በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ አምልኮና የጣዖት አምልኮ የተጋጩበት ቦታ

እውነተኛ አምልኮና የጣዖት አምልኮ የተጋጩበት ቦታ

እውነተኛ አምልኮና የጣዖት አምልኮ የተጋጩበት ቦታ

የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች በቱርክ በስተ ምዕራብ ጠረፍ ላይ በምትገኘው በጥንታዊቷ የኤፌሶን ከተማ ፍርስራሽ ላይ ከአንድ መቶ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ጀምሮ ጠለቅ ያለ ምርምር ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ብዙ ሕንጻዎች ታድሰው የቀድሞ ይዞታቸውን እንዲላበሱ የተደረገ ሲሆን ተመራማሪዎች በበርካታ ግኝቶች ላይ ጥናት በማድረግ ትንታኔ ሰጥተዋል። በመሆኑም ኤፌሶን ቱርክ ካሏት ዋነኛ የቱሪስት መስህቦች መካከል አንዷ ለመሆን በቅታለች።

ስለ ኤፌሶን ምን የታወቀ ነገር አለ? በዛሬው ጊዜ ስለዚህች አስደናቂ ጥንታዊት ከተማ ምን ግንዛቤ ማግኘት እንችላለን? የከተማዋን ፍርስራሽና በኦስትሪያ፣ ቪየና የሚገኘውን የኤፌሶንን ቤተ መዘክር በመጎብኘት በእውነተኛ አምልኮና በጣዖት አምልኮ መካከል የነበረውን ግጭት ማስተዋል እንችላለን። እስቲ በመጀመሪያ የኤፌሶንን ታሪክ እንመልከት።

ብዙዎች ዓይናቸውን የጣሉባት ስፍራ

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ11ኛው መቶ ዘመን በዩሮኤዥያ ሽብርና ስደት ነግሦ ነበር። በዚያን ጊዜ የአዮኒየ ግሪኮች በትንሹ እስያ ምዕራባዊ ጠረፍ መስፈር ጀመሩ። በዚህ አካባቢ በኋላ የኤፌሶኗ አርጤምስ የተባለችውን እናት አምላክ የሚያመልኩ ሰዎች ይኖሩ ነበር።

ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ሲሜራውያን ዘላኖች በስተ ሰሜን ከሚገኘው ጥቁር ባሕር አካባቢ ተነስተው የትንሹን እስያ አካባቢ በመውረር ዘረፋ አካሄዱ። ከዚያም በ550 ከክርስቶስ ልደት በፊት በሀብታምነቱ የሚታወቀው ኃያሉ የልድያ ንጉሥ ክሪሰስ ይህቺን ቦታ መግዛት ጀመረ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ የፋርስን ግዛት እያስፋፋ የነበረው ንጉሥ ቂሮስ ኤፌሶንንና ሌሎች የአዮኒየውያንን ከተሞች በቁጥጥሩ ሥር አደረገ።

የመቄዶንያው እስክንድር ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ334 ጀምሮ በፋርስ ላይ በመዝመት ቀጣዩ የኤፌሶን ገዢ ሆነ። እስክንድር በ323 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአጭር ሲቀጭ ጄኔራሎቹ ኤፌሶንን ለመውሰድ እርስ በርሳቸው ይሻኮቱ ጀመር። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ133 ደግሞ መካን የነበረው የጴርጋሞን ንጉሥ ሳልሳዊ አተለስ ኤፌሶንን ለሮማውያን ስላወረሳት በእስያ ካለው የሮማ ግዛት ጋር ተቀላቀለች።

