በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አሳዛኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝም የሚያረካ ሕይወት አሳልፌያለሁ

አሳዛኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝም የሚያረካ ሕይወት አሳልፌያለሁ

የሕይወት ታሪክ

አሳዛኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝም የሚያረካ ሕይወት አሳልፌያለሁ

ኦድሪ ሃይድ እንደተናገረችው

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍኳቸውን ከ63 የሚበልጡ ዓመታት (59ኙን በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት) መለስ ብዬ ሳስብ ሕይወቴ የሚያረካ እንደነበረ መናገር እችላለሁ። በእርግጥ የመጀመሪያው ባለቤቴ በካንሰር ምክንያት ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ሄዶ በመጨረሻ ሕይወቱ ሲያልፍ፣ ሁለተኛው ባለቤቴ ደግሞ ኦልዛይመርስ በተባለው በሽታ ሲሠቃይ መመልከት ልብ የሚሰብር ነው። እንደዚህ ያለ መከራ ቢደርስብኝም ደስተኛ ሆኜ መኖር የቻልኩት እንዴት እንደሆነ ላውጋችሁ።

የልጅነት ሕይወቴን ያሳለፍኩት በሰሜን ምሥራቅ ኮሎራዶ በነብራስካ ድንበር አጠገብ ባለው ገላጣ አካባቢ በምትገኝ ሃክስተን በምትባል ትንሽ መንደር አቅራቢያ ባለ የእርሻ ቦታ ነው። ወላጆቼ ኦረልና ኒና ሞክ ከወለዷቸው ስድስት ልጆች መካከል አምስተኛዋ ነኝ። ራስል፣ ዌን፣ ክላራ እና አርዲስ የተወለዱት ከ1913 እስከ 1920 ባሉት ዓመታት ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ እኔ ተወለድሁ። በ1925 ከርቲስ ተወለደ።

በ1913 እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (የይሖዋ ምሥክሮች በወቅቱ የሚጠሩበት ስም ነው) ሆነች። ከጊዜ በኋላ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላትም የእርሷን አርአያ ተከተልን።

ጥሩ አስተዳደግ

አባታችን አዳዲስ ሐሳቦችን ለመቀበል ፈጣን ነበር። በዚያ ዘመን የኤሌክትሪክ መብራት እምብዛም ያልተለመደ ቢሆንም በእርሻ ቦታችን ያሉት ቤቶች በሙሉ መብራት ነበራቸው። ከምናረባቸው ዶሮዎች እንቁላል፣ ከላሞቻችን ደግሞ ወተት፣ ክሬምና ቅቤ ስለምናገኝ ከግብርና ውጤቶችም እንጠቀም ነበር። መሬታችንን የምናርሰው ፈረሶች ጠምደን ሲሆን እንጆሪና ድንች እንዲሁም ስንዴና በቆሎ እናመርት ነበር።

አባታችን ሁላችንም ጥሩ የሥራ ልማድ ልናዳብር እንደሚገባ ያምን ነበር። በመሆኑም ትምህርት ቤት ከመግባቴ በፊት እንኳ በእርሻ ቦታችን መሥራት ተምሬ ነበር። ሞቃት በሆኑት የበጋ ቀኖች የአትክልት ቦታችንን ለረጅም ሰዓታት እየኮተኮትኩ አርም እንደነበር አስታውሳለሁ። ንቦች እየነደፉኝና ላብ በላብ ሆኜ አረሙን ስነቅል ‘መቼ ይሆን የምጨርሰው?’ ብዬ አስብ ነበር። ሌሎች ልጆች የእኛን ያህል ከባድ ሥራ ስለማይሠሩ አንዳንድ ጊዜ እንደተበደልሁ ይሰማኝ ነበር። ሆኖም አሁን መለስ ብዬ የልጅነት ጊዜዬን ሳስብ ወላጆቻችን መሥራት ስላስተማሩን አመሰግናቸዋለሁ።

ሁላችንም የሥራ ምድብ ነበረን። አርዲስ ላሞቹን ስታልብ ከእኔ ይልቅ ጎበዝ ስለነበረች እርሷ ስታልብ እኔ ደግሞ የፈረሶቹን ፋንድያ በአካፋ እየዛቅሁ ጋጣውን አጸዳለሁ። አብዛኛውን ጊዜያችንን በሥራ የምናሳልፍ ቢሆንም የምንጫወትበትም ጊዜ ነበረን። እኔና አርዲስ ኳስ እንጫወት ነበር።

