በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በጋና ክረምት አይቋረጡም’

‘በጋና ክረምት አይቋረጡም’

ዕጹብ ድንቅ የሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት

‘በጋና ክረምት አይቋረጡም’

በረሃው ላይ ፀሐይዋ እንደ እሳት ትፋጃለች። በሌሎች የምድር ክፍሎች ደግሞ ቀዝቃዛው ክረምት ካለፈ በኋላ አካባቢውን ታሞቃለች። አዎን፣ የፀሐይ ሙቀት የተለያዩ የአየር ንብረቶች እንዲኖሩና ወቅቶች እንዲፈራረቁ ከሚያስችሉት ዋነኛ መንስኤዎች መካከል አንዱ ነው።

በምድር ዙሪያ ወቅቶች ከቦታ ቦታ ይለያያሉ። ይሁንና የወቅቶች መፈራረቅ ምን ስሜት ይፈጥርብሃል? በበልግ ወቅት በሚጥለው ካፊያ መንፈስህ አይታደስም? ክረምት ሲገባ ምን ይሰማሃል? መስከረም ጠብቶ ጋራ ሸንተረሩ በአበቦች ሲያሸበርቅ በደስታ አትፈነድቅም? የመከር ወቅት አብቅቶ ገበሬዎች ጎተራቸው በእህል በሚሞላበት የበጋዎቹ ወራት ልብህ በደስታ አይሞላም?

ወቅቶች እንዲፈራረቁ የሚያደርገው ምንድን ነው? በአጭሩ ምድር ያጋደለች መሆኗ ነው። ምድር በፀሐይ ዙሪያ ከምትጓዝበት ጠፍጣፋ የሐሳብ መስመር አንጻር ሲታይ ዛቢያዋ 23.5 ዲግሪ ገደማ ዘመም ያለ ነው። የምድር ዛቢያ ያዘመመ ባይሆን ኖሮ የወቅቶች መፈራረቅ ባልኖረ ነበር። የአየሩ ንብረት ዓመቱን በሙሉ አንድ ዓይነት ይሆን ነበር። ይህ ደግሞ በእጽዋቶች እድገትና በሰብል ምርት ዑደት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

የወቅቶች መፈራረቅ እንዲኖር ያደረገው ፈጣሪ መሆኑ ግልጽ ነው። መዝሙራዊው ይሖዋ አምላክን አስመልክቶ በትክክል እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የምድርን ዳርቻ ሁሉ የወሰንህ አንተ ነህ፤ በጋውንም ክረምቱንም አንተ ሠራህ።”መዝሙር 74:17 a

ከምድር ላይ ሆኖ ለሚመለከት ሰው በሰማይ ላይ ያሉ ግዑዝ አካላት አስተማማኝ ጊዜ ጠቋሚዎች ሆነው ያገለግላሉ። አምላክ እኛ ያለንበትን ሥርዓተ ፀሐይ በፈጠረበት ወቅት “ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ” ሲል ደንግጓል። (ዘፍጥረት 1:14 የ1954 ትርጉም) ምድር ምህዋሯን ተከትላ በምታደርገው ጉዞ የምድር ወገብ ላይ ከቀኑ በስድስት ሰዓት ፀሐይ በቀጥታ ከአናት በላይ የምትሆንባቸው ሁለት ቦታዎች አሉ። ይህ ክስተት መሳ ቀንና ሌሊት (equinoxes) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በብዙ አገሮች ጸደይና በልግ የሚጀምርበትን ጊዜ ያመለክታል። መሳ ቀንና ሌሊት በሚሆንባቸው ጊዜያት በምድር ዙሪያ የቀኑና የማታው ርዝመት እኩል ነው።

የወቅቶች መኖርና መፈራረቅ፣ የጠፈር አካላት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። ወቅቶች እንዲሁም የአየር ንብረትና ሁኔታ ውስብስብ በሆነ ሥርዓት እርስ በርሳቸው ተሳስረው ሕይወት ላላቸው ነገሮች የግድ አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎችን ያሟላሉ። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኛው በርናባስ በትንሿ እስያ ለነበሩት አብዛኞቹ ስለ ግብርናና ስለ ሰብል ምርት ሰፊ እውቀት ላላቸው ሰዎች ‘ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን የሚሰጣቸው፣ ደግሞም ልባቸውን በመብልና በደስታ የሚያረካላቸው’ አምላክ መሆኑን ገልጸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 14:14-17