እውነተኛ አምልኮ ከጣዖት አምልኮ ጋር ተጋጨ

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ ሁለተኛውን ሚስዮናዊ ጉዞ ወደ ማጠናቀቁ ሲቃረብ ወደ 300,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች ወደ ነበሯት ኤፌሶን ከተማ ሄደ። (የሐዋርያት ሥራ 18:19-21) በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅትም ወደ ኤፌሶን በድጋሚ በመሄድ በድፍረት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በምኩራብ ሰብኳል። ሆኖም ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላ ከአይሁዳውያን ይደርስበት የነበረው ተቃውሞ እያየለ ስለመጣ በምኩራብ መስበኩን ትቶ በጢራኖስ የትምህርት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ንግግር መስጠት ጀመረ። (የሐዋርያት ሥራ 19:1, 8, 9) በተአምር በሽተኞችን በመፈወስና አጋንንትን በማውጣት ጭምር የስብከቱን ሥራ ለሁለት ዓመታት ማከናወኑን ቀጠለ። (የሐዋርያት ሥራ 19:10-17) በዚህ ምክንያት ብዙዎች አማኝ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም! የይሖዋ ቃል በማሸነፉ ጠንቋይ የነበሩ በርካታ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ውድ ዋጋ የሚያወጡ የጥንቆላ መጽሐፎቻቸውን አቃጠሉ።—የሐዋርያት ሥራ 19:19, 20

ጳውሎስ ያከናወነው ውጤታማ ስብከት በርካታ ሰዎች የሴት አምላክ የሆነችውን አርጤምስን ማምለካቸውን እንዲያቆሙ ቢያደርግም የጣዖት አምልኮ አራማጆችን ቁጣ ቀስቅሶበታል። የአርጤምስን ምስል በብር ማዕድን እየሠሩ መሸጥ ብዙ ትርፍ ያስገኝ ነበር። ድሜጥሮስ የተባለ ሰው የብር አንጥረኞች ገበያቸው ሊቀዘቅዝባቸው እንደሆነ በማስፈራራት እንዲረብሹ አነሳሳቸው።—የሐዋርያት ሥራ 19:23-32

ረብሸኞቹ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ በመጮህ ለሁለት ሰዓት ያህል ከተማይቱን ባወኩ ጊዜ በእውነተኛው አምልኮና በጣዖት አምልኮ መካከል ያለው ፍጥጫ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። (የሐዋርያት ሥራ 19:34) ጳውሎስ ሁካታው ጋብ ካለ በኋላ ክርስቲያን ወንድሞቹን በድጋሚ በማበረታታት ሚስዮናዊ ጉዞውን ቀጠለ። (የሐዋርያት ሥራ 20:1) ይሁን እንጂ፣ የጳውሎስ ወደ መቄዶንያ መሄድ የአርጤምስን የጣዖት አምልኮ ወደ ውድቀት ከማምራት አላዳነውም።

የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ተናጋ

የአርጤምስ አምልኮ በኤፌሶን ሥር ሰድዶ ነበር። ንጉሥ ክሪሰስ ከመንገሡ በፊት ሲብል የተባለች እናት አምላክ በአካባቢው ትልቅ ቦታ ተሰጥቷት የምትመለክ ጣዖት ነበረች። ንጉሡ ሲብል የተባለችውን እናት አምላክና የግሪካውያንን አማልክት፣ በአፈ ታሪካዊ የዘር ሐረግ በማዛመድ በግሪካውያንና ግሪካውያን ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላት አምላክ ለመፍጠር አሰበ። ከዚያም ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ በንጉሡ እርዳታ የሲብል ተተኪ የሆነችው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ሥራ ተጀመረ።