ገላጣ በሆነው የኮሎራዶ አካባቢ ጥርት ባለው ሰማይ ላይ በምሽት ከዋክብቱ ሲታዩ በጣም ያምራሉ። በሺዎች የሚቆጠሩት ከዋክብት ፈጣሪያችንን ይሖዋን እንዳስታውስ ያደርጉኝ ነበር። ልጅ እያለሁም እንኳ “[ይሖዋ] የከዋክብትን ብዛት ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል” የሚለው የመዝሙር 147:4 ጥቅስ ወደ አእምሮዬ ይመጣ ነበር። ጥርት ባሉት በእነዚያ ምሽቶች አብዛኛውን ጊዜ ውሻችን ጃጅ ጭንቅላቱን ጭኔ ላይ አድርጎ አብሮኝ ይቆይ ነበር። ብዙ ጊዜ ከሰዓት በኋላ በረንዳችን ላይ እቀመጥና ንፋሱ የስንዴውን እሸት ወዲያና ወዲህ ሲያወዛውዘው በፀሐይዋ ብርሃን የሚፈጠረውን ብርማ ቀለም እየተመለከትሁ እደመም ነበር።

የእናታችን ግሩም ምሳሌነት

እማማ በጣም አፍቃሪና ታታሪ ሚስት ነበረች። አባባ የቤተሰቡ ራስ እንደመሆኑ ልናከብረው እንደሚገባ አስተምራናለች። በ1939 እርሱም የይሖዋ ምሥክር ሆነ። አባታችን ከባድ ሥራ የሚያሠራን ከመሆኑም ሌላ ባያቀብጠንም እንደሚወድደን ግን እናውቅ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ክረምት ሲመጣ ፈረሶች አንድ ላይ ይጠምድና በበረዶ ላይ የሚንሸራተት ጋሪ ሠርቶ ያጫውተናል። በሚያንጸባርቀው በረዶ ላይ መንሸራተት በጣም ያስደስተን ነበር!

ለአምላክ ፍቅር እንዲያድርብንና ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲኖረን ያሠለጠነችን ግን እናታችን ናት። የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነና የሕይወት ምንጭ እርሱ መሆኑን አስተምራናለች። (መዝሙር 36:9፤ 83:18 NW) ከዚህም በላይ መመሪያዎች የሰጠን ደስታ ሊያሳጣን ሳይሆን ለጥቅማችን መሆኑን ተምረናል። (ኢሳይያስ 48:17) እማማ ልናከናውነው የሚገባ ልዩ ሥራ እንዳለ ሁልጊዜ ትነግረን ነበር። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሎ እንደነገራቸው እናውቅ ነበር።—ማቴዎስ 24:14

ልጅ ሳለሁ ከትምህርት ቤት ስመለስ እማማን እቤት ካላገኘዃት ግቢው ውስጥ እየዞርኩ እፈልጋት ነበር። አንድ ቀን የስድስት ወይም የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ እንደ ልማዴ ስፈልጋት የከብቶቹ በረት ውስጥ አገኘዃት። እዚያው እያለን ኃይለኛ ዶፍ መጣል ስለጀመረ የከብቶቹ ገፈራ በሚደረግበት ቆጥ ላይ ወጥተን ተቀመጥን። በዚህ ጊዜ አምላክ የጥፋት ውኃ ሊያመጣ እንደሆነ ጠየቅዃት። አምላክ ምድርን ዳግመኛ በውኃ ላለማጥፋት ቃል እንደገባ ነገረችኝ። አካባቢያችን በተደጋጋሚ ጊዜያት በኃይለኛ አውሎ ንፋስ ይመታ ስለነበር ከንፋስ መጠለያ እንዲሆን ወደተሠራው በቤታችን አቅራቢያ ወደሚገኘው ምድር ቤት ሮጬ እገባ እንደነበር አስታውሳለሁ።

እማማ እኔ ከመወለዴ በፊትም በስብከቱ ሥራ ትካፈል ነበር። በቤታችን ስብሰባ ይካሄድ የነበረ ሲሆን ሁሉም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመኖር ተስፋ ነበራቸው። እማማ ከቤት ወደ ቤት መሄድ ቢከብዳትም ለይሖዋ ያላት ፍቅር ፍርሃቷን ለማሸነፍ ረድቷታል። ኅዳር 24, 1969 በ84 ዓመቷ እስከሞተችበት ዕለት ድረስ ታማኝ ነበረች። በጆሮዋ “እማማ ወደ ሰማይ መሄድሽ ነው፤ እዚያም ከምታውቂያቸው ሰዎች ጋር ትሆኛለሽ” አልኳት። በሞተችበት ዕለት አጠገቧ ሆኜ በተስፋዋ ላይ ስላለኝ እምነት ልነግራት በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር! እርሷም “በጣም ጥሩ ልጅ ነሽ” ስትል በለሆሳስ መለሰችልኝ።

