በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀጰዶቅያ—በነፋስና በውኃ በተቀረጹ ዋሻዎች ውስጥ መኖር

ቀጰዶቅያ—በነፋስና በውኃ በተቀረጹ ዋሻዎች ውስጥ መኖር

ቀጰዶቅያ—በነፋስና በውኃ በተቀረጹ ዋሻዎች ውስጥ መኖር

ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው የመጀመሪያው ደብዳቤ ላይ ቀጰዶቅያን ጠቅሷል። ደብዳቤውን ከላከላቸው ሰዎች መካከል “በቀጰዶቅያ፣ . . . ተበትነው በመጻተኝነት” የሚኖሩ ክርስቲያኖች ይገኙበት ነበር። (1 ጴጥሮስ 1:1) ቀጰዶቅያ ምን ዓይነት ቦታ ነበር? ነዋሪዎቹስ ከድንጋይ በተወቀሩ ዋሻዎች ውስጥ የሚኖሩት ለምንድን ነው? ከክርስትና ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት እንዴት ነበር?

በ1840ዎቹ ቀጰዶቅያን የጎበኘው እንግሊዛዊው ተጓዥ ዊሊያም ኤፍ ኤንስዎርዝ “በጉዞ ላይ እያለን በድንገት እንደ ጫካ ችምችም ያሉ ረጃጅም ቋጥኞችና የአለት አምዶች የሚገኙበት ቦታ ላይ ደረስን” ብሎ ነበር። ዛሬም ቢሆን ወደዚህ የቱርክ ክፍል የሚመጡ ጎብኚዎች የአካባቢውን ልዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ቅርጽ ሲመለከቱ በአድናቆት ይደመማሉ። በቀጰዶቅያ ሸለቆ ውስጥ እንደ ክብር ዘብ የተደረደሩት ቋጥኞች ከድንጋይ የተቀረጹ “ሐውልቶች” ይመስላሉ። አንዳንዶቹ ግዙፍ ጭስ መውጫዎች የሚመስሉ ሲሆን 30 ሜትር ወይም ከዚያ የሚበልጥ ቁመት አላቸው። ሌሎቹ ደግሞ የሐውልት ወይም የጅብ ጥላ የሚመስል ቅርጽ አላቸው።

ፀሐይዋ በእነዚህ ቋጥኞች ላይ ስታርፍ በጣም የሚያምር ቀለም የምታጎናጽፋቸው ሲሆን ቀለማቱ እንደ ሰዓቱ ይቀያየራሉ። ጎሕ ሲቀድ ፈዛዛ የሆነ ሐምራዊ ቀለም ያላቸው ይመስላል። ቀትር ላይ ደግሞ ሽሮ መልክ የሚይዙ ሲሆን ጀንበር ስትጠልቅ ወደ ቢጫ የሚያደላ ቡናማ ቀለም ይኖራቸዋል። እነዚህ “ረጃጅም ቋጥኞችና የአለት አምዶች” የተፈጠሩት እንዴት ነው? የአካባቢው ሰዎችስ ከእነዚህ አለቶች ተፈልፍለው በተሠሩ ዋሻዎች መኖር የጀመሩት ለምንድን ነው?

በነፋስና በውኃ የተቀረጹ ቋጥኞች

ቀጰዶቅያ እስያንና አውሮፓን በሚያገናኘው የአናቶሊያ ባሕረ ገብ መሬት አማካይ ቦታ ላይ ትገኛለች። በአካባቢው ሁለት የእሳተ ገሞራ ተራራዎች ባይኖሩ ኖሮ አካባቢው ጠፍጣፋ ኮረብታ እንደሆነ ይቀር ነበር። ሆኖም ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በእነዚህ ተራራዎች ላይ የተከሰተው ኃይለኛ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ አካባቢውን በሁለት ዓይነት አለቶች ማለትም ጠንካራ በሆነ ጥቁር ድንጋይና ከእሳተ ገሞራው አመድ በተፈጠረ በሃ ድንጋይ ሸፈነው።