ቤተ መቅደሱ ድንቅ የግሪካውያን የሕንጻ ጥበብ ውጤት ነበር። ከዚያ በፊት በዓይነቱም ሆነ በመጠኑ እንዲህ ያለ ሕንጻ ያልነበረ ከመሆኑም ሌላ ይህን የሚያካክሉ ትልልቅ የእብነ በረድ ማዕዘናት ጥቅም ላይ ውለው አያውቁም። ነገር ግን ቤተ መቅደሱ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ356 በእሳት ቃጠሎ ወደመ። ቀደም ሲል ከነበረው ጋር የሚመሳሰል አስደናቂ ቤተ መቅደስ እንደገና መሠራቱ ጥሩ የሥራ መስክ ከመፍጠሩም በላይ በዋነኝነት ተሳላሚዎችን ለመሳብ አስችሏል። መሠረቱ 73 ሜትር በ127 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ቤተ መቅደሱ ደግሞ 50 ሜትር በ105 ሜትር ያህል ስፋት ነበረው። ሕንጻው በዓለም ላይ ከነበሩት ሰባት አስደናቂ ነገሮች አንዱ ነው። ሆኖም በነገሩ የተደሰተው ሁሉም ሰው አልነበረም። የኤፌሶኑ ፈላስፋ ሄራክሊተስ ወደ መሰዊያው የሚወስደውን ጨለማ መንገድ ብልግና ከሚፈጸምበት ጨለማ ጋር አመሳስሎታል፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከእንስሳት የባሰ አጸያፊ ተግባር እንደሚፈጸም ተናግሯል። ቢሆንም ብዙዎች በኤፌሶን የሚገኘው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ የሚንኮታኮት አይመስላቸውም ነበር። እውነታው ግን ሌላ መሆኑን ታሪክ ይነግረናል። ኤፌሶስ—ዳኖይየ ፉዌረ (ኤፌሶንአዲሱ መመሪያ) የተባለ መጽሐፍ “በሁለተኛው መቶ ዘመን የአርጤምስም ሆነ የሌሎች ታዋቂ አማልክት አምልኮ በድንገት ተቀባይነት አጣ” በማለት ዘግቧል።

በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኤፌሶን በከባድ የመሬት መናወጥ ተመታች። ከዚህም በላይ ጥቁር ባሕርን በመርከብ አቋርጠው የመጡ ጎቶች ውድ የሆኑ የቤተ መቅደሱን ንብረቶች ከዘረፉ በኋላ በእሳት አቃጥለውታል። ከላይ የተገለጸው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ድል የተደረገችውና የራሷን ቤተ መቅደስ ከጥፋት ለመታደግ ያልቻለችው አርጤምስ ከዚያ በኋላ እንዴት የከተማዋ ጠባቂ ተደርጋ ልትታይ ትችላለች?”—መዝሙር 135:15-18

በመጨረሻም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ገደማ ቀዳማዊ ንጉሥ ቲዮዶሸስ “ክርስትና” የአገሪቱ ሃይማኖት እንዲሆን ወሰነ። ብዙም ሳይቆይ ስመ ጥር የነበረው የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ለግንባታ የሚያገለግሉ ጥሬ እቃዎች ማውጫ ሆነ። በዚህ ሁኔታ የአርጤምስ አምልኮ እንዳልነበረ ሆነ። አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ታዛቢ የጥንቱ ዓለም አስደናቂ ቤተ መቅደስ እንደሆነ ተደርጎ ይወደስ የነበረውን ይህን አካባቢ “አሁን ባድማና የተራቆተ ቦታ ነው” በማለት ተናግሯል።

ከአርጤምስ ወደ “የአምላክ እናት” አምልኮ

ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች እርሱ ከሄደ በኋላ ‘እውነትን የሚያጣምሙ ነጣቂ ተኩላዎች’ ከመካከላቸው እንደሚነሱ አስጠንቅቋቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:17, 29, 30) ይህ ነገር በትክክል ተፈጽሟል። በኤፌሶን በክህደት ክርስትና አማካኝነት የሐሰት አምልኮ እያየለ እንደመጣ ከሁኔታዎቹ ማየት ይቻላል።

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ431 በኤፌሶን ስለ ክርስቶስ ማንነት ውይይት የተደረገበት የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ሦስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። ኤፌሶስ—ዳኖይየ ፉዌረ የተባለው መጽሐፍ “ክርስቶስ መለኮት ብቻ ነው የሚል ሐሳብ ይዘው የቀረቡት እስክንድራውያን የተሟላ ድል አግኝተዋል” ይላል። ይህ ውሳኔ የተለያዩ መዘዞችን አስከትሏል። መጽሐፉ አክሎ እንዲህ ይላል፦ “ማርያምን ከወላዲተ ክርስቶስነት ወደ ወላዲተ አምላክነት ደረጃ ከፍ ያደረጋት በኤፌሶን የተላለፈው ውሳኔ ለማርያም አምልኮ መሠረት ከመጣሉም በላይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ መከፋፈል እንዲፈጠር አድርጓል። . . . ክርክሩ እስከ አሁን ቀጥሏል።”

