለመንጻት የሚደረገው ሥነ ሥርዓት የሰውን ልጅ ከኃጢአቱ ለመዋጀትና ፍጹም እንዲሆን ለማድረግ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደሚያስፈልግ እስራኤላውያን እንዲገነዘቡ ይረዳቸው ነበር። በዚህ መንገድ ሕጉ ‘ወደ ክርስቶስ የሚያደርሳቸው ሞግዚታቸው ሆኗል።’—ገላትያ 3:24

15:16-18—በእነዚህ ቁጥሮች ላይ የተጠቀሰው ‘የዘር መፍሰስ’ ምንድን ነው? ይህ ሌሊት በእንቅልፍ ልብ የሚከሰተውንና በተጋቡ ባልና ሚስት መካከል በሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ወቅት የሚከሰተውን የዘር መፍሰስ የሚያመለክት ይመስላል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

11:45 ይሖዋ አምላክ ቅዱስ ስለሆነ ለእርሱ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡትም ቅዱሳን እንዲሆኑ ይፈልጋል። ቅዱስ ለመሆን ጥረት ማድረግ ያለባቸው ሲሆን በአካላዊና በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆን አለባቸው።—2 ቆሮንቶስ 7:1፤ 1 ጴጥሮስ 1:15, 16

12:8 ይሖዋ ድሆች ውድ በሆነው በግ ፋንታ የወፎች መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ፈቅዶላቸዋል። ይህም ለድሆች አሳቢ መሆኑን ያሳያል።

ቅድስና የግድ አስፈላጊ ነው

(ዘሌዋውያን 16:1 እስከ 27:34)

ከመሥዋዕቶች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሥዋዕት የሚቀርበው በዓመታዊው የስርየት ቀን ነበር። ለካህናቱና ለሌዊ ነገድ አንድ ወይፈን ይቀርባል። የክህነት መብት ለሌላቸው ሌሎች የእስራኤል ነገዶች አንድ ፍየል ይቀርባል። ሌላ ፍየል ደግሞ ካህኑ የሕዝቡን ኃጢአት ከተናዘዘበት በኋላ ወደ ምድረ በዳ ተወስዶ ይለቀቃል። ሁለቱም ፍየሎች እንደ አንድ የኃጢአት መሥዋዕት ተደርገው ይቆጠራሉ። ይህ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት እንደሚሆንና ኃጢአታችንን እንደሚያስወግድልን ያመለክታል።

ሥጋ መብላትንና ሌሎች ነገሮችን በሚመለከት የተሰጡት መመሪያዎች ይሖዋን ስናመልክ ቅዱስ መሆን እንዳለብን ያስገነዝቡናል። ካህናቱ ቅድስናቸውን መጠበቃቸው የተገባ ነበር። ሦስቱ ዓመታዊ ክብረ በዓላት የደስታና ለፈጣሪ ምሥጋና ማቅረብ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። በተጨማሪም ይሖዋ ቅዱስ ስሙን ማርከስንና የሰንበትና የኢዮቤልዩ በዓል አከባበርን በተመለከተ እንዲሁም ለድሆች ምን መደረግ እንዳለበትና ባሪያዎች እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ለሕዝቡ መመሪያዎችን ሰጥቶ ነበር። አምላክን መታዘዝ የሚያስገኛቸው በረከቶች ያለመታዘዝ ከሚያስከትለው ቅጣት ጋር ቀርበዋል። እንዲሁም ስዕለትንና ለስዕለት የሚከፈለውን ተመን፣ የእንስሳትን በኩራትና ከማንኛውም ነገር የሚገኘውን አሥራት ‘ለእግዚአብሔር የተቀደሰ’ አድርጎ መስጠትን የሚመለከቱ መመሪያዎችም ነበሩ።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

16:29—እስራኤላውያን ‘ሰውነታቸውን ማድከም’ የነበረባቸው እንዴት ነው? በሥርየት ቀን የሚደረገው ይህ ሥነ ሥርዓት የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ተብሎ የሚፈጸም ነበር። በጊዜው ጾም ኃጢአተኛ መሆንን አምኖ ከመቀበል ጋር ይያያዝ የነበረ ይመስላል። ከዚህ አንጻር ‘ሰውነትን ማድከም’ ሲባል መጾም ማለት ሳይሆን አይቀርም።

