በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደሳች የምረቃ ዕለት

አስደሳች የምረቃ ዕለት

አስደሳች የምረቃ ዕለት

“በጣም ደስ የሚል ቀን ነው። ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ወጥታለች። ሰማዩም ጥርት ያለ ነው። መስኩ አረንጓዴ ሣር ለብሷል። አእዋፍም ሲዘምሩ ይሰማል። አስደሳች ቀን ሆኖ እንደሚውል መጠበቅ እንችላለን። የበረከት አምላክ የሆነው ይሖዋም አያሳፍረንም።”

የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ኸርድ መስከረም 11, 2004 የተካሄደውን የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 117ኛ ክፍል ተማሪዎች የምረቃ በዓል የከፈተው በእነዚህ ቃላት ነበር። ፕሮግራሙ ገንቢ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮችን፣ ተማሪዎቹ በትምህርት ቤት ቆይታቸው ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች እንዲሁም በመስኩ ከሚያገለግሉ የቆዩ ሚስዮናውያን የተገኙ ተሞክሮዎችን ያካተተ ነበር። በእውነትም በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ለተገኙትም ሆነ በብሩክሊንና ዎልኪል ሆነው ሥነ ሥርዓቱን በቪዲዮ ለሚከታተሉት 6,974 ተሰብሳቢዎች አስደሳች ዕለት ነበር።

ለተማሪዎቹ የቀረቡ አበረታች ንግግሮች

የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆን ኪኮት “በሚስዮናዊነት አገልግሎታችሁ ደስተኞች ሁኑ” በሚል ርዕስ አበረታች ንግግር አቀረበ። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደታየው ሁሉ የጊልያድ ተማሪዎች በደስተኝነታቸው እንደሚታወቁ ተናገረ። ተማሪዎቹ ከቅዱሳን ጽሑፎች ያገኙት እውቀት ደስታ ያስገኘላቸው ሲሆን ሌሎችም ይህን ደስታ እንዲቀምሱ ለመርዳት የሚያስችል ሥልጠና አግኝተዋል። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በሚስዮናዊነት አገልግሎታቸው ላይ ሙሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በማዋል ነው። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) አዲሶቹ ሚስዮናውያን እውነትን በልግስና ለሌሎች የሚሰጠውን ‘ደስተኛውን አምላክ’ ይሖዋን በመኮረጅ ደስታቸውን ጠብቀው መመላለስ ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW

ቀጣዩ ተናጋሪ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዴቪድ ስፕሌን ሲሆን የንግግሩ ጭብጥ “በምድብ ቦታችሁ ከሰዎች ጋር ተስማምታችሁ መኖር የምትችሉት እንዴት ነው?” የሚል ነበር። ከሰዎች ጋር ተስማምቶ በአንድነት መኖር መልካምና ደስ የሚያሰኝ እንደሆነ አያጠራጥርም፤ ሆኖም “ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር” መሆን ይጠይቃል። (1 ቆሮንቶስ 9:22፤ መዝሙር 133:1) ወንድም ስፕሌን ተመራቂዎቹ ተማሪዎች የሚስዮናዊነት ሥራቸው ከተለያዩ ሰዎች ጋር ማለትም በአገልግሎት ክልላቸው ከሚያጋጥሟቸው ሰዎች፣ ከሌሎች ሚስዮናውያን፣ በሚሄዱበት ጉባኤ ካሉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ በሚቆጣጠረው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ካሉት ወንድሞች ጋር እንደሚያገናኛቸው ተናገረ። ከዚያም ከሰዎች ጋር በተቻለ መጠን ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት በአካባቢው የሚነገረውን ቋንቋ ለመማር መሞከር፣ የአካባቢውን ባሕል ለመላመድ መጣር፣ በሌሎች ሚስዮናውያን የግል ሕይወት ውስጥ ጣልቃ አለመግባትና የስብከቱን ሥራ ለሚቆጣጠሩት ወንድሞች ታዛዥ መሆን እንዳለባቸው በመናገር ጠቃሚ ምክሮች አካፈላቸው።—ዕብራውያን 13:17

ከዚያ በመቀጠል የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ሎውረንስ ቦውን “አስተሳሰባችሁ ምን ይመስላል?” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። ‘የሰውን ፊት በማየት ይፈርዱ የነበሩት’ ሰዎች ኢየሱስ መሲህ መሆኑን እንዳልተቀበሉ ለተማሪዎቹ አስታወሳቸው። (ዮሐንስ 7:24) ፍጹማን ባለመሆናችን ሁላችንም ‘የእግዚአብሔርን ነገር’ እንጂ ‘የሰውን ነገር’ እንዳናስብ መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 16:22, 23) መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች እንኳን አስተሳሰባቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማስተካከል አለባቸው። ልክ በባሕር ላይ እንዳለ መርከብ ግባችን ላይ መድረሳችን የተመካው በአፋጣኝ ማስተካከያ በማድረጋችን ላይ ነው። ማስተካከያ ካላደረግን ለመንፈሳዊ የመርከብ መሰበር አደጋ እንጋለጣለን። አዘውትረን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በዙሪያቸው ካለው ሐሳብ ጋር እያገናዘብን ማጥናታችን ‘የእግዚአብሔርን ነገር’ እንድናስብ ይረዳናል።

