በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈጣሪህን ለማክበር መንፈሳዊ ግቦች አውጣ

ፈጣሪህን ለማክበር መንፈሳዊ ግቦች አውጣ

ፈጣሪህን ለማክበር መንፈሳዊ ግቦች አውጣ

“አንድ ሰው የሚያርፍበትን ወደብ አስቀድሞ ካልወሰነ ነፋሱ ወደ የትኛውም አቅጣጫ ቢነፍስ ግድ አይሰጠውም።” በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረ ሮማዊ ፈላስፋ እንደተናገራቸው የሚገመቱት እነዚህ ቃላት ሕይወት አንድ ዓይነት አቅጣጫ እንዲይዝ ግብ አስፈላጊ የመሆኑን እውነታ ያጎላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ በግብ ይመሩ ስለነበሩ ሰዎች ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ኖኅ ‘ቤተሰቦቹን ለማዳን የሚያስችለውን መርከብ ለመሥራት’ ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት በትጋት ሠርቷል። ነቢዩ ሙሴ “ወደፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአል።” (ዕብራውያን 11:7, 26) በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱ የከነዓን ምድርን ድል አድርጎ እንዲይዝ አምላክ ግብ አውጥቶለት ነበር።—ዘዳግም 3:21, 22, 28፤ ኢያሱ 12:7-24

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” በማለት በተናገራቸው ቃላት ላይ ያተኮሩ መንፈሳዊ ግቦች እንደነበሩት ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 24:14) ጳውሎስ ‘በአሕዛብ ፊት የኢየሱስን ስም እንዲሸከም’ የተሰጠውን ኃላፊነት ጨምሮ ከጌታ ከኢየሱስ በግል ባገኛቸው መልእክቶችና በገለጠለት ራእይ ተበረታቶ በትንሿ እስያና በአውሮፓ በርካታ የክርስቲያን ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።—የሐዋርያት ሥራ 9:15፤ ቆላስይስ 1:23

አዎ፣ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የይሖዋ አገልጋዮች ጥሩ ግቦች የነበሯቸው ከመሆኑም በላይ ግቦቻቸው ላይ በማድረስ ለይሖዋ ክብር አምጥተዋል። በዛሬው ጊዜ እኛስ መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት የምንችለው እንዴት ነው? የትኞቹ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣጣር አለብን? እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ምን ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?

ትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት ያስፈልጋል

አንድ ሰው በማንኛውም የሕይወት ዘርፉ ግብ ሊያወጣ ይችላል፤ ለእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴዎቻችን ግብ ማውጣት እንችላለን። በዓለማችን ላይ ደግሞ በግብ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች የሚያወጧቸው ግቦች በዓለም ያሉ ሰዎች ከሚደክሙላቸው ምኞቶች ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። በዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች ግብ የሚያወጡት ሀብት ለማካበትና ሥልጣን ለማግኘት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ነው። ሥልጣንና ዝና ለማግኘት መሯሯጥ ትልቅ ስህተት ነው! የምናወጣቸው ግቦች ለይሖዋ አምላክ ክብር የሚያመጡት ለእርሱ ከምናቀርበው አምልኮና የመንግሥቱን ፍላጎት ከማስቀደማችን ጋር የተያያዙ ከሆኑ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 6:33) እንዲህ ያሉ ግቦች ለይሖዋና ለሰዎች ካለን ፍቅር እንዲሁም ለአምላክ ያደርን ለመሆን ካለን ፍላጎት የሚመነጩ ናቸው።—ማቴዎስ 22:37-39፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:7 NW

መንፈሳዊ ግቦችን የምናወጣውና ግቦቻችን ላይ ለመድረስ የምንጣጣረው ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችን ለማግኘትም ይሁን በግል መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ከትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት የመነጨ መሆን ይኖርበታል። ይሁንና ትክክለኛ ውስጣዊ ዝንባሌ ቢኖረንም ግባችን ላይ መድረስ የማንችልባቸው ጊዜያት አሉ። ታዲያ ግቦች ማውጣትና እዚያ ላይ የመድረስ አጋጣሚያችንን ማስፋት የምንችለው እንዴት ነው?

ግባችን ላይ የመድረስ ጠንካራ ፍላጎት የግድ አስፈላጊ ነው

ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን እንዴት እንደፈጠረ ተመልከት። “መሸ፤ ነጋም” የሚሉት ቃላት ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን ለማከናወን ተከታታይ ክፍለ ጊዜያት እንደወሰነ ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 1:5, 8, 13, 19, 23, 31) ይሖዋ በእያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ መጀመሪያ ላይ በዚያ ቀን ለማከናወን ያወጣው በግልጽ የተቀመጠ ግብ ወይም ዓላማ ነበረው። ደግሞም አምላክ ለመፍጠር ያሰባቸውን ነገሮች በሚገባ አከናውኗል። (ራእይ 4:11) ኢዮብ “እርሱ [ይሖዋ] የፈቀደውን ያደርጋል” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 23:13) ይሖዋ “ያደረገውን ሁሉ” አይቶ “እጅግ መልካም” እንደሆነ በተናገረ ጊዜ በሥራው በጣም ረክቶ መሆን አለበት!—ዘፍጥረት 1:31