መስበክ ጀመርን

በ1939 ራስል አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆነ። በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ቤቴል ተብሎ በሚጠራው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት እንዲያገለግል በ1944 እስከተጋበዘበት ጊዜ ድረስ በኦክላሆማና በነብራስካ በአቅኚነት አገልግሏል። እኔም ከመስከረም 20, 1941 ጀምሮ በኮሎራዶ፣ በካንሳስና በነብራስካ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። በአቅኚነት ያሳለፍኳቸው እነዚያ ዓመታት አስደሳች ነበሩ፤ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ መርዳት ከመቻሌም በላይ በእርሱ መታመንን ተምሬያለሁ።

ራስል አቅኚ በሆነበት ጊዜ አካባቢ ዌን ለተወሰነ ጊዜ ሰብዓዊ ሥራ ከሠራ በኋላ ኮሌጅ ገባ። በኋላ ላይ በቤቴል እንዲያገለግል የተጋበዘ ሲሆን ኒው ዮርክ ውስጥ ኢተካ አቅራቢያ በሚገኘው ኪንግደም ፋርም ለተወሰኑ ዓመታት አገልግሏል። በዚያ ለሚገኙት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የቤቴል ቤተሰብ አባላትና በብሩክሊን ቤቴል ላሉት ወደ 200 የሚጠጉ ሠራተኞች የሚሆን ምግብ የሚመረተው በዚህ ቦታ ነበር። ዌን በ1988 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ችሎታውንና ልምዱን ይሖዋን ለማገልገል ተጠቅሞበታል።

እህቴ አርዲስ ጄምስ ከርን የተባለ ወንድም ያገባች ሲሆን አምስት ልጆች አፍርተዋል። አርዲስ በ1997 ሞተች። ክላራ የተባለችው ሌላዋ እህቴ አሁንም ድረስ ይሖዋን በታማኝነት ታገለግላለች፤ እረፍት በምሆንበት ጊዜ ኮሎራዶ ወደሚገኘው ቤቷ እየሄድኩ እጠይቃታለሁ። የመጨረሻው ወንድማችን ከርቲስ በ1940ዎቹ አጋማሽ አካባቢ በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል ጀመረ። የተለያዩ ዕቃዎችንና የግብርና ውጤቶችን በከባድ መኪና ጭኖ ወደ ብሩክሊንና ኪንግደም ፋርም ያመላልስ ነበር። ከርቲስ በ1971 በሞት ያንቀላፋ ሲሆን ትዳር አልመሠረተም ነበር።

ቤቴል የመግባት ምኞቴ እውን ሆነ

ታላላቅ ወንድሞቼ ቀደም ብለው ቤቴል ገብተው ስለነበር በዚያ የማገልገል ፍላጎት አደረብኝ። የእነርሱ መልካም ምሳሌነት እኔም ወደ ቤቴል እንድጠራ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አልጠራጠርም። እናቴ ስለ አምላክ ድርጅት ከምትነግረን ታሪክ በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ቀን ስለሚሆኑት ነገሮች የሚናገረው ትንቢት ሲፈጸም መመልከቴ በቤቴል የማገልገል ፍላጎቴ እንዲያድግ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሖዋ በቤቴል እንዳገለግል ከፈቀደልኝ ልፈጽማቸው የሚገቡኝ ሌሎች ክርስቲያናዊ ግዴታዎች ካላጋጠሙኝ በቀር ፈጽሞ ከቤቴል እንደማልወጣ በጸሎት ቃል ገባሁ።

ሰኔ 20, 1945 ወደ ቤቴል ተጠራሁ፤ የሥራ ምድቤ ጽዳት ነበር። ይህም በየዕለቱ 13 ክፍሎች ማጽዳትን፣ 26 አልጋዎች ማንጠፍን እንዲሁም ኮሪደሮችንና ደረጃዎችን ማጽዳትን ያካትታል። መስታወቶችንም እወለውል ነበር። ሥራው አድካሚ ነው። በየቀኑ ሥራዬን በማከናውንበት ጊዜ ‘ቢደክመኝም የአምላክ ቤት በሆነው በቤቴል ውስጥ ነኝ!’ በማለት ራሴን አበረታታ ነበር።