በዚህ መንገድ የሲብልና የአርጤምስ አምልኮ “ወላዲተ አምላክ” ወይም “የአምላክ እናት” ተብላ በምትጠራው በማርያም አምልኮ ተተካ። መጽሐፉ በተጨማሪ እንዲህ ይላል፦ “ከአርጤምስ አምልኮ ተለይቶ የማይታየው . . . በኤፌሶን የተጠነሰሰው የማርያም አምልኮ እስከ አሁን ድረስ እንደ ወግ ተደርጎ ተይዟል።”

ከዓለም ከጠፉት ነገሮች አንዱ የሆነው የአርጤምስ አምልኮ

የአርጤምስ አምልኮ ከቀረ በኋላ ኤፌሶንም ጠፋች። የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ወባና ቀስ በቀስ የሸፈናት ደለል ተዳምረው በከተማይቱ ውስጥ መኖርን ይበልጥ አስቸጋሪ አደረጉት።

በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስልምና በእጅጉ መስፋፋት ጀመረ። እስልምና የአረብ ጎሳዎችን በትምህርቶቹ አንድ በማድረግ ብቻ አልተወሰነም። የአረብ የጦር መርከቦች ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከሰባተኛው እስከ ስምንተኛው መቶ ዘመን በነበሩት ጊዜያት ኤፌሶንን በተደጋጋሚ ጊዜያት ዘርፈዋል። ወደቡ በደለል ሙሉ በሙሉ በተሸፈነና ከተማዋ የፍርስራሽ ክምር በሆነችበት ወቅት ታሪኳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘጋ። ከዚያች ውብ ከነበረች ትልቅ ከተማ የተረፈችውና እስከ ዛሬ ድረስ ያለችው አያ ሶሉክ (የአሁኗ ሴልቹክ) የተባለች ትንሽ መንደር ብቻ ናት።

የኤፌሶንን ፍርስራሽ መጎብኘት

ኤፌሶን የነበራትን ክብር ለማየት የሚፈልግ ሰው ፍርስራሿን መጎብኘት ይችላል። ጉብኝትህን ከላይኛው መግቢያ ብትጀምር ወደ ሴልሰስ ቤተ መጻሕፍት የሚወስደውን አስደናቂውን የኩሬተስ ጎዳና ትመለከታለህ። መንገዱን ይዘህ ስትሄድ በስተቀኝ በኩል ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ዘመን የተገነባ ቀልብ የሚስብ አነስ ያለ ቲያትር ቤት ታያለህ። ቲያትር ቤቱ 1,500 የሚያህሉ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን ለምክር ቤት መሰብሰቢያነት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ መዝናኛም ቦታ ሆኖ ሳያገለግል አይቀርም። ከኩሬተስ ጎዳና ግራና ቀኝ የተለያዩ ሕንጻዎች ነበሩ፤ ከእነዚህም ውስጥ ስለ አገራዊ ጉዳዮች የሚመከርበት አዳራሽ፣ የሄድሪየን ቤተ መቅደስ፣ ፏፏቴዎችና በኮረብታማ ቦታዎች ላይ የተገነቡ የታዋቂ የኤፌሶን ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ይገኙባቸዋል።

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ዘመን የተገነባውን በጣም ውብ የሆነውን የሴልሰስ ቤተ መጻሕፍት ስትመለከት መደነቅህ አይቀርም። ሰፊ በሆነው የማንበቢያ ክፍል ግድግዳ ላይ በተበጁት መደርደሪያዎች ውስጥ በርካታ ጥቅልሎች ይቀመጡ ነበር። በቤተ መጻሕፍቱ የታችኛው ፎቅ ላይ እንደ ሴልሰስ ካሉ ሮማውያን የሕዝብ አገልጋዮች ለሚጠበቁት ባሕርያት ምሳሌ የሚሆኑ አራት ውብ ሐውልቶችም ነበሩ፤ እነርሱም ሶፊያ (ጥበብ)፣ አሬቲ (ጨዋነት)፣ አኒየ (ታማኝነት) እና ኤፒስቲሚ (እውቀት ወይም ብልሃት) ተብለው ይጠራሉ። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሐውልቶች ቪየና ባለው የኤፌሶን ቤተ መዘክር ውስጥ ይገኛሉ። ከቤተ መጻሕፍቱ ቀጥሎ ያለው ትልቅ በር ወደ ቴትራጎኖስ የገበያ አዳራሽ ያደርስሃል። ዙሪያውን የተስተካከሉ መተላለፊያዎች ባሉት በዚህ ግዙፍ አራት ማዕዘን አዳራሽ ውስጥ ሰዎች የተለመደውን የንግድ ልውውጣቸውን ያከናውናሉ።