እኛም ግባችን እውን እንዲሆን ውጥናችንን ከዳር የማድረስ ከፍተኛ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ያለ ጠንካራ ፍላጎት ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ ምድር ቅርጽ አልባና ባዶ በነበረችበት ወቅት እንኳ ለእርሱ ክብርና ምስጋና የምታመጣ ውብ እንቁ ሆና ትታየው ነበር። እኛም በተመሳሳይ እቅዳችንን ዳር ማድረሳችን በሚያስገኝልን ውጤትና ጥቅም ላይ ማሰላሰላችን ግባችንን ለመምታት ያለንን ፍላጎት ያሳድግልናል። የ19 ዓመቱ ቶኒ ይህን የመሰለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። በምዕራብ አውሮፓ የሚገኝን አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በጎበኘበት ወቅት የተሰማውን ስሜት ፈጽሞ አይረሳውም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘ያን በመሰለ ቦታ መኖርና መሥራት ምን ይመስል ይሆን?’ የሚል ጥያቄ በአእምሮው ይጉላላ ነበር። ቶኒ ቤቴል ስለመግባት ማሰቡን አላቆመም፤ እንዲያውም እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰዱን ቀጠለ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በቅርንጫፍ ቢሮው ለማገልገል ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ በጣም ተደሰተ!

አንድ ግብ ላይ መድረስ ከቻሉ ሰዎች ጋር መቀራረባችን እኛም እዚያ ግብ ላይ የመድረስ ፍላጎት እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል። የ30 ዓመቱ ጄሰን በአሥራዎቹ ዕድሜው መጀመሪያ ላይ ሳለ አገልግሎት መውጣት አያስደስተውም ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ግን የአቅኚነት አገልግሎት በመጀመር የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ ሆነ። ጄሰን አቅኚ የመሆን ፍላጎት እንዲያድርበት የረዳው ምን ነበር? “ከአቅኚዎች ጋር የማደርገው ጭውውትና አብሬያቸው ማገልገሌ በጎ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል” ሲል ተናግሯል።

ግቦቻችንን በጽሑፍ ማስፈር ጠቃሚ ነው

አንድ ያሰብነውን ነገር በቃላት ለመግለጽ ስንሞክር ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል። ሰሎሞን ትክክለኛ ቃላት ልክ እንደ ሹል የከብት መንጃ ሕይወትን አቅጣጫ ለማስያዝ የሚያስችል ኃይል እንዳላቸው ገልጿል። (መክብብ 12:11) እነዚህን ቃላት በጽሑፍ ማስፈር ደግሞ በአእምሮና በልብ ላይ ለመቅረጽ ያስችላል። ይሖዋ የእስራኤል ነገሥታት ለግል ቅጂ እንዲሆናቸው ሕጉን በእጃቸው እንዲገለብጡ ያዘዘው ለዚህ አልነበረም? (ዘዳግም 17:18) እኛም ያወጣናቸውን ግቦች፣ እነዚህ ግቦች ላይ እንዴት መድረስ እንደምንችል፣ ያጋጥሙናል ብለን የምናስባቸውን መሰናክሎችና እነዚህን መሰናክሎች እንዴት መወጣት እንደምንችል በጽሑፍ ማስፈር እንችላለን። ልናውቃቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች፣ ማዳበር ስለሚኖርብን ችሎታ እንዲሁም ሊረዱንና ሊደግፉን የሚችሉ ሰዎችን በአእምሯችን መያዛችንም ሊረዳን ይችላል።

በእስያ በሚገኝ አንድ አገር ውስጥ ባለ ገለልተኛ ክልል ለረጅም ጊዜ ልዩ አቅኚ ሆኖ ያገለገለው ጄፍሪ መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣቱ የመረጋጋት ስሜት እንዲኖረው ረድቶታል። ባለቤቱን በድንገት በሞት ማጣቱ መሪር ሐዘን አስከትሎበታል። የእርሷ ሞት ካስከተለበት ሐዘን ከተጽናና በኋላ ግቦች በማውጣት ሙሉ በሙሉ በአቅኚነት አገልግሎቱ ለመጠመድ ወሰነ። እቅዶቹን በጽሑፍ አስፍሮ በጸሎት ካሰበበት በኋላ በወሩ መጨረሻ ላይ ሦስት ጥናቶች ለማግኘት ግብ አወጣ። በየዕለቱ ስላደረገው እንቅስቃሴ መለስ ብሎ ያስብ ነበር፤ እንዲሁም በየአሥር ቀኑ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማወቅ ራሱን ይገመግም ነበረ። ታዲያ ግቡ ላይ መድረስ ችሎ ይሆን? እንዴታ! እንዲያውም አራት የመጽሐፍ ቀዱስ ጥናቶችን ማግኘቱ አስደስቶታል።