ቤቴል ማገልገል እንደጀመርኩ አካባቢ አንድ የሚያሳፍር ነገር አጋጠመኝ። ያደግሁት ገጠር በመሆኑ ደምዌተር (dumbwaiter) ስለሚባለው ዕቃዎችን ከአንድ ፎቅ ወደ ሌላ ፎቅ ለማጓጓዝ የሚያገለግል አነስተኛ አሳንሰር ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። አንድ ቀን ሥራ ላይ እያለሁ አንድ ወንድም ስልክ ደወለና “እባክሽ ደምዌተሩን ወደታች ላኪው” አለኝ። የደወለው ሰው ስልኩን ቶሎ ስለዘጋው ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ተጋባሁ። ወዲያው ግን እኔ በማጸዳው ፎቅ ላይ ከሚኖሩት ወንድሞች አንዱ አስተናጋጅ (ዌተር) መሆኑን አስታወስኩ። ስለዚህ የዚህን ወንድም ክፍል አንኳኳሁና “ታች ወጥ ቤት ይፈልጉሃል” አልኩት።

ናታን ኖርን አገባሁ

ከ1920ዎቹ ጀምሮ በነበሩት ዓመታት ማግባት የፈለጉ ቤቴላውያን ከቤቴል ወጥተው በሌሎች ምድቦች ላይ እንዲያገለግሉ ይደረግ ነበር። በ1950ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ግን ረዘም ላለ ጊዜ በቤቴል ያገለገሉ አንዳንድ ጥንዶች ከተጋቡ በኋላም በዚያው እንዲቀጥሉ ተፈቀደላቸው። ስለዚህ በወቅቱ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ በኃላፊነት ይመራ የነበረው ናታን ሆመር ኖር ለጋብቻ እንደሚፈልገኝ ሳውቅ ‘እሱን እንኳን በምንም ዓይነት ከቤቴል አያስወጡትም!’ ስል አሰብኩ።

ናታን የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ በበላይነት በመከታተል ረገድ በርካታ ኃላፊነቶች ነበሩት። ስለዚህ ለጋብቻ ያቀረበልኝን ጥያቄ ከመቀበሌ በፊት ጉዳዩን በጥሞና ላስብበት እንደሚገባ የተለያዩ ነጥቦች በማንሳት ግልጹን ነገረኝ። በዚያን ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመጎብኘት አዘውትሮ ይጓዝ ስለነበር በአብዛኛው ለሳምንታት ያህል አይኖርም ነበር። በመሆኑም ረዘም ላሉ ጊዜያት ልንለያይ እንደምንችል ነገረኝ።

ወጣት እያለሁ ከመጋቢት እስከ ግንቦት አካባቢ ባሉት የጸደይ ወራት ለማግባትና ለጫጉላ ሽርሽር በፓስፊክ ወደሚገኙት የሃዋይ ደሴቶች ለመሄድ እመኝ ነበር። ከናታን ጋር የተጋባነው ግን ጥር 31, 1953 በክረምት ወቅት ሲሆን ቅዳሜ ከሰዓትና እሁድ የጫጉላ ጊዜያችንን ያሳለፍነው ኒው ጀርሲ ውስጥ ነበር። ከዚያም ሰኞ ጠዋት ወደ ሥራ ተመለስን። ሆኖም በቀጣዩ ሳምንት ለሰባት ቀናት ያህል ለጫጉላ ሽርሽር ሄድን።

ታታሪ አጋር

ናታን በ1923 ወደ ቤቴል ሲመጣ የ18 ዓመት ወጣት ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በበላይነት ይመራ እንደነበረው እንደ ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ እንዲሁም የሕትመት ክፍል ኃላፊ እንደነበረው እንደ ሮበርት ማርቲን ካሉት ልምድ ያላቸው ወንድሞች ጥሩ ሥልጠና አግኝቷል። መስከረም 1932 ወንድም ማርቲን ሲሞት ናታን የሕትመት ክፍሉ ኃላፊ ሆነ። በቀጣዩ ዓመት ወንድም ራዘርፎርድ በአውሮፓ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ሲጎበኝ ናታንን ይዞት ሄደ። ጥር 1942 ወንድም ራዘርፎርድ ሲሞት ናታን ዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በበላይነት እንዲመራ ኃላፊነት ተሰጠው።