በተከታታይ የቀረቡትን እነዚህን ንግግሮች የደመደመው የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ዋላስ ሊቨራንስ ነበር። ንግግሩ በኢሳይያስ 55:1 [የ1954 ትርጉም] ላይ የተመሠረተ ሲሆን “ምን ትገዛላችሁ?” የሚል ርዕስ ነበረው። ወንድም ሊቨራንስ ተማሪዎቹን ስለ ጊዜያችን ከሚናገረው የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ደስታና እርካታን “እንዲገዙ” አበረታታቸው። የኢሳይያስ ትንቢት የአምላክን ቃል ከውኃ፣ ከወይንና ከወተት ጋር አመሳስሎታል። ታዲያ የአምላክ ቃል “ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ” ሊገዛ የሚችለው እንዴት ነው? ወንድም ሊቨራንስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች በትኩረት በመከታተልና ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ አስተሳሰቦችና መንገዶች ፋንታ የአምላክን አስተሳሰቦችና መንገዶች በመከተል እንደሆነ አብራርቷል። (ኢሳይያስ 55:2, 3, 6, 7) አዲሶቹ ሚስዮናውያን እንዲህ በማድረግ በተመደቡበት ቦታ ለረጅም ጊዜ እያገለገሉ መቆየት ይችላሉ። ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች አብዛኛውን ጊዜ ቁሳዊ ንብረት በማካበት ደስተኛ መሆን እንደሚቻል ይሰማቸዋል። ወንድም ሊቨራንስ ግን እንዲህ አለ:- “ፈጽሞ በዚህ አትታለሉ። ትንቢታዊውን የአምላክ ቃል በጥልቀት ለማጥናት የሚያስችል ጊዜ መድቡ። ይህ መንፈሳችሁን የሚያድስላችሁና የሚያጠናክራችሁ ከመሆኑም በላይ በሚስዮናዊነት አገልግሎታችሁ ደስተኛ እንድትሆኑ ይረዳችኋል።”

አስደሳች ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች

ተማሪዎቹ በትምህርት ላይ በነበሩበት ወቅት በስብከቱ ሥራ አዘውትረው ይሳተፉ ነበር። የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር በሚያቀርበው ክፍል ላይ በርካታ የክፍሉ ተማሪዎች “በወንጌል አናፍርም” የሚለውን ጭብጥ የሚያጎሉ ተሞክሮዎችን በሠርቶ ማሳያ መልክ አቀረቡ። (ሮሜ 1:16) ተሰብሳቢዎቹ እነዚህ የተዋጣላቸው የአምላክ አገልጋዮች ከቤት ወደ ቤት፣ በጎዳናዎች ላይ እንዲሁም በገበያ ማዕከሎች ውስጥ ምሥራቹን እንዴት እንደሰበኩ ሲሰሙ በጣም ተደሰቱ። ሌሎች ቋንቋዎችን የሚያውቁ ተማሪዎች በጉባኤያቸው ክልል ውስጥ ለሚገኙ ባዕድ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ምሥራቹን ለማዳረስ ጥረት አድርገዋል። ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁዋቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በመጠቀም ተመላልሶ መጠየቆችን ማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ችለዋል። ምሥራቹን ለመስበክ ፈጽሞ ‘አላፈሩም።’

ከዚያም በአገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚሠራው ወንድም ዊልያም ኖንኪስ ከቡርኪና ፋሶ፣ ከላቲቪያና ከሩሲያ ለመጡ የቆዩ ሚስዮናውያን ቃለ መጠይቅ አደረገላቸው። ሚስዮናውያኑ “አፍቃሪው ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ይክሳቸዋል” በሚለው ጭብጥ ላይ ተመሥርተው ለተማሪዎቹ ጠቃሚ ምክሮችን አካፈሏቸው። ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ወንድሞች መካከል አንዱ ተማሪዎቹን የጌዴዎንን 300 ወታደሮች እንዲያስታውሱ አበረታታቸው። እያንዳንዱ ወታደር ለዘመቻው መሳካት የሚያበረክተው የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው። (መሳፍንት 7:19-21) በተመሳሳይም በምድብ ቦታቸው ቆይተው የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን ብዙ በረከቶችን ያገኛሉ።