ለስላሳው በሃ ድንጋይ በወንዞች፣ በዝናብና በነፋስ ሲሸረሸር ሸለቆዎች ተፈጠሩ። ከዚያም በጊዜ ሂደት በሸለቆዎቹ ዳርና ዳር ያሉት አለቶች እየተከፋፈሉና እየተሰባበሩ ሲሄዱ እንደ አምድ ቀጥ ብለው የቆሙ በርካታ ቋጥኞች የተፈጠሩ ሲሆን አካባቢውን በሌላ በየትኛውም የምድር ክፍል የማይገኝ ውበት አላብሰውታል። አንዳንዶቹ ቋጥኞች በላያቸው ላይ ካላቸው ቀዳዳዎች የተነሳ የንብ እንጀራ ይመስላሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ለስላሳውን በሃ ድንጋይ እየፈለፈሉ ዋሻዎችን በመሥራት በዚያ የሚኖሩ ሲሆን ቤተሰቡ እያደገ ሲሄድ አለቱን እየወቀሩ ተጨማሪ ክፍሎች ያዘጋጃሉ። ዋሻዎቹ በበጋ ወቅት ቀዝቃዛ በክረምት ደግሞ ሞቃት ስለሆኑ ለመኖሪያነት ተስማሚ ሆነው አግኝተዋቸዋል።

የተለያዩ ሥልጣኔዎች መገናኛ መሥመር

በቀጰዶቅያ ዋሻዎች የሚኖሩት ሰዎች በተለያዩ ሥልጣኔዎች መገናኛ መስመር ላይ የሚገኙ ባይሆኑ ኖሮ ከነመኖራቸው ጨርሶ ትዝ የሚለው አልነበረም። ሲልክ ሮድ ተብሎ የሚጠራውና ከቻይና ወደ ሮም ግዛት ሐር ይጓጓዝበት የነበረው የ6,500 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የንግድ መስመር ቀጰዶቅያን አቋርጦ ያልፋል። ከነጋዴዎች በተጨማሪም የፋርስ፣ የግሪክና የሮም ወታደሮች በዚህ መስመር ተጉዘዋል። አዳዲስ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ለአካባቢው ያስተዋወቁት እነዚህ ተጓዦች ናቸው።

በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በቀጰዶቅያ የሚኖሩ አይሁዳውያን ነበሩ። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከዚህ አካባቢ የመጡ አይሁዳውያን የጰንጠቆስጤን በዓል ለማክበር በኢየሩሳሌም ተገኝተው ነበር። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ ከፈሰሰ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን ምሥክርነት ከቀጰዶቅያ የመጡ አይሁዳውያንም አዳምጠው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-9) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ለመልእክቱ ምላሽ ሰጥተው አዲሱን እምነታቸውን ይዘው ወደ አገራቸው ሳይሄዱ አይቀርም። በመሆኑም ጴጥሮስ በመጀመሪያው ደብዳቤው ላይ የቀጰዶቅያ ክርስቲያኖችን ሊጠቅስ ችሏል።

ይሁን እንጂ ዓመታቱ እያለፉ ሲሄዱ በቀጰዶቅያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአረማዊ ፍልስፍናዎች ተጽዕኖ ሥር ወደቁ። እንዲያውም በአራተኛው ክፍለ ዘመን ሦስት ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸው የቀጰዶቅያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነውን የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ደግፈው ተከራክረው ነበር። እነዚህ መሪዎች የኔዚየንዘሱ ግሪጎሪ፣ ታላቁ ባሲልና ወንድሙ የኒሳው ግሪጎሪ ነበሩ።

ታላቁ ባሲል የብሕትውና ኑሮንም ያበረታታ ነበር። ከድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩት የቀጰዶቅያ ተራ ዋሻዎች ባሲል ያስፋፋው ለነበረው የገዳም ሕይወት ተስማሚ ነበሩ። የገዳሙ ኅብረተሰብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ በትላልቆቹ ቋጥኞች ውስጥ ሁሉም ነገር የተሟላላቸው ቤተ ክርስቲያኖች ይሠሩ ጀመር። በ13ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ሦስት መቶ የሚጠጉ ከአለት የተወቀሩ ቤተ ክርስቲያኖች ተሠርተው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ እስከዛሬ ድረስ ይገኛሉ።

እርግጥ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ቤተ ክርስቲያኖቹና ገዳማቶቹ ከአገልግሎት ውጪ ቢሆኑም የአካባቢው ሰዎች የኑሮ ሁኔታ እምብዛም አልተለወጠም። አብዛኞቹ ዋሻዎች አሁንም በመኖሪያነት ያገለግላሉ። ቀጰዶቅያን የሚጎበኙ ሰዎች የአካባቢው ነዋሪዎች የተፈጥሮ ውጤት የሆኑትን እነዚህን ቋጥኞች እንዴት ፈልፍለው ወደ መኖሪያነት እንደቀየሯቸው ሲመለከቱ በአድናቆት መፍዘዛቸው አይቀርም።

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቀጰዶቅያ

ቻይና (ካቴይ)