በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትልቅ ትርጉም ያለው ልደት

ትልቅ ትርጉም ያለው ልደት

ትልቅ ትርጉም ያለው ልደት

‘ዛሬ መድኅን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው።’ሉቃስ 2:11

የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በቤተልሔም ከተማ ውስጥ አንዲት ሴት ወንድ ልጅ ተገላገለች። ከአካባቢው ነዋሪዎች ውስጥ የዚህ ሕፃን መወለድ ምን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክንውን እንደሆነ የተገነዘቡት ብዙም አልነበሩም። መንጎቻቸውን በሜዳ እየጠበቁ ያደሩ ጥቂት እረኞች ግን በርካታ መላእክት “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!” እያሉ ሲዘምሩ ተመለከቱ።—ሉቃስ 2:8-14

ከዚያም እረኞቹ መላእክቱ በነገሯቸው መሠረት ማርያምንና ባሏን ዮሴፍን በጋጣ ውስጥ አገኟቸው። ማርያም ለሕፃኑ ኢየሱስ የሚል ስም ያወጣችለት ሲሆን መላእክቶቹ እንዳሉት በጋጣው ውስጥ በነበረ ግርግም ላይ አስተኝታው ነበር። (ሉቃስ 1:31፤ 2:12) ይህ ከሆነ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ አልፈዋል። በዛሬው ጊዜ ከዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ የሚል ሲሆን ከኢየሱስ ልደት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙት ክንውኖችም የሰው ዘር በኖረባቸው ዘመናት ሁሉ ከተነገሩት ታሪኮች የበለጠ ተተርከዋል።

የካቶሊክ ወጎች ሥር በሰደዱባትና ባሕላዊ ክብረ በዓላት በደመቀ ሁኔታ በሚከበሩባት በስፔይን ኢየሱስ የተወለደበት ይህ ልዩ ምሽት በተለያዩ መንገዶች ይከበራል።

የገና አከባበር በስፔይን

ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የኢየሱስን ልደት የሚያሳዩ ምስሎችና ቅርጾች የስፔይን የገና አከባበር ሥነ ሥርዓት የተለመዱ ገጽታዎች እየሆኑ መጥተዋል። ብዙ ቤተሰቦች ሕፃኑ ኢየሱስ ከተኛበት ጋር የሚመሳሰል አነስተኛ ግርግም ይሠራሉ። እንዲሁም እረኞቹን፣ ሰብዓ ሰገልን (ወይም “ሦስቱን ነገሥታት”)፣ ዮሴፍን፣ ማርያምንና ኢየሱስን የሚወክሉ ከሸክላ የተሠሩ ምስሎች ይዘጋጃሉ። በገና በዓል ሰሞን በሰው ቁመት ልክ የሚሠሩ ቅርጾች አብዛኛውን ጊዜ በከተማ አዳራሾች አቅራቢያ የሚቆሙ ሲሆን ስለ ኢየሱስ ልደት በሚናገረው የወንጌል ዘገባ ላይ ሕዝቡ ትኩረት እንዲያደርግ በሚል በጣሊያን ይህን ልማድ ያስጀመረው የአሲዚ ተወላጅ የሆነ ፍራንሲስ የተባለ ቄስ እንደሆነ ይታሰባል። ከጊዜ በኋላ የእርሱ ተከታዮች የሆኑ መነኩሴዎች ይህን ልማድ በስፔይንና በሌሎች በርካታ አገሮች አስፋፍተውታል።

የገና አባት በሌሎች አገሮች ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ሁሉ በስፔይን ደግሞ ሰብዓ ሰገል በክብረ በዓሉ ላይ ጎላ ያለ ሚና አላቸው። ኢየሱስ አራስ ልጅ እያለ ሰብዓ ሰገል ስጦታ እንዳመጡለት በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። በመሆኑም በስፔይን ጥር 6 በሚውለው ዲያ ደ ሬይስ (የነገሥታት ቀን) ሰብዓ ሰገል ለሕፃናት ስጦታ ይሰጣሉ ተብሎ ይታሰባል። ይሁን እንጂ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ኢየሱስን ለማየት የመጡት እነዚህ ሰዎች ቁጥራቸው እንዳልተገለጸ ብዙዎች አያውቁም። እንዲሁም ሰዎቹ ነገሥታት ሳይሆኑ ኮከብ ቆጣሪዎች ነበሩ። a ከዚህም በላይ እነርሱ መጥተው ከሄዱ በኋላ ሄሮድስ ኢየሱስን ለመግደል ብሎ በቤተልሔም የተወለዱትን “ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን” ወንዶች ልጆች ማስገደሉ ሰብዓ ሰገል ኢየሱስን ለማየት የመጡት ከተወለደ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደሆነ ይጠቁማል።—ማቴዎስ 2:11, 16

ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ አንዳንድ የስፔይን ከተሞች የኢየሱስን ልደት እንዲሁም እረኞቹና ቆየት ብሎም ሰብዓ ሰገል ወደ ቤተልሔም መጥተው ሲጎበኙት የሚያሳዩ ትርዒቶችን ማዘጋጀት ጀምረዋል። አሁን አሁን ደግሞ በአብዛኞቹ የስፔይን ከተሞች በየዓመቱ ጥር 5 ቀን “ሦስቱ ነገሥታት” በጌጣጌጥ ባሸበረቀ ተሽከርካሪ ላይ ሆነው ለተመልካች ከረሜላ እያደሉ በከተማው መሃል የሚዘዋወሩበት ካባልጋታ ተብሎ የሚጠራ ሰልፍ ይዘጋጃል። ባሕላዊ የገና ጌጣጌጦችና የልደት መዝሙሮች (ቪያንሲኮስ) ለበዓሉ ድምቀት ይሰጡታል።

አብዛኞቹ የስፔይን ቤተሰቦች በገና ዋዜማ (ታኅሣሥ 24) ልዩ እራት ያዘጋጃሉ። ባሕላዊው ምግብ እንደ ቱሮንና ማርዚፓን ያሉ ጣፋጮችን (ከለውዝና ከማር የሚዘጋጁ)፣ የደረቁ ፍራፍሬዎችን፣ የተጠበሰ በግና የባሕር ምግቦችን የሚያካትት ነው። የቤተሰብ አባሎች በዓሉን ተሰባስበው ለማክበር ከሩቅ ቦታዎች እንኳን ሳይቀር ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለው ይመጣሉ። ጥር 6 በሚውለው ሌላ ባሕላዊ ግብዣ ላይ ደግሞ ቤተሰቡ ሮስኮን ደ ሬይስ ተብሎ የሚጠራውንና በውስጡ የተደበቀ ነገር (አነስተኛ ቅርጽ) ያለውን በቀለበት ቅርጽ የሚዘጋጅ “የነገሥታት” ኬክ ይመገባል። በሮማውያን ዘመን ይደረግ በነበረ ተመሳሳይ ልማድ ቅርጹ የተደበቀበት የብስኩቱ ክፍል የደረሰው ባሪያ ለአንድ ቀን “ንጉሥ” የመሆን መብት ያገኝ ነበር።

“የፈንጠዝያና የግርግር ወቅት”

እያንዳንዱ አገር በዓሉን የሚያከብርበት የተለያየ ልማድ ቢያዳብርም ገና በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ግንባር ቀደም በዓል ሆኗል። ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ገናን “በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችና ለአንዳንድ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የዓመቱ የፈንጠዝያና የግርግር ወቅት” በማለት ገልጾታል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ክብረ በዓል አስፈላጊ ነው?

የኢየሱስ ልደት በታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚይዝ ክንውን እንደሆነ አይካድም። መላእክት የእርሱ መወለድ “[አምላክ] ለሚወዳቸው ሰዎች ሰላም” መምጣቱን የሚያበስር እንደሆነ መግለጻቸው ይህን ያረጋግጣል።

ሆኖም ኩዋን አርያስ የተባሉ አንድ ስፔይናዊ ጋዜጠኛ እንደተናገሩት “በክርስትና የመጀመሪያ ዓመታት ከኢየሱስ ልደት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙት ክንውኖች በበዓል መልክ አይከበሩም ነበር።” ታዲያ የገናን በዓል የማክበር ልማድ የመጣው ከየት ነው? የኢየሱስን ልደትና ሕይወት ማስታወስ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ታገኛለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ላ ሳግራታ ኤስከሬቱራ—ቴክስቶ ኤ ኮሜንታርዮ ፖር ፕሮፌሶርስ ደ ላ ካምፓኒያ ደ ሄሱስ የተባለው መጽሐፍ “ሰብዓ ሰገል በፋርሳውያን፣ በሜዶናውያንና በከለዳውያን ዘንድ ምትሃታዊ ድርጊቶችን፣ ኮከብ ቆጠራንና መድኃኒት ቅመማን የሚያከናውኑ ካህናት ነበሩ” ይላል። ይሁን እንጂ ሕፃኑን ኢየሱስን ለማየት የሄዱት ሰብዓ ሰገል በመካከለኛው ዘመን “ቅዱሳን” ተብለውና ሜልክዮር፣ ጋስፓርና ባልታዛር የሚሉ ስሞች ወጥቶላቸው ነበር። አስከሬናቸውም በኮሎኝ፣ ጀርመን በሚገኝ አንድ ካቴድራል ውስጥ እንደተቀመጠ ይነገራል።