ናታን አርቆ ተመልካች ነበር፤ ሁልጊዜም እድገት ሊኖር እንደሚችል አስቀድሞ በማሰብ እቅድ ያወጣል። አንዳንዶች የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በጣም እንደቀረበ ያስቡ ስለነበር የእርሱ አካሄድ ትክክል አልመሰላቸውም። እንዲያውም ናታን ለሕትመት ሥራው እቅድ ሲያወጣ የተመለከተ አንድ ወንድም “ምን ማለትህ ነው ወንድም ኖር? መጨረሻው እንደቀረበ አታምንም ማለት ነው?” በማለት ጠይቆታል። ናታንም “አምናለሁ፤ ሆኖም መጨረሻው እኛ እንዳሰብነው ቶሎ ባይመጣ ዝግጁ እንሆናለን” ሲል መለሰለት።

ናታን ለሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ሊቋቋም እንደሚገባ አጥብቆ ያምን ነበር። በመሆኑም የካቲት 1, 1943 ወንድሜ ዌን በዚያን ጊዜ በሚያገለግልበት ሰፊ የቤቴል የእርሻ ቦታ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ተቋቋመ። በትምህርት ቤቱ የሚሰጠው ሥልጠና ለአምስት ወራት ገደማ የሚዘልቅ ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ያካተተ ቢሆንም ናታን ተማሪዎቹ እንዲዝናኑ ያደርግ ነበር። ትምህርት ቤቱ እንደተጀመረ አካባቢ ከተማሪዎቹ ጋር ኳስ ይጫወት ነበር፤ በኋላ ላይ ግን በጨዋታው ወቅት ጉዳት ደርሶበት በበጋው ወቅት በሚከናወኑት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንቅፋት እንዳይሆንበት በመፍራት መጫወቱን ተወና ዳኛ ሆነ። ተማሪዎቹ ናታን ከሌሎች አገሮች ለመጡት ተጫዋቾች በማድላት ሆን ብሎ የጨዋታውን ሕግ ሲያፈርስ መመልከት ያስደስታቸው ነበር።

ከናታን ጋር መጓዝ

ከጊዜ በኋላ ከናታን ጋር ወደ ተለያዩ አገሮች መጓዝ ጀመርኩ። በቤቴል ከሚያገለግሉት ፈቃደኛ ሠራተኞችና ከሚስዮናውያኑ ጋር መጫወት ያስደስተኝ ነበር። ፍቅራቸውንና ቅንዓታቸውን በቅርበት መመልከት ከመቻሌም በላይ በየዕለቱ ስለሚያከናውኑት ሥራና በተመደቡባቸው አገሮች ስላለው የኑሮ ሁኔታ ይነግሩኝ ነበር። እነዚህ ወንድሞች በዚያ ወቅት ላደረግንላቸው ጉብኝት ምስጋናቸውን በመግለጽ አሁንም ድረስ ይጽፉልኛል።

ከናታን ጋር ስላደረግናቸው ጉዞዎች ሳስብ በርካታ ገጠመኞቻችን ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ። ለአብነት ያህል፣ ፖላንድን በጎበኘንበት ወቅት ሁለት እህቶች እኔ አጠገባቸው እያለሁ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ተመለከትሁ። “ለምንድን ነው በሹክሹክታ የምታወሩት?” ብዬ ስጠይቃቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በፖላንድ ታግዶ በነበረበት ወቅት ባለ ሥልጣናቱ ምሥክሮቹ የሚያወሩትን ለመስማት ቤታቸው ውስጥ የድምጽ መቅረጫ ስለሚደብቁ በሹክሹክታ መነጋገር እንደለመደባቸው በመግለጽ ይቅርታ ጠየቁኝ።

በፖላንድ ሥራችን ታግዶ በነበረበት ወቅት ከነበሩት በርካታ ምሥክሮች አንዷ እህት አዳህ ናት። እህት አዳህ ፀጉሯን ግንባሯ ላይ ትደፋው ነበር። አንድ ቀን ወደ ግንባሯ ያመጣችውን ፀጉር አንስታ ግንባሯ ላይ ያለውን ትልቅ ጠባሳ አሳየችኝ፤ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያሳድድ አንድ ሰው መቷት ነበር። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በተፈጸመባቸው ጭካኔ የተሞላበት በደል የተነሳ የደረሰባቸውን ጉዳት በገዛ ዓይኔ ስመለከት አዘንኩ።

