በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ መታወስ ያለበት እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ መታወስ ያለበት እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ መታወስ ያለበት እንዴት ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ “በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩ ሰዎች አንዱ መሆኑ አሌ የማይባል ሐቅ ነው።”—“ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ”

ታላላቅ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚታወሱት በሕይወት ዘመናቸው ባከናወኑት ነገር ነው። ታዲያ ሰዎች ኢየሱስን ባከናወናቸው ነገሮች ሳይሆን በልደቱ የሚያስታውሱት ለምንድን ነው? በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ከኢየሱስ ልደት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙትን ክንውኖች አንድ በአንድ መዘርዘር ይችላሉ። ይሁን እንጂ በተራራ ስብከቱ ላይ የተናገራቸውን ወደር የሌላቸው ትምህርቶች የሚያስታውሱትና በሥራ ላይ ለማዋል የሚጥሩት ስንቶቹ ናቸው?

የኢየሱስ ልደት ትልቅ ግምት የሚሰጠው ክንውን እንደነበር ባይካድም የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርቱ ጉልህ ቦታ ይሰጡ የነበረው በሕይወት ዘመኑ ላደረጋቸው ነገሮችና ለትምህርቶቹ ነበር። አምላክም ቢሆን የኢየሱስ ልደት ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ካሳለፈው ሕይወት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም የገና በዓል የክርስቶስን ስብዕና በተለያዩ የልደት አፈ ታሪኮችና ተረቶች እንዲድበሰበስ አድርጓል።

ከገና በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ ሌላም አሳሳቢ ጥያቄ ይነሳል። ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ወደ ምድር ቢመለስና በገና በዓል ሰሞን የሚካሄደውን የጦፈ የንግድ እንቅስቃሴ ቢመለከት ምን ይሰማው ነበር? ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ጎብኝቶ ነበር። የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ በዓል የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ትርፍ ያጋብሱ የነበሩትን ገንዘብ መንዛሪዎችና ነጋዴዎች ሲመለከት በጣም ተበሳጭቷል። “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 2:13-16) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ በሃይማኖት ስም መነገድን ይቃወም ነበር።

በርካታ ቅን ልብ ያላቸው የስፔይን ካቶሊኮች የገና በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ ትርፍ የመሰብሰቢያ መንገድ እየሆነ መሄዱ ያሳስባቸዋል። ይሁን እንጂ ከአብዛኞቹ የገና ልማዶች አመጣጥ አንጻር በዓሉ የንግድ መልክ እንዳይዝ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር። ኩዋን አርያስ የተባሉት ጋዜጠኛ እንዲህ ብለዋል፦ “ገና ‘አረማዊ’ መልክ እንደያዘና ከሃይማኖት ይልቅ ወደ ፈንጠዝያና ወደ ንግድ እያዘነበለ እንደሆነ የሚሰማቸው በክርስትና ውስጥ ያሉ ሰዎች ቀድሞውንም ቢሆን በዓሉ አብዛኞቹን ልማዶች የወረሰው [ለፀሐይ ተብሎ ከሚከበረው] የሮማውያን አረማዊ በዓል እንደሆነ አይገነዘቡም።”—ኤል ፓይስ፣ ታኅሣሥ 24, 2001

በቅርብ ዓመታት በርካታ የስፔይን ጋዜጠኞችና ኢንሳይክሎፒዲያዎች የተለመዱት የገና አከባበር ሥነ ሥርዓቶች ከአረማዊ ልማዶች እንደመጡና ትርፍ ማጋበሻ መንገድ እንደሆኑ ገልጸዋል። የገና በዓል የሚከበርበትን ቀን በሚመለከት ኢንሳይክሎፒዲያ ደ ላ ሪሊጅን ካቶሊካ እንዲህ በማለት ሐቁን ይናገራል፦ “የሮማ ቤተ ክርስቲያን የገና በዓል በዚህ ዕለት እንዲከበር የወሰነችው አረማዊ ክብረ በዓላትን በክርስቲያናዊ በዓላት ለመተካት ባላት ፍላጎት ነው። . . . በወቅቱ በሮም ታኅሣሥ 25ን አረማውያኑ ናታሊስ ኢንቪሲቲ ወይም ‘የማትበገረዋ ፀሐይ’ ልደት ብለው ያከብሩት እንደነበር እናውቃለን።”