ከዚያም ወደ ትልቁ ቲያትር ማሳያ ቦታ የሚወስድ ከእብነ በረድ የተሠራ መንገድ ታገኛለህ። በሮማውያን የግዛት ዘመን ለመጨረሻ ጊዜ የማስፋፋት ሥራ የተደረገለት ይህ ቲያትር ማሳያ ቦታ 25,000 የሚያህሉ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም አለው። ፊት ለፊቱ እጅግ በጣም ግዙፍ በሆኑ ዓምዶች፣ ቅርጻ ቅርጾችና ሐውልቶች ያሸበረቀ ነበር። በዚህ ቦታ አንጥረኛው ድሜጥሮስ ቀስቅሶት የነበረውን ትልቅ ሁከት በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ትችላለህ።

ከትልቁ ቲያትር ማሳያ ቦታ አንስቶ እስከ ከተማዋ ወደብ የሚደርሰው መንገድ በጣም ማራኪ ነው። በሁለቱም ጎኖቹ በዓምዶች ያሸበረቀው ይህ ጎዳና ወደ 500 ሜትር የሚጠጋ ርዝመትና 11 ሜትር የሚያህል ስፋት አለው። የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው የቲያትር ቤቱና የወደቡ ጂምናዝየሞችም የተገነቡት በዚሁ መንገድ ዳር ላይ ነው። በጎዳናው መጨረሻ ላይ ያለው ውብ የወደብ መግቢያ ኤፌሶንን ከሌላው ዓለም ጋር የሚያገናኝ በር ነው፤ አስደናቂ ነገሮች ባሉባት የኤፌሶን ከተማ ፍርስራሽ ውስጥ የምናደርገውን ጉብኝት እዚህ ቦታ ላይ እንደመድማለን። በቪየና በሚገኘው የኤፌሶን ቤተ መዘክር ውስጥ ከእንጨት የተሠራ የዚህች ትልቅ ከተማ ናሙናና ሌሎች በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ።

ቤተ መዘክሩን የጎበኘና የኤፌሶኗን አርጤምስ ምስልን የተመለከተ ሰው በከተማይቱ የነበሩትን የጥንት ክርስቲያኖች ጥንካሬ ሳያደንቅ አያልፍም። እነዚህ ክርስቲያኖች በመናፍስት ሥራ በተጠመዱና በሃይማኖታቸው ምክንያት በሚጠሏቸው ሰዎች መሃል ይኖሩ ነበር። የመንግሥቱ ምሥራች ስብከት ከአርጤምስ አምላኪዎች የከረረ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:19፤ ኤፌሶን 6:12፤ ራእይ 2:1-3) በዚህ ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እውነተኛ አምልኮ ሥር ሲሰድ የአርጤምስ አምልኮ ግን ጠፍቷል፤ በተመሳሳይ ዛሬ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶች በሚወድሙበት ጊዜ የእውነተኛው አምላክ አምልኮ ጸንቶ ይቆማል።—ራእይ 18:4-8

በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

መቄዶንያ

ጥቁር ባሕር

ትንሹ እስያ

ኤፌሶን

ሜዲትራንያን ባሕር

ግብፅ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. የሴልሰስ ቤተ መጻሕፍት

2. አሬቲ (ጨዋነት) የምትባለው ሐውልት ከቅርብ ስትታይ

3. ወደ ትልቁ ቲያትር ማሳያ ቦታ የሚወስደው የእብነ በረድ መንገድ