ከቤቴል ቀጥሎ በጣም የምወደው ቦታ ሃዋይ ነው። በ1957 ሃዋይ ውስጥ በሂሎ ከተማ ያደረግነው የአውራጃ ስብሰባ አይረሳኝም። በስብሰባው ላይ በአካባቢው ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተገኙ ሲሆን የማይረሳ ጊዜ ነበር። እንዲያውም ከንቲባው ለናታን የከተማዋን ቁልፍ ሰጥቶታል። ብዙዎች መጥተው ሰላም ያሉን ሲሆን በአበባ ጉንጉኖችም አስጊጠውናል።

ሌላው አስደሳች የአውራጃ ስብሰባ በ1955 በኑረምበርግ፣ ጀርመን የሂትለር ወታደሮች ይሰለፉበት በነበረው ቦታ የተደረገው ስብሰባ ነው። ሂትለር በጀርመን የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን እንደሚያጠፋ መዛቱ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፤ ሆኖም በዚህ ስብሰባ ላይ ስታዲየሙ በይሖዋ ምሥክሮች ተጨናንቆ ነበር! ይህን ስመለከት እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። መድረኩ በጣም ሰፊ ሲሆን ከኋላ በኩል 144 ትላልቅ አምዶች ነበሩ። በመድረኩ ላይ ሆኜ ከ107,000 በላይ የሆኑትን ተሰብሳቢዎች ለመቃኘት ሞከርኩ። ከተሰብሳቢዎቹ ብዛት የተነሳ በመጨረሻው ረድፍ የተቀመጡትን መመልከት ያስቸግራል።

የጀርመን ወንድሞች ያሳዩትን ጽናት እንዲሁም በናዚ አገዛዝ የደረሰባቸውን ስደት መቋቋም እንዲችሉ ይሖዋ ኃይል እንደሰጣቸው መመልከት ችለናል። ይህም እኛ ራሳችን ታማኞች ሆነን ከይሖዋ ጎን በጽናት እንድንቆም አቋማችንን አጠናክሮልናል። ናታን የመደምደሚያውን ንግግር ካቀረበ በኋላ እጁን በማውለብለብ ተሰብሳቢዎቹን ተሰናበታቸው። እነርሱም በምላሹ መሃረቦቻቸውን ሲያውለበልቡ ሜዳው በሚያማምሩ አበቦች ያሸበረቀ ይመስል ነበር።

በታኅሣሥ ወር 1974 ወደ ፖርቹጋል ያደረግነው ጉዞም የማይረሳ ትዝታ ጥሎብናል። የስብከቱ ሥራችን ሕጋዊ ከሆነ በኋላ በሊዝበን በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ነበር የሄድነው። ሥራችን ለ50 ዓመታት ያህል ታግዶ ነበር። በወቅቱ በአገሪቱ የነበሩት የመንግሥቱ አስፋፊዎች 14,000 ብቻ ቢሆኑም በዚያ በተደረጉት ሁለት ስብሰባዎች ላይ ከ46,000 በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። ወንድሞች “ነፃነት ስላገኘን ከአሁን በኋላ መደበቅ አያስፈልገንም” ብለው ሲናገሩ ዓይኖቼ እንባ አቀረሩ።

ከናታን ጋር እጓዝ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ አሁንም ድረስ በአውሮፕላንና በሬስቶራንቶች ውስጥ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመስከርና ከመንገድ ወደ መንገድ ማገልገል ያስደስተኛል። ሁልጊዜ ምሥክርነት መስጠት እንድችል ጽሑፎች እይዛለሁ። በአንድ ወቅት አውሮፕላን ዘግይቶብን ስንጠብቅ ሳለ አንዲት ሴት የት እንደምሠራ ጠየቀችኝ። ይህም ከእርሷና በአጠገባችን ከነበሩ ሌሎች ሰዎች ጋር ውይይት ለማድረግ መንገድ ከፈተልኝ። የቤቴል አገልግሎትና የስብከቱ ሥራ ደስተኛ እንድሆንና በሥራ እንድጠመድ አድርጎኛል።

የናታን መታመምና የስንብት ማበረታቻ

በ1976 ናታን ካንሰር እንዳለበት ታወቀ፤ የቤቴል ቤተሰብ አባላት እርሱን በማስታመም ረድተውኛል። ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ቢሄድም በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለሥልጠና ወደ ብሩክሊን ቤቴል የመጡ የተለያዩ ወንድሞችን ወደ ክፍላችን እንጋብዝ ነበር። ዶንና ኧርሊን ስቲል፣ ሎይድና ሜልባ ባሪ፣ ዳግላስና ሜሪ ገስት፣ ማርቲንና ገርትሩድ ፖትጺንገር፣ ፕሪስ ሂዩዝ እና ሌሎችም በርካታ ወንድሞችና እህቶች እንደጠየቁን አስታውሳለሁ። አብዛኛውን ጊዜ በተመደቡባቸው አገሮች ያጋጠማቸውን ተሞክሮ ያጫውቱን ነበር። በተለይ እገዳ ባለባቸው አገሮች ወንድሞቻችን ያሳዩትን ጽናት የሚገልጹት ተሞክሮዎች በጥልቅ ይነኩኝ ነበር።