መሸጋገሪያ የሚሆኑ የአጭር ጊዜ ግቦችን አውጣ

የምናወጣቸው አንዳንድ ግቦች መጀመሪያ ላይ የሚደረስባቸው ላይመስሉ ይችላሉ። ቀደም ብለን የጠቀስነው ቶኒ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ገብቶ ማገልገል የሕልም እንጀራ መስሎ ታይቶት ነበር። እንደዚህ ሊሰማው የቻለው ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ይመራ ስለነበረና ገና ራሱን ለአምላክ ወስኖ ስላልተጠመቀ ነበር። ነገር ግን ቶኒ ሕይወቱን ከይሖዋ መንገዶች ጋር ለማስማማትና ለጥምቀት የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ግብ አወጣ። ከተጠመቀ በኋላም በቀን መቁጠሪያው ላይ ቀኖቹን ምልክት እያደረገ ረዳት አቅኚ ከዚያም የዘወትር አቅኚ ለመሆን ግብ አወጣ። አቅኚ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቅርንጫፍ ቢሮ ገብቶ ማገልገል ሊደረስበት የሚችል ግብ መሆኑን ተገነዘበ።

እኛም የረጅም ጊዜ ግቦችን በአጭር ጊዜ ሊደረስባቸው በሚችሉ ጥቂት ግቦች መከፋፈላችን ጥሩ ሊሆን ይችላል። እነዚህ የአጭር ጊዜ ግቦች ወደ ዋናው ግባችን ለመድረስ እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ ሆነው ሊያገለግሉን ይችላሉ። ምን ደረጃ ላይ እንደደረስን ለማወቅ ዘወትር መለስ ብለን ራሳችንን መገምገማችን አእምሯችን በግባችን ላይ እንዲያተኩር ይረዳናል። ወደ ይሖዋ በተደጋጋሚ ስለ እቅዳችን መጸለያችንም በጥረታችን እንድንገፋበት ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሳታቋርጡ ጸልዩ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል።—1 ተሰሎንቄ 5:17

የዓላማ ጽናትና መንፈሰ ጠንካራነት ያስፈልጋል

በጣም ያሰብንባቸውና በእጅጉ የምንመኛቸው ቢሆኑም እንኳ አንዳንድ ግቦች ላይ መድረስ ሊያቅተን ይችላል። ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ማርቆስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ይዞት ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምን ያህል አዝኖ ይሆን! (የሐዋርያት ሥራ 15:37-40) ማርቆስ ካጋጠመው አሳዛኝ ሁኔታ ትምህርት ማግኘትና የአገልግሎት እንቅስቃሴውን ከፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ግብ ማውጣት ነበረበት። ደግሞም እንደዚያ አድርጓል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጳውሎስ ስለ ማርቆስ ጥሩ ነገር የተናገረ ሲሆን በባቢሎን ያገለግል ከነበረው ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋርም የቅርብ ወዳጅነት እስከመመሥረት ደርሷል። (2 ጢሞቴዎስ 4:11፤ 1 ጴጥሮስ 5:13) እርግጥ ማርቆስ ያገኘው ከሁሉ የላቀ መብት በአምላክ መንፈስ እየተመራ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት መጻፉ ሳይሆን አይቀርም።

እኛም መንፈሳዊ ግቦቻችን ላይ ለመድረስ ስንጣጣር የተለያዩ መሰናክሎች ያጋጥሙን ይሆናል። ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ከግባችን ምን ያህሉን መፈጸም እንደቻልን መለስ ብለን ራሳችንን መመርመር፣ ያወጣነው ግብ ምክንያታዊና ሊደረስበት የሚችል መሆኑን መገምገምና አስፈላጊ ከሆነም ሌላ ግብ ማውጣት ይገባናል። እንቅፋቶች በሚያጋጥሙን ጊዜ በዓላማችን በመጽናት መንፈሰ ጠንካራ ሆነን ልንጋፈጣቸው ይገባናል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ምሳሌ 16:3

ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች ፈጽሞ ግባችን ላይ እንዳንደርስ ያግዱን ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ጤና ማጣት ወይም የቤተሰብ ኃላፊነቶች አቅማችንን ይገድቡት ይሆናል። ቢሆንም የመጨረሻው ሽልማት በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ወይም ወደ ሰማይ መሄድ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። (ሉቃስ 23:43፤ ፊልጵስዩስ 3:13, 14) ይህ ሽልማት ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:17) ምንም እንኳን ሁኔታችን አንድ ዓይነት ግብ ላይ ለመድረስ ባይፈቅድልንም ‘እግዚአብሔርን መፍራታችንንና ትእዛዛቱን መጠበቃችንን’ መቀጠል እንችላለን። (መክብብ 12:13) መንፈሳዊ ግቦች የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ እንድናተኩር ይረዱናል። ስለሆነም ፈጣሪያችንን ለማወደስ የሚያስችሉ ግቦች እናውጣ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ልናወጣቸው የምንችላቸው መንፈሳዊ ግቦች

መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ

እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትም ማንበብ

የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል

የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራት

አንዳንድ የአገልግሎት መብቶች ለማግኘት መጣጣር

በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ መሆን

በስልክ የመመሥከር፣ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት የመስጠት፣ በሥራ ቦታዎች የማገልገልና የመሳሰሉት ችሎታዎቻችንን ማዳበር