በተመሳሳይም ኢንሳይክሎፒዲያ ኢስፓኒካ እንዲህ ይላል፦ “የገና በዓል የሚከበርበት ታኅሣሥ 25 ቀን ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን በትክክል በማስላት የተገኘ ሳይሆን የክረምቱን ማብቃት አስመልክቶ በሮም የሚከበሩትን ክብረ በዓላት ወደ ክርስቲያናዊ በዓልነት ለመለወጥ ተብሎ የተደረገ ነው።” ሮማውያኑ የክረምቱ ወቅት አልፎ ፀሐይዋ የምትወጣበትን ወቅት ያከብሩት የነበረው እንዴት ነው? በድግስ፣ በፈንጠዝያና ስጦታ በመለዋወጥ ነበር። የቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት እንዲህ ዓይነቱን ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበረው በዓል ለማስቀረት ስላልፈለጉ የፀሐይ ልደት በማለት ፋንታ የኢየሱስ ልደት ብለው በመጥራት ‘የክርስቲያኖች በዓል’ እንዲሆን አደረጉ።

በመጀመሪያ ላይ ማለትም በአራተኛውና በአምስተኛው መቶ ዘመን አካባቢ በገና በዓል ላይ ይደረጉ የነበሩት ከፀሐይ አምልኮ ጋር የተያያዙ ልማዶች አልቀሩም ነበር። የካቶሊኩ “ቅዱስ” አውጉስቲን (354-430 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) የእምነት አጋሮቹ ታኅሣሥ 25ን አረማውያን ለፀሐይ ክብር ሲሉ በሚያከብሩበት መንገድ እንዳያከብሩት ለማሳሰብ ተገድዶ ነበር። ዛሬም ቢሆን የጥንቶቹ የሮም ክብረ በዓላት በገና በዓል አከባበር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አላቸው።

ለፈንጠዝያና ለንግድ የተመቸ በዓል

ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ የገና በዓል ፈንጠዝያ የሚንጸባረቅበትና የንግድ ማስፋፊያ የሆነ ዓለም አቀፋዊ በዓል እንዲሆን በማድረግ ረገድ በርካታ ነገሮች አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከሮማውያኑ በተወረሰው የገና አከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ ከሌሎች የክረምት ክብረ በዓላት በተለይም በሰሜናዊ አውሮፓ ከሚከበሩት በዓላት የተወረሱ ልማዶች ቀስ በቀስ እንዲካተቱ ተደርገዋል። a በ20ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ነጋዴዎችና የገበያ አጥኚዎች ዳጎስ ያለ ትርፍ የሚያስገኝላቸውን ማንኛውንም የአከባበር ሥነ ሥርዓት ያበረታቱ ነበር።

ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የክርስቶስ መወለድ ለሰው ልጆች ከሚያስገኘው ጥቅም ይበልጥ ለልደቱ አከባበር ትልቅ ቦታ ይሰጠው ጀመር። እንዲያውም በአብዛኞቹ ቦታዎች በተለመደው የገና ክብረ በዓል ላይ የኢየሱስ ስም ጨርሶ አይነሳም። ኤል ፓይስ የተባለው በስፔይን የሚታተም ጋዜጣ “[ገና] በቤተሰብ መልክ የሚከበር ዓለም አቀፋዊ ክብረ በዓል ሲሆን ሁሉም በፈለገው መንገድ ያከብረዋል” ብሏል።

ይህ አባባል በስፔይንና በሌሎች በርካታ አገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን ዝንባሌ የሚያንጸባርቅ ነው። ለገና ክብረ በዓል ትልቅ ቦታ እየተሰጠው በሄደ መጠን ሰዎች ስለ ክርስቶስ ያላቸው ግንዛቤ እየቀነሰ ይሄዳል። ከእውነታው እንደሚታየው የገና ክብረ በዓል ቀድሞ በሮም የነበረው መልክ ማለትም የፈንጠዝያው፣ የግብዣውና የስጦታ መለዋወጡ ሁኔታ አሁንም ተመልሶ እየመጣ ነው።

ሕፃን ተወልዶልናል

ገና በተለምዶ የሚከበርበት መንገድ ከክርስቶስ ጋር እምብዛም ተዛምዶ የሌለው ከሆነ እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ልደትና ሕይወቱን ማስታወስ ያለባቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከመወለዱ ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት ኢሳይያስ ስለ እርሱ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 9:6) ኢሳይያስ የኢየሱስ መወለድና ከዚያ በኋላ የሚፈጽማቸው ነገሮች ጉልህ ቦታ እንደሚሰጣቸው የጠቆመው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ኃያል መሪ ስለሚሆን ነው። የሰላም ልዑል ተብሎ የሚጠራ ሲሆን መስፍናዊ አገዛዙም ሆነ የሚያመጣው ሰላም ፍጻሜ አይኖረውም። በተጨማሪም የኢየሱስ አገዛዝ “በፍትሕና በጽድቅ” ላይ የተመሠረተ ይሆናል።—ኢሳይያስ 9:7