ናታን የሚሞትበት ጊዜ እንደተቃረበ ሲገነዘብ ብቸኝነቴን ለመቋቋም የሚረዱኝ ጥሩ ምክሮች ሰጠኝ። “ብዙ ሰዎች የሌላቸው አስደሳች ትዳር ነበረን” አለኝ። ትዳራችን አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ነገር ናታን አሳቢ መሆኑ ነበር። ለምሳሌ በጉዞ ላይ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ስንገናኝ “ኦድሪ፣ አንዳንድ ጊዜ የማላስተዋውቅሽ ስማቸው ስለሚጠፋኝ ነው” ይለኝ ነበር። አስቀድሞ ስለነገረኝ ደስ ይለኛል።

ናታን “ስንሞት ተስፋችን የተረጋገጠ ይሆናል፤ ከዚያ በኋላ አንሠቃይም” ካለኝ በኋላ እንዲህ ሲል አጥብቆ መከረኝ “ሽልማትሽን የምትቀበይው ወደፊት ስለሆነ ያንን ጊዜ አሻግረሽ ለመመልከት ሞክሪ። ምንም እንኳ ትዝታዎቹ ከአእምሮሽ ባይጠፉም ያለፈውን ሕይወትሽን በማስታወስ አትብሰልሰይ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ትጽናኛለሽ። ባጋጠመሽ ሁኔታ ከሚገባው በላይ በማዘን ምሬት እንዲያድርብሽ አትፍቀጂ። እንደዚህ ያለ አስደሳች ጊዜ በማሳለፍሽና ባገኘሻቸው በረከቶች ደስ ይበልሽ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እነዚህ ትዝታዎች ያስደስቱሻል። ያሳለፍነውን ጊዜ የማስታወስ ችሎታችን ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ ነው።” አክሎም “ሌሎችን የሚጠቅም ነገር በማከናወን ሕይወትሽ በሥራ የተጠመደ እንዲሆን ጥረት አድርጊ። እንዲህ ማድረግሽ በሕይወትሽ ደስተኛ እንድትሆኚ ይረዳሻል” አለኝ። ብዙም ሳይቆይ ሰኔ 8, 1977 ናታን ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቀቀ።

ግሌን ሃይድን አገባሁ

ናታን ያለፈውን ሕይወቴን እያሰብኩ መኖር አሊያም አዲስ ሕይወት መጀመር እንደምችል ነግሮኝ ነበር። ስለዚህ በ1978 በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ዋችታወር ፋርምስ ከተዛወርኩ በኋላ ግሌን ሃይድን አገባሁ። ግሌን በጣም ቆንጆ፣ ጭምትና ረጋ ያለ ሰው ነው። የይሖዋ ምሥክር ከመሆኑ በፊት ዩናይትድ ስቴትስ ከጃፓን ጋር ስትዋጋ በባሕር ኃይል ውስጥ አገልግሏል።

ግሌን ይሠራ የነበረው በቶርፔዶ አሳሽ ጀልባ ላይ ሲሆን ምድቡም ሞተሩ ባለበት ክፍል ነበር። ከሞተሩ ድምጽ የተነሳ የመስማት ችሎታው በከፊል ተጎድቷል። ከጦርነቱ በኋላ የእሳት አደጋ መከላከያ ውስጥ መሥራት ጀመረ። በጦርነቱ ወቅት የተመለከተው ነገር ለበርካታ ዓመታት ያቃዠው ነበር። እውነትን የሰማው ጸሐፊው መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክራለት ነው።

ቆይቶም በ1968 ግሌን በብሩክሊን ቤቴል የእሳት አደጋ ተከላካይ ሆኖ እንዲሠራ ተጠራ። ከዚያም በዋችታወር ፋርምስ የእሳት አደጋ መከላከያ ሲቋቋም በ1975 ወደዚያ ተዛወረ። ከጊዜ በኋላ ኦልዛይመርስ በተባለው በሽታ በመያዙ ከተጋባን ከአሥር ዓመታት በኋላ ሕይወቱ አለፈ።