19:27—“የራስ ጠጉራችሁን ዙሪያ አትከርክሙ፤ ጢማችሁን አሳጥራችሁ አትቁረጡ” ሲባል ምን ማለት ነው? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ይህ ሕግ የተሰጠው እስራኤላውያን ከአንዳንድ አረማዊ ልማዶች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ጺማቸውን እንዳይላጩ ወይም ጸጉራቸውን እንዳይከረክሙ ለመከልከል ነበር። (ኤርምያስ 9:25, 26፤ 25:23፤ 49:32) ይሁን እንጂ አምላክ እስራኤላውያን ፈጽሞ ጺማቸውን ወይም ሪዛቸውን እንዳያሳጥሩ መከልከሉ አልነበረም።—2 ሳሙኤል 19:24

25:35-37—እስራኤላውያን በማንኛውም ሁኔታ ወለድ እንዳያስከፍሉ ተከልክለው ነበር? ግለሰቡ ገንዘቡን የተበደረው ለንግድ ዓላማ ከሆነ አበዳሪው ወለድ ማስከፈል ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ሕጉ በድህነቱ ምክንያት ከሚበደር ሰው ወለድ መጠየቅን ይከለክላል። ጎረቤታችን በኢኮኖሚ ችግር ላይ ሳለ በአጋጣሚው ተጠቅመን ለማትረፍ መሞከር ተገቢ አይደለም።—ዘፀአት 22:25

26:19—‘ሰማይ እንደ ብረት፣ ምድር እንደ ናስ’ የሚሆኑት እንዴት ነው? ዝናብ በመጥፋቱ የተነሳ በከነዓን ምድር ላይ የሚገኘው ሰማይ ጠብታ ውኃ በማያሳልፍ ብረት የተጋረደ ያህል ይሆናል። ምድሩ ደግሞ ዝናብ ባለማግኘቱ ነሐስ የሚመስል የበረሃነት መልክ ይኖረዋል።

26:26—“ዐሥር ሴቶች በአንድ ምጣድ ላይ እንጀራ ይጋግራሉ” ሲባል ምን ማለት ነው? አብዛኛውን ጊዜ አንዲት ሴት የሚያስፈልጓትን ነገሮች በሙሉ ለመጋገር እንድትችል የራሷ የሆነ ምጣድ ያስፈልጋታል። ይሁን እንጂ ከላይ ያሉት ቃላት የምግብ እጥረት ስለሚኖር አሥር ሴቶች ያላቸውን ለመጋገር አንድ ምጣድ እንደሚበቃቸው ለማሳየት የገቡ ናቸው። ይህ ቅድስናን አለመጠበቅ ከሚያስከትላቸው ችግሮች አንዱ ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

20:9 የጥላቻና የክፋት መንፈስ በይሖዋ ዓይን ነፍስ ከማጥፋት ተለይቶ አይታይም። በመሆኑም ይሖዋ ወላጁን በሚሳደብ ልጅ ላይ የወሰነው ቅጣት ለነፍስ ግድያ ከወሰነው ቅጣት ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር እንድናሳይ ሊገፋፋን አይገባም?—1 ዮሐንስ 3:14, 15

22:32፤ 24:10-16, 23 የይሖዋን ስም ማቃለል ተገቢ አይደለም። በተቃራኒው ስሙን ማወደስና እንዲቀደስ መጸለይ ይኖርብናል።—መዝሙር 7:17፤ ማቴዎስ 6:9

የዘሌዋውያን መጽሐፍ አምልኮታችንን እንዴት ይነካዋል?

በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሕጉ ሥር አይደሉም። (ገላትያ 3:23-25) ይሁን እንጂ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ ይሖዋ ስለተለያዩ ነገሮች ባለው አመለካከት ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ስለሚያስጨብጠን አምልኮታችንን በእጅጉ ይነካዋል።

ለቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመዘጋጀት ሳምንታዊውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በምታነብበት ወቅት ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ቅድስና እንደሚጠብቅ ስትገነዘብ ልብህ በጥልቅ እንደሚነካ አያጠራጥርም። በተጨማሪም የዘሌዋውያን መጽሐፍ ምንጊዜም ቅድስናህን ጠብቀህ እርሱን በማወደስ ለይሖዋ ምርጥህን እንድትሰጠው ሊያነሳሳህ ይችላል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በሕጉ መሠረት የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ለኢየሱስ ክርስቶስና ለቤዛዊ መሥዋዕቱ ጥላ ነበሩ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቂጣ በዓል እጅግ አስደሳች ወቅት ነበር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እንደ ዳስ በዓል ያሉት ዓመታዊ በዓላት ለይሖዋ ምሥጋና የማቅረቢያ አጋጣሚዎች ነበሩ