መልአኩ ገብርኤል ኢየሱስን እንደምትወልድ ለማርያም የነገራት ከኢሳይያስ አባባል ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። “እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም” በማለት ኢሳይያስ ተንብዮ ነበር። (ሉቃስ 1:32, 33) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የኢየሱስ ልደት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ ከሚያከናውነው ተግባር አኳያ ነው። የክርስቶስ አገዛዝ አንተንና የምትወዳቸውን ሰዎች ጨምሮ ለሁሉም የሰው ዘር ጥቅም ያስገኛል። እንዲያውም መላእክት የኢየሱስ መወለድ ‘አምላክ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ሰላም’ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።—ሉቃስ 2:14

ሰላምና ፍትሕ በሰፈነበት ዓለም ለመኖር የማይናፍቅ ማን አለ? ሆኖም የክርስቶስ አገዛዝ የሚያመጣውን ሰላም ለመቅመስ አምላክን ማስደሰትና ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ያስፈልገናል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ዝምድና ለመመሥረት የመጀመሪያው እርምጃ ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ መማር እንደሆነ ተናግሯል። “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሎ ነበር።—ዮሐንስ 17:3

ስለ ኢየሱስ በቂ ግንዛቤ ካገኘን በኋላ እንድናስታውሰው የሚፈልገው እንዴት ነው የሚለውን ማወቅ አይከብደንም። አንድ የጥንት አረማዊ በዓል ይከበር በነበረበት ዕለት በመብላት፣ በመጠጣትና ስጦታ በመለዋወጥ እንድናስታውሰው ይፈልግ ይሆን? እንደዚያ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባሳለፈው ምሽት ከደቀ መዛሙርቱ ምን እንደሚፈልግ ነግሯቸው ነበር። “የሚወደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ።”—ዮሐንስ 14:21

የይሖዋ ምሥክሮች በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር በማድረግ የአምላክንና የኢየሱስን ትእዛዛት ለመገንዘብ ችለዋል። አንተም ኢየሱስን እርሱ በሚፈልገው መንገድ ለማስታወስ እንድትችል እነዚህን ወሳኝ ትእዛዛት እንድታውቅ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የገና ዛፍና የገና አባት ለዚህ ዋና ዋና ምሳሌዎች ናቸው።

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ድግስ መደገስንና ስጦታ መለዋወጥን ያወግዛል?

ስጦታ መለዋወጥ

ይሖዋ ራሱ ‘የበጎ ስጦታና ፍጹም በረከት’ ሰጪ እንደሆነ ስለተገለጸ መጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ መስጠትን ይደግፋል። (ያዕቆብ 1:17) ኢየሱስ ጥሩ ወላጆች ለልጆቻቸው ስጦታ እንደሚሰጡ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:11-13) የኢዮብ ወዳጆችና የቤተሰቡ አባላት ከሕመሙ ሲያገግም ስጦታ አምጥተውለታል። (ኢዮብ 42:11) ይሁን እንጂ ከእነዚህ ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ ለየት ባሉ ክብረ በዓላት ላይ የተደረጉ አልነበሩም። እነዚህ ስጦታዎች ከልብ በመነጨ ፍላጎት በመነሳሳት የተደረጉ ናቸው።—2 ቆሮንቶስ 9:7

የቤተ ዘመድ ስብሰባ

የቤተሰብ ስብሰባዎች የቤተሰብ አባላትን በተለይም በተለያየ ቤት የሚኖሩትን ለማሰባሰብ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራሉ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በቃና በተዘጋጀ የሠርግ ግብዣ ላይ የተገኙ ሲሆን በቦታው በርካታ ወዳጅ ዘመዶች እንደነበሩ ጥርጥር የለውም። (ዮሐንስ 2:1-10) እንዲሁም ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ አባትየው የልጁን መመለስ አስመልክቶ የቤተሰብ ግብዣ ያዘጋጀ ሲሆን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሙዚቃና ጭፈራም ነበር።—ሉቃስ 15:21-25

ድግስ ማዘጋጀት

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከወዳጆቻቸው ወይም ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ተሰባስበው ምግብ ስለተመገቡባቸው አጋጣሚዎች በብዙ ቦታዎች ላይ ይናገራል። አብርሃም ሦስት መላእክት ሊጠይቁት ሲመጡ የጥጃ ሥጋ፣ ወተት፣ ቅቤና ቂጣ አቅርቦ ጋብዟቸዋል። (ዘፍጥረት 18:6-8) ሰሎሞንም ‘መብላት፣ መጠጣትና መደሰት’ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ ተናግሯል።—መክብብ 3:13፤ 8:15

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ ከወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር ተሰባስበን ግሩም ምግቦችን በመመገብ እንድንደሰት የሚፈልግ ከመሆኑም በላይ ስጦታ መለዋወጥንም ይደግፋል። እነዚህን ነገሮች በዓመቱ ውስጥ በማንኛውም ወቅት ማድረግ እንችላለን።