ሃዘኔን መቋቋም የቻልኩት እንዴት ነው? ናታን መሞቻው እንደተቃረበ ሲያውቅ የሰጠኝ ጥበብ ያዘለ ምክር በዚህ ጊዜም አጽናንቶኛል። የመበለትነትን ሕይወት እንዴት ልቋቋመው እንደምችል የጻፈልኝን ማስታወሻ ደጋግሜ አነበዋለሁ። አሁን ድረስ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ላጡ ሰዎች ይህንን ምክር የማካፍላቸው ሲሆን እነርሱም ናታን በሰጠኝ ምክር ተጽናንተዋል። በእርግጥም ናታን እንዳለኝ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ ይጠቅማል።

ውድ የሆነ የወንድማማች ማኅበር

ሕይወቴ አርኪና አስደሳች እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት በቤቴል ቤተሰብ ውስጥ ያሉት ውድ ጓደኞቼ ናቸው። ከእነዚህም መካከል በ1944 ከጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሦስተኛ ክፍል የተመረቀችው ኤስተር ሎፔዝ ተጠቃሽ ናት። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ወደ ስፓኒሽ በመተርጎሙ ሥራ ለመካፈል የካቲት 1950 ወደ ብሩክሊን ቤቴል ተመለሰች። ናታን በማይኖርባቸው ጊዜያት የቅርብ ጓደኛዬ ነበረች። አሁን እርሷም የምትኖረው በዋችታወር ፋርም ነው። በአሁኑ ጊዜ በ90ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ ሲሆን ጤንነቷ እያሽቆለቆለ በመሆኑ ቤቴል ውስጥ በሚገኘው የአረጋውያን መንከባከቢያ ክፍል እንክብካቤ ይደረግላታል።

ከቅርብ የቤተሰቤ አባላት መካከል አሁን በሕይወት ያሉት ራስልና ክላራ ብቻ ናቸው። ራስል ዕድሜው ከ90 በላይ ቢሆንም አሁንም በብሩክሊን ቤቴል በታማኝነት እያገለገለ ነው። ካገቡ በኋላ በቤቴል ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ከተፈቀደላቸው የመጀመሪያዎቹ ወንድሞች አንዱ ነው። በ1952 ጂን ላርሰን የተባለች ቤቴላዊት አገባ። የጂን ወንድም ማክስ ቤቴል የገባው በ1939 ሲሆን በ1942 ናታንን ተክቶ የሕትመት ሥራው ኃላፊ ሆነ። ማክስ አሁንም በቤቴል በርካታ ኃላፊነቶች ያሉት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ መልቲፕል ስክለሮሲስ በተባለው በሽታ የምትሠቃየውን ውድ ባለቤቱን ይንከባከባል።

ይሖዋን በሙሉ ጊዜ በማገልገል ያሳለፍኳቸውን ከ63 የሚበልጡ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ሕይወቴ አርኪ ነበር ብዬ መናገር እችላለሁ። ቤቴል ቤቴ ሆኗል፤ አሁንም ከልብ በመነጨ ደስታ እዚህ ማገልገሌን እቀጥላለሁ። ወላጆቻችን ጥሩ የሥራ ልማድ እንድናዳብር ስላሠለጠኑንና ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርብን ስለረዱን ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። ከምንም ነገር በላይ በሕይወት ውስጥ እርካታ የሚያስገኘው ግን ድንቅ የሆነው የወንድማማች ማኅበራችን እና ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ታላቁን ፈጣሪያችንን ይሖዋን ለዘላለም እያገለገልን ከወንድሞችና እህቶቻችን ጋር ገነት በሆነች ምድር ላይ የመኖር ተስፋችን ነው።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰኔ 1912፣ ወላጆቼ በሠርጋቸው ዕለት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከግራ ወደ ቀኝ ራስል፣ ዌን፣ ክላራ፣ አርዲስ፣ እኔ እና ከርቲስ በ1927

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1944 በአቅኚነት ስናገለግል፣ በፍራንሲስና ባርባራ መክኖት መካከል ቆሜ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1951 በቤቴል፣ ከግራ ወደ ቀኝ እኔ፣ ኤስተር ሎፔዝና የወንድሜ ሚስት ጂን

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከናታንና ከወላጆቹ ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1955 ከናታን ጋር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከናታን ጋር በሃዋይ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሁለተኛው ባለቤቴ ከግሌን ጋር