በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢየሱስ ተአምራት—እውነተኛ ታሪክ ወይስ ምናባዊ ፈጠራ?

የኢየሱስ ተአምራት—እውነተኛ ታሪክ ወይስ ምናባዊ ፈጠራ?

የኢየሱስ ተአምራት—እውነተኛ ታሪክ ወይስ ምናባዊ ፈጠራ?

“በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ።” (ማቴዎስ 8:16) “እርሱም [ኢየሱስም] ተነሥቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ ‘ጸጥ፣ ረጭ በል!’ አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ [ረ]ጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ።” (ማርቆስ 4:39) እነዚህን ጥቅሶች እንዴት ትመለከታቸዋለህ? በገሃዱ ዓለም የተፈጸሙ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው ብለህ ታምናለህ? ወይስ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው የፈጠራ ታሪኮች ወይም ተረቶች እንደሆኑ ይሰማሃል?

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ፈጽሟቸዋል የሚባሉት ተአምራት እውነተኛ መሆናቸውን እንደሚጠራጠሩ ይናገራሉ። እንደ ቴሌስኮፕና ማይክሮስኮፕ ያሉ መሣሪያዎች በተፈለሰፉበት እንዲሁም በጠፈር ምርምርና በጀነቲክ ምኅንድስና በመጠቀው በዚህ ዘመን ለተአምራዊ ክስተቶችና ከሰው በላይ በሆነ ኃይል ይፈጸማሉ ለሚባሉ ድንቅ ነገሮች ጆሯቸውን የሚሰጡ ሰዎች ያን ያህል ብዙ አይደሉም።

አንዳንድ ሰዎች ስለ ተአምራት የሚናገሩት ዘገባዎች ምናባዊ ፈጠራ ወይም ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ታሪኮች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። የኢየሱስን “እውነተኛ ማንነት” ይመረምራል የተባለለት አንድ መጽሐፍ አዘጋጅ ክርስቶስ ስለፈጸማቸው ተአምራት የሚናገሩት ታሪኮች ክርስትናን ለማስፋፋት የሚያገለግሉ “ማስታወቂያዎች” እንደሆኑ ተናግረዋል።

ሌሎች ደግሞ የኢየሱስን ተአምራት ዓይን ያወጡ የማታለል ድርጊቶች አድርገው ይመለከቷቸዋል። አንዳንድ ጊዜም ኢየሱስ ራሱ አታላይ የሚል ክስ ይቀርብበታል። በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኖረው ጀስቲን ማርቲር እንደዘገበው ተቺዎች ኢየሱስን “አስማተኛና ሕዝቡን የሚያታልል ብለው እስከ መጥራትም ደርሰዋል።” አንዳንዶች ኢየሱስ “ተአምራቱን ለመፈጸም የቻለው አይሁዳዊ ነቢይ ስለነበረ ሳይሆን በአረማዊ ቤተ መቅደሶች ውስጥ የሠለጠነ አስማተኛ ስለሆነ ነው” ብለው ይከራከራሉ።

ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ሲባል ምን ማለት ነው?

ከዚህ ሁሉ ጥርጣሬ በስተጀርባ ሰዎች በተአምራት እንዳያምኑ ያደረጋቸው ጠንካራ ምክንያት ሳይኖር አይቀርም ብለህ ታስብ ይሆናል። በአጭሩ ተአምራቶቹ የተፈጸሙት ከሰው አቅም በላይ በሆነ ኃይል ሊሆን ይችላል የሚለውን ሐሳብ መቀበል ስለሚከብዳቸው ነው። ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም ብሎ የሚያምን አንድ ወጣት “ተአምር የሚባል ነገር ጨርሶ የለም” ካለ በኋላ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ዴቪድ ሂዩም የተባለው ስኮትላንዳዊ ፈላስፋ የጻፈውን በመጥቀስ “ተአምር የተፈጥሮ ሕግጋትን የሚጻረር ነው” ብሏል።

ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች አንድን ክስተት ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው ብለው በእርግጠኝነት ለመናገር አይደፍሩም። ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ተአምር ለሚለው ቃል “እስካሁን በታወቁት የተፈጥሮ ሕግጋት ሊብራራ የማይችል ክስተት” የሚል ትርጉም ሰጥቶታል። በዚህ ፍቺ መሠረት ወደ ጠፈር የሚደረግ ጉዞ፣ ያለ ስልክ ሽቦ መልእክት ማስተላለፍ ወይም በሳተላይት እየተመሩ አቅጣጫን ማወቅ ከመቶ ዓመታት በፊት እንደ “ተአምር” የሚቆጠሩ ነበሩ። በመሆኑም አሁን ባለን እውቀት ላይ ተመርኩዘን ልናብራራቸው ስላልቻልን ብቻ ተአምራት ሊፈጸሙ አይችሉም ማለቱ አስተዋይነት አይደለም።

ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽሟቸዋል የሚባሉትን ተአምራት አስመልክቶ ካሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች መካከል አንዳንዶቹን ብንመረምር ምን መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን? የኢየሱስ ተአምራት እውነተኛ ታሪክ ናቸው ወይስ ምናባዊ ፈጠራ?