ከዚያ በመቀጠል በፓተርሰን አስተማሪ የሆነው ወንድም ሳሙኤል ሮበርሰን “ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሁኑ” በሚል ጭብጥ ከሴኔጋል፣ ከጉዋም፣ ከላይቤሪያና ከማዳጋስካር ለመጡ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ቃለ መጠይቅ አደረገ። በእነዚህ አገሮች ውስጥ በድምሩ 170 የሚያህሉ ሚስዮናውያን ያገለግላሉ። ቃለ ምልልሱ አዳዲስ ሚስዮናውያን ከአገልግሎት ምድባቸው ጋር እንዲላመዱ በመርዳት ረገድ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴዎች ስለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ለተመራቂዎቹ ተማሪዎች ግንዛቤ ያስጨበጠ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሚስዮናውያኑ ከምዕራቡ ዓለም አስተሳሰብ አንጻር ሲታዩ እንግዳ የሆኑ ባሕሎችን መላመድ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ አገሮች ወንዶች፣ የክርስቲያን ጉባኤ አባል የሆኑትም ጭምር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ መመልከት የተለመደ ነው። በጉዋም ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ባሉ አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ያልተለመዱ የምግብ ዓይነቶች ይቀርባሉ። ይሁን እንጂ ሌሎች ሚስዮናውያን ከእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ጋር መላመድ እንደቻሉ ሁሉ አዳዲሶቹ ሚስዮናውያንም እንዲህ ማድረግ አያቅታቸውም።

በመቀጠል የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ጋይ ፒርስ “‘ለጌታችን መንግሥት’ ታማኞች ሆናችሁ ቀጥሉ” በሚለው ጭብጥ ላይ የተመሠረተ ንግግር አቀረበ። ወንድም ጋይ ፒርስ አድማጮችን እንዲህ በማለት አሳሰባቸው:- “ይሖዋ ነገሮችን የፈጠረው በዓላማ ነው። ለፍጥረታቱ ያዘጋጀላቸው ነገር ነበር። ይህ ዓላማው አልተለወጠም። ወደ ፍጻሜው መገስገሱን ይቀጥላል፤ ምንም ነገር ሊያደናቅፈው አይችልም።” (ዘፍጥረት 1:28) ወንድም ፒርስ የመጀመሪያው ሰው አዳም የሠራው ኃጢአት ያስከተላቸው ችግሮች ቢኖሩም ሁሉም በታማኝነት ለአምላክ ሉዓላዊነት እንዲገዙ አሳሰባቸው። “በፍርድ ሰዓት ውስጥ እንገኛለን። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ መርዳት የምንችልበት ጊዜ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። ይህን ጊዜ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ለመስበክ በአግባቡ ተጠቀሙበት” በማለት አበረታታ። በታማኝነት ከአምላክ መንግሥት ጎን የሚቆሙ የእርሱ ድጋፍ እንደማይለያቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።—መዝሙር 18:25

በሥነ ሥርዓቱ መደምደሚያ የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የተላኩ ሰላምታዎችንና የመልካም ምኞት መግለጫዎችን ካነበበ በኋላ ለተመራቂዎቹ ተማሪዎች ዲፕሎማቸውን ሰጠ። በመቀጠልም አንድ ተማሪ ክፍሉን ወክሎ ተማሪዎቹ ላገኙት ሥልጠና የተሰማቸውን አድናቆት የሚገልጽ ደብዳቤ አነበበ። በተሰብሳቢዎቹ ዘንድ የማይረሳ ትዝታ ጥሎ ላለፈው አስደሳች ፕሮግራም ይህ ተስማሚ መደምደሚያ ነበር።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 11

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 22

የተማሪዎቹ ብዛት:- 48

አማካይ ዕድሜ:- 34.8

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 18.3

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13.4

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 117ኛ ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ቶምፕሰን ኤስተር፣ ኖርቬል ግሎሪሴል፣ ፓውል ታንየ፣ ኮዛ ሜሊሳ፣ ማከንታየር ታሚ (2) ራይሊ አንድሪያ፣ ክሌይተን ካራ፣ አለን ጀኒን፣ ብላንኮ አሊስ፣ ሙንዮስ ሉርደስ፣ ረስታድ ኔኦሚ (3) ጉሬሮ ዛከሪ፣ ጋርሲያ ካተሊን፣ ሜከርሊ ዴቢ፣ ኢሺካዋ ቶሞይ፣ ብላንኮ ጉስታቮ (4) ማከንታየር ስቲቭ፣ ክሩስ ኤልቫ፣ ጉሬሮ ጆዲ፣ ሪቺ ኦልጋ፣ አቤያኔታ ሊዝቤት፣ ጋርሲያ ሩቤን (5) ፓውል ጄፍ፣ ፊስካ ሂልደገን፣ ሙንዮስ ቪክተር፣ ባውማን ዳንዬላ፣ ሻው ሰማንታ፣ ብራውን ካቲ፣ ብራውን ላውሬአኖ (6) ሻው ኮርዊን፣ ራይሊ አድሪያን፣ ፔሎክዊን ካርላ፣ ሚዩንክ ኒኮል፣ ሜከርሊ ዴኒስ፣ ኢሺካዋ ካዙኦ (7) ሚዩንክ ማርኩስ፣ ፔሎክዊን ጄፍ፣ ኮዛ ትሮ፣ አቤያኔታ ማርስያል፣ አለን ኬኔት፣ ሪቺ ኤሪክ፣ ኖርቬል ቲም (8) ክሩስ ጆን፣ ባውማን ሄልሙት፣ ክሌይተን ዜብ፣ ፊስካ ኤርሊንግ፣ ቶምፕሰን ማርክ፣ ረስታድ ጄምስ