ፎቶሲንቴሲስ የሚባለው አስደናቂ የሆነ ምግብ የማምረት ሂደት በምድር ላይ አረንጓዴ ተክሎች፣ በባሕር ውስጥ ደግሞ ውኃ ውስጥ የሚኖሩ እጽዋት እንዲኖሩ ያስችላል። ከዚህም የተነሳ የአየር ጠባይና የአየር ንብረት ሕያዋን በሆኑ ነገሮች መካከል ባለው ትስስርና በብዝሃ ሕይወት ላይ የሚያስከትሉት ውጤት በጣም የተወሳሰበ ነው። ጳውሎስ ይህ ሁሉ የይሖዋ እጅ እንዳለበት በትክክል ገልጿል:- “ዘወትር በእርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣና ለሚያርሷትም ፍሬ የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች።”—ዕብራውያን 6:7

የጸደይ ወቅት በሚጀምርባቸው ቦታዎች የሚኖረውን ተስማሚ የሙቀት መጠን፣ ቀኑ ረጅም መሆኑ፣ ከበፊቱ የበለጠ የፀሐይ ብርሃን መገኘቱና ጥሩ ዝናብ መዝነቡን ቆም ብላችሁ ካሰባችሁ ‘በረከት’ የሚለው ቃል ልዩ ትርጉም ይይዛል። አበቦች ያብባሉ፤ ነፍሳት ደግሞ አበቦችን ለማራባት ተዘጋጅተው ከክረምት ቤታቸው ይወጣሉ። እዚህ ላይ የሚታየው ብሉ ጄል የሚባለውን የመሳሰሉ ወፎች ጫካ ውስጥ ውር ውር ሲሉና ሲዘምሩ አካባቢው ነፍስ ይዘራበታል። ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ እንቅስቃሴ ይጀምራሉ እንዲሁም የመውለድ፣ የመዋለድና የማደግ ዑደት እንደገና ይቀጥላል። (ማሕልየ መሓልይ 2:12, 13) በክረምት ማብቂያ ወይም በበጋ መጀመሪያ ላይ የሚኖረው የመከር ወቅት የሚጀምረው በዚህ መልክ ነው።—ዘፀአት 23:16

ይሖዋ ምድር ዘመም ብላ እንድትቀመጥ በማድረግ ቀንና ማታ፣ የተለያዩ ወቅቶች እንዲሁም ዘር የሚዘራበትና የሚሰበሰብበት ጊዜ የሰጠ ሲሆን በዚህም የፍጥረት ሥራዎቹ በግልጽ ይታያሉ። ክረምት አልፎ በጋ እንደሚመጣ የሚጠራጠር ሰው የለም። ደግሞም “ምድር እስካለች ድረስ፣ የዘር ወቅትና መከር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት፣ አይቋረጡም” በማለት ቃል የገባው አምላክ ነው።—ዘፍጥረት 8:22

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የ2004 የይሖዋ ምሥክሮች ቀን መቁጠሪያ ሐምሌና ነሐሴን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ የሰማይ አካል

በታሪክ ዘመናት በሙሉ ጨረቃ የሰዎችን ቀልብ ስትማርክና ስታስደምም ቆይታለች። ይሁንና ጨረቃ በወቅቶች መፈራረቅ ላይ ተጽዕኖ እንደምታሳድር ታውቃለህ? የጨረቃ መኖር፣ ምድር ያጋደለችበት መጠን ማለትም የምትሽከረከርበት ዛቢያ ያዘመመበት መጠን ቋሚ እንዲሆን ይረዳል። ሳይንሳዊ ጽሑፎችን የሚያዘጋጁት አንድሩ ሂል ይህ ሁኔታ “በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲገኙ ወሳኝ ሚና” አለው ሲሉ ገልጸዋል። የምድር ዛቢያ ያዘመመበት መጠን ቋሚ እንዲሆን የሚያስችል ግዙፍ የሰማይ አካል ባይኖር ኖሮ የሙቀቱ መጠን በጣም ስለሚያሻቅብ በምድር ላይ ሕይወት ያለው ነገር አይኖርም ነበር። በመሆኑም አንድ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ቡድን “ጨረቃ በምድር ላይ ያለውን የአየር ንብረት ትቆጣጠራለች ሊባል ይችላል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል።—መዝሙር 104:19

[ምንጭ]

Moon: U.S. Fish & Wildlife Service, Washington, D.C./Bart O’Gara

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሰሜን አፍሪካና በአረቢያ ባሕር ሰርጥ የሚገኙ ግመሎች